ለአፍሪካውያን አዛውንቶች አካል ጉዳተኛ መሆን ቀዳሚ ምክንያቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸውን መቀመጫውን ኬንያ ናይሮቢ ያደረገው ኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ በየዓመቱ ታኅሣሥ 3 የሚከበረውን ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ቀን አስመልክቶ እንዳስታወቀው፣ ዕድሜያቸው ከ60 በላይ የሆኑ አፍሪካውያን በአብዛኛው አካል ጉዳተኛ የሚሆኑት ተላላፊ ባልሆኑ በሸታዎች ምክንያት ነው፡፡
ግሎባል ኤጅዎች ኢንሳይት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሠራው ጥናት እንደሚያሳየው፤ ካንሰር፣ ስኳር፣ የልብ ሕመም፣ ስትሮክና ሌሎችም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በሕይወት ዘመን ሊገጥም ለሚችለው አካል ጉዳተኝነት ዋነኛ ምክንያት ሆነው ተገኝተዋል፡፡
የኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ሪጅናል ዳይሬክተር ዶ/ር ፓራፉላ ማሽራ እንዳሉት፤ በአፍሪካ የአብዛኞቹ አገሮች የጤና ሽፋንና ተደራሽነት ከ50 ዓመት በላይ ያሉ ሰዎችን የዘነጋ ነው፡፡
አዛውንቶች የጤና ሽፋን የማግኘት መብት ላይ ትኩረት አድርጎ በ12 አገሮች የሚገኙ አዛውንቶችን የጤና ሽፋን የዳሰሰው ጥናቱ፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በ2015 በዚምባቡዌ ከተከሰተው ሞት አንድ ሦስተኛ ያህሉን ይዟል፡፡ ከ50 እስከ 69 ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወንዶች ግማሽ ያህሉ፤ ከ70 በላይ ከሚገኙት ደግሞ አንድ ሦስተኛው፤ ከ50 እስከ 69 የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ሴቶች አንድ ሦስተኛ ያህሉ እንዲሁም ከ70 በላይ ካሉት ደግሞ ሦስት አራተኛው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሞተዋል፡፡
በኬንያም ተመሳሳይ የጥናት ውጤት የታየ ሲሆን በአገሪቱ አካል ጉዳተኛ ሆነው ከሚኖሩ ሰዎች 75 በመቶ ያህሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች አማካይነት ለችግሩ መጋለጠቸው ታውቋል፡፡
በ2018 ከ60 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ቁጥር አንድ ቢሊዮን ማለፉን ያስታወሰው ድርጅቱ፤ ለእነዚህ አዛውንቶች ያለው የጤና ሽፋን ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብሏል፡፡
እንደ ጥናቱ በዓለም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት 41 ሚሊዮን ሰዎች ይሞታሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 32 ሚሊዮኑ ሞት ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ነው፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ አገሮች በመረጃ አሰባሰብ እንኳን አዛውንቶችን አያሳትፉም፡፡
እንደ ድርጅቱ በአፍሪካ በዓለም አቀፉን የጤና ድርጅት ዳሰሳ ጥናት ከተካተቱ 40 አገሮች 34ቱ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ ከ64 ዓመት በላይ ያሉ ሰዎችን አላካተቱም፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ታስቦ የዋለውን ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ቀን አስመልክቶ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ፣ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ከአገሪቱ የጤና የፖሊሲ መርሆዎች አንዱ መሆኑን አስታውሷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አሸናፊ ቤዛ እንዳሉት፣ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት መረጋገጥ የሚችለው በየትኛውም ቦታና የሀብት ደረጃ ላይ ያለ ሰው የገንዘብ ዕጦት እክል ሳይሆንበት ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ማግኘት ሲችል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይኼንን ለማሳካት በሽታን በመከላከል ላይ ያተኮረውን የጤና ፖሊሲ በመተግበርና የተለያዩ የጤና ልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ አክለዋል፡፡