Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከሜቴክ ጋር በተያያዘ በሙስና የተጠረጠሩት የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊ መታሰራቸው ጠበቆችንና መርማሪ ፖሊስን...

ከሜቴክ ጋር በተያያዘ በሙስና የተጠረጠሩት የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊ መታሰራቸው ጠበቆችንና መርማሪ ፖሊስን አከራከረ

ቀን:

ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) ያለ ጨረታ በሶማሌ ክልል ለሚተከል የሞይባል ኔትወርክ ማስፋፊያ ታወር ሥራ ሰጥተዋል ተብለው በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የኢትዮ ቴሌኮም የኤንጂፒኦ ፕሮግራም ዳይሬክተር እስር ጠበቆቻቸውንና መርማሪ ፖሊስን አከራከረ፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች ተቃውሟቸውን የገለጹት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን እስከ ታኅሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በተጠርጣሪ አቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ ያለውን የምርመራ ሒደት ማጠናቀቅ አለመቻሉን ጠቅሶ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት በመጠየቁ ነው፡፡

የአቶ ኢሳያስ ጠበቆች ደንበኛቸው ለእስር የተዳረጉት ሕግ ተጥሶ ነው ብለዋል፡፡ በዝርዝር እንደገለጹት፣ በአዋጅ ቁጥር 646/2001 ማለትም የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ አንቀጽ 3(2ለ) መሠረት አንድ የመንግሥት ተቋማት ከሌላኛው የመንግሥት ተቋማት ጋር የሚያደርገው ውልም ሆነ ግዥ ሲፈጸም ጨረታ እንዲያወጣ እንደማይገደድ፣ በመሆኑም አቶ ኢሳያስ የተጠረጠሩት ከኢትዮ ቴሌኮም ለሜቴክ ያለ ጨረታ ሥራ ሰጥተዋል በማለት ስለሆነ፣ ይኼ ደግሞ መርማሪ ቡድኑ የአገሪቱን ነባራዊ ሕጎች ሳያገናዝብ በመሆኑ ለእስር መዳረግ እንዳልነበረባቸው ተናግረዋል፡፡

ደንበኛቸው የተጠረጠሩበት ጉዳይ በሶማሌ ክልል የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ታወር ተከላ ጋር የተገናኘ መሆኑን ያስታወሱት ጠበቆቹ፣ ሥራው የተጀመረው ሜቴክ ከመቋቋሙ በፊት በ1999 ዓ.ም. መሆኑን ጠቁመው፣ በወቅቱ በወጣው ጨረታ ዜዲቲኢ ከፍተኛ ዋጋ በማቅረቡና ሌላ ተጫራች በመጥፋቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽንን ይቆጣጠር የነበረው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር፣ ‹‹በሶማሌ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ሌላ ተጫራች ወይም ድርጅት ገብተው መሥራት ስለማይችሉ የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ታወር ተከላው ለመከላከያ እንዲሰጥላቸው መጠየቃቸውን አስረድተዋል፡፡ ሌላው በወቅቱ በኦጋዴን አካባቢ ለነዳጅ ማውጣት ፕሮጀክት ሥራ ሄደው በነበሩ የቻይና ዜጎች ላይ በተፈጸመው ግድያ ምክንያት፣ ሌሎች ድርጅቶች ገብተው ለመሥራት ፍላጎት ስላልነበራቸው ሥራው ለሜቴክ መሰጠቱን አክለዋል፡፡

በመሆኑም ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በመከላከያ ሥር ሜቴክን ተቋቁሞ ስለነበር ቀደም ባለው ከ204 ሚሊዮን ብር  በላይ ውል 153 ታወሮች እንዲተክል ስምምነት ቢደረግም፣ የታወሮቹን ቁጥር ወደ 185 ከፍ በማድረግና በማሻሻል ባንኩንም ወደ 322 ሚሊዮን ከፍ በማድረግና የቦርዱ ይሁንታ ሲገኝ አቶ ኢሳያስ ውል መፈራረማቸውን ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ሌላ ዓላማ ለማሳካት እንጂ እውነትን ለማውጣት እየሠራ እንዳልመሰላቸው ጠበቆቹ ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶት የምርመራ መዝገቡን እንዲመረምርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ደንበኛቸው በእስር ቆይተው እንኳን ክስ ቢመሠረትባቸው በነፃ እንደሚሰናበቱ እርግጠኛ መሆናቸውን የገለጹት ጠበቆቹ፣ የሚደርስባቸውን ጉዳት መመለስ ስለማይቻል የመርማሪው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮን ብቻ የሚያይ በመሆኑና ወደ ፍሬ ነገር ክርክር መግባት እንደማይችል ቢረዱም፣ እውነቱን ማወቅ እንዳለበትም አክለዋል፡፡ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ የተጠርጣሪን ቃል መቀበል ላይ፣ ‹‹መጀመርያ ወይም ከምርመራ በኋላ›› ባይልም፣ ደንበኛቸውን ቀድመው ቃላቸውን ቢቀበሏቸው ኖሮ ይኼንን ያህል ጊዜ ሊታሰሩ እንደማይችሉና እየደረሰባቸው ያለውን ጉዳት መቀነስ ይቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የሕግ አውጪው ዓላማ እውነትን መጠበቅ ስለሆነ፣ ተጠርጣሪውን ቀድመው ቃል መቀበላቸው የተሻለ እንደነበርም አክለዋል፡፡

ውል ማሻሻልን በሚመለከት የኢትዮ ቴሌኮም መዋቅር እንደሚያስረዳው፣ የአንድ ሥራ ውልን ለማሻሻል የፕሮግራም ዳይሬክተር ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ማሻሻል እንደሚችል ስለሚገልጽ፣ ቀደም ብሎ ያለውን መመርያና አሠራር እየጠቀሰ መርማሪ ቡድኑ አይቻልም ሊል እንደማይገባ ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡ ውሉ እንዲሻሻል የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈጻሚ የፈረመበት ሰነድ እያለ፣ ዝምድናን በመጠቀምና በመመሳጠር እንደተሠራ መግለጽ ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ሌላው መርማሪ ቡድኑ ለሜቴክ የተሰጠው ሥራ 91.8 በመቶ መጠናቀቁን ገልጾ ቀሪው 8.2 በመቶ ጥራት እንደጎደለው ከተናገረ በኋላ፣ በመቀጠል 8.2 በመቶ ሥራው እንዳልተጠናቀቀ የሚገልጸው ክርክር ማቅረቡ ግልጽ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ ተቋሙን የሚቆጣጠረው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሶማሌ ክልል ሄዶ የሚሠራ ስለሌለ ሜቴክ ሁሉንም ሥራ ኃላፊነት ወስዶ እንዲሠራ ፈቅዶ እያለ፣ መርማሪ ቡድኑ የተለያየ ነገር እየጠቀሰ ደንበኛቸው በእስር እንዲቆዩ ማድረጉ ለሌላ ዓላማ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ኢሳያስ የኤንጂፒኦ ፕሮግራም ዳይሬክተር በመሆናቸው ውል ማሻሻል እንደሚችሉ እየታወቀ፣ ቦርዱ ሳይፈቅድ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ያለን ክፍያ ማሻሻል እንደማይችሉ እየተደረገ እየተዛባ ለፍርድ ቤቱ እየቀረበ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ምንም ይሁን ምንም ውልም ሆነ ክፍያ የተፈጸመው የመንግሥት ተቋም ከመንግሥት ተቋም ጋር በመሆኑ፣ ተጠርጣሪው ሊያሳስራቸው የሚችል ነገር እንደሌለ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው የአሥር ቀናት ተጨማሪ ጊዜ የአንድ ሰው ምስክርነት ቃል ብቻ መቀበሉ ተገቢ እንዳልሆነና የተጠርጣሪ የዋስትናም መብት ሊያስከለክል ስለማይችል፣ ፍርድ ቤቱ በሰበር ችሎት ስለዋስትና አሰጣጥ የተሰጠውን አስገዳጅ ትርጉም በማየት ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ፣ ‹‹ተጠርጣሪው የክፍያ ትዕዛዝ መስጠት ይችላሉ? ወይስ አይችሉም? ቦርዱ ፈቅዷል? ወይስ አልፈቀደም? የሚለውን እናጣራለን›› የሚለው ሲጀምር ሥልጣን ሳይኖራቸው ብሎ ደምድሞ ከተነሳ በኋላ በመሆኑ፣ መርማሪ ቡድኑ እየሠራ ያለው ሌላ ሴራ ትንተና ፍለጋ እንዳይሆን የሚል ሥጋት እንዳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ እንዳስረዳው ተከራካሪ ወገኖች መከራከር ያለባቸው በቀረበው የምርመራ ሒደት ላይ እንጂ፣ የሌላውን ተቋም ተከራካሪ ስሜት በሚነካ መንገድ መሆን የለበትም፡፡ ችሎቱንም አይመጥንም፡፡ የሴራ ትንተናና ዳተኝነት የመሳሰሉ ቃላትን መጠቀም ተገቢ ስላልሆነ፣ ፍርድ ቤቱም ማሳሰቢያ መስጠት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ተጠርጣሪው የታሰሩት ኢትዮጵያ ቴሌኮም ለሜቴክ በውል ሥራውን ስለሰጠ ሳይሆን፣ ሥራውን የሠራው ሌላ ተቋም በመሆኑ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ሜቴክ ራሱ ቢሠራው ችግር እንዳልነበረው ጠቁሞ፣ ውሉ ከሜቴክ ጋር ሆኖ ክፍያ የተፈጸመው ከንዑስ ተቋራጩ ጋር በመሆኑ እንደሆነም አክሏል፡፡ በእጅ አዙር ተጠቅመዋል የሚል የወንጀል መነሻ እንዳለውም አስረድቷል፡፡

ደረጃቸውን ላልጠበቁ ነገር ግን ከሜቴክ ሥር ላሉ ንዑስ ተቋራጮች ሥራው በመሰጠቱ ጥራት እንደሌለው፣ በንፋስ ኃይል መውደቁን፣ የተገነባውም እየፈረሰ መሆኑንና ጥራት የጎደለው እንደሆነም መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡

በመጀመርያ በ204 ሚሊዮን ብር ውል መገባቱንና ተሻሸሎ 322 ሚሊዮን ብር መድረሱን ያስታወሰው መርማሪ ቡድኑ፣ ክፍያው በሥራ አስፈጻሚው ትዕዛዝ መፈጸም ሲገባው አቶ ኢሳያስ በቀጥታ ለፋይናንስ በመጻፍ እንዲከፈል ማድረጋቸው ተገቢ እንዳልሆነም አስረድቷል፡፡ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያስከፍል ውል መፈጸምም ሆነ መሻሻል የሚችለው በዋና ሥራ አስፈጻሚው ብቻ መሆኑንም አክሏል፡፡

የበላይ አመራር በማያውቅበት ሁኔታ አቶ ኢሳያስ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው፣ ‹‹ተጫራች አይቀርብም›› በሚል ያለምንም የጨረታ ሙከራ ለአንድ ተቋም እንዲሰጥ ማድረጋቸው ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ አቶ ኢያሳያን እንዳነጋገራቸውና ሪፖርት ስለማድረጋቸው ጠይቋቸው እንዳላደረጉ ምላሽ እንደሰጡትም በመጠቆም፣ መጀመርያ ሳያነጋግራቸው ተብሎ ከጠበቆች የተነሳው ስህተት መሆኑን ገልጿል፡፡ የፈቀደ ቦርድ እንደሌለም አቶ ኢሳያስ እንደነገሩት መርማሪ ቡድኑ አክሏል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የተሠራው 91 በመቶ መሆኑንና ስምንት በመቶ ያልተሠራ መሆኑ ስላሳወቀው፣ ያልተሠራውን ግምት እየሠራ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ ክፍያ ግን ሙሉ በሙሉ ከ322 ሚሊዮን ብር በላይ መፈጸሙንም አክሏል፡፡ አቶ ኢሳያስን አስሮ የማቆየት ፍላጎት እንደሌለው የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ግን ትክክለኛ ፍትሕ ለማሰጠት መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዋስ ቢወጡ ምስክር ሊያባብሉ፣ ሊያስፈራሩና እሳቸውም ሊሰወሩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ስላለው እንደሚቃወም ገልጾ 14 ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ ላቀረበው አቤቱታ ‹‹ለሴራ ትንተናና ለደባ›› የሚሉትን ቃላት ከሕግ ባለሙያ የሚጠበቅ እንዳልሆነ ጠቁሞ እንዲስተካከል አስታውቋል፡፡ ጠበቆች በበኩላቸው ‹‹ለሴራ ትንታኔ እንዳይጋለጥ ነው ያልነው›› ካሉ በኋላ፣ ለመርማሪ ፖሊስ የሚሰጠው ዕድል ለእነሱም እኩል እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የመርማሪ ቡድኑን የምርመራ መዝገብ በአዳር ታኅሳስ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪው ጠበቆች ያቀረቡትን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ፣ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ አሥር ቀናት በመፍቀድ ለታኅሳስ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...