Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ላይ ተጨማሪ የምርመራ ግኝቶች ለፍርድ ቤት ቀረቡ

በሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ላይ ተጨማሪ የምርመራ ግኝቶች ለፍርድ ቤት ቀረቡ

ቀን:

አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በታሰሩበት ቦታ ግለሰቦች እየመጡ እየዛቱባቸው መሆኑን ተናገሩ

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ላይ ተጨማሪ የምርመራ ግኝቶች ለፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዳው፣ ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የህዳሴ ግድብ ኤሌክትሮ ሜካኒካልና ኃይድሮሊክ ሥራዎችንና የተርባይን ግዥዎችን በሚመለከት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ውል ፈጽመዋል፡፡ ውሉንም የተፈራረሙት በ24.4 ቢሊዮን ብር መሆኑንና የ16.7 ቢሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን፣ የተሠራው ግን 23.03 በመቶ እንደሆነና ከተከፈለው ውስጥ 7.2 ቢሊዮን ብር የት እንደ ደረሰ እንደማይታወቅ አስረድቷል፡፡

ሜቴክ የተበላሹና አገልግሎት መስጠት የማይችሉ አምስት ተርባይኖችንም ገዝቶ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልጿል፡፡ ለግድቡ የሚሆን ሲሚንቶ ከአንድ ቦታ በብዛት በመግዛት በብዙ ሺሕ ኩንታል የሚቆጠር ሲሚንቶ እንዲባክን መደረጉን አስረድቷል፡፡ ከተሽከርካሪ ግዥም ጋር በተያያዘ በርካታ ወንጀሎች መፈጸማቸውን አክሏል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ለቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች፣ ከተሽከርካሪ ሞተር ግዥ ጋርና ከሌሎችም 19 ግዥዎች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን መርማሪ ቡድኑ አስረድቶ፣ የሠሯቸውንና የሚቀሩትን የምርመራ ሥራዎች በመግለጽ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች ባቀረቡት የመቃወሚያ ክርክር እንደገለጹት፣ ደንበኛቸው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በሁለት ነገሮች ብቻ ተጠርጥረው መቅረባቸውን በማስታወስ አሁን ግን የተጠረጠሩባቸው ጉዳዮች 19 መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ለእነዚህ ሁሉ የምርመራ ሒደቶች 14 ቀናት እየተጠየቀ መሆኑን ገልጸው፣ እንኳን 19 ጉዳዮችን ቀርቶ በ14 ቀናት ውስጥ አንዱንም መጨረስ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ የደንበኛቸው ጉዳይ እነ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲ ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን ጠቁመው፣ ደንበኛቸውን በእስር ለማቆየት ሆን ተብሎ ለየብቻ መቅረቡ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀድሞ ያሠራውን ኦዲት ስህተት እንዳለበት በመግለጽ፣ በተመሳሳይ የኦዲት ተቋም እንዲመረመር እንደሚያደርግ መናገሩንም ተቃውመዋል፡፡ በሌላ ከፍ ባለ የኦዲት ተቋም ማስመርመር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ሆን ተብሎ ተጠርጣሪውን በእስር ለማቆየት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በየቀጠሮው የሚጠይቀው የጊዜ ቀጠሮ የሚፈቀድ ከሆነ ማብቂያ እንደሌለው ገልጸው ፍርድ ቤቱ ገደብ ሊያበጅለት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ግዥን በሚመለከት ስፔስፊኬሽን ማስቀመጥ ያለበት ገዢው እንጂ ሜቴክ እንዳልሆነ የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ይኼ የጥርጣሬ መነሻ ሊሆን እንደማይገባም አክለዋል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ማቋረጫ ስለሌለው መርማሪ ቡድኑ ማስረጃ ካለው ክስ እንዲያቀርብ እንጂ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድለት እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ የተጠርጣሪ ጠበቆች እንደሚሉት ተጠርጣሪውን ለማሰር ሳይሆን ተገቢ ምርመራ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል፡፡ ጠበቆቹ እንዳሉት የምርመራ ጊዜው ብዙ ጊዜ ቢፈጅም፣ ለፍርድ ቤት በማቅረብ ፍርድ ቤቱ አምኖበት ሲፈቀድለት መሆኑንም አስረድቷል፡፡ በጥቅም ግንኙነት ከግዥ መመርያ ውጪ 70 በመቶ ክፍያ መፈጸሙንና ሌሎችንም ምክንያቶች ገልጿል፡፡ ሰነዶችን ማሰባሰብ፣ በባለሙያ በማስገመትና በማስተንተን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚያከናውን በማስረዳት፣ የጠየቀው 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

በሌላ በኩል በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የታሰሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል መምርያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ፣ የታሰሩበት ቦታ ድረስ ግለሰቦች እየሄዱ እንደሚያስፈራሯቸው ለፍርድ ቤት አሳወቁ፡፡ አንድ ግለሰብ በታሰሩበት መጥቶ ፖሊሶችና ኃላፊዎች ባሉበት ‹‹እሠራልሃለሁ›› ብሎ ዝቶባቸው እንደሄደ ተናግረዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች የኦነግ አባል ያልሆኑ ነዋሪዎችን በሐሰት በመወንጀልና ሽብርተኛ እንደሆኑ በመግለጽ የኦነግ መተዳደሪያ ደንብ፣ ፕሮግራምና ባንዲራ ከቤታቸው ውስጥ በማስቀመጥ፣ ወደ ሥውር ቦታ በመውሰድና በማሰር፣ በመደብደብ፣ በማሰቃየት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ስም ከገቢያቸው በላይ ንብረት በማፍራታቸው በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

አቶ ተስፋዬ የመርማሪ ቡድኑን ሪፖርት ተቃውመዋል፡፡ ቀደም ብሎ በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ የቀረበውን ገልብጦ ማምጣቱን ጠቁመው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም በተሰጠው ዝርዝር የምርመራ ሰነድ ላይ ቀደም ብሎ የፈቀደበት ቀን እንዳለ በማግኘቱ፣ ‹‹ያለፈውን እንዳለ ነው ገልብጣችሁ ያመጣችሁት ምንም ነገር አልሠራችሁም›› በማለት እንዲያስተካክሉ መልሶ በመስጠት እንዲስተካከል አድርጓል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ የምርመራ መዝገቦች ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት በአዳር ለረቡዕ ታኅሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...