Monday, June 17, 2024

ከታሪክ አለመማር የአገር ራዕይ ያጨናግፋል!

የዘመነ መሳፍንት ሥርዓትን በመናድ የማዕከላዊ መንግሥት ምሥረታን የጠነሰሱትና ለዘመናዊ ኢትዮጵያ ግንባታ መሠረት የጣሉት አፄ ቴዎድሮስ 200ኛ ዓመት የልደት በዓል በሚዘከርበት ሰሞን፣ አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን እያወሱ የጊዜው ሁኔታ ላይ መነጋገር የግድ ይላል፡፡ ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም. ተወልደው ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታላቁ ኢትዮጵያዊ ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ፣ አገራቸውን ኢትዮጵያ በዘመኑ ከሠለጠኑ አገሮች ተርታ ለማሠለፍ ትልቅ ራዕይ አንግበው ቢነሱም በአጭሩ የተቀጩ የአገር ባለውለታ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን በጊዜው እሳቸው ያሰቡት የአገር ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ባይሳካም፣ እሳቸው የጣሉት መሠረት ግን በቀጣዩ ትውልድ ተቀባይነት አግኝቶ ከበርካታ ችግሮች ጋር እዚህ ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡ እስረኞችን ለማስፈታት በእንግሊዝ መንግሥት ተልኮ ከመጣው ጄኔራል ናፒየር ጋር ተዋግተው ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ የጻፉለትን ደብዳቤ፣ ለዚህ ዘመን ትውልድ የታሪክ ተመራማሪው ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) አስነብበዋል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ታሪካዊ ደብዳቤ ከያዛቸው ቁምነገሮች መካከል አንዱ ይኼንን ዘመን ለመመርመር ያስገድዳል፡፡ ባለራዕይ ጀግና ሲታሰብ ያለንበትን ጊዜ አለመመርመር ልክ አይሆንም፡፡

አፄ ቴዎድሮስ በእሮጌ ጦርነት ተሸንፈው የጄኔራል ናፒየር ጦር የመቅደላን ምሽግ ሲደበድብ ሕልፈታቸውን በመረዳት ካሠፈሩት መልዕክት መካከል፣ ‹‹… ያረመኔ አገር ነውና ያገሬ ሰው ገብር፣ ሥራት ግባ ብዬ ብለው እንቢ ብሎኝ ተጣላኝ፡፡ እናንተ ግን በሥራት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ…›› የሚል ቁጭት የተሞላበት አባባል ይገኝበታል፡፡ በዘመነ መሳፍንት አገሪቱን እንደ ቅርጫ ተቃርጠው በየጎጡ በነገሡ መሣፍንትና ባላባቶች ተቀጥቅጦ ይገዛ የነበረ ሕዝብን ወደ ሥልጣኔ ለማምጣት ያደረጉት ትግል ከሽፎ፣ በገዛ ሹጉጣቸው ራሳቸውን አጥፍተው ከማለፋቸው በፊት የጻፉት ይህ ኑዛዜ ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮችንም ይዟል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ፣ ‹‹…ያገሬ ሰው የፈረንጅ ሃይማኖት ይዟል፣ አስልሟል እያለ አሥሩን ምክንያት ይሰጠኝ ነበረ፡፡ እኔ ከከፋሁበት እግዚአብሔር መልካሙን ይስጠው፡፡ እንደ ወደደ ይሁን፡፡ እግዚአብሔር ቢሰጠኝ ሁሉን ልገዛ አሳብ ነበረኝ… እንኳንስ የሐበሻ ጠላቴን እየሩሳሌም ዘምቼ ቱርኮችን አስለቅቃለሁ መስሎኝ ነበር…›› ሲሉም የገጠማቸውን ፈተና ከራዕያቸው ጋር ገልጸው ነበር፡፡ በዚያ የጨለማ ዘመን ታላቅ ህልም የነበራቸው ሰው በአጭሩ መቀጨታቸው ያስቆጫል፡፡ ዛሬም የሚያስቆጩ ድርጊቶችን እያየን ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ እንዳሉት በሥርዓት ሆኖ አገርን መገንባት እየከበደ ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡

ይህች ታሪካዊት አገር የአሁኑን ቅርፅ በመያዝ እንደ አገር የቆመችው በአፄ ቴዎድሮስ ፋና ወጊነት ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ የመጡት መሪዎች በተቻላቸው አቅም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገው አገር አቁመዋል፡፡ የአገር ግንባታው ጉዳይ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባይገኝምና በርካታ ውጣ ውረዶች ቢታዩም፣ እንደ ቀደምቶቹ ትውልዶች የአገር ፍቅርና ወኔ ካለ የታሪክ አደራን መወጣት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሟትን መልካም አጋጣሚዎች ለመጠቀም ባለመቻሏ፣ የአገር ግንባታው በሚፈለገው መንገድ አልተከናወነም፡፡ ሌላው ቀርቶ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከተለወጠ ወዲህ ያሉትን 45 ዓመታት ብናስተውል፣ ኢትዮጵያ ምን ያህል ዕድለ ቢስ አገር መሆኗን መረዳት አያዳግትም፡፡ ለአገር ታላቅ ራዕይ የነበራቸው ኢትዮጵያውያን እየተገደሉ፣ እየታሰሩና እየተሰደዱ የባከኑት ዓመታት ያተረፉት አገርን ወደ ገደሉ ጫፍ መግፋት ነበር፡፡ ባለፉት 27 ዓመታትም የጋራ የሆነ ራዕይና ግብ ስላልነበረና ችግሮችም በስፋት በመቀጠላቸው፣ አገሪቱን አደገኛ ቀውስ ውስጥ የሚከት ታላቅ ነውጥ ተፈጥሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በእስር ቤት ከፍተኛ ሥቃይ የደረሰባቸው ወገኖችም ብዙ ነገሮች በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ አገርን በተባበረ ክንድ ከመገንባት ይልቅ የጉልበት መንገድ በመመረጡ የደረሰው ሰቆቃ በፍፁም አይዘነጋም፡፡ አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር የመጣውም በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ነበር፡፡ ከታሪክ መማር ባለመፈለጉ ነው ያ ሁሉ ትርምስ ተፈጥሮ እዚህ ጊዜ ላይ የተደረሰው፡፡

ካለፉት ዘጠኝ ወራት ወዲህ ደግሞ አገር አዲስ የለውጥ ንፋስ ሽው ቢልባትም፣ የተጀመረው ለውጥ ግን በማዕበል እንደሚንገላታ ጀልባ ፈተናው በዝቷል፡፡ በለውጡ አማካይነት በብዙ ሺሕ  የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ተፈተው፣ ነፍጥ አንግበው በረሃ የገቡና በስደት የነበሩ ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ተጠርተው፣ ለሃያ ዓመታት የቆየው የኢትዮጵያና የኤርትራ ፍጥጫ ረግቦ ሰላም ተፈጥሮ፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ጋሬጣ የሆኑ ሕጎች እንዲሻሻሉ ጥናት እየተደረገ፣ በጠላትነት ከመተያየት በመውጣት በፍቅርና በመተሳሰብ እንኑር እየተባለ፣ ከመከፋፈል ይልቅ በአንድነት መኖር ያዋጣል ተብሎ እየተለፋ፣ ወዘተ እየተገኘ ያለው ምላሽ ግን አስደንጋጭ ነው፡፡ በየቦታው ግጭት እየቀሰቀሱ ንፁኃንን መፍጀት፣ የገዛ ወገንን ማፈናቀል፣ የአስተዳደር ተቋማትን ማፍረስ፣ ባንኮችን በጦር መሣሪያ መዝረፍ፣ ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎችን እየዘጉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማሽመድመድና በአጠቃላይ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የማይጠቅሙ ድርጊቶች ተበራክተዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከዛሬ 151 ዓመት በፊት፣ ‹‹…ያረመኔ አገር ነውና ያገሬ ሰው ገብር፣ ሥራት ግባ ብዬ ብለው እንቢ ብሎ ተጣላኝ፡፡ እናንተ ግን በሥራት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ…›› ያሉት ብሶት በዚህ ዘመን እየተደገመ ይመስላል፡፡ ራዕይ አልባዎች ባለ ራዕዮችን የሚያዋክቡበት እዚህ ጊዜ ላይ ሆኖ የታሪክ መደገምን ማሰብ አለመቻል ዕብደት ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሕዝብ የማንኛውም ችግር ምንጭ አይደለም፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የችግሮች መነሻ የዘመኑ ልሂቃን ነበሩ፡፡ አሁንም የችግሮች ጠንሳሾች ልሂቃን ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሆን ብለው አገርን ለማተራመስ አጀንዳ የያዙ በሥልጣን ጥም የተቃጠሉ ልሂቃን ሲኖሩ፣ የእነዚህን አጉል ጀብደኝነት በለዘብተኝነት የሚያዩ ልሂቃን አሉ፡፡ እውነቱን አንነጋገር ከተባለ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች አገር አፍራሾች የበላይነቱን የሚይዙት፣ የታሪክ አደራ እንዳለባቸው የዘነጉ ልሂቃን ችላ በማለታቸው ነው፡፡ አሁንም ካለፈው ስህተት በመማር ለአገራቸው መልካም ራዕይ የሰነቁ ወገኖችን ለማገዝ ጊዜው አልረፈደም፡፡ በሥልጣን ጥም ያበዱ አተራማሾች በፈለጉት ሥፍራ እንደ ጊዜ ቦምብ ግጭት እያፈነዱ አገር ሲያተራምሱ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሊያስቆሟቸው ይገባል፡፡ ትናንት በሕዝብ መስዋዕትነት ነፃ የወጡ ፖለቲከኞች እንዳሻቸው እየፈነጩ አገርና ሕዝብን ሲያምሱ ዝም ማለት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ትግል የማይመጥኑ ራስ ወዳዶች የባለ ራዕዮችን ህልም ማምከን የለባቸውም፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ህልም በአጭሩ የተቀጨውና ለሕልፈት የተዳረጉት፣ ዛሬ አገሪቱን በገጠማት ዓይነት ሁኔታ ነበር፡፡ ከታሪክ አለመማር የአገር ራዕይ ያጨናግፋል እንዲሉ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...