ሰላም! ሰላም! አከራረማችን እንዴት አድርጓችሁ ሰነበተ ይሆን? የሰውን የሐሳብ ነፃነት በመጋፋት በጭብጨባ ማቋረጥ ተጀመረ የሚባል ወሬ ሰማሁ ልበል? ዕድሜና መንጋጋ ይስጠን እንጂ ገና ብዙ ጉድ እንሰማለን፡፡ ‹‹ዘንድሮ በ‘ሳይለንሰር’ ማለቃችን ነው፤›› ያለኝ አንድ አብሮ አደግ ወዳጄ ነው። ድምፁን አጥፍቶ የሚጠፋውና የሚያጠፋን በዝቷል ለማለት ፈልጎ እኮ ነው። ቅኔውም ሳይቀር እንግሊዝኛ ጣል ይደረግበት መጀመሩን ንገረን ባላላችሁኝ! ታዲያ እኛ ደግሞ ሰበብ አይጥፋ እንጂ ሰበብ ከተገኘ ነገር ዓለሙን ለመተው የሚቀድመን የለም አይደል? የሚቀድመንን ተውት የሚደርስብን ሲኖር እኮ ነው! ወደን አይደለም በክፉም በደጉም አንደኛ የምንወጣው ለካ? ቢያንስ በትንሹ ለ48 ሰዓት ‘አይገርምህም? አይገርምሽም’ ስንባባል ኑሮአችን እስር ቤት ይሆናል።
እናላችሁ አዛውንቶች ሳይቀሩ የወጣት ሐሳብ አንሰማም ብለው መሳቂያ መሳለቂያ መሆናቸውን ስሰማ፣ ስምንተኛው ሺሕ የደረሰ መስሎኝ ተሳቀቅኩ፡፡ ለሰው ነፃነት ደንታ ማጣትና ተቃራኒ ሐሳብ አንሰማም በመባሉ መስሎኝ ወጣቱ ትውልድ ተንገሽግሾ ለውጥ ያመጣው፡፡ የባሻዬ ልጅ ደግሞ ሰሞኑን የድለላው ሠፈር እንደ ውርጭ አዘሉ የአየር ንብረት ሥራችን ጭር ብሎ ቢመለከት ተገርሞ፣ ‹‹መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሌብነት ጠርጥሮ እያደነ ከሚያስረው ራሱን በድንጋጤ ያሰረው ብዛቱ፤›› ሲለኝ ሳቄ ይመጣል። እኔም እንደነገርኳችሁ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሐሳብ በነፃነት አይንሸራሸርም ብለው የሚያሳምፁ ጉዶች ወሬ አልጥም ብሎኝ ስለነበር ለባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሰበብ ይገኝ እንጂ ደግሞ ለመቀመጥ!›› ብዬው እጥፍ አልኩ። ‹‹ይታያችሁ ‘ዳገቱ ላይ መቆምም ሆነ መቀመጥ አይፈቀድም’ በተባለበት በዚህ ፈታኝ ጊዜ ምንም ላይፈይድለት ሰው የጭቆና ችግኝ መንከባከቡን አልተወው አለ፤›› ስል ቢሰሙኝ ደግሞ አንዳንዶቹ፣ ‘ከዘንድሮ ስመ አዛውንቶች የወጣቶች ምክር አትራፊ ሆኗል አንበርብር። ዝም ብለህ ነው አንተ!’ አይሉኝ መሰላችሁ? ኧረ እንዲያው በሞቴ እንዲህ ያለውን ጨዋታ ባወጋው ያለእናንተ ማን ያምነኛል? ያውም እምነት ተረት በሆነበት ዘመን? ኧረ ተውኝ! ኋላ እንዲህ የሚሉኝን ዝም ብዬ ባስተውላቸው አንዱ እስኪበቃው በእስር ቤት የተቀጠቀጠ፣ ሌላው ክፋት ያበገነው፣ በአጠቃላይ የአገር ሰላም ማጣት ያንገበገበው ተሰብስቦ እንደሚወርድብኝ ተረዳሁ። ‘በዚህ ከቀጠለ መጨረሻው ምን ይሆን?’ እያልኩ ወዳጆቼን ባዋያቸው፣ ‘ስንቱን እንተንብይ?’ ነበር መልሳቸው። ‘አንዳንዴ እያሰብኩት የዚያችን ልጅ ነገር፣ ካልመሸ አይታወቅ ካልነጋ አይነገር፤’ ያለው አዝማሪ ለካስ ወዶ አልነበረም?
እናላችሁ በዚህ አካሄዳችን እንኳን ሌላ ሌላው ውጥናችን ሊሳካ የተከልነው ችግኝ መፅደቁን መጠራጠር መጀመር አለብን። በአደባባይ ሐሳብ መገደብ ተጀመረ ሲባል ተስፋ መቁረጥ ተጨመረበት የሚለውን አስባችሁታል? ‘መካከለኛ ገቢ ካለቸው አገሮች ተርታ እንሠለፋለን ብለው፣ ታላቁን የዓባይ ወንዝ እንገድባለን ብለው . . .’ እያለ አቤት ስንቱ ይሆን የሚሳቅብን? ‹‹እንዴ! ምንድነው እንዲህ ማለቃቀስ? ከአገርህ ሌላ አገር እንደሌለህ እያወቅህ የሰውን አገር የራስ ማስመሰል ምን የሚሉት በሽታ ነው?›› እያሉ ባሻዬ አንድ ዓይቼው የማላውቅ እንግዳ ሲገስጹ ሰማሁ። ‹‹ስትሸነፍም እኮ በፀጋ ተቀብለህ ለራስም ጥሩ ምክንያት መስጠት ያስፈልጋል!›› ያሉት ግን ሆዴ ውስጥ ቀረ። ከሐዲዱ ያፈነገጠውን በማስተካከል እኮ ባሻዬን የሚደርስባቸው የለም። እንደ ዛሬ ሳይሆን ድሮ የአዛውንት ክብሩ መካሪነቱና አስታራቂነቱም አይደል? በዚያው ልክ ወስላቹና ሂያጁ በዝቶ ከእነ ሽበቱ በአደባባይ መሳቂያ የሚሆነውን እያየን፣ ‘ኧረ ማን ነው የሚታመነው ዘንድሮ?!’ እያሰኘን ግራ አጋባን እንጂ! ምን ልላችሁ ነው ይኼን ያመጣሁት መሰላችሁ? ለመቆምም ለመውደቅም ጥሩ ምክንያት ማለፊያ ነው። በሌላ በሌላው ይሁን ግድ የለም። ለግል ሥልጣንና ክብር ብቻ ተብሎ ለምን ተነካን በሚል እብሪት አገርን ማመስ ለማን ተብሎ? ኧረ ለማን?!
‹‹ሳይንቀሳቀሱ ‘ካሽ’ የሚበጠስላቸው የዘራፊ ልጆች ብቻ ናቸው፤›› ብሎ አንድ ወዳጄ የነገረኝ ትዝ ቢለኝ ተወዝፌ መቅረቴ ትውስ አለኝና መሯሯጥ ጀመርኩ። በከባዱ በብዙ ሺዎች ለሚከራይ ቪላ ቤት የሚመጥነውን ስፈልግ ውዬ ተቀጣጠርኩና ጫማ ላስጠርግ አረፍ አልኩ። አጠገቤ ሁለት ወጣቶች እንደኔው ጫማ እያስቦረሹ ሙግት ገጥመዋል። መስማት ጀመርኩ። ‹‹ኮምፒዩተር ኢትዮጵያ ውስጥ ቢፈለሰፍ የላሊበላን ያህል አይደንቀኝም፤›› ይላል አንደኛው። ይህን የሚለው ኋላ ላይ እንደተረዳሁት ላሊበላን እኛ አልሠራነውም ለማለት ነው። ‹‹እንዴት እንደዚያ ትላለህ?›› ይለዋል ጓደኛው ተማሮበታል መሰል። እኔም ‹‹ለምን?›› ብዬ ጣልቃ ገባሁ። ‹‹መረጃውና ዕውቀቱ በአግቦ፣ በሽሙጥና በሐሜት ላይ የተመሠረተ አገር እንዴት ብሎ ነው በምክንያታዊ አስተሳሰብ ላይ የተንጠለጠለ ያንን የመሰለ ረቂቅ የሥነ ሕንፃ ‘ቴክኒክ’ ሊያሳይ የሚችለው?›› ሲል መልሶ ጠየቀን። ማናችንም ልንመልስለት አልሞከርንም። የዛሬው እኛነታችን ዝብርቅርቅ ቢሆንበት ነው ያ ወጣት ይህን መሰል ሙግት ማንሳቱ መሰለኝ፡፡ ለነገሩ ልክ መስሎ ታይቶኛል። በአደባባይ የሰው የሐሳብ ነፃነት በጭብጨባ ሲጣስ እያየን እኮ ነው? የቀጠሩኝ ደንበኞቼ ደርሰናል ብለው ሲደውሉልኝ ተነስቼ ስሮጥ ኑሮ ቀልባችንን ነጥቆን መጠያየቅ ያለብንን ጥያቄዎች እንደረሳናቸው ታወቀኝ። የዘመናት አፈና ተረስቶ ዛሬ ለምን እንደምንካሰስ በስሱ ገባኝ። በዚሁ መቀጠሉ እስከ መቼ እንደሚያዛልቀን እንጃ!
ታዲያ እውነት የማትጥመን እዚህ እዚህ ላይ ነው። ከኅብረተሰባዊነት ግለኝነት፣ ከጋራ እሴት ይልቅ የግል ፍላጎት ስለተቆጣጠሩን ችግሮቻችን አልተቀየሩም። ‹‹ፎርማታቸው›› ቢቀየር አሁንም የለቅሷችን ዜማዎች አልተቀየሩም። ለቅሶ ብል ይልቅ በቀደም ለታ ባሻዬ ካልጋቸው ሳይወርዱ መርዶ ሰምተው፣ ‹‹ታሞ እያለ ምናለበት ሄጄ ብጠይቀው ኖሮ!›› በማለት በራሳቸው በጣም አዘኑ። ታዲያ ልጃቸው ልብ ብሏቸው ኖሮ፣ ‹‹አሁን ይህን ያህል ራስህን መውቀሱ ፋይዳ የለውም። ባሻዬ አውቀው ያጠፋሉ የሚል ማን አለ? ደግሞም ራስን እየወቀሱ ሆድን በቂም ከመወጠር ይቅርታ የማድረግና የመቀበል ባህል ብናዳብር ኖሮ አረመኔያዊ ድርጊት የሚፈጽሙ ነውረኞችን ንሰሐ ለመግባት የሚቀድማቸው አልነበረም፤›› አይላቸው መሰላችሁ? ደፋር እኮ ነው! ባሻዬ ልጃቸው ያላቸውን ሲነግሩኝ፣ ‹‹ይቅርታ ማለት ውርደት አከናናቢነቱ ጎልቶ ይሆን እንዴ አንድ ይቅር በሉኝ የሚል ሰው መፈለግ የዱር እንስሳ ከማደን በላይ ከባድ የሆነው?’ ስል ራሴን ጠየቅኩ። ይህንን ጉደኛ ነገር ለእናንተው ብተው ይሻላል።
የነገርኳችሁ ቪላ ቤት ደለብ ባለ ረብጣ ሲከራይ ‘ኮሚሽኔን’ ተቀብዬ ወደ ሌላው የድለላ ሥራዬ ሮጥኩ። ታክሲ ተሳፍሬ በጉዞ ላይ ሳለሁ ታዲያ የሰማኋትን ‘ጆክ’ ጣል ላድርግላችሁ። ሁለት እጅግ የሚበሻሸቁ ጓደኛሞች ናቸው። አንደኛው አባቱ በቅርብ ያረፉበት የሚበሻሸቀው አብሮ አደግ ጓደኛው ደግሞ በጠና ታመመበት። ሊጠይቀው ቤቱ ሲሄድ ሳቅ የራቀውን ታማሚ ወዳጁን ፈገግ ሊያሰኝ ያዘጋጀውን ደብዳቤ እየሰጠው፣ ‹‹በል እንግዲህ ለአባቴ የምታደርሰው ነው፤›› ቢለው፣ ‹‹ወዳጄ! እኔ እኮ ወደ ገሃነም አይደለሁም!›› አለው በማለት አንዱ የሴት ጓደኛውን በቀልዱ ሲያስቅ እኔንም ፈገግ አሰኘኝ። በውጥረት ቀኑን አሳልፌ ስለነበር ከልቤ ሳቅኩ። ከሳቄ ጀርባ አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹አይ የሰው ልጅ! ገሃነም መውረድ ፈርቶ፣ ከሥልጣን በሰላም መውረድ ፈርቶ፣ ከሥልጣን ተባሮም በሰላም ኑር ሲባል ይህንንም ፈርቶ ነገር እየጎነጎነ መኖር እንዴት ይሆንለታል?›› ሲል ይሰማ ነበር። ለአምባገነኖች ከሥልጣናቸው መውረድ በቁም ከመሞት በላይ ሲዖል እንደ መውረድ እንደሚቆጥሩት ታሪክ አላነበበም መሰል? ከንባብ የተጣላ ትውልድ እንዳልል እኔም ከእጅ አይሻል ዶማ ነኝ! እኔ ቢያንስ አምናለሁ፡፡ በሉ እንሰነባበት።
የቀረኝን ሥራ አጠናቅቄ ወደ ቤቴ ስመለስ አመል ነውና ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ብቅ አልኩ። በጂን፣ በቢራና በድራፍት ቸበርቻቻ ያለው የግሮሰሪዋ ታዳሚ ወሬው ሁሉ ስለነፃነት ታጋይ ሟቹ ማንዴላ ነበር። የባሻዬ ልጅም በወሬው ዋና ተሳታፊ ስለነበር በቅጡ ሰላም አላለኝም። እየቆየሁ የሚያወሩትን ወሬ ሳዳምጥ ውይይት ሳይሆን ክርክር ይዘው ነበር። ምን መሰላችሁ? ‘ማንዴላ የኖቤል ሽልማት ሲሸለሙ ጋንዲ ሁለት ጊዜ ለኖቤል ሽልማት ታጭተው ሳይሸለሙ የቀሩበት ምክንያት ምንድነው?’ ‘ማንዴላ በአሜሪካ ከአሸባሪዎች ስም ዝርዝር መሀል ስማቸው ቆይቶ ተሰርዞ ከሞቱ በኋላ ምዕራባውያን መሬት ሊነጠፉ መድረሳቸው አያዝተዛዝብም ወይ?!’ ወዘተ. በሚሉ ሐሳቦች ሌላ ዓለም ተፈጥሯል። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደግሞ፣ ‹‹ምንም አልን ምን ማንዴላ ታላቅ ሰው ናቸው። የጥቁሮች ፈርጥ ሆነው ሲታወሱ መኖራቸው ክብራችን ነው፤›› እያለ በስሜት ተናገረ። ነገር ማለዘቡን መቼም እንደ ባሻዬ ልጅ የሚያውቅበት የለም፡፡ እነዚያን ሁሉ ሲንጫጩ የነበሩትን ጠጪዎች ዝም አሰኝቶ፣ ‹‹በአፓርታይድ የሰቆቃ አገዛዝ ፍዳዋን ያየች አገር ነፃ ለማውጣትና እንደ እንስሳ ይቆጠር የነበረን ሕዝብ ሰብዓዊ ክብሩን ለማስመለስ የተደረገ ትግልን የመራ ጀግና ሊወደስና ሊከበር ግድ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ሞት የማይቀር ክስተት ቢሆንም ማንዴላ ሞቱ አይባልም፡፡ ጥላቻን በፍቅር፣ ጭቆናን በእኩልነት፣ ጭፍጨፋን በሰላማዊ ድርድር የቀየረ ጀግና ሞተ አይባልም፡፡ ይልቅስ ጭቆናን እንደገና ካላናገሥን የሚሉ በቁማቸው የሞቱ ናቸው. . .›› እያለ ሲናገር የሁላችንም ልብ አብሮት ነበር፡፡
‹‹ጀግና ይፎከርለታል እንጂ አይፎክርም፡፡ ዓለም ስለማንዴላ ጀግንነት ብዙዎች ተናገሩ እንጂ፣ ከእሳቸው አፍ የወጣው ሰላም፣ እኩልነትና የጋራ ዕድገት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጀግና ይፎከርለታል እንጂ አይፎክርም የሚባለው፡፡ በአገራችን ለውጥ ያመጡልንን ጀግኖቻችንን በዚህ መንፈስ ማክበርና ማወደስ አለብን. . .›› እያለ ድምፁ ሲያስተጋባ ጭብጨባ ጎረፈለት፡፡ በዚህ መሀል አንዱ፣ ‹‹ወጣቶቹን መሪዎቻችን እንዳልከው ማክበር ይገባናል፣ ማወደስም ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን በስተርጅና ከእነ ሙሉ ሽበታቸው አልከበር እያሉ አድማ የሚመቱትን ምን እንባለቸው?›› ብሎ ሲጠይቀው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ማለት ያለብን በቁም ሞታችሁ አትዋረዱ ነዋ!›› ብሎ ሲመልስለት ግሮሰሪዋ በሳቅ ተናጋች፡፡ አዎን! በቁም ከመሞት የበለጠ ውርደት የለም! መልካም ሰንበት!