Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት የብሔራዊ ባንክ የቀድሞ ምክትል ገዥ እንዲተኳቸው አደረጉ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቦርዱ የአዲሱን ፕሬዚዳንት መተካት በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

የአቢሲኒያ ባንክን ከአራት ዓመታት በላይ በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ሙሉጌታ አስማረ ‹‹በቃኝ›› በማለት የሚተካቸውን ኃላፊ ራሳቸው በመፈለግ፣ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የነበሩትን አቶ በቃሉ ዘለቀን እንዲተኳቸው ያቀረቡትን ሐሳብ ቦርዱ ተቀብሎ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ ኃላፊነቶች ከአሥር ዓመታት በላይና በፕሬዚዳንትነት ደግሞ ለአሥር ዓመታት ካገለገሉ በኋላ፣ ከሦስት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሆነው ተሹመው የነበሩት አቶ በቃሉ፣ ከአቢሲኒያ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ ጋር ለሁለት ወራት ያህል ከተወያዩ በኋላ በመስማማታቸው፣ እ.ኤ.አ. ከጥር ወር 2019 ጀምሮ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲሠሩ ቦርዱ ውሳኔ ማስተላለፉን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡

የአቢሲኒያ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መሠረት ታዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፎች ወይም በሌላም የሥራ ዘርፍ ላይ በነበሩና ባሉ ኃላፊዎች ያልነበረና ያልተለመደ እንግዳ ነገር አቢሲኒያ ባንክን ገጥሞታል፡፡ ይኼውም ያለ ማንም አስገዳጅነትና ጣልቃ ገብነት በራሳቸው ፈቃድ የባንኩ ፕሬዚዳንት የሥራ መልቀቂያ አቅርበዋል፡፡ ቦርዱም ሆነ ባለድርሻዎች የመጀመርያ ጥያቄያቸው ‹‹ለምን? ምን ችግር አጋጠመዎ?›› የሚል እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን አቶ ሙሉጌታ ከነበራቸው የሥራ ብቃትና ችሎታ በላይ የሚገርምና ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ተግባር መፈጸማቸውን የተናገሩት የቦርድ ሰብሳቢው፣ ኃላፊነታቸውን መልቀቅ ብቻ ሳይሆን ራሳቸው በመደራደርና በማሳመን ‹‹ከእኔ በላይ ብቃት ያለውና በፋይናንስ ዘርፉ አንቱ የተባለ ባለሙያ ነው፤›› ያሏቸውን አቶ በቃሉ ዘለቀን ተክተው መሆኑንም አክለዋል፡፡ የቦርድ አባላትና ከፍተኛ ባለድርሻዎች ለጊዜው ግራ ቢጋቡም አቶ ሙሉጌታ ያደረጉት ነገር አሳማኝና የተኳቸው ባለሙያ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያላቸው መሆናቸውን ሁሉም ስለሚያውቅ፣ በሙሉ ድምፅ ተቀብለው ማፅደቃቸውን አቶ መሠረት አረጋግጠዋል፡፡ አቶ ሙሉጌታ አምስተኛው የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን ጠቁመው፣ አስተዋይና ከሁሉም ባለሙያዎች ጋር ተግባብተውና ተባብረው ሲመሩ በመቆየታቸው፣ በባንኩ በቆዩባቸው ከአራት ዓመታት በላይ ተከታታይ ዕድገት ያስመዘገቡ ምሥጉን ኃላፊ እንደነበሩ አቶ መሠረት መስክረዋል፡፡ አቶ በቃሉም ከአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ጀምሮ ሥራ እንደሚጀምሩ፣ ሁሉም ነገር አልቆ በቅርቡ የሚገኘውን የብሔራዊ ባንክ ይሁንታ ብቻ እየጠበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባልተለመደ ሁኔታ እንዴትና ለምን ‹‹በቃኝ›› ብለው ኃላፊነታቸውን ራሳቸው ለመረጡት ባለሙያ መስጠት እንደፈለጉ ሪፖርተር አቶ ሙሉጌታን አነጋግሯቸው በሰጡት ምላሽ፣ ከወጣትነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሥር ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ለ18 ዓመታት መሥራታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በአቢሲኒያ ባንክ ደግሞ በምክትል ፕሬዚዳንትና በፕሬዚዳንትነት ለዘጠኝ ዓመታት እንደሠሩ ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ከ26 ዓመታት በላይ መሥራታቸውን ገልጸው፣ ኋላቀር ከነበረው አሠራር ጀምሮ እስከ ዘመናዊ አሠራር ድረስ በዘርፉ ከታች ጀምረው እስከ መምራት ድረስ መዝለቃቸውን ጠቁመዋል፡፡ በ26 ዓመታት የሥራ ልምዳቸው የተለያዩ የሥራ ሒደቶችን ማለፋቸውንና ውጤታማም መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣ የባንክ ሥራ ፈታኝ እየሆነና ዓለም አቀፍ ይዘት ኖሮት እያደገ የሚሄድ ዘርፍ በመሆኑ፣ አዳዲስ ዕውቀቶችንና ጉልበት እየፈለገ እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡ ዕድሜያቸው 50 መሆኑንና ገና ለቀጣይ አሥርና አሥራ አምስት ዓመታት የመሥራት ብቃት ላይ ቢሆኑም፣ ዘርፉ ፈጣንና ተለዋዋጭ እየሆነ ስለሚሄድ፣ ከእሳቸው የተሻለ ጉልበትና ተራማጅ አመራር መተካት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ውስብስብ የሆነ ለውጥና ፍጥነት ተከትሎ ማሰብና መወሰን የሚችሉ ሰዎች ዘርፉን መምራት ስላለባቸው፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ባንኩን የሚመጥን ሰው ሲያስቡ፣ አቶ በቃሉ ዘለቀን የመጀመርያ ምርጫቸው ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ በቃሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተነስተው በምክትል ገዥነት ለብሔራዊ ባንክ ሲሾሙ ስላልተመቻቸው ይሁን ወይም ስላልፈለጉ ባያውቁም ብዙም እንደማይቆዩ በመረዳታቸው፣ ‹‹ከዚህ ኃላፊነት ወጥተህ ወደ ግሉ ዘርፍ የምትመጣ ከሆነ እኔን ተክተህ የአቢሲኒያ ባንክ ኃላፊ ትሆናለህ፤›› ብለው የመጀመርያ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የአቶ በቃሉ መልስ፣ ‹‹ወደ ግሉ ዘርፍ የምመጣ ቢሆንም አቢሲኒያ ባንክ ምርጫዬ አይደለም፤›› የሚል ምላሽ ቢሰጧቸውም፣ ከሁለት ወራት ንግግር በኋላ ማሳመን መቻላቸውን አክለዋል፡፡ በመቀጠልም ለቦርዱ ሲያሳውቁ ቦርዱ ለመቀበል ያንገራገረ ቢሆንም መስማማቱን ጠቁመዋል፡፡ የአቢሲኒያ ባንክ ቦርድ አባላት ደስ ባይላቸውም፣ ባለሀብቱን አሳምነው አቶ በቃሉን በመሾም ከታኅሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የእሳቸውን መልቀቂያ እንደተቀበሏቸው አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ የሥራ ዘመናቸው በሌሎች ባንኮች ተቀጥረው ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት በሚመለከት ተጠይቀው፣ ‹‹ከዚህ በኋላ በግልም ሆነ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተቀጥሬ አልሠራም፡፡ ምናልባት ወደፊት ዘርፈ ብዙ ያልተነኩ ሥራዎች ስላሉ በማማከርና ሌሎች ነገሮችን በግል ልሠራ እችላለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ከመንግሥት በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ሹመት ቢሰጣቸው ስለመቀበላቸው ተጠይቀው፣ ‹‹በእውነት እሱን አስቤው አላውቅም፡፡ ይኼንን ወደፊት የምናየው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ አቢሲኒያ ባንክን ግን በፈለገው ዘርፍ ለማገዝ ሙሉ ፈቃደኛ መሆናቸውን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፎች ብዙ ውጣ ውረድ ያለባቸው መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፣ ምክንያቱ ደግሞ አብዛኛዎቹ የተቋቋሙት በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አቋም በመያዝ መሆኑ ገልጸው፣ ኢትዮጵያዊ ይዘት ኖሯቸው ቢሆን ጥሩ መሆኑን በመጠቆም፣ አሁን አሁን ሕጎችም እየተሻሻሉና ባለድርሻውም ሰከን ስላለ በቀጣይ ይሻሻላል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ የባንክ ደንበኞች የተሻለ አገልግሎት ስለሚፈልጉ በቴክኖሎጂ የዘመነ አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ በተለይ ሴክተሩን ለቀቅ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው፣ ራሱም ብሔራዊ ባንክ አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ለራሱም አቅም አለው ብለው እንደማያስቡና ተገቢውን ቁጥጥር ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሚያሠሩ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ የባንክ ባለድርሻዎች ሥራውን ለባለሙያው ትተው ውጤቱን መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመው፣ ባለሙያውም በዘርፉ ተገቢ ዕውቀት እየጨመረ ለመሄድ፣ ማንበብና መማር እንዳለበት መክረዋል፡፡

ሪፖርተር አዲስ የተሾሙትን የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ አቶ በቃሉ ከሦስት ወራት በፊት የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሆነው የተሾሙ ቢሆንም፣ ከወር በፊት መልቀቂያ አስገብተው ተቀባይነት እንዳገኙ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች