Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ አምስት ኃላፊዎች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ 

የቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ አምስት ኃላፊዎች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ 

ቀን:

በመንግሥት ላይ ከ319.4 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል

ሥልጣናቸውን ያላግባብ ተገልግለው በመንግሥት ላይ ከ319.4 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ፣ አምስት ኃላፊዎችና ሦስት በግል ሥራ ተሰማርተዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሾቹ ላይ ሰባት ክሶችን አደራጅቶ ያቀረበ ሲሆን፣ ተከሳሾች በአጠቃላይ 319,475,287 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን በክሱ አብራርቶ ገልጿል፡፡

- Advertisement -

ተከሳሾቹ የቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኛው፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ፣ የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ማርኬቲንግ ሰፕላይ ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደና በግል ሥራ ላይ ነበሩ የተባሉት አቶ ቸርነት ዳና፣ እሌኒ ብርሃንና አቶ ረመዳን ሙሳ ናቸው፡፡

የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩትና በድለላ ተሰማርተው ነበር የተባሉት ተከሳሾች በዋናነት የቀረበባቸው ክስ፣ ለአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አገልግሎት ከሚውሉ ትራክተሮች ግዥ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ተከሳሾቹ በጥቅም በመመሳጠር በሜቴክ የግዥ አፈጻጸም መምርያ መሠረት ማንኛውም ግዥ በግልጽ ጨረታ መፈጸም እንዳለበት መደንገጉን እያወቁ፣ መመርያውን በመተላለፍና በርካታ ትራክተሮች እንዲገዙ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ሰባት ክሶች ውስጥ በዝርዝር አስረድቷል፡፡ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ በኃላፊነት የሚመሩት ተቋም፣ ከተጣለበት ተልዕኮ አንፃር ማንኛውንም ግዥ በሕጉና በመመርያው መሠረት መከናወኑን፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት የሆነው የውጭ ምንዛሪ ለተገቢ ዓላማ መዋሉን የማረጋገጥና የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ ያንን አለማድረጋቸውን በክሱ ገልጿል፡፡ ጄኔራሉ በተፃራሪ ሁኔታ ከሕጋዊ የግዥ ሥርዓት ውጪ ለሙስና ምቹ የሆነ ሕገወጥ የግዥ ሥርዓት በመዘርጋት ግዥና ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በዕቅድና ጥናት ላይ የተመሠረተ የግዥ ፍላጎት ከኢንዱስትሪው ሳይቀርብ፣ ስለሚገዙት የትራክተሮች ዓይነቶችና ተገቢ ዝርዝር ሁኔታ (Specification) ሳይዘጋጅ፣ ትራክተሮቹ በተጠቃሚ ዘንድ ተፈላጊና የመግዛት አቅምን ያገናዘቡ መሆናቸው ሳይረጋገጥ፣ የጥራትና የዋጋው ሁኔታው በኢንዱስትሪው ባለሙያዎች ጥናት ሳይካሄድና ቀደም ብሎ የተገዙ ትራክተሮች ባልተሸጡበት ሁኔታ የሚገኘውን ሕገወጥ ጥቅም ብቻ በማሰብ፣ ከደላሎችና ከጉዳይ አስፈጻሚዎች ጋር በመመሳጠር ግዥው መፈጸሙን ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡

ሜጀር ጄኔራል ክንፈ፣ ኮሎኔል ጎይቶምና በድለላ ተሳትፈዋል የተባሉ አቶ ረመዳን አይኤምአር (IMR) ከሚባል የሰርቢያ ኩባንያ በተገዙ ትራክተሮች ምክንያት በመንግሥት ላይ 27,201,247 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጿል፡፡ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ፣ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀና ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ ዊቶ (WEITO) ከሚባል የቻይና ኩባንያ በተገዙ ትራክተሮች ምክንያት በመንግሥት ላይ 41,582,289 ብር፣ እንዲሁም አይኤልጂአይ (ILGI) ከሚባል የቱርክ ኩባንያ በገዟቸው ትራክተሮች ምክንያት የ41,612,911 ብር ጉዳት ማድረሳቸውንም አስረድቷል፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል ጠናና ኮሎኔል ደሴ ሻንዶንግ ፋቶን ከተባለ የቻይና ኩባንያ እንዲገዙ ባደረጓቸው ትራክተሮች አማካይነት 1,773,561 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንደዘረዘረው ብርጋዴር ጄኔራል ጠና፣ በድለላ ተሰማርተው ነበር የተባሉት አቶ ቸርነትና እሌኒ ብርሃን ካማኮ (CAMACO) ከተባለው የቻይና ኩባንያ እንዲገዙ ባደረጓቸው ትራክተሮች ምክንያት፣ መንግሥት 10,892,656 ብር ጉዳት እንዲደርስበት ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡

ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቼሪ ሌቪ ኢንዱስትሪ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ትራክተሮች እንዲገዙ ባፀደቁት ግዥ ምክንያት፣ መንግሥት የ114,055,947 ብር ጉዳት እንዲደርስበት ማድረጋቸውን አክሏል፡፡ ሜጀር ጄኔራል ክንፈና አቶ ረመዳን ዩአርዩኤስኤስ (URUSS) ከተባለው የፖላንድ ኩባንያ በተገዙ ትራክተሮች ምክንያት በመንግሥት ላይ 119,856,756 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ተከሳሾቹ በአጠቃላይ 319,475,287 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 33 እና 407 (1ሀ) እና (3)ን ድንጋጌዎች ተላልፈው ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክሱን በችሎት በንባብ ካሰማ በኋላ፣ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ መቃወሚያ ማቅረብ አለማቅረባቸውን ጠይቋል፡፡ የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ ድንጋጌ ዋስትና የሚከለክል በመሆኑ፣ በዋስትና ጉዳይ ላይ ምንም ባይሉም የክስ መቃወሚያ እንዳላቸው በመግለጻቸው የቅድመ ክስ መቃወሚያ ለመስማት ለጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...