Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተግባር ለመከላከል የሚረዳ ጥናት መዘጋጀቱ ተገለጸ

የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተግባር ለመከላከል የሚረዳ ጥናት መዘጋጀቱ ተገለጸ

ቀን:

ግጭት ከደረሰና የዜጎች ሰብዓዊ መብት ከተጣሰ በኋላ ለመከላከል መሯሯጥ ከንቱ ልፋት መሆኑን በመገንዘብ፣ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ከጅምሩ መከላከል የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ሊገባ መሆኑ የተገለጸው፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ 70ኛ ዓመት አከባበርን በሚመለከት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰኞ ታኅሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. (ዲሴምበር 10 ቀን 2018) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ለግማሽ ቀን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

ጥናቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩ የተገለጸ ሲሆን፣ ዝርዝሩ በዚያ በኩል እንደሚገለጽ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1948 የፀደቀውንና 70ኛ ዓመቱን እያከበረ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ከአፍሪካ አገሮች በቀደምትነት የፈረመችና ያፀደቀች አገር ነች፡፡ ነገር ግን ሕጉን ከማፅደቅና ዓመታትን ከማስቆጠር ባለፈ ወደ ትግበራ ተቀይሮ የድንጋጌውን ዓላማ ከመፈጸም አኳያ፣ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

በ70 ዓመታት ውስጥ አፍሪካን ጨምሮ በዓለም ላይ ዘግናኝ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መታየታቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ ስደትና ጥቃት ለማንም እንደማይጠቅም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገንዝቦ፣ ለሰላም መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያም እየታየ ያለው ነገር አበረታችና ሁሉም በትብብር ሊደግፈውና ሊያሻሽለው ስለሚገባ ተባብሮ መሥራትና ውጤቱን ማየት እንጂ፣ ለአንድ ተቋም ብቻ በመተው የሚስተካከል እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ ያ ሲሆን ግን የሰብዓዊ መብትም ሊከበር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

‹‹ዜጎች ሰላም በጣም ናፍቋቸዋል፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ ሁሉም የኅብረተሰብ አካል ሲተባበር የሚረጋገጥ በመሆኑ፣ ሚዲያም ሆነ ማንኛውም ባለድርሻ አካል ኃላፊነት ወስዶ ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ መንግሥት የዜጎችን መብት ማክበርና ማስከበር ቀዳሚ ተልዕኮው አድርጎ መውሰድ እንዳበት ጠቁመው፣ አሁን በዚህ ዙሪያ እየሠራ ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ በአገራችን የምናየው ግጭት ሄዶ ሄዶ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለሚሆን፣ አስቀድሞ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት በጥናት አረጋግጠው መስጠታቸውን (ማሳወቃቸውን) ተናግረዋል፡፡

በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ግጭትን አስቀድሞ መከላከል እንጂ ከተፈጠረ በኋላ የሚደረገው መሯሯጥ እሳት የማጥፋት ሥራ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ይኼ ደግሞ ሄዶ ሄዶ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የሚያመጣው ውጤት የከፋ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ቀደም ባሉ ዓመታት በአገሪቱ የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ጥናት ሠርተው ለፓርላማ ማሳወቃቸውን አስታውሰው፣ አሁን ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአገሪቱ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ተገኙ ስለተባሉ ድብቅ እስር ቤቶች ተጠይቀው ምንም እንደማያውቁም ተናግረዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስወገድና ለመከላከል የፍትሕ ተቋማት ሪፎርም ሥራ መጀመሩንና ፍርድ ቤቶች ነፃ ሆነው የሚሠሩበት ሥርዓትን ለመዘርጋት እየተሠራ መሆኑን፣ በውይይቱ ላይ የተገኙትና ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታዩ ዘመናዊ የሕግ ድንጋጌዎች በተግባር እንዲሠራባቸው የማድረጊያው ጊዜ አሁን መሆኑን በመጠቆም፣ በኬንያ ተሞክሮ ውጤት ያስገኘውን ማኅበረሰባዊ የፍትሕ ሥርዓት (Community Justice System) ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ፕሮፌሰር ዘካርያስ ቀነዓ ናቸው፡፡

በውይይቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢያዊ ቢሮ ተወካይ ሚስ ንዋኔ ቭወዴ አባሆርና ሌሎችም በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...