Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩ ተጠርጣሪ በ100 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ትዕዛዝ...

በኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩ ተጠርጣሪ በ100 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ትዕዛዝ ተሰጠ

ቀን:

በሜቴክ ጉዳይ ተጠርጥረው የታሰሩ ተጠርጣሪ የ50 ሺሕ ብር ዋስ ተፈቀደላቸው

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከሁለት ወራት በላይ በእስር የቆዩት የኢትዮ ቴሌኮም የኤንጂፒኦ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኢሳያስ ዳኛው በ100 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ሰኞ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

አቶ ኢሳያስ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና በአሁኑ ጊዜ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም ሲሆኑ፣ ተጠርጥረው ለእስር የበቁትም ከወንድማቸው ጋር በጥቅም በመመሳጠር የኢትዮ ቴሌኮምን ሥራ ያለ ጨረታ በሌላቸው ሥልጣን ለሜቴክ ሰጥተዋል ተብለው መሆኑን መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

ለኢትዮ ቴሌኮም በሶማሌ ክልልና በባሌ ዞን የሞባይልና ሲዲኤምኤ ማማ (ታወር) ተከላ ጨረታ በማውጣት አወዳድረው መስጠት ሲገባቸው፣ አቶ ኢሳያስ በ204,981,630 ብር ለማስተከል ከሜቴክ ጋር ውል ከመፈጸማቸውም በተጨማሪ ሥልጣኑ ሳይኖራቸው ውሉን በማሻሻል 322,628,124 ብር ለፋይናንስ ደብዳቤ በመጻፍ ሜቴክ እንዲከፈለው ማድረጋቸውን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ ከርሟል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ መመርያ መሠረት ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ውል ሲፈጸም ቦርዱ ማወቅ እንዳለበት የተደነገገ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪው ለቦርዱ ሳያሳውቁ መመርያውን በመጣስ ውል በማሻሻል የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነበር፡፡

አቶ ኢሳያስ በጠበቆቻቸው አቶ ዘረሰናይ ምስግናና አቶ ሀፍቶም ከስተ አማካይነት ባቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ደንበኛቸው ሥራቸውን ያከናወኑት ሕጉንና መመርያውን ተከትለው ነው፡፡ በመጀመርያ የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ታወር ተከላ ሊካሄድባቸው የታሰቡት ቦታዎች የፀጥታ ችግር ስለነበረባቸው ተከላውን ሜቴክ እንዲያከናውን ጥያቄ ያቀረበው፣ ኢትዮ ቴሌኮም ተጠሪ የሆነበት መሥርያ ቤት ሚኒስትር መሆናቸውን አስረድቷል፡፡ ይኼ እንኳን ባይሆን የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ ከአንድ የመንግሥት ተቋም ጋር ያለ ምንም ጨረታ ግዢ መፈጸም እንደሚፈቅድ በማስታወስ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ማኔጅመንት በፍራንስ ቴሌኮም ሲተካ፣ ቀድሞ የነበረው ቦርድ መመርያዎችን በማሻሻል አንድ ዳይሬክተር ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጸሙ ግዥዎችን (የሥራ ውሎችን) ማሻሻልና መዋዋል እንደሚችል ስለሚፈቅድ፣ ደንበኛቸው ከሜቴክ ጋር የነበረውን የውል ማሻሻያ ያደረጉት በሌላቸው ሥልጣን ሊያስብል እንደማይችል ጠበቆቹ ተከራክረዋል፡፡ ሥራውም 92 በመቶ አፈጻጸሙ ጥሩ መሆኑ ተገልጾ፣ መሻሻል ያለበት ወይም ጥሩ አፈጻጸም የለውም የተባለው ስምንት በመቶ ሥራ ክፍያ ተቀንሶ ሌላው ክፍያው መፈጸሙን አክለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በተጠርጣሪው ላይ የምስክሮችን ቃል ከክልልና ከአዲስ አበባ በመቀበል ላይ መሆኑንና ገና ሊቀበል መሆኑን በመግለጽ፣ ከሜቴክ ኦዲት እያሠራ መሆኑን ከኢትዮ ቴሌኮም ክፍያ የተከፈለበትንና ላልተሠራ ሥራ ክፍያ የተቀነሰበትን የሚያሳዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ጠይቆ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ከማስረዳት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ ከርሟል፡፡

ከሁለት ወራት በላይ የምርምራ ሒደቱን ሲከታታል የከረመው ፍርድ ቤቱ፣ መርማሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ የኦዲት ሪፖርት እንደሚቀርብ፣ ተጨማሪ የምስክሮች ቃል እንደሚቀበል ቢገልጽም ተጠርጣሪው ሥራውን ያለ ጨረታ ስለመስጠታቸውና ከወንድማቸው ጋር ስለመመሳጠራቸው የሚያስረዳ የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉን ጠቁሞ፣ አቶ ኢሳያስ በዋስትና እንዲለቀቁ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪው በ100 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲለቀቁና ከአገር እንዳይወጡ ለኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መምርያ የዕግድ ደብዳቤ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩትና በግዳጅ በደቡብ ሱዳን አቢዬ ግዛት የነበሩት ኮሎኔል ካሳ ሮባ ተጠርጥረው ከታሰሩበት የሙስና ወንጀል በ50 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ተጠርጠሪውን ለእስር ያበቃቸው ከሠራዊቱ በጡረታ ከተገለሉ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ቁርጥራጭ ብረቶችን ማሰባሰብና መልሶ መጠቀም ኮርፖሬት የሎጂስቲክስና ሰፕላይ ማኔጅመንት ማርኬቲንግ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ፈጽመውታል ከተባለ የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ነው፡፡

ተጠርጣሪው በኮርፖሬሽኑ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፣ እንዲሠሩ የተሰጣቸውን ቁርጥራጭ ብረታ ብረት የመሰብሰብና መልሶ የመጠቀም ሥራ፣ ባልተሰጣቸው ሥልጣን በሥራቸው ማኅበራትን በማደራጀትና በጥቅም በመመሳጠር ሥራውን አሳልፈው መስጠታቸውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪው ከፍተኛ የሆነ ክፍያ ለማኅበራቱ እንዲከፈላቸው በጽሑፍ በማዘዝና በማስከፈል በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ በማስረዳት ተጨማሪ የምርመራ ሥራዎችን ለመሥራት ተጨማሪ ጊዜ ሲጠይቅባቸው ቆይቷል፡፡

ተጠርጣሪው በራሳቸውና በጠበቃ በመታገዝ ባቀረቡት የመከራከሪያ ሐሳብ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ የነበሩት በግዳጅ ላይ ደቡብ ሱዳን ነበር፡፡ በወንጀል መጠርጠራቸውን የቅርብ አለቃቸውን ነግረዋቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ሲጠይቋቸው፣ ያለ ምንም ማንገራገር ያለ አጃቢ መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው ወደ ሕግ ይመጣሉ እንጂ ሕግ ወደ እሳቸው እንዲመጣ እንደማፈልጉ የተናገሩት ኮሎኔል ካሳ፣ የፈጸሙት ወንጀልና የሚያስፈራቸው ጉዳይ ቢኖር ኖሮ በእጃቸው ላይ የአንድ ዓመት መጠቀሚያ ቪዛ ስለነበራቸው ወደፈለጉበት አገር መሄድ ይችሉ እንደነበር ለፍርድ ቤቱ ጠቁመው፣ ሲሠሩ የከረሙት በተቋሙ መመርያና በአለቆቻቸው ትዕዛዝ መሠረት መሆኑን ተናግረው ‹‹እኔ ወታደር ነኝ፣ ፈጽሞ የተባልኩትን መፈጸም ነው፣ ባልፈጽምስ ኖሮ?›› በማለት ጠይቀው እንደመጡ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ተይዘው ቤተሰቦቻቸውን እንኳን ሳያዩ መታሰራቸውን ባይቃወሙም፣ የዋስትና መብታቸው ግን እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ዋስትናውን ተቃውሞ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቢጠይቅም የግራ ቀኙን ክርክር ሲሰማ የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ተረኛ ችሎት፣ ተጠርጣሪው በዋስትና እንዲለቀቁ መወሰኑን ሰኞ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪው በ50 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁና ከአገር እንዳይወጡ ለኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መምርያ የዕግድ ደብዳቤ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...