በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት ተግባራዊ የአገር በቀል ጥበብ ላይ የሚያተኩረው የደራሲ ውብሸት ጌታሁን (ኮሎላ ደ) ‹‹ኮቱ – ዱፌ›› በሚል ርዕስ ያዘጋጁት መጽሐፍ ለምርቃትና ለውይይት ሊበቃ ነው፡፡ ደራሲው በመግቢያው ላይ እንዳሠፈሩት፣ ‹‹በቀደምት አባቶች ተጀምሮ ዘመናትን ያስቆጠረው ወርቃማ የአስተዳደር፣ የግጭት አፈታትና የማኅበራዊ ተግባቦት ባህል በሰነድ መልክ ለማስተላለፍ እንዲቻል ‹ኮቱ – ዱፌ› በመጽሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ከምክንያቶቹ አንዱ የሆነው የመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ባህል በአገር ደረጃ እንዲዳብር እገዛ ለማድረግ ነው፡፡››
የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ መጽሐፉ ታኅሣሥ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በ10 ሰዓት በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ይመረቃል፡፡
መሰንበቻውን የኅትመት ብርሃን ያየውና በኦሮሞ አገር በቀል ዕውቀት ላይ የሚያጠነጥነው መጽሐፍ ስያሜው፣ ‹‹ኮቱ – ዱፌ›› ትርጉም ኮቱ የሚለው በአፋን ኦሮሞ ቀጥተኛ የቃል ትርጉም ና እንደ ማለት ሲሆን፣ ዱፌ የሚለው ደግሞ መጣሁ እንደማለት ነው፡፡ ይሁንም እንጂ በዚህ መጽሐፉ አገባብ በቀረበበት ሁኔታ ግን ኮቱ – ዱፌ ማለት ‹‹ስማ–ሰማሁ›› የሚለውን የመጠራራት በሐሳብ የመቀራረብ፣ የመጠያየቅ፣ የመወያየትና የመመካከር ጥልቅ የመግባባት ትርጉም እንደሚይዝ ደራሲው ገልጸዋል፡፡
ኮቱ ዱፌ በስድስት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን እነሱም የአገር በቀል ዕውቀት ሥርዓት ማብራሪያዎች፣ የአባ ገዳ ሥርዓት መዋቅርና አሠራር ማሳያ፣ የገዳ ሥርዓትና ሕግጋት፣ የኮቱ ዱፌ (ስማ–ሰማሁ) ተሳትፎ መስፈርቶች፣ በምርመራ ለመታየት የሚበቁ የኮቱ ዱፌ ሥርዓት የግጭት ደረጃዎች ናቸው፡፡ አባሪዎችና ተጨማሪ መረጃዎች በመጨረሻው ክፍል ተካትተዋል፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ 91 ብር ነው፡፡