Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስንቱ ነገር ይሆን የሚያንገበግበን?

ሰላም! ሰላም! ባለፈው ሰሞን ምን ሆነ መሰላችሁ? አቤት! እናንተን ሳገኝ የወሬ አባዜዬ ያንቀለቅለኛል አይገልጸውም። ‹‹ሲያንቀለቅልህ አዋዜ ወይ ሚጥሚጣ ላስ›› ትል ነበር እናቴ። እኔ ግን በወሬ ተክቼዋለሁ። መቼም አንድ ቀን ብሎልን ወደ ሀብት ማማ የምንደርሰው መጀመርያ ወሬን አጥፍተን መሆን አለበት። አሊያማ ከሁለቱም አጥተን ስናልቅ ታሪክ ነጋሪ አናስተርፍም። እና መቼ ለታ ለወሬ ነጋሪ እንዳንተርፍ አድርጎ የወሬኛ መንጋ ሊጨርሰን ነበር። ያውም ቦሌ። አንድ የማሻሽጠው ቪላ ቤት ነበረኝ። በቦሌ ቆነጃጅት ሽቶ አፍንጫዬ ፈካ ብሎ ከየት መጣ ሳይባል ታዲያ የወሬ መንጋ ቦሌን በቁጥጥሩ ሥር አዋለው። ስንቴ በቁጥጥር ሥር እንደምንውል ግን አልገባኝም! በቁጥጥር ሥር ስንውል ደግሞ ይደርስብን የነበረው ግፍ እየተተረከ እኮ ነው!

 ‘ወገኔ’ መባባል የአፍ አመል መሆኑን እንድታዘብ በዚያ ሰዓትና ሥፍራ እግዜር እንደከሰተኝ ቆይቶ ገባኝ። ምክንያቱማ ለምን እንደሚሮጥ የሚያውቀው፣ ሲሮጡ ዓይቶ የሚሮጠው፣ ስትጮህ ሰምታ የምትጮኸው፣ በጠቅላላው ራሱን ለማዳን መንገደኛው መጨፈላለቅ ሆነ ተግባሩ፡፡ ለነገሩ መጨፈላለቁ ብዙም የሚደንቅ ነገር አልነበረውም። ድሮም የእኛ ሰው የራስን ዕድል በራስ ሳይወስን፣ የሰውን ዕድል ራሱ እየወሰነ ነበር ሲጨፈላለቅ የኖረው። ‘ይኼ የገዥዎች ታሪክ ነው’ የሚል ካለ እኔ ደላላ እንጂ ገዥ እንዳልሆንኩ ልብ ይባል እላለሁ። እግረ መንገዴን የአዛውንቱን ባሻዬ፣ ‹‹ስም ይወጣልናል ብላችሁ ሀቅን አሳልፎ ከመስጠት ይሰውራችሁ›› የምትል ምርቃት ልጨምርላችሁ። አሜን በሉ እንጂ! አሜን የማይሉ በጭካኔ ልባቸው የደነደነ ነው ይባላል አይደል?

 እና ምን እያወራሁ ነበር? አዎ፣ . . . ሐበሻ እርስ በርሱ ሲጨፈላለቅ መኖሩን፣ አሁንም እንዳለቀቀው ማስታወስ ነበረብኝ። ታዲያ ትውስታ እንኳን የእኔ ቢጤ የደነገጡትን፣ አደብ የገዙ የተባሉትንም እያቀዣበረ መሆኑን ከእናንተ በላይ ታዘብኩ አልልም። እውነቴን ነው! ይገርማችኋል ከልጅነቴ ጀምሮ በሁለት ነገር እንዳልሞት አጥብቄ እፀልያለሁ። አንዱ በእባብ መርዝ ነው። ይኼኛው ፀሎቴ ልክ እንዳልነበር ያወቅኩት ቃሉ ማለት ከእባብ የሰው መርዝ ሐሳብ እንደሚከፋ ሲያሳየኝ ነው። ሁለተኛው ግን ስህተት የተገኘበት አልመሰለኝም። እንዲያውም የወሬ መንጋ እንዳይገለኝ የፀለይኩት ምን ያህል እንደተደመጠ እንዳይ ይመስላል ‘እዝዝዝ’ የሚል የወሬ ሠራዊት፣ ኑሮ በቁሙ እንዲያጎላጅ የፈረደበትን ወገኔን ቀልቡን ሲገፈው መሀሉ ተገኘሁ። ቆይ! ቆይ! ግን እኛ ምንም ሳንበላ ገንዘባችን፣ ጉልበታችን እየተበላ እስከ መቼ ነው የምንዘልቀው? ዘንድሮ ሰው ‘ፌስቡክ’ ሲከፍት የአፍ ‘ፌስቱላ’ ያለበት ሁሉ ይመስላል። ቀላል ነገር ይነድፋል? ባሻዬ ደግሞ፣ ‹‹ምነው ግን የዘመኑ ልጆች እንደ ሥራ ፈት ወሬ አነፍናፊ ሆኑ? ወሬና ነገር ቢነድፉት፣ ቢያከሩት፣ ቢፈትሉት ቤት ያፈርሳል እንጂ አያሞቅ! ወይስ ሲኒማና ካፌ በመጎለት የወሬ ፈትል ‘አርት’ አናናቁም?›› ይሉኛል። ምኑን አውቄ ባሻዬ? ምኑን አውቄ? ዘንድሮ የጭካኔ ድርጊት ሰለባዎችን እማኝነት እየሰማን ልናብድ እኮ ነው!

ካልታሰበው የወሬ መንጋ ተነድፎም ሳይነደፍም ሮጦ ያመለጠ፣ ትንፋሽ ለመሰብሰብ የሆነ ጥግ ተሰባሰበና አንድ አንድ ተጀመረ። ‹‹50 ሜትር የማትሆነውን ማራቶን እንደ ሮጥን ሁሉ ስናለከልክ ለታዘበን ልማቱ ‘ጂምናዚየም’ ማስፋፋት ላይ ማተኮር እንዳለበት ይረዳል። ኑሮ ራሱ ‘ጂም’ በሆነበት ዘመን ለ50 ሜትር ትንፋሽ ማጣታችን ያስቆጫል፤›› አለ አንዱ እግረኛ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ። አንዷ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ወይኔ አገሬ! የአትሌቶች አገር ትመስለኝ ነበር። በዚህ አያያዛችን ለጥቂት ጀግና አትሌቶቻችን ስንዘምር ብንኖር ምን ይገርመናል?›› አለች። ‹‹እሱን እንኳ ተይው። እዚህ አገር ያለ ወሬና ሩጫ ሥራ የለም እንዴ?›› ብሎ ሌላው ወሬውን ነዛ። ድንጋጤ እስኪለቀው ወሬውን የነዙት ለዓይን እስኪሠወሩ ጊዜ ወስዶ እየተረጋጋ የነበረው ደግሞ ሌላ ሽኩቻ ውስጥ ገባ። ‹‹እንዲያማ ሊሆን አይችልም። እኛ እኮ ከዚያ እስከዚህ የሮጥነው ሌሎች ሲሮጡ ዓይተን እንጂ ምን እንደሆነ አልሰማንም፤›› ብሎ ነገሩን አጦዘው። ምፀቱ የምር የመሰለው ነፍሱ ስትጨነቅ ይታያል። ቀሪው ያላግጣል። በመሀል አንዱ ሲጋራ አውጥቶ ይለኩሳል። ‹‹ነፍሱ ሕዝብ በተሰበሰበበት መሀል ማጨስ ክልክል ነው፤›› ይለዋል አጠገቡ የቆመ ጉንጮቹ የተወጠሩ ወጣት። ‹‹መበተን ነዋ! ወትሮም መንጋ የሚሰበሰበውም የሚበተነውም በወሬና በጭስ ነው። አይ እኛ! የእሳት የእሳቱ ጊዜ አፍሽን ዘግተሽ የጭሱ ሰዓት ታፈንኩ ትያለሽ. . . ›› እያለ አጫሹ ከስብስቡ ተነጠለ። ወይ እሳትና ጭስ? ከወሬ በልጦ ይኼን ያህል ያናግራል እስኪ? ያውም በዚህ የሰቆቃ ታሪክ በሚሰማበት ጊዜ!

‹‹ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም። ወሬ ተፈርቶ ቀልቤን ልጣ?’›› ብዬ እኔም ከስብስቡ ከመለየቴ በፊት ሰውን ያራኮተው ምን እንደሆነ ሳጣራ፣ ሁለት ጎረምሶች በአንዲት ቀዘባ ምክንያት ፈጠሩት የተባለው ግጭት ወደ ብሔር ተለውጦ ነው ሲባል ዘመናችንን ሳይሆን ራሳችንን ረገምኩ። ራሳችንን መርገም ብቻ ሳይሆን ከገባንበት ማጥ ውስጥ በቶሎ ካልወጣን መጭው ትውልድ ይፋረደናል፡፡ ያልኳችሁን ቪላ አዋክቤ አከራየሁና ‘ኮሚሽኔን’ ስቀበል ሆዴ ሲጮህ ሰማሁ። ይህንን የተረገመና የተወገዘ ነገር ስበላ ምግብ አለመብላቴን ረስቻለሁ (ከረሱ ይረሳል ሆድም አገርም ቢሆን)፡፡ ወደ ቤቴ ልሄድ ስል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደወለ። “እህ?” ስለው፣ ‹‹ምሳ እየበላን የማዋይህ ነገር አለ ቶሎ ድረስ፤›› አለኝ። ወደ ፒያሳ ገሰገስኩ።

እንዳየኝ ጠኔ እንደጠናብኝ ከፊቴ አንብቦ፣ ‹‹በል ቶሎ ወደ ሸራተን!›› አለኝ። ልቤ ተንሸራተተ! ‹‹ምን ልንሠራ?›› ስለው፣ ‹‹ምሳ ልንበላ!›› አለኝ ከአፌ ነጥቆ። ‘ይኼ ሰውዬ፣ ዛሬ ምሳዬን ሸራተን አብልቶ ቀሪ ዘመኔን በአምሮት እንዳሳልፍለት ይፈልጋል? ምነው ፈጣሪ አንድ ያለኝን ወዳጅ ሳዝንበት ዝም ባትል?’ እያልኩ ተከተልኩት። ጥቂት ሄደን የሆነ ምግብ ቤት ይዞኝ ገባ። አስተናጋጁ፣ ‹‹እንኳን ወደ ሸራተን በሰላም መጡ!›› ሲለኝ ነፍሴ ገባች። ለስሙ ብቻ ክፈሉ ካልተባልን የእኔም የእሱም ምሳ እንደ ወረደ ከምንጠጣው የእግዜር ውኃ ጋር ከ100 ብር እንደማይበልጥ አወቅኩ። የደሃ አምላክ የት ሄዶ ያለ ግጦሽ መሬታችን እንሰማራና? አስተናጋጁ በስም ብቻ ሳይሆን በግብርም አንድ ነን በሚል መንፈስ በቀልጣፋ መስተንግዶው ሲያረካኝ ሳየው ወደ ባሻዬ ልጅ ዘወር ብዬ፣ ‹‹ምናለበት የዴሞክራሲ ጠበቆች ነን የሚሉንም እንዲህ ለመርሐ ግብራቸው ዕውን መሆን ሲተጉ ብናይ?›› ማለት። መቼም አፌ አያርፍ! ‹‹ምርጫው ደርሶ የመፈተኛቸው ጊዜ ላይ እንደ ጴጥሮስ ባይከዱን ለማለት ፈልገህ ነው?›› አለኝ። እሱም አፉ አያርፍ! አፋቸው አላርፍ ያለ ጨካኞች ደግሞ እንዴት እንደሚያሾፉ እያያችሁ ነው አይደል?   

ሆዳችንን ሞልተን ስናበቃ ለምን እንደፈለገኝ ስጠይቀው ለሽምግልና እንደሆነ አጫወተኝ። “ሽምግልና?” ስለው አንድ የማውቀውን ስም ጠርቶ፣ ‹‹ይኸው ሁለት ዓመቱ 50 ሺሕ ብር ተበድሮኝ አልመለሰም። ጭራሽ ለመጭው ጥምቀት ሰሞን ቀለበት ያስራል። ደግሞ ከስንት ሰው መሰለህ ተበድሮ ሰው እያስለቀሰ ያለው?›› አለኝ። “እና?” ስለው፣ ‹‹ብሩን ባይመልስ ቢያንስ በሕዝብ ገንዘብ ቀለበት መንገድ እንጂ ቀለበት እንደማይታሰር ሊገባው ያስፈልጋል። ምነው ሰውየው ይኼን ያህል ኃፍረት ራቀው?›› አለኝ። አንዴ ሳልወድ ታጭቻለሁና ሌላ አንድ ወዳጄን አስከትዬ ከመሄዴ በፊት ስልክ ደወልኩ። አነሳው ለምን እንደፈለግኩት ጫፍ ጫፉን ስነግረው (መቼም ለነገር አለመፈጠር ስንት ነገር ያበላሻል መሰላችሁ) ‹‹. . . ቆይ መልሼ ልደውል። አንዴ! አንዴ!›› ብሎ ስልኩን ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ነኝ በል አለው። ይህንንማ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሰብዓዊ ፍጡራን ወገኖቻችን ላይ ጭካኔ በፈጸሙትና በሜቴክ ሰዎች ላይ እንዳደረገው ፍርድ ቤት ገትሮት ፍትሕ ካልተገኘ በስተቀር፣ የባሻዬ ልጅ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያፈራው አንጡራ ገንዘቡ ተበላ ማለት ነው፡፡ እኔን አፈር ይብላኝ!

ሽማግሌ የተባልኩት ሰውዬ መናደድ ጀመርኩ። እንደ ፀበኛ ሰተት ብዬ ቤቱ ስሄድ አገኘሁት። ሲያየኝ ቆፍጠን ብሎ፣ ‹‹እኔ ካንተ ይኼን አልጠብቅም፡፡ ቀጥረኸኝ መልሼ ስደውል ስልክህን ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ታስብላለህ?›› ብሎ ወቀሰኝ። አቤት? ስንት ፈጣጣ አለ እባካችሁ! እንዲያው ልክ ልኩን ነግሬው ዛሬ ወጥቶልኝ ስል ደግሞ ቀድሞኝ፣ ‹‹ይልቅ በጣም ስፈልግህ ደረስክ። በቅርቡ ቀለበት አስራለሁ። ቀለል ያለ ምሳ ነገር ይኖራል። እንዳትቀር አደራ! የፈለግኩህ ከሁለት ሳምንት በኋላ የምመልስልህ አንድ 50 ሺሕ ብር እንድታበድረኝ ነው፤›› ብሎኝ አረፈው። ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ! ፍርድ ቤት የቀረቡ ባለ ቢሊየነርና ሚሊየነር ተጠርጣሪዎች ምንም የለንም ብለው መንግሥት ጠበቃ ያቁምልን እያሉ ምለው ሲገዘቱ፣ ይኼ ደግሞ ዓይኑን በጥሬ ጨው አጥቦ ፍጥጥ ይልልኛል፡፡ ወይ ነዶ አለ የአገራችን ሰው! እንዴት አይል? ይህንን ሁሉ ጭካኔ እየሰማና እያየ!

በሉ እንሰነባበት። ለሽምግልና የሄድኩት ሰውዬ በሽማግሌ ተገላግዬ የሌለብኝን ሙልጭ አድርጌ ተሳድቤ ተለያየሁ። ያለችኝን ቆጥሬ ከባንክ ትንሽ አውጥቼ ለወር የሚሆናትን እንድታደርግበት ልሰጥ ወደ ውዲቷ ማንጠግቦሽ ገሰገስኩ። ለወትሮው ምንም ብሰጣት የምታምነኝ ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ዓይኔ እያየ፣ ሁለት ኩባያ ውኃ ጠጥታ እስክትጨርስ ምራቋን ‘ቱቱ’ እያለች ደጋግማ ገንዘቡን ስትቆጥር አየሁ። ሕልም ውስጥ ያለሁ መሰለኝ። ለአንድም ቀን ተጠራጥራኝና ፈትሻኝ የማታውቀዋ ባለቤቴ የሰጠኋትን ገንዘብ አገላብጣ ስትመነጥር ሳያት ከየት እንደ መጣ አላውቅም ይሁዳን የማይ መሰለኝ። ቆጥራ ስትጨርስ ከመቀመጫዋ ተነስታ ጉንጬን ስትስመኝ፣ ከአሁን አሁን ጠፍንገው የሚይዙኝ ወረበሎች ቤቴን ደርምሰው የሚገቡ መስሎኝ በፍርኃት ተርበደበድኩ። “ምነው?” ስትለኝ ሁኔታዬን ታዝባ እኔ ድንጋጤዬ ሳይለቀኝ፣ “ምንም!” እላለሁ። የቁም ቅዠት ጨረሰን እኮ እናንተ! ይህ ሁሉ እየተሰማ ባንቃዥ ነበር የሚገርመው!

      ማንጠግቦሽ ወደ ገበያ ስትሮጥ እኔ ወደ ባሻዬ ቤት ተጣደፍኩ። በእርጋታ ከልጃቸው ጋር እየተጫወቱ የነበሩት ባሻዬ ትኩር ብለው ሲያጤኑኝ ቆዩና “ምን ሆነሃል?” አሉኝ። ‹‹ባሻዬ ይሁዳን አየሁት መሰለኝ?›› አልኳቸው። እንደ መሳቅም እንደ መገረምም ብለው የት እንዳየሁት ሲጠይቁኝ ሁሉንም ተረኩላቸው። ‹‹ዘመኑን ነዋ ያየኸው! ዘመኑን ነው! በይሁዳ ተመስሎ ያየኸው ዘመኑን ነው! ያቺ ሰላሳ ዲናር ምንዛሪዋ እያደር ጨምሮ ይኼው ምድረ ጨካኝና ዘራፊ ለገንዘብ የማይሆነውን እየሆነ፣ ሰብዓዊ ክብሩን አዋርዶና በሕዝብ ላይ አላግጦ ሲኖር አንዳች ፀፀት የሚሰማው አይመስልም። ይሁዳን ሳይሆን ያየኸው የይሁዳን መንፈስ፣ ክፋትና ስግብግብነት የፀነሰውን የፈረሰ እምነት፣ የቀዘቀዘ ፍቅርና የጣረ ሞት መንፈስ ነው። እሱን አይተህ ነው. . . ›› አሉኝ። ‹‹የዘመን ትንሳዔ የለውም ነው የሚሉኝ ባሻዬ?›› ብዬ ብጠይቃቸው፣ ‹‹እሱን የላይኛው ጌታ ብቻ ነው የሚያውቀው፤›› ብለው ዝም አሉ። በዝምታችን ውስጥ የፊቱ ወደ ኋላ የኋላው ወደ ፊት ያልተገለበጠበት፣ የግራው ወደ ቀኝ የቀኙ ወደ ግራ ያልተቀያየረበት ዘመን መጠማታችን ታውቆናል። የዘመን ትንሳዔ ናፍቆትና ጥማት አቁነጠነጠኝ። እንዲያው ወገኖቼ ስንቱ ነገር ነው የሚያንገበግበን? ስንቱስ ነገር ነው እህህ የሚያሰኘን? እሱ ይሁነን ብቻ! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት