Saturday, June 22, 2024

ኃላፊነት በጎደላቸው ድርጊቶች ምክንያት አገር አይታመስ!

ሕዝብና አገርን ችግር ውስጥ የሚከቱ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ እነዚህ ድርጊቶች በአመዛኙ እየተፈጠሩ ያሉት ለሕዝብም ሆነ ለአገር ኃላፊነት በማይሰማቸው ወገኖች ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠሩ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ፣ ኢትዮጵያን ከአምባገነናዊ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የሚረዱ በርካታ ወሳኝ ዕርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የተጀመረውን ለውጥ አደጋ ውስጥ የሚከቱ በርካታ ነውጠኛ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ የንፁኃንን ደም በከንቱ ያፈሰሱ ግጭቶች አገርን ቀውስ ውስጥ ከተዋል፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች በመብዛታቸው ሕዝብ ለመከራ ተዳርጓል፡፡ በአገር ውስጥ እንደ ልብ በመዘዋወር ለመሥራት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በአንድ በኩል ልዩነቶችን የፀብና የውድመት መሣሪያ ከማድረግ በሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ለመፎካከር የሚያስችል ዓውድ እንዲፈጠር ተባብረን እንሥራ ሲባል፣ በሌላ በኩል በተለመደው የጉልበተኝነት ባህሪ ‹‹ይለይልን!›› ዓይነት ፉከራና ሽለላ ይሰማል፡፡ ያለፈው አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ ተዘግቶ በተባበረ ክንድ አገርን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እናሸጋግር እየተባለ ተማፅኖ ሲደረግ፣ የዕልቂት ጎዳና የሚያመቻቹ እኩዮች ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶችን እየፈጸሙ ሕዝብ ያሳቅቃሉ፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አዙሪት ውስጥ በፍጥነት መውጣት የግድ ይላል፡፡

በዚህ የለውጥ ጊዜ ችግሮች ማጋጠማቸው የማይቀር እውነት ቢሆንም፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከመጠን በላይ እያጋጋሉ አገርን ቀውስ ውስጥ ለመክተት መጣደፍ ግን ነውር ነው፡፡ በየአካባቢው ማኅበረሰቡ ለሰላሙና ለደኅንነቱ ሲል ነውጠኞችን ፊት መንሳት አለበት፡፡ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የመሳሰሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ዳር ሆነው ከመታዘብ ለአገር የሚበጀውን መላ ማለት አለባቸው፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ ዝግጁ መሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ችግሮች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው የሕዝብና የአገርን ደኅንነት አደጋ ውስጥ እንዳይከቱ ማድረግ ነው፡፡ ችግሮች ካጋጠሙም በተቻለ መጠን ከስሜታዊነት በመራቅ ምክንያታዊ መሆን ይገባል፡፡ ለዚህም ሲባል በማንም ሰው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ፣ የአካባቢ ሰላም እንዳይናጋ መጣር፣ አለመግባባት ሲፈጠርም በውይይት መፍታት፣ እንዲሁም በመከባበርና በፍቅር አብሮነትን ለማጎልበት ትልቅ ትኩረት መስጠት ያሻል፡፡ ኃላፊነት በጎደላቸው ግለሰቦች ወይም ስብስቦች እየተነዱ ነውጥ መፍጠር ግን ጉዳቱ ለአገር መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡

ከዚህ ቀደም ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ሲታገሉ የነበሩ ወገኖች ነውጠኛ ባህሪያትን የማረቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ትናንት ለማኅበራዊ ፍትሕ ሲታገሉ ከፍተኛ የሆነ ሥቃይ የተቀበሉ ወገኖች ራሳቸውን ከበቀል በመቆጠብ ለሕዝብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሲመክሩ፣ የገፈቱ ቀማሽ ያልነበሩ የድል አጥቢያ አርበኞች አገር ሲያምሱ ዝም ማለት አይገባም፡፡ በሥቃይ ውስጥ ያለፉ ወገኖች የደረሰባቸውን ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ተቋቁመው ሕዝብና አገርን ለመታደግ ጥሪ ሲያሰሙ፣ በተቃራኒው የተደላደለ ሕይወት እየመሩ በሕዝብ ስም ሲነግዱ የነበሩ ወፍ ዘራሾች በአገርና በሕዝብ ላይ እንዲቆምሩ መፈቀድ የለበትም፡፡ ኅብረተሰቡም ይህ ለውጥ የመጣው አገርን ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማሸጋገር ነው በማለት፣ ከነውጥ ይልቅ ለዴሞክራሲያዊ ውይይትና ድርድር ሽንጡን ገትሮ መከራከር ይገባዋል፡፡ በሕዝብ ደም መነገድ የለመዱ የግለሰቦችን ፀብ የብሔር ታርጋ እየለጠፉ የእርስ በርስ ግጭት ሲቀሰቅሱም ማጋለጥ አለበት፡፡ የፈለገውን ያህል ስህተት ቢሠራ እንኳ ስህተቱ ዳግም እንዳይመለስና በሕግ አግባብ መፍትሔ እንዲያገኝ መታገል ሲገባ፣ በስሜት በመነዳት የዕልቂትና የውድመት ተባባሪ መሆን አገር ያጠፋል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ ክፋት የሚያተርፉት ኃላፊነት የጎደላቸው አገር አጥፊዎች መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡

እያንዳንዱን የአገር ጉዳይ ከግልና ከቡድን ጥቅም አንፃር በማስላት አገርን ቀውስ ውስጥ መክተትና ሕዝብን ማተራመስ የጤነኛ ፖለቲከኞች ተግባር አይደለም፡፡ የአገር ህልውና ከምንም ነገር በላይ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተቀባበለ ያኖራት አገር ታሪክ በሚመስሉ ተረቶች እንደሚወሳው ሳይሆን፣ ለተስፋፊዎችና ለወራሪዎች ያልተንበረከከች ደማቅ ታሪክ ያላት አገር ናት፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያወሳው ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለአገሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ የፖለቲካ አቋምና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድቡት እርስ በርሱ የተገመደ ነው፡፡ ይህ ጨዋ ሕዝብ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሥነ ልቦናው በጣም የተቀራረበ ከመሆኑ የተነሳ በዓይን ጥቅሻ ጭምር የሚግባባ ነው፡፡ ይህንን የተከበረ ሕዝብ በተራ ጉዳዮች በማጋጨትና አገር በማተራመስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት መሆን ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው፡፡ መንግሥት በመጀመርያ ራሱ ሕግ እያከበረ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ በተጨማሪም ውስጡን እያጠራና የሕዝብና የአገር ኃላፊነት የሚሰማቸውን ብቁ ዜጎችን ለተገቢው ኃላፊነት እየመደበ፣ ለአገርና ለሕዝብ ደንታ የሌላቸውን ማራገፍ ይኖርበታል፡፡ አገር መጫወቻ እንዳትሆን ልዩ ጥንቃቄ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጣው ለውጥ ባለቤቱ መላው ሕዝብ መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ ይህ ለውጥ የኢትዮጵያ ሕዝብን ፍላጎት ማዕከል አድርጎ መንቀሳቀስ ስለሚገባው፣ የአገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በከፍተኛ ኃላፊነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር ካለመቻሉም በላይ፣ የደረሱ የግብርና ምርቶችን ገበያ ማውጣት አዳጋች በሆነበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ፣ የድል አጥቢያ አርበኞች አገር እያመሱ ሕዝብ ለችግር መዳረግ የለበትም፡፡ የፀጥታ ኃይሎች የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በአግባቡ መጠበቅ ሲገባቸው፣ ችግር ሲያጋጥም ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ጉዳት ሲያደርሱ በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ሕዝቡ ውስጥ እየተሹለኮለኩ ቀውስ ለመፍጠር የሚራወጡ አካላትም በሕግ የበላይነት አደብ ሊገዙ ይገባል፡፡ በሕዝብ መስዋዕትነት የተገኘን ለውጥ አቅጣጫውን አስቶ የቀውስ ማዕበል ውስጥ መክተት እንደማይቻል፣ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ በሕግ አግባብ ማሳየት መቻል ይጠበቅበታል፡፡ በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ወደ አገር ቤት የተመለሱ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው፣ በሕጉ መሠረት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ማወቅ ግዴታቸው ነው፡፡ በዚህ መሠረት መንቀሳቀስ የማይፈልጉትን ደግሞ ሕግ ፊት መገተር የመንግሥት ኃላፊነትም ግዴታም ነው፡፡ ኃላፊነት በጎደላቸው ድርጊቶች ምክንያት አገር መታመስ የለበትም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...