Monday, April 15, 2024

ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ክስተት የሆነው የክልል መንግሥታት የቃላት ጦርነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በትጥቅና በኃይል የሚከናወን የፖለቲካ ሥልጣን ግድድር የተለመደ ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ገጾች ያዘሏቸው ሀቆችና የዚህ ውጤትም እስከ ዛሬ ድረስ ዘልቆ በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አዝማችነት በሕዝቦች መካከል የቁርሾ ምንጭ መሆኑ አያጠያይቅም።

የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ሥልጣን የያዘው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ፌዴራላዊ ሥርዓትን በመመሥረት፣ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት በማወጅ የፈነጠቀው ዴሞክራሲያዊ መንገድ አገሪቱን ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ይዞ መጓዝ ቢችልም፣ የጉዞው ስኬት ሚስጥር የተከለው ዴሞክራሲያዊ ባህል ሳይሆን ያሰፈነው ፖለቲካዊ አፈናና ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ልሂቃን ያስረዳሉ።

 የፖለቲካዊ ስኬቱ ምክንያት በልማት ላይ በማተኮር ያስመዘገበው የኢኮኖሚ ውጤት እንደሆነ የሚገልጸው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ፖለቲካዊ አፈና፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የሙስና ልኩን ማለፍ የሚመራውን ሕዝብ ቁጣ አስገንፍሎ አሁን ወደ ደረሰበት የፖለቲካ ምዕራፍ እንዳሸጋገሩት በይፋ ያምናል።

ገዥው ፓርቲ አሁንም ሥልጣን ላይ ቢሆንም በተለየ ገጽታ ነው። በኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን ውስጣዊ ትግል አሸንፈው በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን የመጡት የግንባሩ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ ተቀባይነትን በአገር ውስጥ፣ እንዲሁም ከኃያላኖቹ ምዕራባውያን እስከ መካከለኞቹ የውጭ መንግሥታትና የጎረቤት አገሮች ጭምር ማትረፍ ችለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊ የሆነ የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ በመጀመር በከፍተኛ ሙስና የተጠረጠሩ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከፍተኛ አመራሮችን በሕግ ቁጥጥር ሥር ማድረጋቸው፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በዜጎች ላይ ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ የአገሪቱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት አመራሮች በቁጥጥር ሥር ውለው በሕግ እንዲጠየቁ ማድረጋቸው ከፍተኛ አድናቆትን ያገኙበት ሰሞነኛ መነጋገሪያ ጉዳይ ቢሆንም፣ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው የሚል ትችት የሚያቀርቡባቸው አሉ ይገኛል።

ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ክስተት የሆነው የክልል መንግሥታት የቃላት ጦርነት

 

ወደ ሥልጣን ከመጡ ገና ዘጠነኛ ወራቸው መጀመርያ ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ካገኙት ሰፊ ተቀባይነት በተቃራኒ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው በገሀድ የሚታይ ከመሆኑ ባሻገር፣ በአገሪቱ በበርካታ አካባቢዎች ብሔር ተኮር ችግሮች መቆም አለመቻላቸው ከፍተኛ የሥጋት ምንጭ ሆኗል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ አካባቢዎች በቅርቡ በግልጽ ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችና የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ አባላት መገደላቸውን ተከትሎ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ አባላት ስብሰባ በፓርቲው ሊቀመንበር ዓብይ አህመድ ተካሄዶ የጥቃቱን መንስዔ የሚገልጽ የአቋም መግለጫ ይፋ አድርጓል።

የመግለጫው ይዘት በተለያዩ የኦሮሚያ አካቢቢዎች ኦሮሞዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መከፈቱ ምክንያት እንዳለው፣ ይኸውም ለበርካታ ዓመታት በዝርፊያና በሰብዓዊ መብት ረገጣ ላይ ተሰማርተው የነበሩትን ወደ ሕግ ማቅረብ መጀመሩና አገሪቱ የጀመረችውን የለውጥና የነፃነት ጉዞ ለማደናቀፍ በሕግ መጠየቃቸው እንደማይቀር የተገነዘቡ በእጅ አዙር የጀመሩት የተደራጀ ሴራ መሆኑን ይገልጻል።

 ‹‹የዚህ የተደራጀ ወንጀል ዓላማም በጥቅሉ ሲታይ የኦሮሞ ልጆችን ደም በማፍሰስ ኦሮሚያን የጦር አውድማ በማድረግ አንድነታችንን በማፍረስ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር አድርገው የሕዝብን ሀብት ለመዝረፍ፣ እንዲሁም ሕዝቡ ወደ ነፃነት የሚያደርገው ጉዞ እንዲደናቀፍ በማድረግ ለሌብነት፣ ለዝርፊያና ለባርነት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፤›› ሲል መግለጫው አትቷል።

የኦሮሞ ሕዝብ ይኼንን ሴራ ተገንዝቦ ቀዳዳ ባለመክፈት ከክልሉ መንግሥት ጋር በመቆም ብልህ መሆን እንዳለበት መክሯል፡፡

 ‹‹ምንም ያህል ችግር ውስጥ ብንሆንና በተለያየ መንገድ ቀዳዳ በመክፈት ጥቃት እየፈጸሙ ሊያዘናጉን ቢሞክሩም፣ የሕዝቡን ፍላጎትና ጥቅም ለማረጋገጥ ለመስዋዕትነት የተዘጋጀን በመሆኑ ለአፍታም አንዘናጋም፤›› የሚለው የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ‹‹በሕዝባችን ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አካላትንም የገቡበት ጉድጓድ በመግባት ለሕግ በማቅረብ ተመልሰው ጉዳት ማድረስ እንዳይችሉ እንሰብራቸዋለን፤›› በማለት አቋሙን ገልጿል።

ይህ መግለጫ የፀጥታ ችግሮችን እየፈጠሩ የሚገኙት ኃይሎችን ማንነት ባይገልጽ፣ ሙስናና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ መንግሥት መውሰድ የጀመረው የሕግ ተጠያቂነትን የማስፈን ዕርምጃ፣ በሕወሓት አመራሮችና በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ በማኅበረሰቡ ውስጥ ግንዛቤን (Perception) ፈጥሯል።

ከሰሞኑ በአማራ ክልል በጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ግጭት በርካታ ሰዎች መሞታቸው፣ ይህም በአካባቢው አለመረጋጋትን መፍጠሩ ይታወቃል።

ይኼንን ተከትሎ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በዚህ ሳምንት ውይይት ያደረጉት የአማራ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴል ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጀርባ የሕወሓት እጅ መኖሩን በግልጽ ተናግረዋል።

ሴራው የአማራን ሕዝብ መበጥበጥና ትግሉን ማጨናገፍ መሆኑን የክልሉ ማኅበረሰብ ተገንዝቦ አንድ ላይ እንዲቆም የጠየቁት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው፣ የክልሉን ፀጥታ ለመጠበቅ ከመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች በተጨማሪ በተለያዩ የክልሉ ወሰኖች የሚገኙ አርሶ አደሮችንና ወጣቶችን የክልሉ መንግሥት በማሠልጠን ላይ እንደሚገኝ በይፋ ተናግረዋል።

በአገሪቱ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን በማቀነባበር እየተወገዘ የሚገኘው ሕወሓትና የትግራይ ክልል መንግሥት አፀፋዊ መልስ በመስጠት የቃላት ጦርነቱን ተቀላቅለዋል። ቅዳሜ ኅዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ክብረ በዓልን አስታኮ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሕወሓት ሊቀመንበርና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ‹‹ታጋይና ኩሩ የሆነው የትግራይ ሕዝብ ትናንት በትግል ያሸነፋቸውና ተስፈኛ ኃይሎች የውሸት ታሪኮችና ስም የማጥፋት ዘመቻ እያካሄዱ ነው፤›› በማለት፣ የተጀመረው ዘመቻ በትግራይ ሕዝብ ላይ የኢኮኖሚና ሌሎች ጫናዎችን በመፍጠር ማንበርከክን ዓላማው እንዳደረገ ተናግረዋል።

‹‹በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚተጉ አካላት የሁሉም ችግሮች ምክንያትን ከትግራይ ተወላጆችና ከድርጅቱ ሕወሓት ጋር ማስተሳሰር ቀላል ሆኖ አግኝተውታል፤›› ብለዋል። የትግራይ ሕዝብ ከዛሬ ነገ የአገሪቷ ሁኔታ ይሻሻላል፣ ይለወጥም ይሆናል በማለት በተሰፋ ላይ ተስፋ ሰንቆ መቆየቱን የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የትግራይ ሕዝብና የመንግሥት ፍላጎት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲከበርና ሕጋዊ ሥርዓት በመላ አገሪቱ እንዲሰፍን ቢሆንም፣ በቁጥርና በዓይነት የሕገ መንግሥት ጥሰት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹የትግራይ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱ ሳይሸራርፍ እንዲከበር እንደ ሕዝብ አንድ ሆኖ መሠለፍ ብቻም ሳይሆን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲነግሥና የአገራችን የለውጥ ሒደት በትክክለኛው መስመር እንዲጓዝ የብሔር ብሔረሰቦችና መላ ሕዝቦች መብትና ጥቅም እንዲከበርም፣ ከመላው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ለመታገል ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ ይፈልጋል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን ያለው ይህ የዕብደት አካሄድ›› ነው ያሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ውጤቱም ለአንድ ወገን ብቻም ሳይሆን፣ ሁሉም ላይ ጉዳት የሚያደርስና የሚያጠፋ አስተሳሰብ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት ሥልጣን ለመያዝና ለማደላደል የተሰማሩትን አካላት ሰላምና ልማት ፈላጊው ሕዝብ ሥርዓት ሊያስይዛቸው ይገባል፡፡ ለዚህም ቀጣይነት ያለው ትግል ካልተደረገ፣ ተያይዘን እንድንጠፋ የሚቋምጡ ኃይሎች ትልቅ አደጋ እንደሚያደርሱ አውቀን፣ ሁላችንም እንድንመክታቸውና በደል የፈጸሙትንም በሕግ እንዲጠየቁና ሥርዓት እንዲይዙ ለማድረግ መታገል አለብን፤›› ሲሉ ብለዋል፡፡

አሁን መፍትሔው ምንድን ነው? በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የተለየ ክስተት ሆኖ የመጣው ይህ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ የክልል መንግሥታት የቃላት ጦርነት ብሔር ተኮር መሆኑ፣ በግልጽም ማኅበረሰቡን በተለይም ወጣቶችን እያሳተፈ መገኘቱ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የደኅንነትና የግጭት አፈታት ባለሙያ ያስረዳሉ።

ቅራኔ ውስጥ የገቡት የፖለቲካ አመራሮች ከሚያደርጉት የቃላት ጦርነት አልፈው ማኅበረሰቦቻቸውን በግልጽ ለትግል እየቀሰቀሱ መሆናቸው ደግሞ ሥጋቱን ከፍተኛ እንደሚያደርገው፣ ተቃርኖ ውስጥ የገቡት ፖለቲካኞች በቅራኔዎቻቸው ዙሪያ ወደ መመቻመች (Compromise) እንዳይመጡ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል፣ ወደዚህ መስመር ቢገቡ እንኳን ለትግል እያነሳሱ የሚገኙት ማኅበረሰብ ክህደት እንደተፈጸመበት የመቁጠር ስሜት ሊፈጠርበት እንደሚችል፣ ይህም ማኅበረሰቡን በፖለቲካዊ ማግባባት ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ሥጋታቸውን ይገልጻሉ።

ቅራኔ ውስጥ የገቡት ፖለቲከኞች ከያዙት መንገድ ወጥተው በመፍትሔው ላይ መሥራትና በአገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ ወደ መፍጠር ፊታቸውን መመለስ እንደሚገባቸውና ይህም ኃላፊነታቸው መሆኑን የሚያስረዱት እኚሁ ባለሙያ፣ በሕወሓት በኩል ከቁጥጥሩ ውጭ ሆነው ግጭቶችን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንዲሠራጭ (Violence Export) የሚያደርጉ ኃይሎችን በመለየት ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚገባ ያሳስባሉ።

ሕወሓት ለዚህ ቁርጠኝነቱን በተግባር ካሳየ በፌዴራል ሥልጣን ላይ የሚገኘው የፖለቲካ ኃይል፣ በገዥው ፓርቲ የመስመር ልዩነቶችን በማመቻመች ለመፍታት ወደሚያስችል ፖለቲካዊ ውይይት ለመግባት መንቀሳቀስ እንደሚገባ ይመክራሉ።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል በበኩላቸው፣ መፍትሔው በኢሕአዴግ የተወሰኑ ውሳኔዎችን ማስፈጸም መሆኑን ይናገራሉ።

በዚህ ውሳኔ መሠረት ሁሉም የፖለቲካ ኃይል ኃላፊነቱን መወጣት እንጂ፣ ፖለቲካዊ ማመቻመች መፍትሔ ሊሆን እንደማይችልና ይህም የሕወሓት አቋም እንደሆነ ይናገራሉ። በኢሕአዴግ መድረክ በተደረገው ውይይት የተደረሰው ስምምነት ኢሕአዴግ ብዙ ያጠፋቸው ነገሮች እንዳሉ፣ ይህንን አምኖና ንፁህ ሆኖ ሕዝብን በሀቅ ለማገልገል መሆኑን የገለጹት የሕወሓት አመራር፣ ‹‹ሁላችንም በገባነው ቃል መሠረት ካገለገልን ማመቻመች (Compromise) አያስፈልግም፣ ብዥታ ካለ ይህንን ለመቅረፍ የኢሕአዴግን መድረክ መጠቀም ይቻላል፤›› ብለዋል።

በኢሕአዴግ መድረክ ችግሮችን መፍታት ካልተቻለ ኢሕአዴግ ሊፈርስ እንደሚችል፣ ነገር ግን አገር እንዲፈርስ መፈቀድ የለበትም ሲሉ ይሞግታሉ።

 አሁን እየተካሄደበት ያለው መንገድ ከኢሕአዴግ ውሳኔ የሚቃረን ስለመሆኑ ሲያስረዱም፣ ኢሕአዴግ ለፈጸማቸው ጥፋቶች በደል ፈጻሚውን ቀይሮ ለመምታት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ይህ አገር ያፈርሳል እንጂ ኢሕአዴግን ንፁህ እንደማያደርገው ገልጸዋል።

‹‹አንድ ሠፈር የሀቅ ሞኖፖሊ አለ፣ የተጠያቂነት ሞኖፖሊ ደግሞ ሌላ ሠፈር አለ ብሎ መንገድ መጀመር አገር አያድንም፤›› የሚሉት እኚህ የሕወሓት አመራር፣ መፍትሔው በኢሕአዴግ ውሳኔ መሠረት መንቀሳቀስና ካስፈለገም የኢሕአዴግን መድረክ መጠቀም ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የወቅቱን ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ መምህር፣ ሁሉም ተገዳዳሪ ወገኖች በንፁህ ኅሊና አገርንና ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ይላሉ፡፡ የሕግ የበላይነት ተጥሶ ዜጎች የሥቃይ ሰለባ ሲደረጉና በገደብ የለሽ ሥልጣን የአገር ሀብት መዘረፉ ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ሆኖ ሳለ፣ እንደተለመደው በማድበስበስ ለማለፍ መሞከር ተቃርኖ ይፈጥራል ብለዋል፡፡ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚወስደው ዕርምጃ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ መሆን እንደሚገባው፣ ተጠያቂነት ያለባቸው ወገኖች ደግሞ ከፍርድ በፊት ንፁህ ሆነው በመታሰብ መብታቸው ተከብሮ ፍትሕ ፊት መቅረብ ይኖርባቸዋል ሲሉ አክለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ውጪ ተጠያቂነትን ከሕዝብ ጋር እያያያዙ ያልተፈለገ ምሥል መፍጠር፣ የበቀልተኝነት ስሜት ይዞ አተካራ መፍጠርና አገርን ሌላ ዙር ችግር ውስጥ መክተት ውጤቱ አደገኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -