Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ በሠራተኞች የደመወዝ መነሻ ላይ ተስማሙ

ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ በሠራተኞች የደመወዝ መነሻ ላይ ተስማሙ

ቀን:

ከኢትዮጵያ በቤት ሠራተኝነት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚሄዱ ዜጎች መነሻ ወርኃዊ ደመወዝ 1,000 ሪያል እንዲሆን ስምምነት ላይ መደረሱ ታወቀ፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ይከፈል ከነበረው የተሻሻለ ቢሆንም፣ አሁንም ከጎረቤት አገሮች ከኬንያና ከኡጋንዳ የሚሄዱ ዜጎች ጋር ሊመጣጠን አለመቻሉን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ወደ ዓረብ አገሮች በሄዱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ በተለይ በሳዑዲ ዓረቢያ ደረሶ በነበረው ሞት፣ እንግልትና የአካል ጉዳት ምክንያት ለአራት ዓመታት ማለትም ከ2006 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ዕግድ ጥሎ ከቆየ በኋላ፣ ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ በተወሰኑ አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ፣ ሠራተኞች እንዲሄዱ በ2010 ዓ.ም. የተጣለውን ዕግድ ማንሳቱ ይታወሳል፡፡

ይኼንንም ተከትሎ በሳዑዲ ዓረቢያ አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ በተለይ በቤት ሠራተኝነት ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚሄዱ ዜጎች መነሻ ደመወዝ 850 ሪያል እንዲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መስማማታቸውን የሚገልጽ ሐሰተኛ መረጃ በመግለጻቸው፣ የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ማኅበር ያደረገውን ስምምነት ሰርዞ ቆይቷል፡፡ ስምምነቱ የተሰረዘው ቢያንስ ቢያንስ ከጎረቤት አገሮች ከሚሄዱ ዜጎች ጋር የሚጠጋጋ ወይም የሚመሳሰል የደመወዝ መነሻ ሊቀመጥ ይገባል በሚል ነበር፡፡

- Advertisement -

ሠራተኞች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እንዲሄዱ በአዋጅ ቁጥር 923/2008 ድንጋጌ መሠረት የተቀመጡ መሥፈርቶችን ማሟላት እንዳለባቸው ተገልጾ የተፈቀደ ቢሆንም፣ በደመወዝና በተለያዩ ችግሮች እስካሁን ሳይሳካ መቅረቱን ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የኤጀንሲ ባለቤት ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን እ.ኤ.አ. በ2017 በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረሰውን የሠራተኛ ልውውጥ ስምምነት ተግባራዊ በሚሆንበት ላይ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከሳዑዲ ዓረቢያ አቻቸው ሚስተር አህመድ ቢን ሱሌይማን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይታቸውም የሠራተኞች መነሻ ደመወዝ 1,000 ሪያል እንዲሆን ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በውይይቱ  ወቅት ከሠራተኛ የመነሻ ደመወዝ በተጨማሪ፣ የሠራተኛውና የአሠሪው መብት ስለሚጠበቅት ሁኔታም ስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ስምምነት በተግባር መፈጸም አለመፈጸሙን፣ ከሁለቱም አገሮች የተውጣጣ ቡድን በየስድስት ወራት እየተገናኘ አፈጻጸሙን እንዲገመግም መስማማታቸውን ከሚኒስትሩ ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡  

በመጨረሻም በተደረሰባቸው ስምምነቶች ላይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ (ዶ/ር) የሳዑዲ ዓረቢያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ልማት ሚኒስትር አብዱላህ አቡስ ነይን (ዶ/ር) ፊርማቸውን በማኖር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን እንዳረጋገጡ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ዝርዝር ጉዳዮን በሚመለከት ሁለቱም መንግሥታት በኤምባሲዎቻቸው በኩል የሰነድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ መስማማታቸው ታውቋል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል ስለተደረሰው ስምምነት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ሪፖርተር ጥረት ቢያደርግም፣ የሚኒስቴር ኃላፊዎች ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...