Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ዳይሬክተር የተጠረጠሩበት የ44.5 ሚሊዮን ዶላር ግዥ ውድቅ ተደረገ

የኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ዳይሬክተር የተጠረጠሩበት የ44.5 ሚሊዮን ዶላር ግዥ ውድቅ ተደረገ

ቀን:

የዓለም ገነት ቆርቆሮ ባለቤት የክስ መመሥረቻ ጊዜ ተራዘመ

በሶማሌ ክልልና በባሌ ዞን የሞባይልና ሲዲኤምኤ (የቴሌ ታወር ሥራዎች) ግንባታን በጥቅም ተመሳጥረው ያለ ጨረታ ለሜቴክ ሰጥተዋል ተብለው በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮ ቴሌኮም የኤንጂፒኦ የቀድሞ ዳይሬክተር፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ኔትወርክ ግንባታ ጋር በተያያዘ ቀርቦባቸው የነበረው የ44.5 ሚሊዮን ዶላር ግዥ ውድቅ ተደረገ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ተጠርጣሪው አቶ ኢሳያስ ዳኘው የኮርፖሬሽኑን የግዥ ማኑዋልና አሠራር ሒደቶች በተፃራሪ በተዋረድ ያለውን አመራር ማለትም የግዥ ኮሚቴ፣ የኮርፖሬሽኑ ማኔጅመንትና የሥራ አመራር ቦርድ ውሳኔ ሳይሰጥ የውል ማሻሻያ ስምምነት ማድረጋቸውን በአቤቱታው አቅርቧል፡፡ ዳይሬክተሩ ውል ያሻሻሉት ዜድቲኢ ከሚባለው የቻይና ኩባንያ ጋር መሆኑንና ስምምነቱም ኩባንያው ቀደም ብሎ ይዞት ከነበረው ፕሮጀክት ጋር ተያያዥነት እንዳለው በመግለጽ፣ የ44,510,971 ዶላር መሆኑን አክሏል፡፡ አቶ ኢሳያስ የውል ማሻሻያ ስምምነት ያደረጉት ለግዥው የሚያስፈልጉ ስፔስፊኬሽኖች ሳይዘጋጁና ኩባንያው ያቀረባቸውን ቴክኒካልና ስፔስፊኬሽን ብቻ በመቀበል መሆኑን አስረድቷል፡፡ ኩባንያው ያቀረባቸው መሥፈርቶች በኮርፖሬሽኑ ኢንጂነሪንግ ክፍል ሳይፈተሽ ስምምነቱን በመፈራረማቸው፣ መንግሥት ከዋጋ ውድድርም ሆነ ከጥራት አኳያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎት መስጠት ከሚችሉ ተመሳሳይ ኩባንያዎች ሊያገኝ የሚችለውን ጥቅም ማሳጣታቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ቡድኑ አቶ ኢሳያስን የጠረጠረበትን ከላይ የተጠቀሰውን አዲስ ሐሳብ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ማጣራት እንዲችል የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

- Advertisement -

የአቶ ኢሳያስ ጠበቆች አቶ ዘረሰናይ ምሥግናና አቶ ሀፍቶም ከሰተ ባቀረቡት የመቃወሚያ ክርክር እንደተናገሩት፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ደንበኛቸው ‹‹ውል አሻሽለዋል›› ከማለት ውጪ የገለጸው ነገር የለም፡፡ ተጠርጣሪው ውሉን ያሻሻሉት በተሰጣቸው ሥልጣን ይሁን ወይም ሥልጣናቸውን አልፈው ያላግባብ ውል ስለማሻሻላቸው ምንም ያለው ነገር እንደሌለም አስረድተዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪው ውል  እንዳሻሻሉ ከመግለጽ ባለፈ፣ ወንጀል ስለመፈጸሙ ወይም ከቦርድ ውሳኔ ውጪ ስላደረጉት ነገር የሚያሳይና ለወንጀል መነሻ የሚሆን ቅድመ ማስረጃ (Prima Facie Evidence) አለማቅረቡን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት፣ የቀረበው ሐሳብ ውድቅ እንዲደረግላቸው ተከራክረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበውን ተጨማሪ የጥርጣሬ ሐሳብ በብይን ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡ መርማሪ ቡድኑ ጉዳዩን እንደገና ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ የሠራውንና የቀረውን የምርመራ ሥራ በማስረዳት፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ የተጠርጣሪው ጠበቆች ባቀረቡት የመቃወሚያ መከራከሪያ ሐሳብ እንዳስረዱት፣ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ባለው ችሎት አቅርቦት ፍርድ ቤቱ በብይን ቀሪ አድርጎታል፡፡ ጉዳዩን እያየው ባለው ፍርድ ቤት ውድቅ የተደረገ ክርክር ለቀጣይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ከሚቀርብበት ባለፈ፣ በተመሳሳይ ችሎት ተሻሽሎ ሊቀርብ የሚችልበት የሕግ አሠራር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ብይን የሰጠበትን ጉዳይ መልሶ የሚያይበት ሥልጣንም፣ የሕግ አግባብም እንደሌለው አክለዋል፡፡  

ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ተከራከሩበትና ችሎቱ በብይን ዕልባት ይሰጥበታል›› በማለቱ መርማሪ ቡድኑ አሻሽሎ ያቀረበውን፣ የሠራውንና የቀረውን የምርመራ ሥራ አስረድቶ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣው ጠበቆች ብይን ባረፈበት ጉዳይ ላይ በተመሳሳይ ችሎት መከራከር አግባብ እንዳልሆነ እያወቁ እንደሚከራከሩ አስታውቀው፣ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አክብረው ግን ምላሽ እንደሚሰጡ በማሳሰብ ተከራክረዋል፡፡ አቶ ኢሳያስ በተጠቀሰው ጉዳይ ምንም የሚያስጠረጥራቸው ነገር እንደሌለ ጠበቆቻቸው ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ደንበኛቸው ውል ያሻሻሉት ከግዥ መመርያ ከሥራ አመራር ቦርድ ውሳኔ ውጪ መሆኑን የገለጸው፣ ማንን አነጋግሮ ነው? ኢትዮ ቴሌኮምን? ቦርዱን? ወይስ በራሱ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነው? ድምዳሜ ላይ ከደረሰ ደግሞ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ የለበትም ካሉ በኋላ፣ ያቀረበው መከራከሪያ ያልተረጋገጠ በመሆኑ ለፍርድ ቤቱም መቅረብ እንዳልነበረበት አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን ማኔጅመንት በፈረንሣዩ ፍራንስ ቴሌኮም ተቀይሮ ኢትዮ ቴሌኮም ሲባል፣ ቦርዱና አሠራሩ መቀየሩን ተናግረዋል፡፡ አሁን ደንበኛቸው አሻሻሉት የተባለው ውል ኢትዮ ቴሌኮም ከተቀየረ በኋላ ለስድስት ወራት ሲሠራ ቆይቶ እንዲቀየር አዲስ የተቋቋመው ቦርድ ከወሰነ በኋላ መሆኑንም አክለዋል፡፡ አዲስ የተቋቋመው ቦርድ ግዥን በሚመለከት በዳይሬክተር ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ውል እንዲዋዋሉ ሥልጣን መስጠቱን፣ የተቋሙን ሰነድ በማሳየት ጭምር ክርክራቸውን በስፋት አብራርተዋል፡፡ ደንበኛቸው አንድ ወር ከ20 ቀናት በላይ ያለ ምንም ጥፋታቸው ታስረው ቅጣት እያወራረዱ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ደንበኛቸው አገራቸውን ለረዥም ዓመታት በሙያቸው ያገለገሉ ባለሙያ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ክርክሩ ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት ብይን የተሰጠበትና የታለፈ መሆኑን በመግለጽ፣ በአብላጫ ድምፅ ለሁለተኛ ጊዜ ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

አቶ ኢሳያስ በሶማሌ ክልልና በባሌ ዞን ይገነባ የነበረን የኔትወርክ ማስፋፊያ ቴሌኮም ታወር ዝርጋታን ያለ ምንም ጨረታ ለሜቴክ ከመስጠታቸውም በተጨማሪ፣ ከሥልጣናቸው ውጪ ውል በማሻሻል በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንና በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን በሚመለከትም ተከራክረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በተፈቀደለት ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጪ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ከኢትዮ ቴሌኮም የተለያዩ ማስረጃዎችን መቀበሉን፣ ላልተጠናቀቁ ሳይቶች ክፍያ ተቀናሽ የተደረጉበትን ሰነድ መሰብሰቡን፣ ከሜቴክ የኦዲት ሪፖርት መጠየቁንና ሌሎችንም የምርመራ ሥራ ማከናወኑን አስረድቷል፡፡

ከአዲስ አበባ ውጪ የምስክሮችን ቃል መቀበልና ከኢትዮ ቴሌኮም ሰነዶች መቀበል እንደሚቀረው፣ ከሜቴክ የኦዲት ምርመራ ውጤት እንደሚቀረውና ሌሎች ቀሪ ሥራዎች እንደሚሠራ ጠቁሞ፣ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የአቶ ኢሳያስ ጠበቆች ባቀረቡት የመቃወሚያ ሐሳብ እንደገለጹት፣ መርማሪ ቡድኑ የሚያቀርበው የምርመራ ሒደት ሁሉም ተመሳሳይ ነው፡፡ ምስክሮችን በስልክ እየተከታተለ መሆኑን መግለጹ አግባብ እንዳልሆነና ደንበኛቸው የተጠረጠሩት ከሥልጣናቸው ውጪ ውል ማሻሻላቸው  ሆኖ እያለ፣ ከክልል ምስክር የሚያስፈልግበት ምክንያት እንዳልገባቸውም አስረድተዋል፡፡ ሁሉም ያቀረበው የምርመራ ሒደት ተደጋጋሚና ፍርድ ቤቱም ብይን የሰጠባቸውንም አካቶ እያቀረበ መሆኑን አክለዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ባለ ክርክሩ በአቶ ኢሳያስ ትዕዛዝ  ለሜቴክ መቶ በመቶ ክፍያ መፈጸሙን ከገለጹ በኋላ፣ እንደገና ብልሽት ላጋጠመው ስምንት በመቶ አፈጻጸም እንዳልተከፈለ መናገሩን አስታውሶ አንድ ጊዜ ኦዲት እንደሚያሠራ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ክፍያው የተቀናነሰበትን ሰነድ እንደሚፈልግ በመግለጽ ደንበኛቸው በሆነ ባልሆነ መከራከሪያ ሐሳብ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን እያጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ምርመራው ወደኋላ እየተመለሰ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ሊያስቆመው እንደሚገባ ጠቁመው፣ የመርማሪውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ፣ የጠበቆቹን የመከራከርያ ሐሳብና የዋስትና ጥያቄ በማለፍ ከተጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ሰባት ቀናት በአብላጫ ድምፅ  በመፍቀድ ለጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሌላው የተመለከተው በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩትንና በእስር ላይ የሚገኙትን የዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁምን ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ባለው ቀጠሮ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን ጨርሶ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ በማስረከቡ፣ ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ እንዲቀርብ አሥር ቀናት ፈቅዶለት ነበር፡፡ ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ በተባለበት ዕለት ክሱን ማቅረብ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ክሱን አደራጅቶ መጨረስ አለመቻሉ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ከአቶ ዓለም ጋር በተለይ ከሪቬራ ሆቴልና ከፕላስቲክ ፋብሪካ ግዥ ጋር በተያያዘ አብረዋቸው የተጠረጠሩና የክስ መዝገባቸው በአንድ መጠቃለል ያለባቸው ሌሎች ግለሰቦች በመኖራቸው፣ የምርመራ ሒደቱ ውስብስብና ብዛት ያለው በመሆኑ በተባለበት ዕለት ማድረስ አለመቻሉን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109 መሠረት ክስ መመሥረቻ ጊዜ የሚፈቅደው 15 ቀናት በመሆኑ፣ ክሱን መሥርቶ እንዲቀርብ አምስት ቀናት እንዲጨመርለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች ደንበኛቸው የተጠረጠሩበት ጉዳይ ግልጽ መሆኑንና ዓቃቤ ሕግም በምርመራው ወቅት አብሮ ይሠራ እንደነበር አስረድተው፣ ውስብስብ እንደሆነ መግለጹ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ዓቃቤ ሕግ የጠየቀውን አምስት ቀናት በመፍቀድ ለጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...