ተሸላሚዋ ፎቶ አንሺ ዓይዳ ሙሉነህ በኢትዮጵያ ተወልዳ በልጅነቷ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ የመን አቅንታለች፡፡ ከዚያም ወደ እንግሊዝ፣ ቆጵሮስ፣ ካናዳና አሜሪካ ዘልቃለች፡፡ በዋሽንግተን ፖስት ፎቶ ጋዜጠኛ ሆና ከሠራችና ከሦስት አሠርታት ግድም ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ በመመለስ በዋነኛነት በፎቶግራፍ ዘርፍ የሚንቀሳቀስ ደስታ ፎር አፍሪካ የሚባል ድርጅት አቋቁማለች፡፡ ዓላማውም አገር ውስጥ ያልበለፀገውን የፎቶ ግራፍ ተግባርን ለማሳደግ ነው፡፡
ከስምንት ዓመት በፊት ዓይዳ በየሁለት ዓመቱ የሚከናወን ‹‹አዲስ ፎቶ ፌስት›› የተሰኘ ክብረ በዓልን ማዘጋጀት ጀምራለች፡፡ ይህም በዓይነቱ በአዲስ አበባም ሆነ በአኅጉሪቱ ታላቅ መድረክ መሆኑ የተነገረለት ዝግጅት ከኅዳር 27 ቀን እስከ ታኅሣሥ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. አስተናግዷል፡፡ ከ61 አገሮች 152 ፎቶ አንሺዎች ሲሳተፉበት ዋና ግቡ የአፍሪካን ፎቶግራፍ ለማሳደግ ነው፡፡
በፌስታው መክፈቻ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን የጠቆመችው ዓይዳ፣ ‹‹አፍሪካውያን ፎቶ አንሺዎች ዓለም አቀፉን ገበያ እንዲቀላቀሉ እየጣርሁ ነው፤ ይህም መድረክ ግንኙነትን ለመፍጠር ያግዛል፤›› ብላለች፡፡
አፍሪካውያን የራሳቸውን ምስሎች ራሳቸው በማንሳት ለዓለም ማስተዋወቅ ይገባቸዋል እንጂ በምዕራቡ ዓለም ሚዲያ መተማመኑ መቀጠል የለበትም የሚል ዕይታም አላት፡፡
‹‹ፎቶግራፍ በኢትዮጵያ›› በሚል በተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ 34 ኢትዮጵያውያን ፎቶ አንሺዎች ተሳትፈውበታል፡፡ የአዲስ ፎቶ ፌስት አካል በሆነው ዓውደ ጥናትም ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከአኅጉሪቱ 20 ፎቶ አንሺዎች በሥራዎቻቸው ዙሪያ ከፍተኛ ልምድ ካላቸው አምስት ፎቶ አንሺዎች ሒስ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዓውደ ርዕዩ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡት ኢትዮጵያውያን መካከል የታረቀኝ ተስፋዬ ‹‹ይታይሽ››፣ የመክብብ ታደሰ ‹‹ትውስታ›› የሙሉጌታ አየነ ‹‹ኢትዮጵያን ስፕሪንግ›› [የኢትዮጵያ መፀው] የናዴር አደምን ጨምሮ ከቤተሰብ እስከ አገራዊ ባህልና ፖለቲካ የተንፀባረቀባቸው ፎቶዎች ታይተዋል፡፡