በዓለም በየዓመቱ ከመወለጃ ጊዜያቸው ቀድመው የሚወለዱ 30 ሚሊዮን ያህል ሕፃናት በዘርፉ ስፔሻላይዝድ ባደረጉ የሕክምና ባለሙያዎች መታከም እንዳለባቸው ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅትና ዩኒሴፍ ያወጡት ሪፖርት አመለከተ፡፡
ድርጅቶቹ ባለፈው ሳምንት ባወጡት ሪፖርት፣ ሕፃናትና እናቶች በተገቢው ሰዓት ተገቢ የጤና አገልግሎት ማግኘት ከቻሉ በሕፃናትና እናቶች ላይ እየተከሰተ ያለውን ሞት መቀነስ ይቻላል፡፡ ሆኖም እናቶችና ሕፃናት ደረጃቸውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ባለማግኘታቸው በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ይሞታሉ፡፡
አዲስ ከተወለዱ ሕፃናት፤ ከጊዜያቸው ቀድመው የተወለዱት፣ በመወለድ ጊዜ የአዕምሮ ጉዳት ያጋጠማቸው፣ ከባድ የባክቴሪያ ኢንፌክሽንና በሌሎችም የሚጠቁት የሞት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው ሲልም ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ለሁሉም ሕፃናትና እናቶች ከእርግዝና ጀምሮ ከወሊድ በኋላ አንድ ወር ድረስ የሚደረግ የጤና ክትትል ወሳኝ እንደሆነም አመልክቷል፡፡
በሠለጠኑ ባለሙያዎች የሕክምና አገልግሎት መስጠት ካልተቻለ አብዛኞቹ ጨቅላ ሕፃናት አደጋ ላይ እንደሚወድቁ፣ በ2017 ብቻ 2.5 ሚሊዮን ጨቅላ ሕፃናት መሞታቸውና ብዙዎቹ ምቾት የተመዘገቡትም መካከልና መቆጣጠር በሚቻሉ በሽታዎች እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ ሕፃናት የሞቱት ካለጊዜያቸው በመወለድ ሲሆን፣ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ታመው የተወለዱ ሕፃናት ደግሞ የተረፉት አካል ጉዳተኛ ሆነው ነው፡፡
በ2030፤ 68 በመቶ ያህሉ የተወለዱ ሕፃናት ሞት እንደሚቀለበስ ለዚህም ጡት ብቻ ማጥባት፣ ለተወለዱ ሕፃናት ከእናትና አባት ጋር ንክኪ በመፍጠር ሙቀት እንዲያገኙ ማስቻል፣ መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ማሟላት፣ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግና እናቶች ደም እንዳይፈሳቸው ቀድሞ መከላከል ወሳኝ ናቸው ተብሏል፡፡