Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበተቀነባበረ ሴራ እንድንታሰር ተደርገናል ያሉ 34 ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረቡ

በተቀነባበረ ሴራ እንድንታሰር ተደርገናል ያሉ 34 ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በከፍተኛ ሁኔታ ተቀስቅሶ የነበረውን የሕዝብ ቁጣ ለማድበስበስና አቅጣጫ ለማስቀየር ሲባል በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. ከፍተኛ የመንግሥት አመራር በነበሩና በታዛዦቻቸው በተቀነባበረ ሴራ ለእስር መዳረጋቸውን የገለጹ የመንግሥትና የመንግሥት ልማት ተቋማት ከፍተኛ አመራር የነበሩ 34 ግለሰቦች፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አቤቱታ አቀረቡ፡፡

አቤቱታውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በተለያዩ ክፍሎች በኃላፊነት ይሠሩ የነበሩ ስምንት፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን 17፣ ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ሦስት፣ ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አምስት፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት አንድ፣ በአጠቃላይ 34 አመራር የነበሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡

‹‹በሙስና ወንጀል ተጠርጥራችኋል›› ተብለው ላለፉት 17 ወራት በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የገለጹት ግለሰቦቹ ምንም ዓይነት የሙስና ወንጀል እንዳልፈጸሙ፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የሰበሰባቸውን ማስረጃዎችና እነሱም ያቀረቧቸውን የተለያዩ ሰነዶች በተጣበበ ጊዜያቸው ውስጥ ሆነውም ቢሆን እንዲመለከቱላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተማፅነዋል፡፡

- Advertisement -

ካለው አገራዊና ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በተለያዩ ሥራዎች ተወጥረው ጊዜ ቢያጡ እንኳን አብረዋቸው ታስረው የነበሩና የተቋማት መሪዎች የነበሩ አለቆቻቸው ክስ ተቋርጦላቸው መፈታታቸው አንዱ የንፅህናቸው ማሳያ መሆኑን፣ ያለ ምንም ምክንያት የወቅቱ የተጋጋለ የፖለቲካ ውጥረትና የሕዝብ ጥያቄ ማስተንፈሻ መደረጋቸውን የሚያሳይ መሆኑን እንዲረዱላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መሪነት ከመጡ ካለፉት ዘጠኝ ወራት ጀምሮ በአገር ውስጥ በተለያየ መንገድ በሕገወጥ መንገድ ታስረው የነበሩ በርካታ ዜጎች በይቅርታና ክሳቸውን በማቋረጥ እንዲፈቱ ማድረጋቸውን በማስታወስ፣ እነሱም ሕገወጥ ተግባር ከተፈጸመባቸው ንፁሃን ዜጎች መካከል በመሆናቸው ዕድሉ ሊነፈጋቸው እንደማይገባ ጠይቀዋል፡፡

ከኤክስፐርትነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ለበርካታ ዓመታት በቅንነት አገራቸውን ሲያገለግሉ እንደነበር በየተቋማቸው የሚገኙ ማኅደሮቻቸውና የየተቋማቱ ሠራተኞች ህያው ምስክር መሆናቸውን የጠቆሙት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ በተለይ አሁን ባለው ለውጥ ውስጥ ሆነው ሕዝባቸውንና መንግሥትን ባላቸው የረዥም ጊዜ ልምድና ዕውቀት ማገዝ ሲገባቸው፣ በሐሰት በተቀነባበረ ማስረጃና ምስክር ማረሚያ ቤት ተወርውረው መቅረታቸው አሳዛኝና የነበረውን የወቅቱን የመንግሥት አመራር  ብልሹ አሠራር ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን አክለዋል፡፡

በተጠቀሱት ተቋማት በተለይ በተወሰኑት ላይ ከፍተኛ አመራርና መሪ የነበሩ ግለሰቦች ምን እንደፈጠሩ ስማቸው በአደባባይ ውሎ እያለ እነሱን ላለመንካት ወይም የማያስነካቸው አካል ስላላቸው በማለፍ፣ በተቀነባበረና በሐሰተኛ ማስረጃ በማረሚያ ቤት ተወርውረው መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ የሚቀርብባቸው የሰነድና የሰው ምስክር ውኃ ስለማያነሳ፣ በወንጀል ሕግ ለትክክለኛ ዓላማ የተቀመጠን ‹‹የመንግሥትን ሥራ በማያመች ሁኔታ መምራት ወይም ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም›› የሚለውን አንቀጽ በመጥቀስ ዋስትና ተከልክለው በእስር እየማቀቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በግፍ የታሰሩት እነሱ ብቻ ሳይሆኑ መላው ቤተሰባቸው ጭምር መሆኑን የሚናገሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ የተፈጸመባቸውን ደባ በመተንተን በትክክለኛ መንገድ የመንግሥት አካል መርምሮ ፍትሕ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ  ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚመለከታቸው የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም፣ በሥራ ብዛት ይሁን ወይም በሌላ ምላሽ ባለማግኘታቸው በድጋሚ ለማስታወስ መፈለጋቸውን አስረድተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንደ አዲስ የተዋቀረው ካቢኔ ቀድሞ የነበረው አመራር ለዓመታት ያበላሸውን በማስተካከል ላይ መሆኑን ባሉበት ማረሚያ ቤት ሆነው ሲሰሙ ደስተኞች እንደነበሩና ለአገርም ተስፋ ሰጪ መሆኑን መገንዘባቸውን የሚናገሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ ለእነሱም የእስር መነሻ የፖለቲካ አመራሩ የነበረበትን የውስጥ ችግር ለመሸፈንና በወቅቱ ሕዝቡ እያቀረበ የነበረውን የለውጥ ጥያቄ አቅጣጫ ለማስቀየር የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከአመራሩ ለውጥ በኋላ በሐሰት የተወነጀሉበት ጉዳይ ዕልባት ያገኛል የሚል ተስፋ እንደነበራቸውም በአቤቱታ ደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡

አቤቱታ አቅራቢዎቹ በዝርዝር እንዳስረዱት፣ በወቅቱ አብረው በዘመቻ ከታሰሩት 152 ተጠርጣሪዎች ውስጥ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አምስት፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን ሦስት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ዘጠኝ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አሥር፣ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ውበትና ፅዳት ኤጀንሲ 35፣ እንዲሁም ከባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሁለት ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ መፈታታቸውን አስረድተዋል፡፡ ያለ ምንም በቂ ማስረጃ በሐሰተኛ ውንጀላ ለአሥር ወራት አብረዋቸው ከታሰሩ በኋላ መፈታታቸው እጅግ በጣም የሚያስደስትና ትክክለኛ ዕርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ያለ ምንም አሳማኝ መሥፈርት በተመሳሳይ የሐሰት ውንጀላ እነሱም ታስረው እያለ በእስር እንዲቆዩ መደረጋቸቸው ግራ እንዳገባቸውና በነጋ በጠባ ቁጥር፣ ‹‹እኛ ምን አጥፍተንና በድለን ነው?›› የሚል ጥያቄ እያነሱና እየቆዘሙ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

ሌላው ሰሞኑን እየገረማቸውና ግራ እያጋባቸው የሚገኘው ነገር በሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩ አንድ የስኳር ኮርፖሬሽንና አምስት የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ‹‹የወሰዱትን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አምነው በመክፈላቸው ክሳቸው ተቋርጧል፤›› በማለት በሌሉበት የተከሰሱ ግለሰቦች ጭምር መካተታቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ማጥፋቱን ያመነና ተፀፅቶ ገንዘቡን የመለሰ በይቅርታ ከተፈታ፣ ንፁህ መሆናቸውን እየተናገሩና እየለፈለፉ በሐሰተኛ የሰነድና የሰው ማስረጃ ታስረው የሚገኙት ዕጣ ፈንታ ምን መሆን እንዳበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መፍትሔ እንዲሰጡበት ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ወደ መሪነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እየተናገሩት ያለና የሕግ መርህ የሆነው፣ ‹‹አንድ ንፁህ ሰው ያላግባብ ከሚታሰር መቶ ወንጀለኛ ቢፈታ ይሻላል፤›› የሚለው ተጥሶ፣ እነሱም ምንም ዓይነት ወንጀል ሳይፈጽሙ መታሰራቸው የህሊና ዕረፍት እየነሳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው የወቅቱ ተደራራቢ ኃላፊነት ለጠቅላይ ሚኒስተሩ አቤቱታ ማቅረብ የተገደዱት፣ ጥያቄያቸው የፍትሕ በመሆኑ እንደሆነ አክለዋል፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጊዜ ባይኖራቸው እንኳን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እንዲጎበኟቸው አድርገው፣ ዝርዝር ጉዳዮችን አጣርተው እንዲያቀርቡላቸውና ተመልክተውት ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡              

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...