Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ብሔራዊ ባንክ መቼ እንደሚመለስ የማይታወቅ ገንዘብ ነው ለመንግሥት የሚያበድረው›› አቶ አብዱልመናን መሐመድ፣ የተመሰከረላቸው የሒሳብ አዋቂና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ተንታኝ

አቶ አብዱልመናን መሐመድ በ1988 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ንግድ ሥራ ኮሌጅ በመመረቅ በባንክ ውስጥ ለአጭር ጊዜ ካገለገሉ በኋላ፣ በውጭ ኦዲተርነት እስከ 1998 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ከጀማሪ እስከ ከፍተኛ ኦዲተርነትና የኦዲት ኃላፊ ባለው ዕርከን አገልግለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው ክፍለ ጊዜ ጎን ለጎን በመማር፣ ከዚያም በተመሠከረላቸው የሒሳብ አዋቂዎች ማኅበር (ኤሲሲኤ) ተመዝነው ማረጋገጫቸውን አግኝተዋል፡፡ ከዚያም የማኅበሩ አባል ከሆኑ በኋላ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪያቸውን ከሠሩ በኋላ በእንግሊዝ የሥራ ፈቃድ በማግኘታቸው ወደዚያው አመሩ፡፡ በዚያም ለሁለት ዓመታት በአካውንታንትነት ከሠሩ በኋላ ወደ ሌላ ኩባንያ በመዛወር በአካውንት ማኔጀርነት የግልና የመንግሥት ትልልቅ ንብረቶችን በሚያስተዳድረው ተቋም ውስጥ ለአሥር ዓመታት እየሠሩ፣ እግረ መንገዳቸውንም በኤድንብራ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ ስኩል የማስትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮም በፋይናንስ መስክና በተያያዥ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የዘወትር ዓምደኛ በመሆን በተለይ በአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ሲጽፉ ቆይተዋል፡፡ ሙያዊ አስተያየታቸውንም ሲያቀርቡና በሌሎችም የኅትመት ውጤቶች ላይ ሲሳተፉ ይታወቃሉ፡፡ አቶ አብዱልመናን ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ሪፖርትና ኦዲት ዝግጅት ጀምሮ፣ ከግል ባንኮችና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር ስላላቸው ግንኙነት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጫናዎች፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ስለሚገኝበት ሁኔታ፣ የስቶክ ገበያ በኢትዮጵያ ስለሚያስፈልግበትና ሌሎችም መሠረታዊ የፋይናንስ ጉዳዮች ከአሥራት ሥዩም ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- እየመጣ ያለው ዓለም አቀፍ የፋናንስ ሪፖርት ስታንዳርድ ዝግጅት፣ ወይም ‘ኢንተርናሽናል ፋይናንሺያል ሪፖርቲንግ ስታንዳርድ’ የተሰኘውን አሠራር የሚደነግገው ሕግ ከወጣ ከአራት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ትግበራው እንደሚጀመር ሲጠበቅ ቆየት ብሏል፡፡ ቢዘገይም አሁን ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ትልልቅና የሕዝብ ፍላጎት አለባቸው ተብለው የሚታሰቡ ኩባንያዎች በዚህ ሕግ መሠረት እንዲሠሩ እየተደረጉ ነው፡፡ ኩባንያዎቹም አማካሪ ከመቅጠር ጀምሮ ያሉትን ዝግጅቶች እያካሄዱ ነው፡፡ ይሁንና ከዚህ ቀደም በነበረው ‹‹ጄነራሊ አክሴፕትድ አካውንቲንግ ፕሪንሲፕልስ-ጋፕ›› በሚባለውና በአሁኑ መካከል መሠረታዊ የሒሳብ አያያዝ ላይ ልዩነት አለ? ሪፖርት ላይ ያተኮረ ይመስላልና ይህስ ምን ማለት ነው?

አቶ አብዱልመናን፡- በፊት የነበረው በደፈናው ‘ጋፕ’ የሚባለው የአሜሪካ ሥርዓት የተሻሻለና የተወሰነ የሒሳብ አያያዝ ላይ የሚያተኩር አይደለም፡፡ አዲሱ ግን በኮድ የተወሰነና የተሰጠውን ስታንዳርድ ተከትሎ የሚሠራ ነው፡፡ ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት የቆየው ጋፕ በአሜሪካ ሲተገበር የቆየ ነው፡፡ ይሁንና እንደ ዘርፉ የተለያየ የሒሳብ ሥርዓት ይተገበራል፡፡ ንግድ የራሱ አለው፡፡ የበጎ አድራጎትና ሌላውም እንደዚሁ፡፡ እኛ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በአሜሪካ መጻፍሕት ንድፈ ሐሳቡን በደፈናው እንማርና ወደ ተግባር ዓለም ስንመጣ፣ አብዛኞቹ ሕጎች ግን ከእንግሊዝ የተቀዱ በመሆናቸው ሒሳብ አሠራሩን ከአሜሪካ፣ ሕግና አተገባበሩን ከእንግሊዝ እያደባለቅን ስንሠራ ቆይተናል፡፡ አንዳንዴ ከሁለቱም ያልሆነ በልማድ የመጣም አለ፡፡ ለምሳሌ በ1979 ዓ.ም. ደርግ ያወጣው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማኑዋል ላይ የተቀዱ አሠራሮችም በሒሳብ አሠራርና አያያዝ ውስጥ ይተገበሩ ነበር፡፡ ነገሩ ሁሉ እዚህም እዚያም የተበታተነ ነበር፡፡ አካውንቲንግ ወይም የሒሳብ አያያዝና ፋይናንሺያል ሪፖርት ስንል ልዩነቱ አካውንቲንግ የመዝገብ አያያዝን የሚያይ መሆኑ ነው፡፡ የፋይናንስ ሪፖርቱ ደግሞ የመዝገብ ሪፖርት አቀራረቡን ወይም የሒሳብ ሪፖርት አቀራረቡን የሚያይ ማለታችን ነው፡፡ አመዘጋገብና ሪፖርት አያያዝ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተበታትኖ የነበረውን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ወዳለው አንድወጥ አሠራር እንዲመጣ ወደማድረጉ ነው የመጣው፡፡ ኦዲተሮች በሒሳብ ኦዲት ወቅት የሚከተሏቸው የአሠራር ደረጃዎች አሉ፡፡ መዝገቦች የሚመረመሩትና የሒሳብ ሪፖርት አቀራረቡ የሚፈተሽበት አሠራር አለ፡፡ ከዚህ በፊት በልማድ ከየቦታው የተወሰዱ አሠራሮች ታክለውበት በደፈናው ተቀባይነት ያለው የሒሳብ ኦዲት ይባል የነበረው፣ አሁን ያለው እያንዳንዱ ሒደቱ በሙሉ በቁጥር ወይም በኮድ የተቀመጠ የአሠራር ሒደት ዓለም አቀፍ አሠራር ነው፡፡ ኦዲተሩ በሥራው ወቅት መከተል ያለበት በዝርዝር የተቀመጡ የአሠራር ደረጃዎች አሉ፡፡ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ህንድ፣ አውስትራሊያና ሌላውም የየራሱ የሒሳብ አያያዝና ሪፖርት አደራረግ ሕግ ነበራቸው፡፡ ይሁንና አንድ ወጥ ወደሆነ አሠራር እየመጡ ነው፡፡ ዓለም ወደ አንድ ዓይነት አሠራር እየመጣ ሲሆን እኛም ይህንኑ ተቀላቅለናል፡፡ ይህ ማለት ዓለም አቀፍ አካል ግን አለ፡፡ የሒሳብና የኦዲት ደረጃዎችን የሚያወጣውን አካል ኢትዮጵያ ትከተላለች፡፡     

ሪፖርተር፡- ከቀደመው ሥርዓት ወደ አዲሱ የሚደረገውን ሽግግር እንመልከት፡፡ አዲሱ የሒሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ ሕግ ከወጣ በኋላ አብዛኞቹ ተግባራዊ ለማድረግ እየተፍጨረጨሩ ነው፡፡ ለብዙዎቹ ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ ሌሎች አገሮች ከነባሩ ወደ አዲሱ አሠራር ሲገቡ እንዴት ነበር የተቀበሉት?

አቶ አብዱልመናን፡- በእነ እንግሊዝ ውስጥም ቢሆን ብዙ ክርክር ያስከተለ ነበር፡፡ አንዳንድ ነገሮች ከየአገሮቹ ሁኔታ አኳያ የተለያዩ በመሆናቸው ወጥነት ወዳለው ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ለመምጣት ብዙ ጊዜ ወስዶባቸዋል፡፡ የእንግሊዝ ሒደቱ ላይከብደን ይችላል፡፡ አውጪዎቹ ራሳቸው ከእንግሊዝ በብዛት ያሉበት በመሆኑ ነው፡፡ እንደ እኛ ያሉ አገሮች የሚከተሉት ግን ላደጉ አገሮች የወጣውን ስታንዳርድ በመሆኑ፣ ብዙዎቹ ባደጉ አገሮች ውስጥ ያሉት ነገሮች የሉንም፡፡ ለምሳሌ የፋይናንስ ሀብት፣ ዴሪቬቲቭስ፣ ወዘተ. የሚባሉት መረጃዎች የሉም፡፡ በእኛ አገር የሒሳብ ሪፖርቱ ሲዘጋጅ ሕጉ የአክሲዮን ገበያን በገበያ ዋጋ አቅርብ ሊል ይችላል፡፡ በስቶክ ገበያ የሚገበያይ ኩባንያ ቢሆን ኑሮ ገበያ ላይ ያለውን የዋጋ ሁኔታ በቀላሉ ከገበያው ማግኘት ይቻላል፡፡ እኛ አገር አንድ ባንክ ውስጥ ድርሻ ያለውን ኩባንያ የገበያ ዋጋ ማወቅ ከባድ ይሆናል፡፡ የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ የገበያ ዋጋ አይደለም፡፡ አንድ አካውንታንት የአክሲዮን ደርሻን እንዴት ነው በገበያ ዋጋ መሠረት የሚመዝነው የሚለው ላይ ውስብስብ ነገር ያጋጥማል፡፡ ሌላው ጉዳይ አንዳንድ የፋይናንስ ሪፖርት ስታንዳርድ ሕጎች የማይገጥሙባቸው ሁኔታዎች መኖራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ከብሔራዊ ባንክ ሕጎች ጋር የማይገጥምበት አሠራር አለው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከተበላሹ ብድሮች ሥሌት ጋር ለጥንቃቄ ብሎ ያስመቀጣቸው አሠራሮች አሉ፡፡ የፋይናንስ ሪፖርት ስታንድርድ ደግሞ የሚፈቅደው የተባለሸ ብድር ሥሌት ደረጃ አለ፡፡ በዚህ የተነሳ በርካቶች የሒሳብ ሪፖርት ደረጃው የተዘጋጀው በሌሎች አገሮች በመሆኑ፣ ወደ እኛ አገር ሲመጣ አልተጣጣመም እያሉ እየተቸገሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አጠቃላይ ተቀባይነት ባገኙ የሒሳብ መርሆዎች ወይም ጋፕ በሚባለው አሠራር መሠረት አብዛኛው አገር ይመራ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የሚመሠከርላቸው የሒሳብ አዋቂዎችን ዕውቅና ሲሰጡ ወይም ሰርቲፋይ ሲያደርጉ እንግሊዞች ኤሲሲኤ የሚሉት የራሳቸው አላቸው፡፡ አሜሪካኖች ሲፒኤ ሌሎችም የየራሳቸው አሠራር አላቸው፡፡ ዓለም እንዴት ነበር ከዚህ ቀደም በሒሳብ ቋንቋ የሚግባባው? 

አቶ አብዱልመናን፡- ያደጉ አገሮች የሒሳብ መዝገብ አያያዝና ሪፖርት አዘገጃጀት ሥርዓት ላይ ብዙ ተጠቃሚ አላቸው፡፡ በተለይ ሪፖርቱን የሚጠቀምበት በርካታ ክፍል ስላላቸው አገሮች የየራሳቸውን ደረጃ አውጪ ሥርዓት በማስመቀጥ ይገለገሉ ነበር፡፡ አውስትራሊያ፣ ህንድና ሌሎቹም የየራሳቸው ደረጃ ነበራቸው፡፡ በአገሮች መካከል የሕግ፣ የፖለቲካ፣ የባህል ልዩነት አላቸው፡፡ ኢንፎርሜሽኑን የሚጠቀምበት አካልም እንዲሁ ስለሚለያይ፣ የአሜሪካ ሒሳብ አቀራረብ ከእንግሊዝ ይለያያል፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ወጥ የሒሳብ አቀራረብ ስታንዳርድ ለብዙ ዓመታት አልነበራትም፡፡ ዓለም እንዴት ይግባባ ነበር ለሚለው እንግሊዝ ውስጥ የሚሠራ የአሜሪካ ኩባንያ፣ በእንግሊዝ አገር የሒሳብ ሪፖርት መሠረት ያቀርባል፡፡ አሊያም ሁለት ሪፖርት ለሁለት አገሮች ሕጎች እንዲስማማ አድርጎ ያቀርባል፡፡ ከሞላ ጎደል የተወሰነ ልዩነት ቢኖራቸውም ባደጉ አገሮች ያለው ስታንዳርድ በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚያ ላይ ግንኙነት ስለነበራቸው በመጨረሻ ወደ አንድ ዓይነት ስታንዳርድ እንምጣ ሲሉ አልተቸገሩም፡፡ በእኛ አገር ግን ሪፖርቱን የሚፈልጉት ግፋ ቢል ድርጅቶች እንጂ ሌላ ተጠቃሚ ወገን ብዙም የለም፡፡ ስለዚህም ጥራት ያለው ሪፖርት ላይ ብዙም አልተጨነቅንበትም፡፡

ሪፖርተር፡- የዚህን ዓይነት የሪፖርት ስታንዳርድ በአብዛኛው እንዲተገበርለት የሚጠይቀው የታክስ አስተዳደሩ አካል እንደሚሆን ይታሰባል፡፡

አቶ አብዱልመናን፡- ሁለት ነገሮች ላብራራ፡፡ የፋይናንስ ሪፖርትና የታክስ ሪፖርት የሚባል ነገር አለ፡፡ የፋይናንስ ሪፖርት ዒላማ የሚያደርገው የመረጃ ተጠቃሚ አካል አለ፡፡ የታክስ ሪፖርትንም የሚጠቀምበት የመረጃ አካል አለ፡፡ የታክስ ሪፖርትን የታክስ ጉዳይ ባለሥልጣን ነው የሚጠቀመበት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ የቆዩ የታክስ ሕጎች ነበሯት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2002 የተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ በርካታ ያልተብራሩ ነገሮች አሻሽሎ ነበር፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት የወጣው አዲሱ አዋጅም በርካታ ነገሮችን አሻሽሏል፡፡ የአዋጁ ዓላማ አንድ ግብር ከፋይ እንዴት ሒሳቡን መያዝ እንዳለበት፣ የተለያዩ ግብይቶችን በምን አግባብ መመዝገብ እንደሚገባው፣ ወዘተ. የሚደነግግ ከታክስ ባለሥልጣኑ ዓላማ አኳያ የሚቀርብ  ነው፡፡ ሌላው ግን የኩባንያ ባለቤቶች፣ የአክሲዮን ድርሻ መገበያያ ስቶክ ገበያ ቢኖር ኑሮ ብሔራዊ ባንክና ሰፊው ተጠቃሚ የሚፈልጉት የሪፖርት አቀራረብና አመዘጋገብ ከታክስ በሰፊው  ይለያል፡፡ ድርጅቶች ሁለት መዝገብ ነው ያላቸው፡፡ የታክስ መዝገብና የፋይናንስ ሪፖርት መዝገብ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ የአንድን ድርጅት ትክክለኛ አቅም የሚያሳይ መዝገብ በአብዛኛው የሒሳብ ሪፖርት ውስጥ የሚታይ ሲሆን በባህሪው ከታክስ መዝገብ ይለያል፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ዓለም አቀፍ የሒሳብ ሪፖርት ስታንዳርድም ሆነ ጋፕ የሚባሉት ከታክስ መዝገብ አኳያ መሠረታዊ ልዩነት አላቸው እያልን ነው?

አቶ አብዱልመናን፡- እንደየአገሮቹ ሁኔታ ይለያያል፡፡ በተለይ የታክስ መዝገቡ ለየአገሮቹ ተጨባጭ ሁኔታ ተጣጥሞ የሚዘጋጅ ነው፡፡ የሒሳብ መዝገብና ሪፖርት አቀራረብ ስታንዳርድ ዋና ዓላማው ግን የአንድን ድርጅት ትክክለኛ የንብረት መጠን በትክክለኛ መጠን ማሳየት፣ ስለድርጅቱ በቂ መረጃ መስጠት፣ መረጃውን የሚፈልጉት አካላት በተገቢው መንገድ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ነው ታክስ ግን ዓላማው ይህ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ሪፖርት በማዘጋጀት ሥርዓት ውስጥ በዓለም አቀፉ የፋይንስ ሪፖርት ስታንድርድና በጋፕ መካከል ያለው መሠረታዊ ሊባል የሚችል ልዩነት ምንድነው?

አቶ አብዱልመናን፡- በዓለም አቀፉ ስታንዳርድ መሠረት እያንዳንዱ ጉዳይ የየራሱ ሒደት ተቀምጦለታል፡፡ ቋሚ ንብረት ወይም ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ፣ የፋይናንስ ነክ ኢንቨስትመንት ላይ የሚከተለው የዋጋ አወጣጥ ላይ ዓለም አቀፉ ስታንድርድ እንዲህ ሥራ እንዲያ አድርግ ብሎ ያስቀመጣቸው ኮዶች አሉት፡፡ ይህ በጣም ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ጋፕ ግን የተለያዩ አሠራሮች የተካተቱበት በመሆኑ አንዱ ጉዳይ ላይ ከአሜሪካ ወስደህ ስትሠራ ሌላው ላይ ከእንግሊዝ ወስደህ ትሠራለህ፡፡ አሰያየም ወይም ተርሚኖሎጂዎችን ሳይቀር ወስደናል፡፡ ቋሚ ንብረትን የምትመዘግበው ከአሜሪካ በተዋስከው አሠራር ቢሆን፣ ተንቀሳቃሽ ንብረትን ደግሞ ከእንግሊዝ ሊሆን ነው፡፡ ይህ በመሆኑ አሠራሩ አንድ ወጥ ያልነበረ ነው፡፡ ጥሩ የሒሳብ አያያዝ አላቸው በሚባሉት በእኛ አገር ባንኮች እንኳ የነበረው የሒሳብ ሪፖርት አቀራረብ ብዙ ልዩነቶች ያሉት ነው፡፡ የዓለም አቀፉ የሒሳብ ሪፖርት ስታንድርድ ሌላው ጥቅሙ ለተጠቃሚው በርካታ መረጃዎችን ማቅረቡ ነው፡፡ በፊት ልማዱ ስላልነበር መረጃ የማግኘት ዕድላችን ጠባብ ነበር፡፡ በዚያም ላይ የመረጃ አቀራረቡ በራሱ ወጥነት የሌለው ነበር፡፡ ወጥነት መኖሩ አንዱን ባንክ ከሌላው ለማወዳደር ሒደቱን ቀላል ያደርግዋል፡፡ ይህ እንግዲህ አቀራረብ ላይ ያለው ነው፡፡ በሒሳብ አያያዝ ላይም እንደዚሁ ልዩነቶች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- የአንድን ኩባንያ ሀብት፣ ገቢና መሰል ሒሳቦችን በማሥላት ወይም ግምት በማውጣት ሒደት ላይ አዲሱ የሒሳብ ሪፖርትና አያያዝ ሥርዓት ለውጥ ያመጣል?

አቶ አብዱልመናን፡- ልዩነት ሊያመጣ ይችላል፡፡ ለምሳሌ የአገልግሎት ተቀናሽ ሥሌት ላይ አንተ የምትጠቀመው የሒሳብ ሥሌት እኔ ከምጠቀም ሊለይ ይችላል፡፡ በአዲሱ አሠራር ግን እንዴት ማሥላት እንዳለብህ መመርያዎች ተቀምጠዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር መሠረት አስገዳጅ የአመዘጋገብ ሒደት ስላልነበር፣ አንድ ኩባንያ የአክሲዮን ድርሻ ሲገዛ አንድ አክሲዮን በገዛበት ዋጋ መሠረት ሊመዘገብ ይችላል፡፡ አንዳንዱ ትክክለኛውን የአክሲዮን ዋጋ በገበያ አስተምኖ ሊመዘገብ ይችላል፡፡ በፊት የነበረው አሠራር የሒሳብ ባለሙያውን ውሳኔ መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ ለምሳሌ ዕቃ በክምችት የሚይዙ ድርጅቶች የተበላሹባቸውን ዕቃዎች በተመለከተም የተለያየ አመዘጋገብ ነበር፡፡ አንዳንዱ ከዓመት በላይ በክምችት የቆየን ዕቃ 50 በመቶው እንደከሰረ እንቁጠረው ሊል ይችላል፡፡ ሌላው 30 በመቶው ነው የከሰረው ሊል ይችላል፡፡ አንድ ወጥ አሠራር ባለመኖሩ ሁሉም እንደመሰለው የሚሄድበት ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ በሥርዓተ ትምህርት ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ይኖር ይሆን?

አቶ አብዱልመናን፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ሁኔታ ለማስረዳት ከበፊቱ ልነሳ፡፡ የአካዴሚክ መጻሕፍቱ አብዛኞቹ ከአሜሪካ ነበር የሚመጡት፡፡ ችግሩ ግን መጻሕፍቱ የቆዩና ያለፈባቸው መሆናቸው ነው፡፡ ሒሳብ እንደ ሕግ በየጊዜው የሚለዋወጥ ቢሆንም መጻሕፍቱ ግን እንደዚያ አይደሉም፡፡ ወደ ተግባር ዓለም ስትመጣ ደግሞ ኢትዮጵያ ሕጎቿን የቀዳችው ከእንግሊዝ በመሆኑ፣ በትምህርት ቤት የተማርነውና በሥራው ዓለም ስንሰማራ የሚገጥመን ነገር የማይገናኝ ነበር፡፡ በአዲሱ የሒሳብ አያያዝና አቀራረብ ሥርዓት ላይ ዩኒቨርሲቲዎች ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ሥርዓተ ትምህርታቸውን ወደዚህ ማምጣት አለባቸው፡፡ የምንከተለው ዓለም አቀፉን የሒሳብ ሪፖርት ስታንዳርድ ከሆነ መጻሕፍቱም በዚህ ላይ ያተኮሩ መሆን አለባቸው፡፡ የሒሳብ ባለሙያዎችን በዚህ መስክ ማፍራት ከፈለግን ከአሜሪካው የቆየ ሥርዓት መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ ግን ብዙ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል፡፡ በየዓመቱ ስለሚለዋወጥ አዳዲስ መጻሕፍት መምጣት አለባቸው፡፡ የኦዲትና የሒሳብ አያያዝ ላይ የሚያስተምሩ ተቋማት ሥርዓተ ትምህርታቸውን በዓለም አቀፉ ስታንዳርድ መሠረት ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ ይህ ግን ምን ያህል ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ላይ ጥያቄ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፉን የሒሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ ስታንዳርድ የሚያስተገብረው ቦርድ በዚህ ላይ ምንድን ማድረግ አለበት?

አቶ አብዱልመናን፡- ቦርዱ የተለያዩ ሥልጠናዎችና ዓውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት እያደገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግን እኮ የሥርዓቱ አስፈላጊነት ላይ እንጂ መሠረታዊ የሥርዓተ ትምህርት ሥልጠና እየሰጠ ነው ሊባል አይችልም፡፡

አቶ አብዱልመናን፡- እርግጥ አስፈላጊነቱ ላይ ቢሆንም የተለዩ ሥልጠናዎችን እንዴት ነው ማዘጋጀት ያለበት? ምን ያህልስ ባለሙያዎች አሉት? የሚለውና ከ40 በላይ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡትን ትምህርት መቀየሩ ላይ ቦርዱ ምን ያህል አቅም አለው የሚለውን ብናይ አቅም ያለው አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመነጋገር ለውጥ እንዲያደርጉ፣ ሥርዓተ ትምህርት እንዲቀይሩና በየዓመቱም ለውጦችን እያዩ በዚያው ልክ እንዲሠሩ ቦርዱ ቢያደርግ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ቦርዱ በራሱ ትምህርትና ሥልጠና የመስጠት አቅም የለውም፡፡ እንኳንስ ለቦርዱ ለዩኒቨርሲቲዎችም ከባድ ሥራ ነው፡፡ ግን ደግሞ ግዴታ ነው፡፡ በባለሙያ እጥረት ኩባንያዎች እየተቸገሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ባንኮች እንሂድ፡፡ በሚጽፏቸው በርካታ ጽሑፎች ውስጥ ስለባንኮች ብዙ ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት አላቸው፡፡ በአንጻሩ ንግዱ ወይም ኢኮኖሚው በጅምላ በገንዘብ እጥረት ሲቸገር ይታያል፡፡ ሁለቱ ሲጣጣሙ አይታይም፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ አብዱልመናን፡-   ከስምንት ዓመታት በፊት ባንኮች ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት ነበራቸው፡፡ ይሁንና የ27 በመቶው የብሔራዊ ባንክ መመርያ ከእያንዳንዱ ብድራቸው እየቀነሱ ለገዥው ባንክ እንዲያስገቡ በመደረጋቸው፣ የብር እጥረት እስኪገጥማቸው ድረስ ችግር ሆኖባቸዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የመጠባበቂያ ክምችት ድንጋጌውን እስከ አምስት በመቶ ዝቅ እስከማድረግ የገባበት ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የገንዘብ ሀብታቸው ትልቅ ሆኗል፡፡ የባንኮቹ የገንዘብ ክምችትና ኢኮኖሚው የሚፈልገው መጠን ለምን አልተጣጣመም ለሚለው አንደኛው ምክንያት፣ ባንኮቹ የሚከተሉት ጥብቅ የብድር መመርያ  ነው፡፡ ለብድር የሚጠይቁት ዋስትናና ሌላውም መሟላት ያለበት መሥፈርት ለበርካታ ተበዳሪዎች ፈተና ነው፡፡ የብድሩን እጥረት በተወሰነ ደረጃ ያመጣው የገንዘብ እጥረት ነው ቢባልም፣ የገንዘቡ አቅርቦት እያላቸውም ሰዎች ከባንክ ብድር ለማግኘት የሚቸገሩት ግን ጥብቅ የዋስትና መመርያ ስለሚከተሉ ነው፡፡ አንዳንዴ ለሚሰጡት ብድር ከሚያስፈልገው በላይ ዋስትና ይጠይቃሉ፡፡ ከሰሞኑ ባንኮች ብዙ ገንዘብ እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡ ብዙ ተበዳሪ ግን የላቸውም፡፡ በተለይም ተገቢውን መሥፈርት የሚያሟላ ተበዳሪ እያገኙ አይደለም፡፡ ባንኮቹ የሚጠይቁት የብድር ማስያዣ ዋናው መንስዔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ሁኔታ ወደፊት እንዴት ነው የሚቀጥለው? መፍትሔውስ ምንድነው?

አቶ አብዱልመናን፡- የባንኮቹ ብቻ ችግር አይደለም፡፡ ብሔራዊ ባንክ የሚይዘው የተበዳሪዎች ማንነትና የብድር ሁኔታ ዝርዝር መረጃ አለ፡፡ ይህ ምን ያህል የተሟላ ነው የሚለው አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ የተሟላ የብድር አሰጣጥ ሥርዓት፣ የተጠናከረ የብድርና የተበዳሪዎች ግምገማ ሥርዓት፣ የተበዳሪዎችን የቢዝነስ ፕላን ለመገምገም የሚያስችል በቂ ዕውቀት እየተሟላና እየተደራጀ ሲመጣ፣ ሰዎች በቂ ባይሆንም እንኳ ባቀረቡት የቢዝነስ ፕላን መሠረት ብድር ማግኘት መጀመራቸው አይቀርም፡፡ ችግሩ ግን የባንኮች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሥርዓቱ ነው፡፡ የሚቀርበው የቢዝነስ ፕላን ባንኮችን ሊያሳምን የማይችል ደካማ ከሆነና ጠንካራ የመረጃ ሥርዓት ካልዳበረ ባንኮች ብቻ ሊኮነኑ አይችሉም፡፡ ስለሚያበድሩት ሰው በቂ መረጃ ካላገኙ፣ የተበዳሪውን ማንነት፣ የሥራ፣ የብድር ታሪክና መሰል መረጃዎች ሊሰጥ የሚችል ብሔራዊ መታወቂያ ቢኖር ነገሩን በመጠኑ ያቀለው ነበር፡፡ ተበዳሪው በግል ታማኝ መሆኑ ለብድር እንደ በቂ ማስረጃ ሊታይ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ የሰውየውን ታማኝነት መረጋገጥ በማይቻልበትና በቂ መረጃ በሌለበት ወቅት የግል ብድር ስጡኝ ቢል ብዙ አያስኬድም፡፡ 

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ባንክ የ27 በመቶ መመርያ የአጨቃጫቂነቱን ያህል ከልክ በላይ ተከማችቷል ሲባል የነበረውን የባንኮች የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ታስቦ ተተግብሯል መባሉ ባንኮች የምናበድረውን ገንዘብ ብቻም ሳይሆን፣ ለሥራ ማስኬጃ የምናውለውን ገንዘብ ሁሉ እየወሰደብን በማለት አቤቱታ ሲያሰሙበት ቆይተዋል፡፡ በቅርቡ ከወጡ መረጃዎች እንደታየው ከሆነም ባንኮች ካበደሩት ውስጥ እስከ 40 በመቶ በዚህ 27 በመቶ የብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት የተያዘባቸው ነው፡፡ ይህንን እንዴት ነው ተቋቁመው መዝለቅ የቻሉት?

አቶ አብዱልመናን፡- መመርያው ከመውጣቱ በፊት ባንኮች የተከማቸ ገንዘብ ነበራቸው፡፡ ከጠቅላላው የተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ የብድር ምጣኔ ሲሠራ እስከ 60 በመቶ ነበር፡፡ ከመመርያው መተግበር መጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ የነበራቸውን የተከማቸ ገንዘብ ብቻ ባንኩ ይወስድ ስለነበር፣ ባንኮቹ በሥራቸው ላይ ብዙም ችግር አልሆነባቸውም ነበር፡፡ በቂ ብድር ሰጥተውም የተከማቸ ገንዘብ ነበራቸው፡፡ እየቆየ ሲመጣ ግን መመርያው ባንኮችን መጭመቅ ጀመረ፡፡ በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ፈተና ሆኖባቸው ነበር፡፡ ይሁንና ጥሩው ነገር አምስት ዓመታት ያስቆጠረው የ27 በመቶ ብድር እየተመለሰላቸው መሆኑ ነው፡፡ የ27 በመቶው መመርያ ተመላሽ የማይደረግ ቢሆን ኑሮ፣ ባንኮች የሚሰጡት ብድር እየቀነሰ ይልቁንም ለቦንድ የሚያወጡት እየጨመረ በመሄድ ከባድ ሁኔታ ውስጥ ይከታቸው ነበር፡፡ ቦንድ ለመግዛት የሚያወጡት ገንዝብ ከጠቅላላው ተቀማጭ ውስጥ እስከ 27 በመቶ ገደማ ይዟል፡፡ ምንም እንኳ አሁንም ቦንድ እየገዙ ቢሆንም የተጣራ ጫናው አነስተኛ እየሆነ መጥቷል፡፡ የመጀመሪያዎቹን አምስት ዓመታት ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳይ የቆየው የቦንድ ግዥና ጫናው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ እያነሰ ነው የመጣው፡፡

ሪፖርተር፡- ምናልባት ጫናው እየቀነሰ መጥቷል የተባለው ለቦንድ ግዥ የሚውለው ዋናው ገንዘብ ነው፡፡ ስለወለዱ እንነጋገር፡፡ ብሔራዊ ባንክ ለቦንድ የሚከፍለው ወለድ፣ ባንኮች ከደንበኞች የሚሰበስቡትና ለቦንድ ግዥ በሚያውሉት ገንዘብ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ሲታይ ባንኮችን ያከስራቸዋል፡፡ 

አቶ አብዱልመናን፡- ባንኮች ሁለት ዓይነት ተቀማጭ አላቸው፡፡ አንደኛው የቁጠባ ሲሆን፣ ሌላኛው ተንቀሳቃሽ የሚባለው ነው፡፡ ተንቀሳቃሽ ሒሳብ የሚባለው ወይም በቼክ ሒሳብ የሚንቀሳቀስበት ቁጠባ ምንም ዓይነት የወለድ ወጪ የለውም፡፡ አብዛኞቹ ባንኮች ምናልባትም 70 በመቶውን ገንዘብ ከአስቀማጩ የሚያሰባስቡት ከተንቀሳቃሽ ሒሳብ ነው፡፡ በዚህ ሒሳብ ላይ ለአስቀማጩ ወለድ አይከፍሉም፡፡ ይህንን ፈንድ ነው ለብሔራዊ ባንክ ቦንድ ግዥ የሚጠቀሙበት፡፡ ባይሆንማ ኖሮ ለሁሉም ሒሳብ የአምስት ወይም የሰባት በመቶ ወለድ እየከፈሉ፣ በሦስት በመቶ ወለድ ለቦንድ ቢያበድሩማ በኪሳራ ይዘጉ ነበር፡፡ በ30 በመቶ የተቀማጭ ቁጠባ ላይ ነው አምስት በመቶ ሲከፍሉ የቆዩት፡፡ ይህ ወደ ሰባት በመቶ አድጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ግን እንዴት ነው ከተቀንቀሳቃሽ ሒሳብ ተቀንሶ ለረጅም ጊዜ ብድር ክፍያ የሚውለው? ይህስ እንዴት ነው የሚሠራው? አስቀማጩ በማንኛውም ጊዜ ቢጠይቅ ይከፍሉት የለም እንዴ?

አቶ አብዱልመናን፡- ይህ የሚስተናገድበት የራሱ የባንክ አሠራር አለው፡፡ ‹‹ፍራክሽናል ሪዘርቭ›› ይባላል፡፡ አንተ ከምታስቀምጠው ገንዘብ ውስጥ ብሔራዊ ባንክ የተወሰነውን ገንዝብ በመጠባበቂያነት እንዲቀመጥ ባንኮችን ያስገድዳል፡፡ አስቀማጩ ሁሉ በአንድ ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት አይመጣም የሚል ሐሳብ ስላለ፣ የተወሰነ ገንዘብ ተቀማጭ በጥሬ ገንዘብ የተወሰነው በተቀማጭ ይቀመጣል፡፡ በመሆኑም ተንቀሳቀሽ ሒሳብ ላይ የሚያመጣው ጫና አይኖርም፡፡ የተለየ አጋጣሚ ሲፈጠር ወይም የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥም፣ ትርፍ ካለው ቅርንጫፍ በማምጣት ጥያቄውን ያስተናዳሉ፡፡ በጣም አሥጊ ሁኔታዎች ቢፈጠሩ ብሔራዊ ባንክ ጣልቃ በመግባት ያስተካክላል፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ባንክ የ27 በመቶ ቦንድ ግዥ ባንኮች ላይ ጫና ሊያሳርፍ የሚችልበት ሌላ አጋጣሚ ሊኖር ይችላል?

አቶ አብዱልመናን፡- የቦንዱ ግዥ ከዚህ በላይ መሄድ የማይችልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ለታሰበለት ዓላማ ውሏል ወይ የሚለው መታየት አለበት፡፡ ለተፈለገው ዓላማ ካልዋለ ግን ለግል ባንኮች ይሰጥና ሥራ ላይ እንዲያውሉት ቢደረግ የተሻለ ነው፡፡ ከግል ባንኮች የተሰበሰበው ገንዘብ በብሔራዊ ባንክ በኩል ወደ ልማት ባንክ እየተሻገረ ለልማት እንዲውል ነበር ሐሳቡ፡፡ ልማት ባንክ በብድር ይወስድና በረጅም ጊዜ ለሚከፈልባቸው የልማት ፕሮጀክቶች ብድር ይሰጣል ተብሎ ነው የታሰበው፡፡ የግል ባንኮች ለኢንዱስትሪና ለግብርና ብድር አይሰጡም የሚል ወቀሳ ነው የቦንድ ግዥው መነሻ፡፡ አገሪቱ ካላት የልማት ፖሊሲ ጋር መራመድ አልቻሉም የተባሉት የግል ባንኮች፣ ለንግድና ለአገልግሎት ዘርፍ ብቻ ማበደራቸው ሲያስወቅሳቸው ቆይቷል፡፡ የግል ባንኮች በርካሽ ለብሔራዊ ባንክ የሰጡትን ልማት ባንክ በርካሽ ለልማት ፕሮጀክቶች እንዲያበድር ታስቦ ነበር፡፡ በዚህ መነሻና ሙግት ለቦንድ ግዥ የዋለው ገንዘብ ግን ለተባለው ዓላማ ውሏል ወይ ሲባል አልዋለም ነው ምላሹ፡፡ ከግል ባንኮች የተሰበሰበው ወደ 70 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ወደ ልማት ባንክ የላከው ስንት ነው ሲባልም ወደ 50 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የቀረውን ገንዘብ ለግምጃ ቤት ሰነድ ግዥ ነው ያዋለው ማለት ነው፡፡ ልማት ባንክ የተሰጠውን ገንዘብ ለፕሮጀክቶች ከማዋል ይልቅ የብሔራዊ ባንክን የግምጃ ቤት ሰነድ እየገዛበት ነው፡፡ በቅርቡ እንዲያውም ብዙ መግዛቱ ታውቋል፡፡ በተዘዋዋሪም ቢሆንም መንግሥት ፋይናንስ እንደተደረገበት ነው ማለት ነው፡፡ መንግሥት መጀመርያውኑም 70 ቢሊዮን ብር አያስፈልገውም ነበር ማለት ነው፡፡ ገንዘቡ ለታሰበው ለዓላማ ስላልዋለ ለግል ባንኮች መመለስ አለበት፡፡ እንዴት የሚለው ላይ ነው ማሰብ የሚያስፈልገው፡፡ ይህ ሁሉ ገንዘብ አንዴ ሲመጣ መልሶ የዋጋ ግሽበት እንዳያስከትል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ልማት ባንክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምናልባትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ላይ ሳሉም በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ ባንኩ የሚሰጣቸው ብድሮች ትልቅ ጥያቄ የሚነሳባቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ለአብነት ያህል የተበላሸ ብድር መጠኑ 39 በመቶ እንደደረሰ፣ የሀብት ጥራቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ እንደመጣና ባንኩ በአግባቡ ራሱን ካልፈተሸ ወደፊት መጓዝ የሚከብደው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ልማት ባንክ ሥራ ቢያቆም ወይም አሁን በሚሄድበት መንገድ መጓዝ ቢያቅተው የግል ባንኮችን ጉዳት ላይ አይጥላቸውም?

አቶ አብዱልመናን፡- ጉዳት ያስከትልባቸዋል እንጂ፡፡ ባንኮቹ ቦንድ የገዙት ከብሔራዊ ባንክ ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ ዕዳውን ሊከፍላቸው ይችላል፡፡ እንደ አገር ስናስበው ግን የልማት ባንክ ዕዳ እንደ ኪሳራ መልሶ ብሔራዊ ባንክ ላይ ይመጣበታል፡፡ ገንዘቡ ትልቅ በመሆኑ ጉዳቱ ትልቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ደግነቱ ልማት ባንክ ተቀማጭ የሚያሰባስብ ተቋም ባለመሆኑ፣ ባንኮችን ይዞ የመጥፋትና ቀውስ የማስከተል ደረጃ ላይደርስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ትልቅ ጫና ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ ልማት ባንክን ከኪሳራ መታደግ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ገንዝብ የማተም ችግር ስሌለበት አትሞም ጫናውን ሊወጣው ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡን በዋጋ ግሽበትና በታክስ ሊጎዳው እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ችግሩን መወጣት ይቻላል፡፡ ሕግና ሥርዓት ቢኖረው ኖሮ ከባድ ጉዳይ በሆነ ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- የፋይናንስ ተቋማትን ዓመታዊ ሪፖርቶችን ሲቃኙ ከታዘቡዋቸው መካከል ልማት ባንክ ወዴት እያመራ ነው ይላሉ? የባንኩን ህልውና የሚፈታተኑ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

አቶ አብዱልመናን፡- ልማት ባንክ የመንግሥት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ባንክ ነው፡፡ በግብርናና ማኑፋክቸሪንግ መስኮች ድጋፍ እንዲያደርግ ይጠበቃል፡፡ እርግጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮችም ተፅዕኖ አላቸው፡፡ የፖለቲካ ብጥብጥ በእነዚህ ዘርፎች ላይ ጉዳት ያመጣል፡፡ ብድሮቹ ከተበላሹም አፈጻጸሙ ችግር ውስጥ ይወድቃል፡፡ ገንዘቡ ታጥቦ ያልቃል፡፡ በየጊዜው ካልተሰጠው በቀር የገንዘብ አቅርቦትም ላይኖረው ይችላል፡፡ ይህ በፋይናንስ በኩል ያለው ችግር ነው፡፡ ባንኩ ሊከስርም ይችላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትልልቅ ብድሮችን እያየዘ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የተባለሸ ብድር መጠኑ ባንኩ ብድር ስለሚሰጥባቸው መስኮች የሚናገረው ነገር አለ፡፡ 40 በመቶ ብድሮች በሕጉ መሠረት አይከፈሉም ማለት ነው፡፡ የግብርናውና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ብዙ ይናገራሉ ማለት ነው፡፡ በአግባቡ እየሠሩ አይደሉም፡፡ ግብርናው በጣም በተለጠጠ የብድር ጥቅም አቅርቦት እያገኘ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ መስኩም ቢሆን ከሚያገኘው በላይ ችግር ውስጥ ነው፡፡ እንደ አይካ አዲስ ስንትና ስንት ብድርና ሌሎች ድጋፎች አግኝተውም ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ የግብርናውና የማኑፋክቸሪንጉ ችግር ልማት ባንክ ላይ ይንፀባረቃል፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ የልማት ባንክ ብድር አሰጣጥ ሒደቶች ትክክለኛውን አሠራር ተከትለው ነው ወይ የሚያልፉት የሚለውንም ጥያቄ ውስጥ ይከቱታል፡፡ ባንኩ ከራሱ ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ውጫዊ ምክንያቶች ነው ይህ ሁሉ የተበላሸ ብድር የመጣበት? ወይስ በውስጡ ባሉ ችግሮች? ማለትም የተቀመጡ አሠራሮች ተጥሰው የማይገባቸው ሰዎች ብድር አግኝተዋል ወይ? ጥናትና ምዘና ሳይሠራ ነው ወይ ብድር የሚለቀቀው? ልማት ባንክ ሥራውን ሠርቶ ከቁጥጥሩ ውጪ በሆኑ በፖለቲካ ትኩሳት፣ የሚያበድርበት ዘርፍ አትራፊ ባለመሆኑ፣ የድርጅቶች የፋይናንስ አስተዳደር ችግር፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የኃይል ችግር፣ ወዘተ. ከባንኩ ውጪ ያሉ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህ የባንኩን የፋይናንስ አቅም አዳክመው ካፒታሉን በሙሉ ሊያሳጡት ይችላሉ፡፡ ከዚያ ባሻገር ግን የመንግሥትንም ፖሊሲ ጥያቄ ውስጥ የሚጥለው ነው፡፡ መንግሥት እንደሚለው የግብርናውና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እያበቡ ከሆነ ልማት ባንክ ለምንድነው እየተዳከመ የመጣው የሚለውን መመርመር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ዘርፍ የባንክ ኢንዱስትሪው ነው፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮችን የሚቆጣጠርባቸው መንገዶች ጥያቄ ሲያስነሱ ይታያል፡፡ አብዛኛው የመቆጣጠሪያ ሥልቶቹ ወደ ገንዘብ ፍሰት ያደሉ ናቸው ይባላል፡፡ ለምሳሌ ከባንኮቹ ማግኘት የሚችለውን ገንዘብ ለማግኘት ሲል የሚከተላቸው አሠራሮች መንግሥት ወጪዎቹን ለመሸፈን ብሎም አትሞ በሚያስገባው ገንዘብ የዋጋ ግሽበት እንዳይከሰት ለመቆጣጠር በማሰብ የተቃኙ እንጂ፣ ሌላ ትኩረት የላቸውም የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ ወገን ባንኮች ጤነኛ የሆነ የባንክ አሠራር እንዲኖራቸው በማሰብ የተቃኘ ነው የሚሉም አሉ፡፡ በእርስዎ ግምገማ ብሔራዊ ባንክ የቱ ጋ ይመደባል?

አቶ አብዱልመናን፡- ከቅርብ ጊዜ በተለይም ከአሥር ዓመታት ወዲህ ባንኩ የመንግሥት ፖሊሲ አስፈጻሚ እየመሰለ መጥቷል፡፡ መንግሥት የልማታዊነት አካሄድን መከተል ከጀመረ ወዲህ መንግሥት ሁሉን አድራጊ እንደሆነ አፉን አውጥቶ ባይናገርም፣ የኢኮኖሚ ልማት የማመጣው እኔ ነኝ ዓይነት አካሄድ ይታይበታል፡፡ የግሉ ዘርፍ በማይገባባቸው ቦታዎች እኔ መግባት አለብኝ እያለ፣ የትኛውም የገበያ ድክመት ታይቶበታል ብሎ በጠረጠረው ቦታ ሁሉ ለመግባት ያልከፈታቸው የልማት ድርጅቶች የሉም፡፡ ለዚህ ሰፊ ሀብት ያስፈልገዋል፡፡ ንግድ ባንክ ብቻውን በቂ ስላልሆነ የግል ባንኮችን ወደ ራሱ ፍላጎት ወደ ማምጣት ገብቷል፡፡ አንዳንዶቹ የብሔራዊ ባንክ ድንጋጌዎች ወይም መመርያዎች ራሱ ባንኩን አላስፈላጊ ወዳልሆኑና ዘርፉን ወዳልተፈለገ ማነቆ የሚከቱ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የቦርድ አባላትን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እስከመወሰን እኮ የደረሰ ነው፡፡ ይህ በጣም የበዛ ቁጥጥር ነው፡፡ እርግጥ የትርፍ ድርሻ ሲካፈሉም ብሔራዊ ባንክ ድርሻው እኔ ጋ መጥቶ ማፅደቅ አለብኝ እስከማለት ደርሷል፡፡ ይኼንን በሚመለለከት በንግድ አዋጁ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ ምን ያህል እንደሚወሰን፣ እንዴት እንደሚወሰን በሕጉ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አልፎ እኔንም አሳውቁኝ ማለት ግን አላስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኮቹ የተወሰነውን በጀት ለሥልጠና ያዙ መባላቸውስ እንዴት ይታያል?

አቶ አብዱልመናን፡-  በተወሰነ መልኩ ጥሩ ነው፡፡ በግዴታ መጫኑ ግን ነው የሚያጠያይቀው፡፡ እርግጥ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ይህንን ያወጡት የግል ባንኮች ወደ ፊት ለሚጠበቃቸው ውድድር ጠንክረው እንዲዘጋጁ በማሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር በዚህን ያህል ደረጃ በጉልበት ይህንን አድርጉ ያንን አታድርጉ መባል የለበትም፡፡ ባንኮቹ ራሳቸውን ባለባቸው ውድድር የሚበጃቸውን እኮ ያደርጋሉ፡፡ በፍላጎታቸው ማድረግ እንዲችሉ እንጂ በመመርያ እያስገደድህ መሆን የለበትም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ሁለት ሥራዎች ነው የሚሠራው፡፡ ከፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥር ባሻገር የዋጋ ግሽበት እንዳይከሰት የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ይሠራል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሥራውን ትቶታል ማለት ይቻላል፡፡ ሁለተኛው ሥራው የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን የተረጋጋ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ የባንክ መጠባበቂያ ማውጣትና መቆጣጠር፣ የገንዘብ ፍሰትን፣ የተባለሸ ብድር መጠንን ሁሉንም የባንክ እንቅስቃሴዎችን የመከታተል በመመርያ አሊያም በሪፖርት፣ እንዲሁም በአካል እየሄደ በመገምገም መቆጣጠር ይጠበቅበታል፡፡ አንዳንድ አገሮች የገንዘብ ፖሊሲ ቁጥጥር ሥራውን ለሌሎች ተቋማት ይሰጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ይበልጥ እንዲነግሩን የምፈልገው የገንዘብ ፖሊሲን የሚያስፈጽመውና የፋይናንስ ተቋማትን የሚቆጣጠረው አካል መለያየት አለበት?

አቶ አብዱልመናን፡- ችግሩ ኢትዮጵያ ያላትን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በሁለት ተቋማት እንዲመራ ማድረጉ፣ ያላደገ ዘርፍ በመሆኑ ብዙም ትርጉም ላይሰጥ ይችላል፡፡ ያደገ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ቢኖረን ኖሮ የፋይናንሱም የገንዘብ ፖሊሲ መቆጣጠሪያም ለየብቻቸው ተቋማት ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ በእኛ ሁኔታ ብሔራዊ ባንክ ሁለቱንም ሥራዎች መሥራቱ አይከፋም፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር ሥራውን ረስቶ አብዛኛው ትኩረቱ ባንኮች ላይ ብቻ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን የሚነሳ ክርክር አለ፡፡ ባደጉ አገሮችና ገበያቸውም በዚያው ልክ ባደገ አገሮች ውስጥ ገበያው የሚወሰነው በወለድ ምጣኔ ነው፡፡ እንደ ወለድ ያሉ ሥልቶችን በመጠቀም የገንዘብ ፖሊሲውን ማስፈጸምና መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ብሔራዊ ባንክ እንዲህ ያሉ የመቆጣጠሪያ ሥልቶች ስለሌሉት በቀጥታ ጣልቃ እየገባ በመመርያና በደንብ ገበያውን የሚመራባቸው አሠራሮች ላይ ይመሠረታል፡፡ ገበያ ተኮር የሆኑ አሠራሮችን መከተል ያልቻለው፣ የገንዘብ ፖሊሲና የፋይናንስ ተቋማትን የመቆጣጠር ሥራው ተደባልቀውበት ሊሆን ይችላል የሚልም መከራከሪያ ይነሳል፡፡

አቶ አብዱልመናን፡- የባንኩን መመርያዎች ብታይ የተወሰኑት የገንዘብ ፖሊሲ ባህሪይ  አላቸው፡፡ ለምሳሌ የብድር መጠናችሁ ይህን ያህል ይሁን ሲል ዓላማው የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ነው፡፡ የብድር ጣሪያ ሲያበጅ ዋናው ዓላማ ግሽበትን ለመከላከል ነው፡፡ የተቀላቀሉበት አሠራሮች አሉ፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት ገደማ የሠራቸውን ሥራዎች አበጥረህ ስታይ ግን፣ አብዛኛው ሥራው በፋይናንስ ተቋማት መረጋጋት ሥራ ላይ ተጠምዶ ታገኘዋለህ፡፡ በሌላ ጎኑ ለመንግሥት የሚሰጠው ብድር ላይ ትልቅ ቧንቧ ከፍቷል፡፡ ለመንግሥት ብድር በገፍ እየሰጠ የዋጋ ግሽበትን እቆጣጠራለሁ ሊል አይችልም፡፡ ዋናው ቀዳዳ እዚህ ጋ ነው መደፈን ያለበት፡፡ ሌሎች አገሮች ውስጥ ገደብ አለ፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች መንግሥት ከማዕከላዊ ባንክ መበደር አይችልም፡፡ በኬንያ፣ በቅርቡ በጋናም ለመንግሥት ብድር መስጠት በጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ነው፡፡ ምናልባት ቢበደርም እንደ ‹ኦቨር ድራፍት›› ካልሆነ በቀር ከባድ ነው፡፡ የመንግሥት የታክስ ገቢ አንድ ወጥ ስላልሆነ፣ መንግሥት ቢበደርም በዓመቱ መጨረሻ መመለስ አለበት፡፡ የተቀመጠው የብድር ወለድም የማያላውስ ነው፡፡ እስከ 18 በመቶ ሊደርስ ይችላል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ግን መቼ እንደሚመለስ የማይታወቅ ገንዘብ ነው ለመንግሥት የሚያበድረው፡፡ ሁለተኛ የብድር ወለድም ላይኖርበት ይችላል፡፡ መንግሥት ያለገደብ እንደፈለገ ሊበደር ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህ ሙሉ በሙሉ እንደ ኬንያና ጋና መቆም አለበት፡፡ ለሚበደረው ገንዘብ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠየቅ ሲያውቅ መንግሥት ጥንቃቄ ማድረግ ይጀምራል፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከላዊ ባንክ በብዙ አገሮች ተጠሪነቱ ለፓርላማ ሆኖ ገለልተኛ ነው፡፡

አቶ አብዱልመናን፡- በብዙ አገሮች ተጠሪነቱ ለፓርላማ ነው፡፡ አመራሮቹም በጣም የተማሩ ሰዎች ሲሆኑ፣ የሚሾሙትም በፓርላማ ነው፡፡ የፖሊሲ ኮሚቴ አባላትም በጣም የተማሩና በውድድር የሚገቡ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ተሿሚዎች አይደሉም፡፡ በጣም ወሳኝነት ያለው የኢኮኖሚ ተቋም ነው፡፡ ይህንን ተቋም የሚመራ አካል በአንድ የምርጫ ወቅት የሚቀያየርና ተፅዕኖ ውስጥ የሚወድቅ ማድረግ አይገባም፡፡

ሪፖርተር፡- በዘመነ ኢሕአዴግ የመጀመሪያው የግል ባንክ ከተቋቋመ 24 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በብዙ ከለላና ከውጭ ውድድር ነፃ ተደርጎ የቆየው የባንክ ኢንዱስትሪ ከዓመታት በኋላ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል ብሎ መጠየቅ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ደረጃ የቆየው የባንክ ኢንዱስትሪ ለአክሲዮን ባለድርሻዎች አጓጊ የትርፍ ድርሻ ከመስጠትና የተወሰኑ የባንክ አገልግሎቶችን ከማቅረብ በቀር፣ ዘርፉን በፈጠራ የታገዘና በልዩ ልዩ መንገዶች ማስፋፋት አልቻለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በዚህ ቀጣና እንደ ኬንያ ካሉ ባንኮች ጋር መፎካከር እንኳ አልቻለም ተብሎ ይተቻል፡፡ ይህ ምን ያህል የሚያስኬድ ትችት ነው? ሌላው የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚደረግበት ጊዜ መጥቷል ማለትስ ይቻላል?

አቶ አብዱልመናን፡- ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ከዜሮ ነው የጀመረው ማለት ይቻላል፡፡ በርካታ ቅርንጫፎችን የከፈቱ 16 ባንኮች፣ በካፒታል ደረጃም አንድ ቢሊዮን ዶላር የደረሱ፣ በተወሰነ ደረጃ የመንግሥት ባንክን ጫና ተቋቁመው መሥራታቸውም እንደ ልብ እንዳያድጉ አድርጓቸዋል፡፡ የንግድ ባንክ ሁለት ሦስተኛውን የኢንዱስትሪውን ድርሻ በመያዙ የግል ባንኮች እንደ ልብ እንደያድጉ አድርጓል፡፡ በተወሰነ ደረጃ መሻሻሎች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካቶች የባንክ ሒሳብ ከፍተው ገንዘብ ያጠራቅማሉ፡፡ የባንክ አገልግሎት የሚያገኘው ሰው ብዛት በጣም ጨምሯል፡፡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ትልቅ ለውጥ አለ፡፡ ብድሩና ቁጠባው ላይ ብዙም ለውጥ አታይም፡፡ አዳዲስ አገልግሎቶች እንዳይመጡ ያደርገው የነበረው ዝቅተኛ ውድድር ይመስለኛል፡፡ ውድድር ከሌለ ፈጠራ ብዙም አይኖርም፡፡ ጠንካራ ውድድር ሲኖር አዳዲስ ሥራዎች ይመጣሉ፡፡ ቴክኖሎጂውም የመጣው እኮ በተቆጣጣሪው ባንክ ጫና ነው፡፡ የኮር ባርንኪንግና ሌላውም በብሔራዊ ባንክ ምክንያት ነው ሥራ ላይ የዋለው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ግፊት ያስፈልጋል፡፡ ገበያው የሚጠይቅ ሲሆን ራሳቸው ያደርጉታል፡፡ የኃይል አቅርቦትና የኢንተርኔት ጥራት ላይ ችግሮች መኖራቸው ቴክኖሎጂው በሥፋት ሥራ ላይ እንዳይውል አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ የኅብረተሰቡም ችግሮች አሉ፡፡ የትምህርት ደረጃም ወሳኝ ነው፡፡ ከተማ አካባቢ ባንኮች ለምሳሌ ሞርጌጅ ወይም የቁጠባ ቤት ባንክ መክፈት አልቻሉም፡፡ ይህ የተወሳሰበ ዘርፍ አይደለም፡፡ ለምን እንዳልደፈሩት ግን አላውቅም፡፡ የመኖሪያ ቤት ብድር ላይ እርግጥ የመንግሥትም ችግር አለበት፡፡ የቤት ግንባታ ኢንዱስትሪው ከባንኮች ጋር በቅንጅት መሠራት አለበት፡፡ ሰፊ የመኖሪያ ቤት ብድር እንዲፈጠር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ የተበዳሪዎች የብድር ታሪክና ማኅደር በአግባቡ ሊሠራበትና ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ ሞርጌጅ ባንክ በደርግ ጊዜ ነበር፡፡ ያንን ማሳደግ ይገባ ነበር፡፡ በወቅቱ የመንግሥት ሠራተኞች ቤት ሲሠሩ ብድር መስጠት ነበር ሐሳቡ፡፡ ይህ ጥሩ ሐሳብ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ይህንን ባንክ ወደ ንግድ ሥራ ከማስገባት ይልቅ እንደነበረው እንዲቀጥል ቢያደርገው ኖሮ ጥሩ ነበር ባይ ነኝ፡፡ በመጨረሻም ባንኩ ትኩረት የሚሰጠው አጥቶ ተንገዳገደ፡፡ መንግሥት ወደ ንግድ ባንክ እንዲጠቃለል አደረገው፡፡ መንግሥት ሞርጌጅ ባንክን እንደነበር በማስቀጠል፣ የቤት ብድር ሰጪ በማድረግ ጥሩ ሥራ ሊሠራበት ይችል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ንግድ ባንክ የ40/60 እና ሌሎች የቤት ፕሮጀክቶችን መውሰዱ ጥያቄ ሲያንሳ ቆይቷል፡፡ እንዲያውም 40/60 ፕሮጀክት ለመጓተቱም ተወቃሽ እየሆነ ነው፡፡

አቶ አብዱልመናን፡- እንደ እኔ ንግድ ባንክ በዚህ ሥራ ውስጥ መግባት አልነበረበትም፡፡ ትልልቅ የተለመዱ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ማድረግ እንጂ፣ የቤት ግንባታ ሥራዎች ላይ ስፔሻላይዝድ የሆነ ባንክ ነበር እንዲቀጥል መደረግ የነበረበት፡፡

ሪፖርተር፡- ንግድ ባንክ የመንግሥትን በጀት በመከታተል፣ የመንግሥት ድርጅቶችን የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ የዘለለ ሚና የለውም፡፡ በመሆኑም ይህ ባንክ ነጋዴ ነው ወይስ ማዕከላዊ ባንክ ነው የሚል ጥያቄ ሲያስነሳ ይሰማል፡፡ አንዳንዶቹ የብሔራዊ ባንክ መመርያዎች ንግድ ባንክን እንዳይመለከቱት ይደረጋል፡፡ ይኼ በሌሎች አገሮች የተለመደ አሠራር ነው? 

አቶ አብዱልመናን፡- የእኛ አገር የበዛ ነው፡፡ ንግድ ባንክ እንደ ማንኛውም ባንክ ነጋዴ ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ግን እንደ ልማት ባንክ የፖሊሲ ማስፈጸሚያም ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የቤቶች ልማት ላሉት ተቋማት አበዳሪያቸው ንግድ ባንክ ነው፡፡ ይሁንና ባንኩ የተሰጠው ከለላ ግን የበዛ ነው፡፡ በግል ባንኮችና በንግድ ባንክ መካከል ተገቢ ያልሆነ ውድድር እንዲፈጠርና ንግድ ባንክ የበላይነቱን እንዲቆጣጠር የሚያደርግ ከለላ ተሰጥቷል፡፡ እርግጥ መንግሥት ንግድ ባንክ ከግል ባንኮች የሚመርጠው በርካሽ ስለሚያበድረው ነው፡፡ ግል ባንኮች እስከ 20 በመቶ ወለድ ሊጠይቁት ይችላሉ፡፡ የፖሊሲ ባንክ ስለሆነ ግን መንግሥት ከንግድ በርካሽ ለመንግሥት ያበድራል፡፡  

ሪፖርተር፡- ንግድ ባንክ ችግር ቢገጥመው ከፍተኛ ውድቀት የሚያስከትልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ማለት እንችላለን?

አቶ አብዱልመናን፡- ብሔራዊ ባንክ ይህ እስኪሆን ድረስ ዝም አይልም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ባንኩ በዚህ ደረጃ እስኪዳከም ያደርሰዋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ሆኖም የሚያሠጉኝ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሰጡት ብድሮች በጣም ያሳስባሉ፡፡ ለስኳር ኮርፖሬሽን የተሰጡትም በጣም አሳሳቢዎች ናቸው፡፡ አንድን ባንክ በዚህ ደረጃ ተጋላጭ ማድረጉ ተገቢ አይደለም፡፡ ሆኖም ለውድቀት የሚያሠጋው ደረጃ ላይ ግን አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ንግድ ባንክ ለትልልቅ መንግሥታዊ ድርጅቶች አበድሯል፡፡ ለግሎችም ጭምር፡፡ ልማት ባንክ ለእነ አይካ አዲስ አበድሮ ችግር ገጥሞታል፡፡ ንግድ ባንክ ግን ላበደራቸው ፕሮጀክቶችና ድርጅቶች የሰጠው ብድር ስለመበላሸቱ አሊያም ችግር ውስጥ ስለመግባቱ ሲናገር አንድም ጊዜ አንሰማም፡፡ ብሔራዊ ባንክ በንግድ ባንክ ውስጥ ከጀርባ ይገባል ማለት ነው?

አቶ አብዱልመናን፡- እንደ ሌሎች ባንኮች የንግድ ባንክን ዓመታዊ ሪፖርት አላገኝም፡፡ በድረ ገጻቸው የሌሎች ባንኮችን ስታገኝ የንግድ ባንክን ግን አታገኝም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የተፈጠረ ነገር አለ ወይ ያስብላል፡፡ ለህዳሴው ግድብ የዋለው ገንዘብ እየተከፈለ አይደለም፡፡ ግድቡ ገና ግንባታ ላይ ነው፡፡ ለፕሮጀክቱ የሚሰጠው ብድር በሰባት ዓመታት ውስጥ የሚፈከል ነው፡፡ በኮርፖሬት ቦንድ አግባብ ቢሰጠውም እየተከፈለ ግን አይደለም፡፡ ብድሩን በብድር እየከፈሉ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እየተጠራቀመ መጥቷል፡፡ የንግድ ባንክ ሰዎች ይህ ነገር ሳያሳስባቸው የቀረ አይመስለኝም፡፡ መንግሥት ልማት ላይ እንደሚያደርገው የንግድ ባንክ መረጃዎችን ይፋ አያደርግም፡፡ ንግድ ባንክ ባለው ሁኔታ በተለይም ከሰጣቸው ትልልቅ ብድሮች አኳያ መታየት ያለበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ውስጥ የስቶክ ገበያ ለማስጀመር ፍኖተ ካርታ አውጥቷል፡፡ ቀድሞ ነገር ይህንን የካፒታል ገበያ ለማስጀመር የታያዘው ሁለት ዓመት ማለትም እ.ኤ.አ. 2020 ነው መባሉ ምክንያታዊ የጊዜ ገደብ ነው ወይ? የካፒታል ገበያን መንግሥት የሚፈራበት ንድፈ ሐሳባዊ አመክንዮስ ምንድነው?

አቶ አብዱልመናን፡- የኢትዮጵያ መንግሥት የካፒታል ገበያን በተመለከተ ለ20 ዓመታት ጥያቄው ሲቀርብለት ቆይቷል፡፡ የስቶክ ገበያ አንደኛው ዓላማ ፋይናንስ እንዲገኝ ማድረግ ነው፡፡ መንግሥት ብዙም አያምነውም፡፡ የካዚኖ ቁማር ነው ብሎ ሊያስበውም ይችላል፡፡ ዕድገት ለማምጣት የባንክ ኢንዱስትሪው ብድር ይበቃል የሚል መከራከሪያ አለው፡፡ እኔ በበኩሌ የካፒታል ገበያ ካዚኖ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምናልባት መንግሥት ከሰሞኑ የካፒታል ገበያ እንዲጀመር የፈቀደበት ምክንያት እየተካሄዱ ሪፎርሞች አኳያ ለቀቅ የተደረጉ፣ ከልማታዊ መንግሥትነት እያፈገፈገ ወደ ሊበራልነት የመሄድ አዝማሚያ እየታየበት በመሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ግን በጣም አጭር በመሆኑ እውነታውን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ለስቶክ ገበያ ከሚያስፈልጉት ውስጥ ጥራት ያላቸው የፋይናንስ ሪፖርትና ኦዲት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በስቶክ ገበያ የሚሸጠው የሚጨበጥ ሸቀጥ አይደለም፡፡ የሚሸጠው የፋይናንስ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ዋጋ ለማውጣት የፋይናንስ መረጃ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የፋይናንስ መረጃ ደግሞ የፋይናንስ ሪፖርት ነው፡፡ ይህንን የሚመሰከር ጥራት ያለው ኦዲት ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን የተጀመረው የእነዚህ ሥራ ነው፡፡ ለስቶክ ገበያ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትና የሠለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋል፡፡ የስቶክ ብሮከሮች ያስፈልጋሉ፡፡ የኢንቨስትመንት አማካሪዎች፣ ዝርዝር የአሠራር ሕግ፣ የግብይት ማቀፉን የሚያሳይ ሥርዓት፣ የተቆጣጣሪ አካል መመሥረትና ሌሎችም መሠረታዊ ጉዳዮች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ በሁለት ዓመታት ውስጥ ማሟላት የሚሳካ አይደለም፡፡ መንግሥት ምናልባት በሁለት ወይም በሦስት ዓመታት ውስጥ ተጀምሮ ከዚያ በኋላ ነገሮች በሒደት ይስተካከላሉ ሊል ይችላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ቦንድ በተወሰነ ደረጃ ‹‹ፕራይሜሪ ማርኬት›› እየተባለ ግብይት እየተፈጸመበት ነው፡፡ ለዚህም ቢሆን ግን የስቶክ ገበያው ስላልመጣ ብዙም ሲንቀሳቀስ አይታይም፡፡ የስቶክ ገበያው ቢመጣ ለመንግሥት ቦንድ ግብይት እንደ ‘ሰከንደሪ’ ወይም ሁለተኛ ገበያነት ሊያገለግል ይችላል ማለት ነው?

አቶ አብዱልመናን፡- አዎ፡፡ ‘ሰከንደሪ ማርኬት’ በመንግሥት የቀረበውን ቦንድ ለመገበያየት ይውላል፡፡ ፕራይሜሪ ገበያው ላይ አዲስ የሚቀርቡ ቦንዶች ከመነሻው የሚሸጡበት ሲሆን፣ እንደ ድሮው በየሚያዲያው የሚቀርብ ሳይሆን በስቶክ ገበያው በተቀመጡት አሠራሮችና አማካሪዎች አማካይነት ግብይት የሚፈጸምበት ሲሆን፣ ሰከንደሪ ማርኬት በሚባለው ውስጥ ደግሞ ይህንን ቦንድ ማንኛውም ሰው ግብይት ይፈጽምበታል ማለት ነው፡፡ ገበያው ለቦንድ ዋጋ በማውጣት ያገበያያል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሐሳብ ማቅረብ ባልተገባ መንገድ የሚያስበይን ከሆነ እንደ አገር በአጠቃላይ የሳትነው ነገር አለ ብዬ እገምታለሁ›› ደስታ ጥላሁን፣ የኢሕአፓና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና...

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹እርስዎ ንጉሥ ነዎት ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትር?›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረበች በሰፊው ሲወራ ሰንብቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት የቅርቡ...

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...