Sunday, June 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ሪሰርቸር ጋር እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ባለሀብት ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

  • ክቡር ሚኒስትር ምንድነው የሚሠራው?
  • ምንድነው የሚሠራው ማለት?
  • እኛ እኮ ሌላ አገር የለንም፡፡
  • አንተ አሁንም ትቀልዳለህ አይደል?
  • የምን ቀልድ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ሦስት ፓስፖርት አይደለም እንዴ ያለህ?
  • ክቡር ሚኒስትር እትብቴ የተቀበረው ግን እዚሁ ነው፡፡
  • ለምን ታዲያ የሌላ አገር ዜግነት ኖረህ?
  • እኔ ፓስፖርቴን ለመቅደድም ዝግጁ ነኝ፡፡
  • እሱን እንኳን ተወው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ሌሎቹ እኮ የወረቀት አገሮቼ ናቸው፣ ኢትዮጵያ ግን የልቤ አገር ናት፡፡
  • ታዲያ ኢትዮጵያ ምን ሆነች?
  • ከዚህች አገር የት እንድንሄድ ነው የምትገፋፉን?
  • ማን ገፋህ?
  • ትልቅ ቦታ ለመድረስ አይደል እንዴ የሁላችንም ጥረት ክቡር ሚኒስትር?
  • እውነት ነው፡፡
  • ታዲያ የት ሄደን ምን እንሥራ?
  • አልገባኝም፡፡
  • በጣም ነው ያዘንኩት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምኑ ነው ያሳዘነህ?
  • ወሰዱት እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምኑን?
  • መሬቱን ነዋ፡፡
  • አንተ በየቦታው አይደል እንዴ መሬት ያለህ?
  • ይኸው ሁሉንም እኮ ነው ጠራርገው የወሰዱት፡፡
  • ታዲያ መገንባት ነበረብሃ?
  • እኔ እኮ በርካታ ዜጎችን ቀጥሬ የማሠራ ባለሀብት ነኝ፡፡
  • ለዚያ እኮ ነበር መሬቱ የተሰጠህ፡፡
  • ታዲያ መሥሪያ ጊዜ ሊሰጠኝ ይገባ ነበር፡፡
  • አንተ ግን አጥረህ ብድር ስትጠይቅበት ነበር፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር የተወሰደብኝ መሬት እኮ አንድ ክፍለ ከተማ ያክላል፡፡
  • አሁን ምን ይደረግ ነው የምትለው?
  • ክቡር ሚኒስትር መሬቴ እንኳን ይወሰድ፣ በሁሉም ላይ እንደወሰናችሁት ገብቶኛል፡፡ እኔ ግን ምን በልቼ እንዳድር አስባችሁ ነው?
  • ማለት?
  • ቢዝነሴም ታግዷል፡፡
  • ታግዷል ስትል?
  • ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳላደርግ ቢዝነሴ ታግዷል፡፡
  • ለምን?
  • እኔ ምን አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር? ምን ባጠፋ ነው እንደዚህ የምታደርጉት?
  • እንግዲህ ቢዝነስህ የታገደበት በቂ ምክንያት ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
  • እኮ ምን አጠፋሁ?
  • አሁንም አንተ ከቀድሞው ሥርዓት ጋር ያለህ ቁርኝት እንደጠነከረ ነው አይደል?
  • እሱማ ይኼ ሁሉ ሀብት የመጣው በዚያ ነው፡፡
  • ይኼን ሁሉ ሠርተህ እንዳማታመጣውማ ግልጽ ነው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ከቀድሞው ሥርዓት ጋር እኮ በጋብቻ ሳይቀር የተዛመድኩ ነኝ፡፡
  • ከጋብቻው በላይ እኮ የሙስናው ዝምድና ይበልጣል፡፡
  • እሱስ ልክ ነዎት፡፡
  • ስለዚህ አሁንም ከድሮው ሥርዓት ጋር ያለህ ግንኙነት አልተቋረጠም፡፡
  • ምን ባደርግ ይሻላል?
  • ቶሎ ከአገር ውጣ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ከኤርፖርት እኮ ነው የመለሱኝ፡፡
  • አንተ ሦስት ፓስፖርት አይደል እንዴ ያለህ?
  • በየትኛውም ፓስፖርቴ መውጣት አልቻልኩም፡፡
  • እኔ ምን ላድርግህ  ታዲያ?
  • የት ልትግባ ክቡር ሚኒስትር? ምከሩኝ እስኪ?
  • ለምን ገዳም አትገባም?
  • እዚያም አውቀውኝ አባረሩኝ፡፡
  • እንግዲያው መግባት ያለብህ አንድ ቦታ ነው፡፡
  • የት ክቡር ሚኒስትር?
  • ገደል!

[ክቡር ሚኒስትር ቢሮ አማካሪያቸው ገባ]

  • ምነው ክቡር ሚኒስትር ፊትዎ ጠቆረብኝ?
  • ኧረ ተወኝ፡፡
  • ምን ተፈጠረ?
  • እስኪ ተወው፡፡
  • ምን ሆኑ?
  • አንድ የሚያስደነግጥ ዜና ሰምቼ ነው፡፡
  • የምን ዜና?
  • አባረሩት እኮ፡፡
  • ማንን?
  • ዋናውን ቆራጡ መሪያችንን ነዋ፡፡
  • ለምንድነው የሚያስደነግጡኝ ክቡር ሚኒስትር ማን ነው የተባረረው?
  • አንተ ለመሆኑ ሚዲያ ትከታተላለህ?
  • ኧረ በጣም ነው የምከታተለው፡፡
  • ታዲያ እንዴት መባረሩን አልሰማህም?
  • እኔ እንግዲህ ዛሬም ሶሻል ሚዲያ ስከታተል ነበር የተባረረ ወሬ አልሰማሁም፡፡
  • ሁሌም ተዓማኒ የዜና ምንጮችን ተከታተል የምልህ ለዚህ ነው፡፡
  • ለመሆኑ ማን ነው የተባረረው?
  • ጆዜ ሞሪኖ ነዋ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር የእሱ መባረር ይኼን ያህል አንገብጋቢ ነው እንዴ?
  • ጉዳዩ የገባህ አይመስለኝም፡፡
  • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
  • ሰውዬው እኮ ክለቡን ወደ ተሻለ ዕድገት የሚያሸጋግረው መሪ እንደነበር ማንም ያውቀዋል፡፡
  • እኔ እንደሰማሁት ግን ቡድኑን ችግር ውስጥ የከተተው እሱ ነው የሚል ነው፡፡
  • እንዳትሳሳት፣ ሞሪኖ የባለ ዕራዩን መሪ አሌክስ ፈርጉሰንን ሌጋሲ ለማስቀጠል ወሳኝ ሥራ ሊሠራ የነበረ አሠልጣኝ ነው፡፡
  • እ. . .
  • በክለቡ ውስጥ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን ፍልስፍና ሰርፆ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡
  • እንዴት?
  • ተጨዋቾቹ ከአሠልጣኙ ብቻ የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ እንዲፈጽሙ በማድረግ የፈርጉሰንን አመራር አስቀጥሏል፡፡
  • ስለዚህ ሊባረር አይገባም ነበር እያሉ ነው?
  • የራስህ እግር ላይ እንደ መተኮስ ነው ስልህ?
  • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ ግን ከዘመኑ ጋር መራመድ የቻሉ አልመሰለኝም፡፡
  • እንዴት?
  • በቃ የእርስዎ እኩዮችና እርስዎ እንደ ድሮው በአፈና በጭቆና ምናምን ነው መግዛት የምትወዱት፡፡
  • ምን እያልክ ነው?
  • አሁን የእግር ኳስ ፍልስፍና ተቀይሯል፡፡
  • ወደ ምን?
  • ወደ ፍቅር፣ መደመር፣ አንድነት ነዋ፡፡
  • የማታውቀውን ነገር አትዘባርቅ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር የሊቨርፑልና የማንቸስተር ሲቲ አሠልጣኞች በዚህ ፍልስፍና ነው ውጤታማ የሆኑት፡፡
  • ለእኔ ከሞሪኖ የሚበልጥ አሠልጣኝ የለም፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ሰውዬው እኮ የክለቡን ሀብት አባክኗል፡፡
  • እንዴት አድርጎ?
  • ይኸው ለስምንት ተጨዋቾች ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥቶ ግዥ ፈጽሟል፡፡
  • ለክለቡ ሲል ነዋ፡፡
  • ስነግርዎት ያለዕቅድና ፍላጎት ነው የሚገዛው፡፡
  • ይኼን እንኳን አልቀበልም፡፡
  • እንዲያውም በዚህ ምክንያት ቅፅል ስም ወጥቶለታል፡፡
  • ማን ተባለ?
  • ሜቴክ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ሪሰርቸር ጋር እያወሩ ነው]

  • ክቡር ሚኒስትር ለውጡን እንዴት እያዩት ነው?
  • ለውጡ ጥሩ ነው ግን የሚጎድሉት በርካታ ነገሮች አሉት፡፡
  • ምንድነው የሚጎድለው?
  • ትግሉ አሁንም አልቆመም፡፡
  • የምን ትግል?
  • በረሃም ታግለናል፣ አሁንም እንታገላለን፡፡
  • ለምንድነው የምትታገሉት?
  • የዕለት ተዕለት ኑሮን ከማሸነፍ ጀምሮ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ነዋ፡፡
  • አሁንም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አልተገነባም ብለው ነው የሚያስቡት?
  • አንተ ተገንብቷል ልትለኝ ነው?
  • እየተገነባ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እንዴት ሆኖ?
  • በፊት እኮ ለየት ያለ የፖለቲካ አመለካከት የነበረው ዜጋ ምን እንደሚደረግ እናውቃለን?
  • እ. . .
  • የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት እስር ቤት ነበር የሚኖሩት፡፡
  • ምን እያልክ ነው?
  • መንግሥትን የሚቃወሙ ጋዜጠኞች ወይም ብሎገሮች ማዕከላዊ ነበር ቤታቸው፡፡
  • ያኔ የነበረው አሠራር የዓለምን ፖለቲካ የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡
  • ምን ማለት ነው?
  • ዓለም በአሸባሪዎች ላይ ጦርነት ስላወጀ እኛም የሚያሸብሩንን እስር ቤት እንከት ነበር፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር እሱን እንኳን ተውት፡፡
  • ምን እያልክ ነው?
  • ይኸው አሁን ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ መንግሥት ቢሰድብም፣ የትኛውም ግለሰብ በሐሳቡ ምክንያት እየታሰረ አይደለም፡፡
  • ምነው ጓደኞቻችን አንድ ክልል ውስጥ ታስረው አይደል እንዴ ያሉት?
  • እነሱን ያሰራቸው የራሳቸው ሐሳብ ነው፡፡
  • ስማ በአሁኑ ወቅት ሕገ መንግሥቱ እየተጣሰ መሆኑን አታውቅም?
  • መጀመርያ ሕገ መንግሥቱን ማን ነበረ የሚጥሰው?
  • እኛው፡፡
  • ታዲያ አሁን መጣሱ ምን ይገርማል?
  • ለሕዝቡ በአንዴ ዴሞክራሲን በአካፋ እየዛቅህ አትሰጥም፡፡
  • አልገባኝም?
  • ዴሞክራሲን በማንኪያ ለለመደ ሕዝብ በአንዴ በቡልዶዘር ዝቀህ ስትሰጠው ይኸው አገሪቱ ተተራመሰች፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ ዴሞክራሲ በዛብኝ ብሎ አያውቅም፡፡
  • ዴሞክራሲ መቼ አግኝቶ ያውቅና?
  • አሁንማ ሕዝቡ የመናገር መብቱን ተጠቅሞ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እያጣጣመ ነው፡፡
  • አገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲ አለ እያልክ ነው?
  • በሚገባ፡፡
  • አንተ ስለዴሞክራሲ ያለህ አመለካከት የተሳሳተ ነው፣ ለዚያ ነው እኛም እየታገልን ነው ያልኩህ፡፡
  • ቆይ ለእርስዎ ዴሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው?
  • አንድና አንድ ነገር ሲሆን ነው፡፡
  • ምን ሲሆን?
  • የድሮው ሥርዓት ሥልጣን ላይ ሲወጣ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ወዳጃቸው ደወለላቸው]

  • በቲቪ ዓይቼዎት ነው እኮ የደወልኩልዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • የትኛው ቻናል ላይ?
  • ምን ቻናል ላይ ብቻ አሁንማ በየሶሻል ሚዲያውም የእርስዎን ቪዲዮ ሕዝቡ እየተቀባበለው ነው፡፡
  • ምንድነው ያየኸው?
  • ፕሮቶኮል የሚባል ነገር አያውቁም እንዴ?
  • እኔ በፊትም ስለአለባበሴ ግድ እንደሌለኝ ታውቃለህ?
  • እኔ ስላለባበስዎ አይደለም፡፡
  • ታዲያ የምን ፕሮቶኮል ነው?
  • በአጠቃላይ ሥነ ሥርዓትዎና ሕዝብ ፊት ስለሚያደርጉት ድርጊት ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡
  • ሳንቀላፋ ታየ እንዴ በቲቪ?
  • አላንቀላፉም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ጥፍሬን መብላት ደግሞ ሚስቴ አስትታኛለች፡፡
  • እርስዎ ጥፍር ይነቅላሉ እንጂ መቼ ጥፍር ይበላሉ?
  • ታዲያ ስልኬን ስነካካ ዓይተኸኝ ነው?
  • እኔ እሱን አይደለም የምልዎት፡፡
  • ታዲያ ምንድነው?
  • ቲቪ ላይ በተደጋጋሚ ስለሚቀርቡ ፕሮቶኮልዎን መጠበቅ አለብዎ፡፡
  • እኮ የምን ፕሮቶኮል?
  • ለማንኛውም እኔ በራሴ ወጪ ላስተምርዎ ወስኛለሁ፡፡
  • ምንድነው የምታስተምረኝ?
  • ማጨብጨብ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ ዛሬ ሥራ ይጀምራል

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ አምሽተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ‹‹ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን›› የሚለውን የቴሌቪዥን ዜና ተመልክተው ለብቻቸው ሲስቁ አገኟቸው]

ስልክ እያወራሽ ነበር እንዴ? ኧረ በጭራሽ... ምነው? ታዲያ ምንድነው ብቻሽን የሚያስቅሽ? አይ... በቴሌቪዥኑ የሚቀርበው ነገር ነዋ። ምንድነው? ድሮ ድሮ ዜና ለመስማት ነበር ቴሌቪዥን የምንከፍተው፡፡ አሁንስ? አሁንማ ቀልዱን ተያይዘውታል... አንተ ግን በደህናህ...

[ክቡር ሚኒስትሩ የቢሮ ስልካቸው ጠራ። ደዋዩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊ እንደሆኑ ሲነገራቸው የስልኩን መነጋገሪያ ተቀበሉ]

ሃሎ፡፡ እንዴት አሉ ክቡር ሚኒስትር። ደህና ነኝ። አንተስ? አስተዳደሩስ? ሕጋዊ ሰውነታችን ተነጥቆ እንዴት ማስተዳደር እንችላለን ክቡር ሚኒስትር? ለዚህ ጉዳይ እንደደወልክ ገምቻለሁ። ደብዳቤም እኮ ልከናል ክቡር ሚኒስትር፡፡ አዎ። ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውኛል።...

[ክቡር ሚኒስትሩ አየር መንገዱ ወጪ ቆጣቢ የሥራ እንቅስቃሴ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን በሚያሳድግበት ሁኔታ ላይ ከተቋሙ ኃላፊ ጋር እየተወያዩ ነው]

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ትልቁ ወጪያችን ለነዳጅ ግዥ የሚውለው ነው። ክቡርነትዎ እንደሚገነዘቡት የዩክሬን ጦርነት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በእጅጉ አሻቅቧል። ቢሆንም አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ...