Thursday, June 20, 2024

የአገር ጉዳይ የልጆች ጨዋታ አይደለም!

በዚህ ዘመን ምራቃቸውን የዋጡ ሰዎች የወጣቶች መካሪ፣ የአገር ሽማግሌ፣ የትውልድ አርዓያና የተጣመመውን የሚያቀና መሆን ሲገባቸው፣ እንደ ሠፈር ጎረምሳ የብጥብጥና የሁከት ምንጭ ሲሆኑ ያሳዝናል፡፡ በፖለቲካው መስክ ከ40 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ፖለቲከኞችና የሚመሩዋቸው ድርጅቶች አድረው ቃሪያ ሲሆኑ ያሳፍራል፡፡ ለዓመታት በመሣሪያ ያልተሳካላቸውንና በሰላማዊ ጥሪ ያገኙትን መልካም አጋጣሚ የሚያበላሹ ያሳቅቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የተለያዩ አመለካከቶችና አጀንዳዎች ያሉዋቸው የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት የሚፎካከሩበትን ምኅዳር ለማመቻቸት በጋራ እንረባረብ ሲባል፣ በተሳሳተ መንገድ ለመንጎድ የሚሞክሩ ወገኖች ቆም ብለው ቢያስቡ ይበጃል፡፡ ዴሞክራሲን ገፍትሮ በጣለ ጉልበተኝነት ከአገር ተገፍተው ተባረው በስደት የቆዩ ወገኖች፣ ይኼንን መልካም አጋጣሚ በመታበይ ሊያበላሹት ሲያደቡ ሕዝብ ተፅዕኖ ማሳደር አለበት፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕዝብ ስም እየተንቀሳቀሱ ለሕዝብና ለአገር የማይበጅ ድርጊት ሲፈጽሙ አይሆንም ብሎ የማስገደድ ኃይል ያለው ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ እንደ ልጆች ጨዋታ ተጀምሮ ‹ጨዋታው ፈረሰ…› ተብሎ የሚያልቅ ስላልሆነ፣ ሕዝብ በስሙ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞችንም ሆነ ድርጅቶችን መገሰፅ አለበት፡፡ በአገር ቀልድ የለምና፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሰንበቻውን ከመምህራን ጋር በነበራቸው ውይይት፣ በአሁኑ ጊዜ በመከናወን ላይ ባለው ለውጥ አማካይነት አገሪቱ ትታወቅበት የነበረውን የኃይልና የጭቆና አገዛዝ ለመለወጥ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ይኼንን ጥረትና ዴሞክራሲያዊ ቻይነት እንደ ድክመት መውሰድ ተገቢ አለመሆኑን አስምረዋል፡፡ የአገሪቱን መንግሥት ለዴሞክራሲ ቅርብ አለመሆን በማውሳት፣ መንግሥትን ወደ አምባገነናዊ ጠርዝ መግፋት ትክክል እንዳልሆነም አስታውቀዋል፡፡ በሐሳብ ልቆ ማሸነፍ ሲቻል በጠመንጃ ሥልጣን ለመያዝ ማሰብም ቅዥት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ለምርጫ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁና እሳቸው የሚመሩት ድርጅት ከተሸነፈ አቅፈውና ስመው ሥልጣን ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ ይህ ቁምነገር የሚያመላክተው ካሁን በኋላ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እንጂ የአምባገነንነት መፈንጫ መሆን እንደማይገባት ነው፡፡ ይኼንን በኩር ሐሳብ በመተላለፍ የማይሆን ድርጊት ውስጥ መገኘት ጠቡ ከሕዝብ ጋር ይሆናል፡፡ አሁንም በሰበብ አስባቡ ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል ለማደናቀፍና አገር ትርምስ ውስጥ ለመክተት መሞከር ሊቆም ይገባል፡፡ የአገር ጉዳይ የልጆች ጨዋታ ስላልሆነ አደብ መግዛት የግድ ይላል፡፡

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል የሚጠበቅበት የአገሪቱን ሕጎች ማክበር ሲሆን፣ በዚህ መሠረት አባላቱንና ደጋፊዎቹን በማደራጀት የፖለቲካ ሜዳውን በአግባቡ ለመጠቀም መዘጋጀት አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ጠመንጃ አንግቶ እንደፈለግኩ እሆናለሁ ማለት በፍፁም አይቻልም፡፡ የትኛውንም ዓይነት ስምምነት ፈጽሞ አገር ቤት የገባ የፖለቲካ ፓርቲ ሠራዊቱን ትጥቅ አስፈትቶ በሕጉ መሠረት ሥምሪት ከማስደረግ ባለፈ፣ የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር ሰላማዊውን ድባብ መረበሽ አይችልም፣ ሕገወጥ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከመንግሥት ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ቢኖሩም፣ ትጥቅ ይዞ ፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ መንቀሳቀስ አይፈቀድም፡፡ ሕዝብም እንዲህ ዓይነቱ ፍላጎት ተቀባይነት እንደሌለው አበክሮ ማስገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ለበርካታ ዓመታት በጎረቤት አገር ተቀምጦ የከረመ ኃይል ሰላማዊ ጥሪ ተደርጎለት አገር ቤት ከገባ በኋላ፣ እስከ መጪው ምርጫ አልታገስም ብሎ አቧራ ሲያስነሳ ሕዝብ ደግሞ አደብ ግዛ ማለት አለበት፡፡ የሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊመጣ የሚችለው አንዱን ጉልበተኛ በሌላ በመተካት እንዳልሆነ በግልጽ መነገር አለበት፡፡ የአገር ጉዳይ የልጆች ጨዋታ ስላልሆነ፡፡

በዚህ ዘመን ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ በማስተናገድ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር መዘጋጀት ሲቻል፣ በዘመናት ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮች እየደራረቡ አገርንና ሕዝብን ማተራመስ ኋላቀርነት ነው፡፡ ከዚህ በፊት ተሞክረው ተግባራዊ መሆን ያልቻሉ ስህተቶችን ለመድገም መሞከር ትርፉ ውድቀት ነው፡፡ በተለይ በነጋ በጠባ ከመንግሥት ጋር ንትርክ ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞች ካለፈው ስህተታቸው መማር አለባቸው፡፡ ገና ለገና ሕዝብ ይደግፈናል በሚል አጉል ሥሌት ያልተገባ ድርጊት ውስጥ የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ራሳቸውንም ድርጅታቸውንም መሳቂያ ባያደርጉ ይሻላቸዋል፡፡ ሕዝብ ውስጥ መሽጎ ጦርነት መክፈት፣ ግጭትን የዓላማ ማስፈጸሚያ ማድረግና ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማፈንገጥ ስህተት ውስጥ መነከር የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ ለኪሳራ ይዳርጋል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ወይም ፉክክርን ከጠመንጃ ጋር ለማቆራኘት መሞከር የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን ጠመንጃ ነካሽነት በሕዝብ ያስንቃል፡፡ ሕዝብ ደግሞ በአገሩ ጉዳይ ቀልድ አያውቅም፡፡

አሁን ተወደደም ተጠላም አገሪቱ በለውጥ ማዕበል ውስጥ ናት፡፡ ይህ የለውጥ ማዕበል የመጣው ደግሞ በሕዝብ ግፊት ነው፡፡ ይኼንን የሕዝብ ግፊት የፈጠረው ደግሞ ለዓመታት የነበረው የነፃነት ዕጦት ነው፡፡ ሕዝብ ነፃነት እፈልጋለሁ ሲል ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮለት የሚኖርበት ሥርዓት እንዲገነባለት ነው፡፡ ይኼንን ሥርዓት ማምጣት የሚቻለው ደግሞ በዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሐሳቦች በነፃነት የሚወዳደሩበት ገበያ ማለት ነው፡፡ ለሐሳብ ነፃነት የሚተጉ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ይሳተፉበታል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የተሻለ ሐሳብ አለን የሚሉ ፖለቲከኞች በነፃነት የሚፎካከሩበት እንጂ፣ ጠመንጃ አንግበው የሚንጎራደዱ የሚያስፈራሩበት ወይም የሚፈነጩበት አይደለም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ ጠመንጃ ይዞ ለመደራደርም ሆነ ዓላማን ለማስረፅ በፍፁም አይሞከርም፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የታጠቀ ኃይል የሚኖረውና የሚያሳማራው መንግሥት ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ሆኖ አገር ለመምራት ደግሞ ሕጋዊው መንገድ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍ ነው፡፡ ምርጫ እንዲኖር ደግሞ የአገር ሰላም መከበር አለበት፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩም ለሁሉም እኩል ሆኖ መደላደል ይኖርበታል፡፡ ይህንን ዕውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ሲገባ እንቅፋት መሆን ከሕዝብ ጋር ያጣላል፡፡ ሕዝብ የተጣላው ደግሞ ለኪሳራ ይዳረጋል፡፡ ሕዝብ ከአገሩ በላይ የሚያስቀድመው ስለሌለ፣ የአገሩን ጉዳይ የልጆች ጨዋታ ማድረግ አይገባም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...