Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርየጉምሩክ ሕግ ማስከበር ሥራ ከትናንት እስከ ዛሬ

የጉምሩክ ሕግ ማስከበር ሥራ ከትናንት እስከ ዛሬ

ቀን:

ይህ ጽሑፍ በቅርቡ የጉምሩክ ኮሚሽን ተቋቁሞ የራሱ ጉምሩክ ፖሊስም እንደሚኖረው በመገለጹ፣ እኔም በመሥሪያ ቤቱ ለረዥም ዓመታት በማገልገሌ ያለኝን ልምድና ዕውቀት ባካፍል ሊጠቅም ይችል በሚል የተጻፈ ነው፡፡

ቀድሞ የነበረውንና አሁን የሚታየውን ኮንትሮባንድ የመከላከል ሥራ በማነፃፀር መጪው የጉምሩክ ፖሊስ በምን መልኩ መደራጀትና መተዳደር አለበት የሚል ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

የቀድሞው ጉምሩክ ፖሊስ

- Advertisement -

ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የቀድሞውን ጦር ሠራዊት፣ ፖሊስና ደኅንነት መሥሪያ ቤቶችን አፍርሶ ሲበትን፣ በዚህ ዕርምጃ ሳይነካ የተረፈው መለዮ ለባሽ ክፍል የፊናንስ ፖሊስ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ሠራዊት እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ በሥራው ላይ ቆይቶ ሲበተን፣ በምትኩ የጉምሩክ ፖሊስ ተብሎ የሚጠራ አዲስ ኃይል ተቋቋመ፡፡ ይህ የጉምሩክ ፖሊስ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን (በወቅቱ አጠራር) ሕግ ማስከበር መምሪያ ሥር የሚተዳደር ሆኖ ከመላው ክልል በተመለመሉ ወጣቶች የብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር የተመሠረተ ነበር፡፡

በሠራዊቱ የምልመላ መሥፈርቱ መሠረት በጽሑፍ ፈተና ተወዳድረው ያለፉና በኅብረተሰቡ መካከል መልካም ሥነ ምግባር እንዳላቸው በቀበሌ ተገምግመው የተመረጡ ወጣቶች ነበሩ የሚቀላቀሉት፡፡ የጉምሩክ ፖሊስ ሥልጠናውን አጠናቆ ወደ ሥራ ሲሰማራ በቂ ትጥቅ፣ ተሽከርካሪ፣ መጠለያ ካምፕ፣ አልባሳትና ሌሎችም የሎጅስቲክስ አቅርቦቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ፣ ብሎም ከተሰማራበት ሰፊ የሥራ ቀጣና ጋር የማይመጣጠን የሰው ኃይል ይዞ ቢንቀሳቀስም ኮንትሮባንድን በመከላከል በኩል ከፍተኛ ውጤት ሲያስመዘግብ ቆይቷል፡፡

የውጤታማነቱን ያህል ግን ትኩረት አልተሰጠውም ነበር፡፡ ምናልባትም በዓለም የውትድርና ታሪክ በዘጠኝ ዓመታት አገልግሎት ውስጥ አንድም የሠራዊት አባል ምንም ዓይነት ወታደራዊ ማዕረግ ሳያገኝ የቆየበት የሠራዊት ክፍል ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ሁሉም የጉምሩክ ፖሊስ አባል ‹‹ወታደር›› በሚል ማዕረግ ሲጠራ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሕግ የተፈቀደለትን የያዥ አበል እንደ ሥራው መጠን እንዳይከፈለው ሲደረግ ነበር፡፡ ሌሎች በርካታ አስተዳደራዊ በደሎችም ሲደርሱበት ነበር፡፡

 በመጨረሻም አቶ መላኩ ፈንታና ምክትላቸው አቶ ገብረዋህድ ገብረ ጊዮርጊስ ወደ መሥሪያ ቤቱ መምጣታቸውን ተከትሎ ለሲቪል ጉምሩክ ሠራተኞች ከፍተኛ የደመወዝ ጭማሪ ሲደረግ፣ የጉምሩክ ፖሊስን ግን በአዋጅ እንዲፈርስና ኮንትሮባንድ የመከላከል ሥራውም ለፌዴራል ፖሊስ በአደራ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

ኮንትሮባንድን መከላከል በአሁኑ ወቅት ምን ይመስላል?

ዛሬ በገሃድ እንደሚታየው የኮንትሮባንድ ፍሰት በዓይነትም በብዛትም ጨምሮ የተገኘበት አንዱ ምክንያት፣ በሥራው የካበተ የመከላከልና የመቆጣጠር ልምድና ክህሎት ያለውን የራሱን ሠራዊት በትኖ ለሥራው ባዳ በሆነ፣ ተቋማዊ ተልዕኮውም በሌላ አካል እንዲመራ በመደረጉ ነው፡፡

ኮንትሮባንድን እንዲከላከል በተመደበው ኃይል ውስጥ ከታች እስከ ላይ በተዘረጋው የዘረፋ መረብ የአገሪቱ ሀብት በሕገወጥ ይወጣል፡፡ ቀረጥ ያልተከፈለበትና እንዳይዘዋወር ገደብ የተጣለበት ሸቀጥ፣ መድኃኒትና የጦር መሣሪያ በገፍ ይገባል፡፡ በአንድ ጊዜ ብቻ ከ500 በላይ የቁም ከብት ለጥ ባለው የጅግጅጋ ሜዳ እየተነዳ ሶማሌላንድ ሲገባ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የጫኑት ምን እንደሆነ የማይታወቅ በርካታ ትልልቅ መኪኖች ሸራ እንዳሰሩ ድንበር አቋርጠው በሠልፍ ከየአቅጣጫው የሚገቡት፣ ይህን እንዲከላከል ከተመደበው ኃይል ፈቃድና ይሁንታ አግኝተው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከኮንትሮባንድ አዘዋዋሪዎች ጋር በጥቅም የተሳስረው ቡድን ከታች እስከ ላይ በዘረጋው መረብ አማካይነት የፈረጠመ በመሆኑ፣ ኮንትሮባንድ ለመያዝ የሚሞክር አባልን በግልጽ ያስራል፣ ይገመግማል፣ ከሥራ ያባርራል፡፡

ለአብነት ያህል በሕገወጥ ከአገር ሊወጣ የነበረን 400 ሺሕ ዶላር ጥሬ ገንዘብ ቶጎጫሌ ድንበር ላይ በቁጥጥር ሥር አውሎ ለጉምሩክ ያስረከበው የፖሊስ አባል፣ በማዕከላዊ እንዲታሰርና ከሥራም እንዲባረር ተደርጓል፡፡ የበቀል አርጩሜው ከእሱ አልፎ ዶላሩ እንዲያዝ ጥቆማ ያቀረበው ግለሰብም በሕግ የተፈቀደውን የጠቋሚ አበል ክፍያ እንዳያገኝ ተከልክሏል፡፡ በዚህ መሰል ምክንያት ዛሬ ኮንትሮባንድን መያዝ በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ ፍልሰቱ ጨምሮ፣ የመከላከል ኃላፊነት ለተጣለባቸውም የሀብት መበልፀጊያቸው የሆነበት አግባብ የሚያስጠይቅ መሆኑ ዘበት ሆኗል፡፡

ከዚህ በኋላስ?

በቅርቡ የጉምሩክ ኮሚሽን እንደተቋቋመና የራሱ ጉምሩክ ፖሊስም እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ ለዚህ ውሳኔ የተደረሰው ከላይ ለመግለጽ የሞከርኩትን ችግር በሚገባ በመረዳት እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ሆኖም ግን አዲስ የሚቋቋመው የጉምሩክ ፖሊስ ተጠሪነቱ ለፌዴራል ፖሊስ እንዲሆን መታሰቡ ያለፈውን ስህተት መድገም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ላለፉት ዓመታት ኮንትሮባንድን የመከላከል ሥራ የተሰጠው ለፌዴራል ፖሊስ እንደሆነ ይታወቃልና ነው፡፡ ችግር መበራከቱ ከታመነበት ደግሞ በዚያው አሠራር መቀጠል መፍትሔ አያመጣም፡፡

ከዚያ ይልቅ አዲስ ሊቋቋም የታሰበው የጉምሩክ ፖሊስ በራሱ የጉምሩክ ኮሚሽን የሕገ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ሥር ሆኖ ቢደራጅ ቀጥተኛ የዕዝ ሰንሰለት ስለሚኖር ቀልጣፋና ውጤታማ አሠራር እንዲኖር ያስችላል፡፡ የቁጥጥርና ግምገማ ሥርዓቱንም ለመተግበር ይረዳዋል፡፡ ለፖሊሱም የራሴ መሥሪያ ቤት የሚል የእኔነት ስሜት ስለሚፈጥርለት የተቋሙን ዓላማ፣ ራዕይና ተልዕኮ ተገንዝቦ ሥራውን በሞራል እንዲወጣ ይረዳዋል፡፡

ምናልባት የጉምሩክ ፖሊስ በጉምሩክ ኮሚሽን ሥር መሆኑ ከሌሎች የጉምሩክ ሲቪል ሠራተኞች ጋር ተስተካካይ ደመወዝ ጥያቄ ያስከትላል የሚል የአስተዳደር ወጪ ሥጋት ካለም፣ ሌላ መፍትሔ መፈለግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ደመወዙን በፌዴራልና በክልል ፖሊስ የደመወዝ ስኬል መሠረት በማድረግ፤ ነገር ግን ከሥራው አጠቃላይ ባህሪይ አንፃር የያዥ አበል ክፍያን መፍቀድና እንደ ሥራው ውጤት መጠን ክፍያ እንዲያገኝ ማድረግ አንድ አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡

ሌላው ምክረ ሐሳብ፣ አዲሱ የጉምሩክ ፖሊስ የራሱ የሆነ ዓርማ፣ መለዮና ደንብ ልብስ ኖሮት በሚገባ የታጠቀና በሎጀስቲክ የተደራጀ የጉምሩክና የድንበር ጠባቂ (Customs and Border Guard) ኃይል መልክና ቁመና ያለው ሆኖ የተደራጀ ውጤታማ ሠራዊት መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀድሞ የነበሩትን የጉምሩክ ፖሊስ አባላት መልሶ በመጥራትና በአመራር ቦታ በመመደብ ያላቸውን ልምድና ክህሎት መጠቀም ለመሥሪያ ቤቱ ዓላማና ተልዕኮ መሳካት ይረዳል እላለሁ፡፡

(ወንደሰን ተክለ ሚካኤል፣ ከአዲስ አበባ)

***

የህልውናችን ምሰሶዎች

ኢትዮጵያ የ3,000 ዓመታት ታሪክ እንዳላት ይነገራል፡፡ ሕልውናችን እንዲህ ዕድሜ ጠገብ በመሆኑ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም ሕልውና የተፈጥሮ ፀጋ ናትና፡፡ ደስታ ጊዜያዊ ነው፡፡ ዘላለማዊ ደስታ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ የትኛውም ፍጡር ዕውቀትና ፍቅር እንዳለው ይነገራል፡፡ የአሁኑ የሰው ዝርያ 150 ሺሕ ዓመታት በምድር ላይ ቆይቷል ይባላል፡፡ ነባራዊው የተፈጥሮ ሒደት ለሰው ያስባል ወይም ያደላል ለማለት ግን ያስቸግራል፡፡

ፍጡራን ሦስት የሕልውና መሰናክሎች አለባቸው፡፡

  1. ፍጡር እንደ ምግብ ሰንሰለቱ እርስ በርሱ ይባላል፡፡ አንዱ ፍጡር በሌላው ሕይወት ላይ ይዘልቃል፡፡ በዚህ ምክንያት ዘር ይመናመናል፡፡
  2. ትውልድ ሁሉ ለኑሮው ከሚያስፈልጉት ነገሮች በላይ እየተዋለደ ይባዛል፡፡ ይህም ለማኅበረሰብ መረጋጋት ትልቅ እንቅፋት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡
  3. ፍጡር ሁሉ ለምግብ፣ ለውኃ፣ ለቦታ ወዘተ. ሲል እርስ በርሱ ይሻኮታል፡፡ ሽኩቻው በቅርብ ዘመዳሞች ወይም ወንድማማቾች መካከል የበለጠ ይግላል ይባላል፡፡ ይኸውም አስተሳሰባቸው፣ ፍላጎታቸውና ልማዳቸው ስለሚመሳሰልና ስለሚቀራረብ ነው፡፡

ሰው እንደ ግለሰብ ተወልዶ እንደ ማኅበረሰብ ይኖራል፡፡ ሰላማዊና ደስተኛ ኑሮ ሊያገኝ የሚችለው ግን የሕዝብ ብዛቱን ከተፈጥሮ ሀብቱ ጋር ሲያጣጥምና ማኅበረሰባዊ ግንኙነቱንም በሕግ የበላይነት፣ በእኩልነትና በነፃነት ሲያዳብር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በረዥሙ ውጣ ውረድ ታሪካችን ውስጥ እነኚህን ተግባራት በቅጡ ማወቅም ሆነ መከወን አልቻልንም፡፡ ለም አፈራችን ታጥቦ፣ ድንጋዩ ገጦ፣ ዕፅዋት ቀጭጨው፣ እንስሳት ኮስሰው እኛም ተኮራምተን ቆይተናል፡፡ መሪዎቻችን እንዳሻቸው እየገዙን በማያቋርጥ የእርስ በርስ ሽኩቻና ግጭት ውስጥ ስንተራመስ ቆይተናል፡፡

ከሠለጠነው ዓለም አኳያ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የታሪክ ዕድሜ ቢኖረንም፣ እነሱም እንደኛ ሲማስኑ ኖረው የኋላ ኋላ በዴሞክራሲ ሥርዓት ታንፀውና በሥልጣኔ ተመንድገው ኑሯቸውንና ዕድሜያቸውን በማሻሻል በዕውቀት ጎዳና ምድርንና ህዋውን እንዳሻቸው ሲዘውሩት ይታያሉ፡፡ የተሻለ ኑሮ ለመቋደስ ፈለጋቸውን ብንከተል ይጠቅመናል፡፡ ችግሩ ግን ዕውቀት ያጥረናል፡፡ አዲስ ነገር መፍጠሩ ቀርቶ ኮርጀንም አልቻልንበትም፡፡ የሥልጣኔ ውጤቶችን በደስታ እየተቋደስን ዕውቀትንና አዋቂውን ግን እናናንቃለን፡፡ በሳይንስ የሚደካሄደው የዕውቀት ፍለጋ ትኩረት አንድ ነገርን ለማወቅ ነው፡፡ ሃይማኖት ግን በተቃራኒ ያጣጥለዋል፡፡

ይህ ዝንባሌ ሐሳብን መግታት ብቻም ሳይሆን፣ በተለዋዋጭ ተፈጥሮ ሕልውናችንን ያሰናክልብናል ብዬ እሠጋለሁ፡፡ ሃይማኖት ስላልተረጋገጠው ፅድቅ ሳይሆን፣ በተፈጥሮ ልዩ ፀጋ ስለሆነችው ሕይወትና ዘላቂነት ተጨማሪ ብርሃን እንዲፈነጥቅልን እሻለሁ፡፡ አውሮፓውያን ሃይማኖተኞች በሳይንስ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ለምሳሌ የፊዚክስ ሊቁ ሰር አይዛክ ኒውተን ያፈለቃቸው የቁስ አካል መገናኛ ሕጎች ይደነቃሉ፡፡ ‹‹አንድ ቁስ አካል በሌላ ቁስ አካል ሲገፋ በተገፋው ኃይል መጠን በተቃራኒው ተመልሶ ይገፋል›› የሚለው ሕግ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ እንዴት እንደሚሠራ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‹‹የዘራኸውን ታጭዳለህ›› በሚል እንደተገለጸ የሚጠቅሱ አሉ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን ሕግ ተጠቅሞ ‹‹ነገርን በነገር አትፍቱ›› በማለት ለሰው ሕልውና እንዳስተማረ ይነገራል፡፡ ሕጉ ለዴሞክራሲ መመሥረት ሲጠቀስ፣ መንኮራኩር ወደ ሕዋ የሚመነጠቀውም በዚህ ሕግ መሠረት እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡

የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የትግል መነሻው በትግራይ በተከታታይ የተከሰተው ድርቅና ረሃብ ነው፡፡ መሳፍንታዊ አስተዳደሩም ችግሩን እንዳባባሰው ይታወቃል፡፡ ሕወሓት በቁጭትና በእልህ ደርግን ተዋግቶና አሸንፎ ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን አስተዳድሯል፡፡ የአገራችን ዋና ችግር አቆርቋዥ አስተዳደር መሆኑን ተረድቶ ረሃብና ጥማቱን ያስታገሰባት ኢትዮጵያ፣ ያሉባትን ችግሮች በአግባቡ ፈትቶ ወደ ብልፅግና ቢያሸጋግራት ኖሮ፣ በአዲስ አበባ ከአፄ ምኒሊክ ጎን የድል ሐውልት ይቆምለት ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አስተዳደር ቢያሰፍን ኖሮ፣ እኩልነትንና ነፃነትን በማስረፅ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያሸጋግረን ነበር፡፡ ያለቅጥ እየተለጠጠ የመጣውን የሕዝብ ብዛትም በቸልተኝነት ከመመልከት ይልቅ ከተመናመነው የተፈጥሮ ሀብታችን ጋር ያጣጥምልን ነበር፡፡ ባለማወቁ ግን ራሱን በራሱ ጥሏል፡፡

ከኢሕአዴግ የወጡትና ለአገራችን ህዳሴ የሚንቀሳቀሱት እነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር)፣ እነ አቶ ለማ መገርሳንና አጋሮቻቸውን ላመሠግን እወዳለሁ፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስፈን ብቻ ሳይሆን፣ መዋለድና ምርታማነታችንን እንዲያጣጥሙልንም አደራ እላለሁ፡፡

 (ፍቅሩ አማረ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...