Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ ላይ የሚከናወነው ምርመራ በፍርድ ቤት...

በቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ኃላፊ ላይ የሚከናወነው ምርመራ በፍርድ ቤት ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

ጭካኔ የተሞላበት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸምና በማስፈጸም ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ በነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የምርመራ ሒደት በፍርድ ቤት ጥያቄ አስነሳ፡፡

ፍርድ ቤቱ ጥያቄ ያነሳው መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በነበረ ችሎት የሚቀረውን የምርመራ ሒደት በማስረዳት ለተጨማሪ የምርመራ ሥራ በተፈቀደለት 12 ቀናት ውስጥ ያከናወነውን የምርመራ ሒደትና ተጨማሪ የሚሠራው የምርመራ ሒደት እንዳለው በመግለጽ፣ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት መጠየቁን የተጠርጣሪው ጠበቆች ጠንከር ያለ መቃወሚያ በማቅረባቸው ነው፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተፈቀዱለት የምርመራ ቀናት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች ቃል መቀበሉን፣ በተለያዩ አካባቢዎችም ተጎጂዎች መኖራቸውን ሰምቶ መረጃ ማሰባሰቡን፣ ተጠርጣሪው ከገቢያቸው በላይ ሀብት ማከማቸታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ለማግኘት ለሚመለከታቸው ተቋማት ደብዳቤ መጻፉን፣ ተጨማሪ ሀብት በሌላ ቦታ እንዳላቸው ጥቆማ ደርሶት በእሱ ላይ እየሠራ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ተጨማሪ የምርመራ ሥራ እንደሚቀረው የገለጸው ደግሞ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ተጨማሪ ተጎጂዎችን ቃል መቀበል፣ የሕክምና ማስረጃ ሰነድ መሰብሰብ፣ የተጠርጣሪውን ቃል መቀበል፣ ፎቶ ማስነሳት፣ አሻራ መውሰድ፣ ድብቅ እስር ቤቶችንና ተጠርጣሪውን በተጎጂዎች ማስለየት፣ ለተለያዩ ተቋማት የተጻፉ ደብዳቤዎችን ምላሽ መሰብሰብና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ሀብት ሕጋዊ አስመስለው በማቅረባቸው የመለየት ሥራ እንደሚቀረው መርማሪ ቡድኑ ገልጾ 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ባቀረበው የምርመራ ሒደትና በጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ላይ የአቶ ያሬድ ጠበቆች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የመርማሪ ቡድኑ በ12 ቀናት ውስጥ ሠራሁና ይቀረኛል የሚለው የምርመራ ሒደት ግነት የተሞላበት መሆኑን በመግለጽ መከራከር የጀመሩት ጠበቆቹ፣ ደንበኛቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ምክትል ኃላፊ መሆናቸው እንደ ወንጀል ተደርጎ ለፍርድ ቤቱ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡ ቡድኑ ምርመራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአራት ምስክሮችን ቃል እንደተቀበለና የቀሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው እየገለጸ የሚገኘው፣ ቀደም ባለው ችሎት ያቀረበውን የሥራ ዝርዝር ገልብጦ በማቅረብ መሆኑን ጠቁመው፣ የሠራ ለማስመሰልና ትኩረት ለመሳብ አንዳንድ ነገሮችን ብቻ እንደሚጨምር አስረድተዋል፡፡

በግማሽ ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ የሚችሉ የምርመራ ሒደቶችን ከባድ አድርጎ በማቅረብ ተጠርጣሪውን በእስር ለማቆየት ካላቸው ፍላጎት ውጪ ትኩረት ተሰጥቶ ምርመራ እየተከናወነ አለመሆኑን ገልጸው፣ ምንም እንኳን ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገብ ከመርማሪ ቡድኑ እየተቀበለ የሚመለከት መሆኑን የሚገነዘቡ ቢሆንም በትኩረት እንደገና እንዲያይላቸው ጠበቆቹ አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡

ሌሎች ተግባራትን የሚያሳይ ጥቆማ ተቀብለናል ማለት ምን ማለት ነው? ሥውር እስር ቤቶችን በተጎጂዎች ማስለየት ይቀረኛል የሚለው ሪፖርት ያለቅጥ የችሎቱን ትኩረት ለመሳብ እየጣረ መሆኑ ከሚያሳይ በስተቀር ሥራ እየሠራ እንዳልሆነ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ ይዞታቸው ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ሥራ ከመሥራቱ ውጪ ትኩረት ሰጥቶ ውጤት ያለው ምርመራ እየሠራ አለመሆኑን አክለዋል፡፡ ደንበኛቸው የሠሩት ወንጀል ካለ ተለይቶና አንድ ሁለት ተብሎ ሊቀርብ ይገባል እንጂ፣ የኦዲት ሥራ የሚመስል ሪፖርት በየጊዜው ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አቶ ያሬድ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሠሩት ከኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ለሁለት ዓመታት ብቻ በመሆኑ፣ በዚህ ወቅት የሠሩት ወንጀል ካለ ተለይቶ መቅረብ እንዳለበትም ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ አንድን ነገር በተለያየ መዝገብ ለሚያቀርባቸው ተጠርጣሪዎች ሁሉ ለጊዜ መጠየቂያ እያቀረበ መሆኑን የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ለምሳሌ ያህል በተቋሙ ውስጥ አደገኛ መርዝ ስለመገኘቱ፣ ከተጎጂዎችና ከቤተሰቦቻቸው በማስፈራራት ስድስት ሚሊዮን ብር እና 200,000 ዶላር ተቀብለው ለግል መጠቀሚያ ስለማድረጋቸው አውስተዋል፡፡

አንድ ድርጊት በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ በጅምላ እየተገለበጠ መቅረቡ ተገቢ አለመሆኑን፣ ወንጀል በባህሪው ግላዊ በመሆኑና በአንድ ወቅት ሕጋዊ የነበረን አሠራር ወንጀል እንደሆነ ተወስዶ በቡድን ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂዎችን ቃል መቀበል›› እየተባለ ተቆጥሮ የማያልቅና ማባሪያ የሌለው ሥራ መሥራት ሌላው ቢቀር እንደሚያስተዛዝብ ጠቁመዋል፡፡ ደንበኛቸው ገና በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ፣ በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት የተጠረጠሩበት ወንጀል በሚገባቸው ቋንቋ ተገልጾላቸው የእሳቸውን ግላዊ መረጃ (Profile) መጠየቅ ቢኖርባቸውም፣ እስካሁን አለመጠየቃቸውንና የተከሳሽነትም ቃል አለመስጠታቸውን በመግለጽ፣ እየተሠራ ያለው ምርመራ በአግባቡ ካለመሆኑም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድ እንደማይገባ ገልጸው፣ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

የጠበቆቹን የክርክር ሒደት የሰማው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት፣ ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡ በጠበቆች እንደተገለጸው መርማሪ ቡድኑ በአንድ ቀጠሮ ያቀረበውን የምርመራ ጅምር በቀጣይ ቀጠሮ የት እንዳደረሰው፣ ማለትም ምርመራው ስለመጠናቀቁ ወይም ስለቆመበት ሁኔታ ሳይናገር ሌላ የምርመራ ሒደት ይዞ እንደሚቀርብ ገልጿል፡፡ በተቋሙ ተገኘ ስለተባለው አደገኛ መርዝ ማስረጃ ማሰባሰብ፣ የተጠርጣሪውን ባለቤት እናት የሀብት ምንጭ ማጣራት፣ ጭካኔ በተሞላበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሕይወታቸው ያለፈ ግለሰቦች አስከሬን ምርመራ ውጤት ማቅረብና የመሳሰሉት የምርመራ ሒደቶች ምን ላይ እንደደረሱ መርማሪ ቡድኑ አለማስረዳቱን ጠቁሞ፣ ‹‹የት ደረሱ?›› ሲልም ጠይቋል፡፡ ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ብቻ እያቀረቡ አንዱን በመያዝና አንዱን በመጣል ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ጊዜ ይፈቅዳል የሚል እሳቤ ይዘው የሚሠሩ ከሆኑ ትክክል አለመሆኑንም ተናግሯል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በጠበቆቹና ፍርድ ቤቱ ለተነሱ መከራከሪያ ሐሳቦችና ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በደኅንነት ተቋም ውስጥ የተገኘን መርዝ በሚመለከት ላነሳው ጥያቄ፣ ከተቋሙ ውስጥ በማውጣት ወደ ፌዴራል ፖሊስ ፎረንሲክ ወንጀል ምርመራ መወሰዱንና ለማስመርመር በተደረገው ጥረት ማሽን ሊያነበው አለመቻሉን ተናግሯል፡፡ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሎ በመፈራቱና መጀመርያ ወደ ጨረራ መለኪያ ተቋም ተልኮ ምላሽ እየተጠበቀ እንጂ፣ ምርመራው አለመቋረጡን አስረድቷል፡፡ የአቶ ያሬድ ባለቤት እናት ሀብት ምንጭን በሚመለከትም ከተቋማት ጋር የደብዳቤ ልውውጥ ማድረጋቸውንና በሒደት ላይ እንደሚገኝም አስረድቷል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች ደንበኛቸው በተቋሙ መሥራታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሯል ማለታቸው ተገቢ እንዳልሆነና መርማሪ ቡድን እነሱ እንዳሉት ሪፖርት አለማቅረቡን፣ ነገር ግን በዚያ ተቋም ውስጥ በሚሠሩበት ጊዜ ከአለቃቸውና አሁን በመፈለግ ላይ ካሉት ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በመመሳጠር የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውንና ማስፈጸማቸውን እንዳስረዳ ተናግሯል፡፡ ተጠርጣሪው እንደተያዙ የግል ሕይወታቸውን በሚመለከት በወቅቱ ተጠይቀው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊቀበላቸው እንዳልቻለም መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ጠበቆቹ ቀደም ብሎ የቀረበ ምርመራ እየገለበጠ ይቀርባል የሚሉትን ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ዓይቶ ማረጋገጥ እንደሚችል፣ የምስክርነት ቃል መቀበል፣ ተጠርጣሪውንና ሥውር እስር ቤቶችን በተጎጂዎች ማስለየት የተለያዩ ሥራዎች መሆናቸውንም መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

አቶ ያሬድ ስድስት ሚሊዮን ብርና 200,000 ዶላር ለግል ጥቅማቸው ወስደዋል ስለመባሉ መርማሪ ቡድኑ እንዳስረዳው፣ ገንዘቡ በበታች ሠራተኞች እንዲወሰድ ያደረጉት እሳቸው መሆናቸውንና በመመሳጠር በጋራ የተጠቀሙበት መሆኑን ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...