Thursday, June 20, 2024

የክቡር ሚኒስትሩ ውሻ በጥሶ የአካባቢውን በርካታ ሰዎች ነክሶ፣ ፖሊስ ቤታቸው ይመጣል

[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ስብሰባ ላይ ከዲፕሎማት ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • በጣም ስፈልግህ ነው ያገኘሁህ፡፡
 • ምነው በሰላም ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • አንድ ነገር አስቤ በእሱ ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ነው፡፡
 • ምንድነው?
 • አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት አለ እና አገሬን ወክዬ የድርጅቱ አመራር ለመሆን አስቤ ነው፡፡
 • ደስ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንደምሆን ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡
 • አንድ ጥያቄ ግን አለኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው?
 • አሁን ያለዎትን ሥራ ሊተውት ነው ማለት ነው?
 • ምን ይኸው የአገራችንን ሁኔታ እንደምታየው ነው፡፡
 • በዚህ ጊዜ እኮ ነው አገርዎን ማገልገል ያለብዎት?
 • እሱ ለእኔ ምንም አያዋጣም፡፡
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት?
 • እውነተኛ አገልጋይ ከሆኑ አገርዎ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ባለችበት ወቅት ትተው መሄድ አይገባዎትም፡፡
 • ስማ በእኛ አገር ተረት መጀመርያ የመቀመጫዬን አለች ዝንጀሮ ይባላል፡፡
 • ይኼ ትክክለኛ አካሄድ አይመስለኝም፡፡
 • ምን ነካህ በደህና ጊዜ ነው እንጂ መጦሪያህን ማመቻቸት ያለብህ?
 • ለመሆኑ ለሚፈልጉት ሥራ የሚመጥን ብቃት አለኝ ብለው ያስባሉ?
 • ከበቂ በላይ የሆነ ብቃት ነው እንጂ ያለኝ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ስንት ዲግሪ እንዳለኝ ታውቃለህ?
 • ሁለት ነበር ያሉኝ?
 • በሚገባ፡፡
 • ግን ያው ሁለቱም ፌክ እንደሆኑ ሰምቻለሁ፡፡
 • እ. . .
 • እሱ በቂ አይመስለኝም፡፡
 • ምን ነካህ ሦስት ማስተርስም አለኝ?
 • እየተዋወቅን ክቡር ሚኒስትር?
 • ምኑን ነው የምንተዋወቀው?
 • በግዥ አይደል እንዴ ማስተርሶቹ የሚመጡት?
 • እ. . .
 • ዓለም ላይ ፌክ ኒውስ እንደበዛ ሁሉ በአገራችሁ ባለሥልጣናት እኮ ፌክ ዲግሪዎች በዝተዋል ተብሏል፡፡
 • ቢሆንም እኔ እኮ ከፍተኛ የሥራ ልምድ ነው ያለኝ፡፡
 • የስንት ዓመት የሥራ ልምድ አለዎት?
 • የ27 ዓመታት ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እሱ እኮ የሥራ ልምድ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምንድነው?
 • የጥፋት ልምድ፡፡
 • አንተ ጥሩ ሰው ትመስለኝ ነበር?
 • እኔማ ጥሩ ሰው ነኝ፡፡
 • ታዲያ ጥሩ ሰው ከሆንክ ለምን አትጽፍልኝም?
 • ምንድነው የምጽፍልዎት?
 • የድጋፍ ደብዳቤ ነዋ፡፡
 • ከዚያ በፊት እርስዎ ማምጣት ያለብዎ ነገር አለ፡፡
 • ምንድነው?
 • የብቃት ማረጋገጫ!

[ክቡር ሚኒስትሩ በሙስና ተጠርጥሮ የታሰረ ወዳጃቸውን ለመጠየቅ እስር ቤት ይሄዳሉ]

 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ተስማምቶሃል ልበል?
 • ምን እሆናለሁ ብለው ነው?
 • እኔማ ትጎሳቆላለህ ብዬ ሥጋት ይዞኝ ነበር፡፡
 • ኧረ ምንም ጉስቁልና የለም፡፡
 • ያው አሁን በየሚዲያው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምናምን እየተባለ ስለሚወራ አሥግቶኝ ነው፡፡
 • እሱማ በቀድሞው ሥርዓት ነበር፣ አሁን በጥሩ ሁኔታ ነው የተያዝነው፡፡
 • እኔማ መድኃኒት ምናምን ካስፈለገህ ከውጭም ላስመጣልህ ብዬ ነበር፡፡
 • ችግር የለም ክቡር ሚኒስትር፣ ሁሉ ነገር በትክክል ነው እየሄደ ያለው፡፡
 • እና እስር ቤቱን ወደኸዋል?
 • እሱማ እንዴት እወደዋለሁ? ድብርቱን አልቻልኩትም፡፡
 • የምን ድብርት ነው?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ መጠጣት ሲያምረኝ ተነስቼ ዱባይ ነበር የምሄደው፡፡
 • እሱስ ልክ ነው፡፡
 • ማሳጅ ሲያምረኝ ባንኮክ ነበር የምበረው፡፡
 • መቼም እስር ቤት ውስጥ ማሳጅና መጠጥ ቤት አትጠብቅም?
 • ክቡር ሚኒስትር አንድ የምቆጭበት ነገር ቢኖር እሱ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • ያኔ ባለሥልጣን ሳለሁ እነሱን ነገሮች እስር ቤት ባሠራ አሁን ብዙ አይደብረኝም ነበር፡፡
 • እ. . .
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ አሁን ከቻሉ ሐሳቡን ቢያነሱት ሁሉም ይቀበሉታል፡፡
 • ለምን?
 • የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሁሉም ባለሥልጣን መጨረሻው እዚህ ነው፡፡
 • የአሁኖቹ እኮ አገር ወዳድ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡
 • እንዳይሸወዱ ክቡር ሚኒስትር፣ በፊት እኛም እንደዚህ እንል ነበር፡፡
 • እሺ አሁን ለድብርትህ መጽሐፍ ላምጣልህ?
 • ክቡር ሚኒስትር አሁንማ መዝናናት ለምጄ፣ ፍላየር ራሱ ማንበብ አልወድም እኮ፡፡
 • ይኼን ያህል?
 • ክቡር ሚኒስትር ከቀረቡብኝ ክሶች መካከል እኮ ግማሹን ሳላነብ በተስማማሁባቸው ጉዳዮች ነው፡፡
 • ምን ተሻለ ታዲያ?
 • ከቻሉ አንድ ፊልም አለ እሱን ያምጡልኝ፡፡
 • የምን ፊልም?
 • የውጭ አገር ፊልም ነው ግን በአማርኛም ተተርጉሟል አሉ፡፡
 • ምን የሚል ፊልም?
 • Prison Break!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]

 • ምንድነው ግን እዚህ አገር ላይ እየተደረገ ያለው?
 • ምን ተደረገ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕግ የለም እንዴ?
 • የምን ሕግ?
 • በቃ በየቦታው የሚሰማው እኮ ሥርዓተ አልበኝነት ነው፡፡
 • አዎ ያው ለውጥ ላይ አይደለን እንዴ?
 • አይ ቢሆንም በየቦታው የሚሰማው ወሬ ጥሩ አይደለም፡፡
 • ምን ሰሙ ክቡር ሚኒስትር?
 • ማለቴ በየቀኑ በርካታ ሰዎች ነው የሚደውሉልኝ፡፡
 • ምን ብለው?
 • ይኸው አንዳንድ ክልሎች መንገዱን ዘግተው ሌሎች እህል ማግኘት ተቸግረዋል፡፡
 • እሱን እኔም ሰምቻለሁ፡፡
 • እዚያ አካባቢ ያሉ ዜጎች እኮ በኑሮ ውድነት እየተሰቃዩ ነው፡፡
 • እንደነገርኩዎት አገራችን በለውጥ ሒደት ላይ ናት፡፡
 • ቢሆንስ?
 • ነገሮች መስተካከላቸው አይቀርም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በየቦታው የምትሰማው ዝርፊያ አሳሳቢ ነው፡፡
 • እሱስ ልክ ነዎት፡፡
 • መንግሥት ስለመኖሩ ራሱ ያጠራጥራል እኮ?
 • የአሁኑ መንግሥት እኮ እንደ ቀድሞ መንግሥት ባለመሆኑ ነው፡፡
 • ምንድነው እንደዚህ መልፈስፈስ?
 • ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ተልፈስፍሶ ሳይሆን ትዕግሥተኛ በመሆኑ ነው፡፡
 • የበፊቱ መንግሥት ግልፍተኛ ነበር እያልከኝ ነው?
 • መቼም ይረሱታል ብዬ አላስብም?
 • ቢሆንም ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ እየሆኑ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የዚህኛው መንግሥት ፍልስፍና እኮ መደመር ነው፡፡
 • በእሱ እንኳን እኔ አላምንም፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • በመደመር ሒሳብ በርካቶች እየተቀነሱ አይደል እንዴ?
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው ስንቶቹ ከእስር ቤት ሲፈቱ፣ አሁን ደግሞ በምትካቸው በርካቶች ካልገቡ እየተባለ ነው፡፡
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ምነው?
 • ከእስር ቤት እኮ የተለቀቁት በመጀመርያም ያላግባብ በመታሰራቸው ነው፡፡
 • ታዲያ አሁን ማሰር ምን አስፈለገ?
 • እነዚህማ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው የነበሩ ናቸው፡፡
 • ቢሆንም ይኼ ለእኔ Double Standard ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ለውጡን አይቀበሉም ማለት ነው?
 • የምን ለውጥ?
 • በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ነዋ?
 • እኔ ለውጡ አልታየኝም፡፡
 • እ. . .
 • ምነው?
 • አሁን የምን ሰው እንደሆኑ ገባኝ፡፡
 • የምን ሰው ነኝ?
 • የቤቴልሔም!

[የክቡር ሚኒስትሩ ውሻ በጥሶ የአካባቢውን በርካታ ሰዎች ነክሶ፣ ፖሊስ ቤታቸው ይመጣል]

 • ልትይዘኝ ነው እንዴ የመጣኸው?
 • አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምነው ታዲያ?
 • በዓል እንዴት ነበር ክቡር ሚኒስትር?
 • በዓል ድሮ ቀረ እባክህ፡፡
 • እኛም ጠርጥረን ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንዴት?
 • ለበዓል ጠቦት ነገር አላረዱም መሰለኝ?
 • ደግሞ ይኼን መርምሩ ተብላችሁ ተላካችሁ?
 • አይ እየመረመርን አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምን ፈልጋችሁ ነው?
 • ውሻዎ ቢያንስ ቅንጥብጣቢ ሥጋ አላገኘም ወይ ብለን ነው?
 • የሰውን ደኅንነት ከመጠበቅ አልፋችሁ የውሻንም እንጠብቃለን እያላችሁ ነው?
 • ኧረ እንደዛ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ስለውሻዬ ምን አገባችሁ? እኔ ነኝ የምቀልበው?
 • ቢቀልቡትማ ኖሮ እንደዚህ አካባቢውን ሊያሸብር አይችልም ነበር፡፡
 • አልገባኝም?
 • ክቡር ሚኒስትር፣ ውሻዎ በጥሶ ወጥቶ በርካቶች ላይ ጉዳት ከማድረሱም ባሻገር ለአካባቢው የሥጋት መንስዔ ሆኗል፡፡
 • ምን?
 • ስለዚህ ክቡር ሚኒስትር ውሻዎ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ዕርምጃ እንዲወሰድበት ጠይቀዋል፡፡
 • ስማ ይኼ ውሻ እኮ ለእኔ የቤተሰቤ አካል ነው፡፡
 • ሊሆን ይችላል ክቡር ሚኒስትር፣ ሆኖም ውሻዎ አካባቢውን በማሸበሩና ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ለእኛ ተላልፎ ሊሰጠን ይገባል፡፡
 • ለምን?
 • ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች እኮ ስለጤንነታቸው እየሠጉ ነው፡፡
 • ለምንድነው የሚሠጉት?
 • ለመሆኑ መቼ ነው የተከተበው?
 • የዛሬ 27 ዓመት፡፡
 • ስለዚህ እኛ የምንፈልገው አንድ ነገር ነው?
 • ምንድነው?
 • ውሻውን. . .
 • ምን?
 • አሳልፈው እንዲሰጡን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት ሐዘን ለመድረስ ጎረቤት ተገኝተው ለቀስተኛው በሙሉ የሚያወራው ነገር አልገባ ብሏቸው ወደ ቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸውን ስለጉዳዩ እየጠየቁ ነው] 

ጎረቤታችን ሐዘን ለመድረስ ብሄድ ለቀስተኛው በሙሉ በሹክሹክታ ያወራል። ግን የሚያወሩት ነገር ሊገባኝ አልቻለም። ምንድነው የሚያወሩት? እኔ ምን አውቄ? እንዴት? የሚያወሩትን ምንም አልተሰማሽም? እኔ እንድሰማ የፈለጉ አይመስልም ግን ... ግን...

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት የሚታወጁ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ማለቴ ነው። ምን ታወጀ? አንዴ ከዕዳ ወደ ምንዳ አላችሁ፡፡ እሺ? የእሱን ውጤት እየጠበቅን ሳለ ደግሞ... እ...? ኢትዮጵያ ታምርት...

[ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን በተጀመረው አገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ስለተላለፉ መልዕክቶች በተመለከተ ከባለቤታቸው ጋር እያወጉ ነው] 

እኔ ምልህ? እ... አንቺ የምትይው? አለቃህ በምክክር መድረኩ ላይ ያስተላለፉትን መልዕክት አደመጥክ? አዎ፡፡ የሚገርም እኮ ነው አልተገረምክም? ምኑ ነው የሚያስገርመው? ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ምከሩና አምጡ ብለው የምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ ካደረጉ በኋላ...