Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ታዝላችሁ ገብታችሁ ምነው ባታስቁን?

እነሆ ከሽሮ ሜዳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ‹‹እዚህ ጋ ጠጋ! ጠጋ! ‘ለማዘር’ እዚህ ተጠጉላቸው፤›› የወያላው ተለምዷዊ ቀጭን ትዕዛዝ ናት። ዛሬ ግን መብት አስከባሪ ገጥሞታል። ‹‹አልጠጋም! ለምንድነው የምጠጋው? የከፈልኩህ ለአንድ መቀመጫዬ ብቻ መሰለህ?›› ተጠጊ የተባለችው ወይዘሮው ብልጭ ብሎባታል። ከዓመት ዓመት ባርቆብን እንዴት ልንሆን ነው? ‹‹ምናለበት በሁለቱም መቀመጫችን ተዘፍዝፈን ወያላና መንግሥትን ከማማት እርስ በርስ ብንተባበር? አይ እኛ ተቀምጦ ሰማይ ቀዶ መስፋት ብቻ፤›› ወያላው አጋዥ ለማግኘት አሳባሪ መንገዶችን በሙሉ በመጠቀም ላይ ነው። ‹‹ደግ አደረግን! እዚያ ያስለመዱህ ይጠጋጉልህ! ጊዜው የመጠጋጋት ነው ብለህ ከሆነ በጊዜ የማያምን ደግሞ አለ፤›› ወይዘሮዋ እንደ እንዝርት ትሾራለች። ‹‹ምናለበት ብትጠጋና ብንንቀሳቀስ? አንድ ላይ ከመደህየት ተደጋግፎ ማደግ አይሻልም? ይገርማል!›› ይላል አጠገቤ የተቀመጠ ወጣት። ከኋላችን ሦስተኛው ረድፍ ላይ ደግሞ፣ ‹‹ይኼው ነው በቃ እንዳትሰሚው፤›› እያለ የጠወለገ ኑሮ ጀምሮት መጠጥ የጨረሰው ጎስቋላ ያጉተመትማል።

አጠገቡ ‘ማች በማች’ የለበሰች ዝንጥ ያለች ወጣት ቦርሳዋን እንቅ አድርጋ ታቅፋ፣ አልሰማሁም አላየሁም የሚመስል ስሜት ውስጥ ያለች ትመስላለች። ከመጨረሻ ወንበር አንድ አዛውንት፣ አንድ ጎልማሳና ዕድሜያቸው በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገመቱ ወጣቶች ጎን ለጎን ተሰይመዋል። ወያላው እልህ ይዞት አጠጋግቶ ሊያስቀምጣቸው የነበሩትን ተሳፋሪዎች አንዱን ጎማ ላይ፣ አንዱን ከጋቢና ወንበር ጀርባ፣ ሌላውን ሞተር ላይ አደላድሎ አስቀምጦ “ሳበው!” ብሎ በሩን ከረቸመ። ወይዘሮዋ በድል አድራጊነት ስሜት ፈገግ ብላ፣ ‹‹እኛን የሰለቸን ከእናንተ ጀምሮ ጉድለታችንና ክፍተታችንን ምክንያት አድርጎ ሙሴያችሁ ነኝ ተቀበሉኝ፣ ተከተሉኝ፣ እመኑኝ የሚለን የሐሰተኛ ነብይ ብዛት ነው። ራሳችን ለራሳችን መብት ብንቆም ከመጀመሪያው መቼ በየአቅጣጫው ነጂ ይላክብን ነበር፤›› ብላ በራሷ ዓለም በፈጠረችው የፖለቲካ ስላቅ ተረተች። ነገሩ ከምኔው የነጂና ተነጂ አተካራ ውስጥ እንደገባ ፈጣሪ ይወቀው!

ጉዟችን ተጀምሯል። በዚህ መሀል አልሰክን ስላለው ፖለቲካ ጨዋታ የጀመሩ አሉ። ‹‹እኔ መጀመሪያ ‘መቼስ በኑሯችን መቀለድ እንጂ መደሰት ስለማናውቅ እናጋንናለን’ ብዬ ትቼው ነበር ለካ እውነት ነው፤›› እያለ ከአዛውንቱ አጠገብ የተቀመጠው ሞላ ያለ ተክለ ሰውነት ያለው ጎልማሳ ያወራል። “ምኑ ነው እውነት?” አዛውንቱ አፋቸውን ማንቀሳቀስ የደከማቸው ናቸው። ‹‹የእኛ አገር ፖለቲካ እንደ ሰነፍ ተማሪ ተመርቆ ቶሎ ሥራ አይጀምርም ሲባል የሰማሁት ተረብ እውነት መሆን እያደረ ገርሞኛል፤›› አለ ጎልማሳው። “ኤድያ! አትተወውም?” አዛውንቱ ነገሩን በአጭሩ ለመቅጨት ትግል የያዙ ይመስላሉ። “ምኑን ነው የምተወው?” ጎልማሳው መነዝነዙን ተያያዘው። ‹‹ፖለቲካውንም፣ ሐሜቱንም፣ አሉባልታውንም፣ ወሬውንም፣ ፖለቲከኛ ተብዬዎችንም ሁሉንም መተው ተለማመድ እንደ እኔ. . .›› ብለው እግራቸው ሥር ማየት ጀመሩ። ወያላው አበደ። ‹‹ምን ነካዎት ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ? እንዴት የሕዝብ ተስፋ ላይ ያላግጣሉ?›› ሲላቸው ወያላው፣ ‹‹ድንቄም! አንተ ደግሞ ምን ቤት ነህ እንደ አበደ ሰባኪ የምትውረገረገው. . .›› ሲሉት አነጋገራቸው በሳቅ አውካካን፡፡  

ወያላው በንዴት ሁላችንንም ተራ በተራ ሲያየን ቆይቶ፣ ‹‹አሁን እናንተ አይደለም ተሠልፋችሁ መዋል፣ ምንስ ብትሆኑ ይታዘንላችኋል?›› እያለ ፊቱን ሲያዞር፣ ‹‹ምን ያበሳጨዋል ይኼ! ይኼው ዙሪያችንን የሌለ መመርያና ነቀፌታ፣ ሕግና ትዕዛዝ ያለጠፍክበት ቦታ የለም። የመሰላችሁን አስተያየት አትስጡ የሚል ግን አለ? ንገረኛ! ከየትኛው ሕግ ጠቅሰህ ነው የምትከሰኝ? አንተም የሰው የሐሳብ ነፃነት ለመገደብ ነው የምትፈልገው? ገና ከመሬት ሳትነሳ የሰው መብት ለመደፍጠጥ ከፈለግክ ነገ የተመቻቸ ነገር ካገኘህ ደግሞ ለሌላ ነገር አትመለስም አይደል?›› ብለው አዛውንቱ ባሱ። ይኼን ጊዜ ጎን ለጎን የተቀመጡት ወጣቶች ቀበል አድርገው፣ ‹‹ወይ ነፃነት በሰማሽ ስንቱን እንስማ?›› ሲባባሉ ሰማን!

ወያላው ሞተር ላይ ያስቀመጠው ተሳፋሪ ስልኩ ትጮሀለች። በስንት ስቃይ በስንት አሳር ካለችበት ታስሳ ወጣች። ‹‹ይኼ ሰውዬ ነዳጅና የከበሩ የተፈጥሮ ማዕድናት ላይ ቢሠራ፣ መጀመርያ ራሱን ከዚያ ምናልባት አገሩን ሊጠቅም የሚችል ሰው ይመስላል፤›› ይላል ከጎኔ የተቀመጠው። ባለ ስልኩ “ሃሎ!” የጆሯችን ታንቡር እስኪበሳ መጮህ ጀመረ። ‹‹ይሰማኛል ቅድም እኮ ተቋረጠ። ምን ይታወቃል ሚሊዮን እያልኩ ሳወራ ቴሌ ትን ብሎት ይሆናላ! ሃሃሃ. . .›› ገልመጥ ገልመጥ እያለ እያየን ንግግሩን ቀጥሏል። ‹‹ስድስት ሚሊዮን እጄ ላይ አለ። ቀሪው እህል እጃችን ሲገባ በባንክ ትራንስፈር ይደረግልሃል ብለውኛል። አዎ ተፈራርመናል እንጂ. . .›› እያለ ቀጠለ። ይኼኔ ተሳፋሪዎች እያርጎመጎሙ ወሬ ጀመሩ።

‹‹እህም ወይ ሚሊዮን እንዲህ ሳናስበው እንደ ማስቲካ አፋችን ውስጥ እናላምጠው?›› አለች ከወያላው የተናቆረችው ወይዘሮ። ‹‹እኛ የአፋችን ነገር መቼ ቸገረን የሆዳችን እንጂ የሚያንገዋልለን። እንይዘዋለን ባዶ። መቶ ብር ብን ሲል አይራራ። አብሮ በልቶ ጠጥቶ የሚንሸራተተው ወዳጅ በዛ ብለን ሳንጨርስ፣ በስንት መከራ በላባችን የምናመጣው ገንዘብ ረድኤተ ቢስ መሆን ባሰ፤›› ትላለች አጠገቧ የተመቀጠች ደርባባ። ሦስተኛ ረድፍ ላይ ደግሞ ያ ጎስቋላ ጎልማሳ፣ ‹‹እኔ ግን  እንደ ምንም ብዬ ፌስታል ነው ማምረት ያለብኝ። አይመስልሽም?›› ከመነጽር እስከ ሎቲ በ‘ማች’ ያበደችውን ተሳፋሪ ጨዋታ ለማስጀመር ሙከራ አደረገ። በፍጥነት ዞር ብላ “አልገባኝም?” ከማለቷ፣ ‹‹በዚህ አያያዝ እንደ ዚምባቡዌ በዘንቢልና በፌስታል ገንዘብ ተሸክመን ጉልት መውጣታችን አይቀርማ! ዋናው ግን ማደጋችን ነው፤›› ሲላት እንሰማለን። ሰው ግን እንዴት አዙሮ ተኳሽ ሆኗል?!

ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። ወያላችን አንድ ሚሊየነር ሞተር ላይ አስቀምጦ እየተጓዘ መሆኑን ሲሰማ የባሰውን ተናደደ። ‹‹ወይ አይጠቀሙ ወይ አያስጠቅሙ፣ ወይ አይጠጉ ወይ አያስጠጉ፤›› ይላል። ነጋዴው ስልኩን እንደ ቀጠለ ነው። ጋቢና የተሰየሙት ተሳፋሪዎች ሳይቀሩ ወያላውን ሰምተውት ኖሮ፣ ‹‹እባክህ በተጠጋጋ ብቻ አይደለም ዕድል ያስፈልጋል። ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ሲሄድ የሚታለፍ አለ። የማይታይ። እንደ እኔ ያለው ደግሞ አለላችሁ በትንኝ የሚጋለጥ። ሌብነትም እኮ ‘ታለንት’ ይጠይቃል፤›› አለ አንደኛው። ‹‹በቃ እኛ ግን መጠቃቀም መጠጋጋት ስንባል የሚታየን ሌብነት ብቻ ነው? የሥራ ዕድል ማግኘትና በጎ በሆነ መንገድ መረዳዳት አይታየንም?›› ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠችው አቋርጣ ገባች።

‹‹ሆሆ መጀመርያ ያለ ‘አይዲ’ የሚያስጠጋህ አለ እንዴ? የለም እኮ! እንደ እኛ ዓይነቱ ከምኑም የሌለበት የረባ ዕድል የለውም፣ ወይም ተዘጋግቶበታል፣ እንዲሁ ሳንቲም እያንቃጨለ ዕድሜው በታክሲ ሠልፍ ያልቃል። ምናልባት ከቀናህ ደግሞ አገርህ በሀብት ከ184 አገሮች 171ኛ ሆነች የሚል ዜና ቢመረቅልህ ነው። በማትሞቀው እሳት አገርህ በደረጃ ስትመደብ፣ አንተም ቶሎ ብለህ ምድብህን ማስተካከል ነው፤›› ከጎኔ የተሰየመው ይለፈልፍብኛል። ይኼን ሲል የሰማው ሌላ ጎልማሳ፣ ‹‹ማስተካከል ካልቻልክስ? ምድቡ የሞት ምድብ ከሆነስ?›› ብሎ መጣብን። ‹‹አሁን ይኼ ጥያቄ ነው? ልማታዊ ኑሮ ካቃተህ በልማታዊ መንገድ መሞት ነዋ!›› ብሎ የተሳፋሪዎችን ወሽመጥ በጠሰው። ‹‹ልማታዊ ኑሮን በሚመለከት ብዙ እየሰማን ነው፣ ልማታዊ ሞት ደግሞ እንዴት ያለ ነው?›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ‹‹ለመንግሥት ሳያሳሙ፣ ቀባሪ ሳያስቸግሩ ‘ሳይለንት’ ሆኖ ማለፍ ማለት ነዋ። ሌላ ምን ይሆናል? ወይ ስም ሳያስነሱ መመንተፍ ወይ ተረስቶ ማለፍ ነው፤›› ብትል ቆንጂት ተናጋሪው ተገርሞ እየተገላመጠ አያት። ብሶት በታረዘና በተጠማ መሀል ብቻ ነው ያለው ግን ማን ይሆን?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ታክሲያችን በጉዟችን መገባደጃ መክለፍለፍ ጀምራለች። ‹‹የምን ሩጫ ነው በአትሌቶች እንጂ በታክሲ ሾፌሮች እኮ የተሰበረ ‘ሪከርድ’ የለም ቀስ በል አቦ!›› ይላል ተሳፋሪው። ሾፌሩ መልሶ፣ ‹‹ያራገፈ እንጂ ሩጫውን የጨረሰ ታክሲ የለም እያለ፤›› እንደ ፍጥርጥራችሁ ይለናል። ‹‹በጎን ወያላው፣ ለሃምሳ ሳንቲም መልስ ምን ያጨቃጭቃችኋል?›› ብሎ መልሱን ዓይን በዓን ካላስቀረሁ ይለናል። ‹‹በል አምጣ! ሃምሳ ሳንቲም ይጎለኛል ሙላና ውሰደኝ ብልህ ታሳፍረኛለህ? እንደ ራስ ማየት ነው፤›› ይላሉ አዛውንቱ። ወያላው ሳንቲም የለኝም ብሎ ድርቅ ሲል ነገር ተባባሰ። ተሳፋሪዎች ተንጫጩ። ‹‹ምን ያድርግ ብላችሁ ነው ሕግ አክብሮ የሚያስከብር ብናጣ፣ ቁስላችን አመርቅዞ ‘ኢንፌክሽን’ ካልሆነ በቀር ዞር ብሎ የሚያየን እንደሌለ ቢያይ እኮ ነው፤›› ሲል አንዱ፣ ‹‹እኮ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ብረት ማንሳትና ብረት መግፋት አለብን መብት ለማስከበር. . .›› ትላለች ደርባባዋ እየተቆጣች።

‹‹ያዝ እንግዲህ! ወሬኛ ቢሸፍት ከፌስቡክ አይወጣም፤›› እያለ አፍ ይካፈታል ወያላው። ‹‹እኮ በስተርጅና ከዚህ ሁሉ የደም ታሪክና የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ እንደገና መተነኳኮስ ተጀመረ?›› ሲሉ አዛውንቱ ከጎናቸው የተሰየመው ጎልማሳ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ተናግሮ ሊያናግረን ነው። ኃላፊነት የጎደለውን የሰብዕና አምልኮ ናፋቂ ፉከራና ቀረርቶ በሰማን ቁጥር ደንፍተንማ አይሆንም፤›› ይላል። ‹‹ኧረ ተወኝ በዕድገት፣ በመልካም አስተዳደር መሻሻል፣ በፍሕት ሥርዓት፣ በዴሞክራሲ እንጂ በጦርነትና በብጥብጥ ማንም ሪከርድ ያስመዘገበ የለም በለው፤›› ሲል ከወደ ጋቢና ወያላው “መጨረሻ!” ብሎ በሩን ከፈተው። ብር ዘርዝሮ ሳንቲም ይዞ እስኪመጣ ንቅንቅ ያለ የለም። እያንዳንዳችን ተራ በተራ መልሳችንን እየተቀበልን ስንበታተን ሌሎች የባሱብን ችግሮች ላይ ለምን ይህን ታህል ተሰባስበን መብት እንደማናስከብር ተገርመን እንተያይ ነበር። በዚህ መሀል ነበር አንዱ ወፈፍ ያደረገው የሚመስል፣ ‹‹. . . ገቡ አሉ፡፡ ታዝለው ገብተውም ይደነፋሉ አሉ፡፡  በእርግጥ ገብተዋል? እግራቸውን ነው ያስገቡት? ወይስ ጭንቅላታቸውን? መግባቱንስ ገቡ መውጪያውን አውቀውታል. . .›› እያለ ሲለፈልፍ ከግርምታችን ወጥተን ሳቅ በሳቅ ሆንን፡፡ ወፈፌው የነገረን እኮ የሰሞኑን ሁኔታችንን ታዝቦ እኮ ነው፡፡ ታዝሎ የገባ ሁሉ ሲደነፋ ምን ይበል ታዲያ? እንሳቀው እንጂ ሌላ ምን ይባላል? መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት