ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያንና የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳሳት 45ኛ መደበኛ ጉባዔያቸውን ተከትሎ ሰሞኑን ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት በዚሁ መልዕክታቸው፣ መንግሥት ለሕዝብ ሰላም ዋስትና የመስጠት ኃላፊነት ስላለበት ይህንን ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነት እንጂ ብሔርተኝነት መስበክ ለሕዝባችን አይጠቅመንምና የተሻለውን ሁሉ እንምረጥ፤›› ያሉት ጳጳሳቱ፣ ሁሉም ልብ ለልብ ተቀራርቦ ስለአገሩ ኢትዮጵያ የሚነጋገርበትና የሚግባባበት፣ የሚረዳዳበት ብሎም ሰላምና ደስታ የሚጎናፀፍበት ዘመን እንዲመጣ ተግተን እንድንሠራና እንድንጸልይ ያስፈልጋል ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ጳጳሳቱ አያይዘውም፣ ሕግና ሥርዓት ተከብሮ ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በሰላም መኖር ይችሉ ዘንድ፣ ማንም በአገሩ ባዳነት ሳይሰማው ተከብሮ ይኖር ዘንድ፣ ሕዝባችን እርስ በርሱ እንዲቻቻል፣ እንዲሁም ሕግ አስከባሪው አካል ሕግን እንዲያስከብር ማንኛውም ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን እንዲገታ በእረኝነትና በአባትነት መንፈስ እናሳስባለን ሲሉ አስተጋብተዋል፡፡