Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የታሰሩ 33 ግለሰቦች የምርመራ መዝገባቸው እንዲለይ ጠየቁ

በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የታሰሩ 33 ግለሰቦች የምርመራ መዝገባቸው እንዲለይ ጠየቁ

ቀን:

በርካታ ዜጎችን በድብቅ እስር ቤቶች እስከ አምስት ወራት ድረስ ከቤተሰብ ደብቆ በማሰር፣ በመግረፍ፣ በተለያዩ ሁኔታዎች በማሰቃየት፣ አካል በማጉደል፣ በጨለማ ቤት በማሰር፣ በመደብደብና ሌሎች ድርጊቶችን በመፈጸም ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማድረስ ተጠርጥረው የታሰሩት፣ በእነ አቶ ጎሃ አጽብሃ የምርመራ መዝገብ የተጠቃለሉ 33 ግለሰቦች፣ ‹‹የምርመራ መዝገባችን ተለይቶ ይቅረብልን›› በማለት ለፍርድ ቤት አመለከቱ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የምርመራ መዝገቡ እንዲለይላቸው የጠየቁበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ 33 ተጠርጣሪዎች ከፌዴራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ማረሚያ ቤትና ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተውጣጡ ናቸው፡፡ በመሆኑም አራቱም ተቋማት የየራሳቸው አደረጃጀትና የሥራ ድርሻ ስላላቸው፣ የሚጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት አንድ ዓይነት ስለማይሆን፣ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በጥቅል የሚያቀርብባቸው የጥርጣሬ የወንጀል ድርጊት ማንና የየትኛው ተቋም ሠራተኛ እንደተጠረጠረበት ግልጽ ስላልሆነላቸው መከራከር ስልላቻሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ቀደም ብሎ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የሠራውን እንዳስረዳው፣ የ21 ተጎጂዎች ምስክርነት ቃል ተቀብሏል፡፡ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኝ ድብቅ እስር ቤትን የመለየት ሥራ ማከናወኑን፣ ተጠርጣሪዎችን በተጎጂዎች ለማስለየት ሞክሮ ተጠርጣሪዎቹ በመቃወማቸው ሳይችል መቅረቱን፣ በተቋማቸው ያላቸውን ኃላፊነት ለማወቅ በደብዳቤ መጠየቁን፣ በድብደባና በተለያዩ ማሰቃያዎች ሕይወታቸው ያለፈ ዜጎችን አስከሬን ምርመራ ውጤት የሚያሳይ ሰነድ ከቅዱስ ጳውሎስና ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በደብዳቤ መጠየቁን፣ የተለያዩ መዝገቦችን ከፖሊስ ምርመራ ቢሮ በማስመጣት በመፈተሽ ላይ መሆኑን፣ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቀረቡ አቤቱታዎችን ለመለየት ማስረጃ መጠየቁን አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

በመቀጠልም በተለያዩ አካባቢዎችና ክልሎች የሚገኙ የጉዳቱ ሰለባዎችን የምስክርነት ቃል መቀበል፣ ተጠርጣሪዎችን በተለየ ቴክኒክ በተጎጂዎች የማስለየት ሥራ ማከናወን፣ የሕክምና ማስረጃዎችን ማሰባሰብ፣ በተጎጂዎች ላይ የደረሰውን የንብረት ጉዳት መለየትና በባለሙያ ማስገመት፣ በቂሊንጦ ማቆያ ቤት ቃጠሎ ምክንያት ሸዋ ሮቢት ተወስደው የተደበደቡና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች ቃል መቀበል፣ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉና የአካል ጉዳት ስለደረሰባቸው መንቀሳቀስ የማይችሉ ተጎጂዎችን ቃል መቀበል፣ የምርመራ ቡድን አቋቁሞ መላክና የተለያዩ ሰነዶችንም ማሰባሰብ እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡ እነዚህን ቀሪ ሥራዎችን ለመሥራትም ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከላይ የተጠቀሱትን ሥራዎችና ቀሩ ያላቸውን ተጨማሪ የምርመራ ሒደቶች በሚመለከት፣ ተጠርጣሪዎቹ በተመሳሳይ ተቃውሟቸውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት አስረድተዋል፡፡  

ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች መሆናቸውን በተደጋጋሚ በመግለጽ፣ የምርመራ መዝገባቸው እንዲለይላቸውና እያንዳንዳቸው የፈጸሙት ወንጀል እንዲነገራቸው ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በደፈናው የ21 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን ከመግለጽ ባለፈ በማን ላይ ስንት ምስክር እንዳሰማ፣ መቼና የት ድርጊቱ እንደተፈጸመ፣ በእያንዳንዳቸው ላይ ስንት ምስክር እንደቀረበ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ 33 ተጠርጣሪዎችን አንድ ላይ ሰብስቦና በጥቅል ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም›› በማለት በየቀጠሮው በመናገር ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ ተገቢ እንዳልሆነና መዝገቡ ካልተለየ ማብቂያው ራሱ መቼ እንደሆነ ሊታወቅ እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ ምርመራ ከተጀመረባቸው ስድስት ወራት እንዳለፈ ጠቁመው፣ አሁን እንደ አዲስ መቀጠሉ ተገቢ እንዳልሆነና መርማሪ ቡድኑ ሥራውን እየሠራ እንዳልሆነ ስለሚያሳይ፣ 14 ቀናት ሊፈቀድለት እንደማይገባም ጠይቀዋል፡፡

አንዳንዶቹ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ታኅሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በተለያዩ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተላለፈውን ዶክመንተሪ ፊልም ተቃውመዋል፡፡ ማን ምን እንዳጠፋ ሳይለይና እነሱ በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው እያለ ስማቸው እየተጠራ በሕዝብ እንዲፈረድባቸው ማድረግ፣ ተፈጽሟል የተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መጨረሻው ሳይታወቅ፣ ሌላ ሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸምና የፍርድ ቤትን ሥራ ማከናወን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዶክመንተሪው ፊልም ቀርበው ምስክርነታቸውን የሰጡት ሰዎች በወቅቱ ተከሰውና በፍርድ ቤት ጥፋተኛ መሆናቸው ተረጋግጦ የተቀጡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነሱ ሌላ ዓላማ ኖሯቸው ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ በተሰጣቸው ኃላፊነት የሠሩት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶክመንተሪው አንድ ብሔርን የሚያጠቃና እየፈረደባቸውም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ምን እየሠራ ነው? ወይም ለእነሱም ሚዲያው ተፈቅዶ ቀርበው ለመከራከር በመጠየቅ፣ ፍርድ ቤት ወንጀለኞች ናቸው ብሎ አስሯቸው ሳለ፣ አሁን ወንጀላቸውን ለማጠብ ነው . . . ሲሉ፣ ፍርድ ቤቱ በመሀል ገብቶ፣ ‹‹ስለሚዲያው ብዙ ብላችሁ አዳምጠናችኋል፡፡ ይኼ የፍርድ ቤቱ አጀንዳ አይደለም፣ ወደ ሌላ ክርክር ግቡ፤›› በማለቱ ወደ ሌላ ክርክር ገብተዋል፡፡ ሲሠሩ የነበረው ብሔር ለይተው አለመሆኑንና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደነበር በመግለጽ፣ ጥፋተኛ መሆናቸው በፍርድ ቤቱ ሳይረጋገጥ የሚታወጅባቸው ፍርድ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን ቢሠራ ምንም ተቃውሞ እንደሌላቸው በማከል፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም በሰጠው ምላሽ፣ የወንጀሉ አፈጻጸም በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች መሆኑን ጠቁሞ፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሆኑንና አንድ ምስክር በስምንትና ከዚያም በላይ ተጠርጣሪዎች ላይ የምስክርነት ቃል ስለሚሰጥ፣ የምርመራ መዝገቡን መለየት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጿል፡፡ ማንንም አስሮ ማቆየት የመርማሪ ዓላማ አለመሆኑን ጠቁሞ፣ ዓላማው እውነትን ማውጣት ብቻ እንደሆነም ገልጿል፡፡

የተፈጸመው ወንጀል ከባድ የመብት ጥሰት በመሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች በዋስ ቢወጡ በቀላሉ መረጃ ሊያጠፉ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ ዶክመንተሪ ፊልሙን በሚመለከት ከምርመራው ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ገልጾ፣ ምናልባት መንግሥት ለኅብረተሰቡ መረጃ እንደሚያቀርብ በገባው ቃል መሠረትና ሕዝቡም ባለው የማወቅ መብት የተፈጸመ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል፡፡

ሁሉም ተጠርጣሪዎች ድርጊቱን የፈጸሙት በቡድን በመሆኑ አንዱን ከአንዱ መለየት ስለሚያስቸግር፣ የምርመራ መዝገቡ ባለበት እንዲቀጥል ትዕዛዝ እንዲሰጥለትና የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን በአዳር አስቀርቦ ከተመለከተ በኋላ፣ ሐሙስ ታኅሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የተጠረጠሩበትን ጉዳይ በሚገባቸው ቋንቋ ወዲያውኑ እንዲናገሩ እንጂ፣ ቃላቸውን እንዲቀበላቸው መርማሪ ቡድኑን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(1) ድንጋጌ እንደማያስገድድ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ‹‹እስካሁን ቃላችንን አልተቀበለንም፤›› በማለት ሕገ መንግሥቱን ጠቅሰው የሚያቀርቡትን ተቃውሞ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ተጠርጣሪዎችን በተጎጂዎች ማስለየት በመልክ ብቻ የሚያውቋቸውን ለመለየት ስለሚረዳ ተገቢ መሆኑን በመንገር፣ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን ተቃውሞም ውድቅ አድርጎታል፡፡ ምስክሮችን በሚመለከትም አንድ ምስክር በብዙ ተጠርጣሪዎች ላይ እንደሚመሰክር ከምርመራ መዝገቡ መረዳቱን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ የምርመራ መዝገቡን መለየት እንደማይቻልም አስታውቋል፡፡ ሚዲያን በሚመለከት ተለይቶ ስላልቀረበለት ለይቶ ማቅረብ ሲቻል የሚታይ መሆኑን በመግለጽ፣ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት በመፍቀድ ለታኅሳስ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...