Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሁለት የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሹማምንት ፍርድ ቤት ቀረቡ

ሁለት የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሹማምንት ፍርድ ቤት ቀረቡ

ቀን:

የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ የተባሉና በቱርክ ኢስታምቡል ለሥራ ተመድበው በመጠባበቅ ላይ የነበሩት አቶ መአሾ ኪዳኔ፣ በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ ሌላው ተጠርጣሪ አቶ ሀዱሽ ካሳም አብረዋቸው ቀርበዋል፡፡

አቶ መአሾ በተጠረጠሩበት ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ቅዳሜ ኅዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤታቸው መሆኑን ጠቅሶ፣ የፌዴራል  ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ሰኞ ታኅሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሥረኛ ወንጀል ችሎት አቅርቧቸዋል፡፡

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ የተባሉት አቶ መአሾ፣ በወቅቱ በፓርላማ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩት የኦነግና የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ናቸው ተብለው በሐሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ፣ ለበታች ሠራተኞች ትዕዛዝ መስጠታቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ በሐሰተኛ ማስረጃ በቁጥጥር ሥር የሚውሉትን ዜጎች ዓይናቸውን ሸፍኖ በማሰር በሥውርና በሕግ ባልፈቀደ ቦታ በማሰር ከቤተሰብ እንዲደበቁ ማድረጋቸውን፣ በመደብደብና በተለያዩ ማሰቃያ ነገሮች ከፍተኛ የሆነ ሥቃይ እንዳደረሱባቸውም መርማሪ ቡድኑ ተናግሯል፡፡

ተጠርጣሪው ከገቢያቸው በላይ ሦስት ቤቶች መገንባታቸውንና ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አከማችተውና ለባለቤታቸው ውክልና ሰጥተው በመገኘታቸው በሙስና ወንጀልም እንደጠረጠራቸው አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተመሳሳይ ቀን በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት ያቀረባቸው፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የኦፕሬሽን ክፍል ዳይሬክተር መሆናቸው የተገለጸው አቶ ሀዱሽ ካሳ ናቸው፡፡ መርማሪ ቡድኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዳው፣ እሳቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ የኦነግና የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባል ሳይሆኑ በሐሰት አባል መሆናቸው እየተገለጸ በቁጥጥር ሥር የዋሉ በርካታ ዜጎች በሥውር እስር ቤት እንዲታሰሩ፣ ከቤተሰብ በመደበቅ እንዳይገናኙ በማድረግ፣ ድብደባ በመፈጸም፣ የተለያዩ ማሰቃያ ዘዴዎችን በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸምባቸው ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪው ከገቢያቸው በላይ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማከማቸታቸውንም በመግለጽ፣ በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውንም አክሎ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡  

ተጠርጣሪዎቹ፣ ምንም እንኳን የሕግ ዕውቀት ባይኖራቸውም ለጊዜው በራሳቸው መልስ ሰጥተው፣ በቀጣይ ቀጠሮ የመንግሥት ሠራተኛና ደመወዝተኛ በመሆናችን መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ ያቆምልናል በማለት ለፍርድ ቤቱ ከገለጹ በኋላ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አቶ መአሾ እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገሪቱን መምራት ከጀመሩ ወዲህ፣ በቱርክ ኢስታምቡል ለሥራ ተመድበዋል፡፡ የዲፕሎማሲ ሥልጠናም ወስደው የሚሄዱበትን ቀን በቤታቸው ሆነው እየተጠባበቁ እያለ፣ ‹‹በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረሃል›› ተብለው መታሰራቸውን አስረድተዋል፡፡ በተቋሙ ውስጥ ረዥም ዓመታት የሠሩ ቢሆንም፣ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች እንጂ የልዩ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሳይሆኑ የሌላ ክፍል ዳይሬክተር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የተከሰስኩበትና በቁጥጥር ሥር እንድውል የተደረገበት ምክንያት ሁለት ነው፡፡ አንደኛው የትግራይ ተወላጅ መሆኔ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በፖለቲካ ውሳኔ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ውጪ እሳቸው ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው የሚሠሩ መሆናቸውንና በዚህም የምሥጋና ቅፅል ስም የተሰጣቸው ንፁህ ሠራተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አሳሪም፣ መርማሪም ሆነ ከዚህ ጋር የተገናኘ ሥራ ሠርተው እንደማያውቁና ዶሴ ተቀናብሮ የቀረበባቸው ክስ እንደማይመለከታቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እየተደረገብኝ ያለው ነገር ሞራሌንና ሰብዕናዬን ለመንካት እንጂ፣ እውነተኛ መጠርጠሪያ ድርጊት ሆኖና መቀጣጫ በማድረግ በመሆን ሌሎችን ዜጎች የሚቀርፅ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ የሥራ ባልደረቦቻቸው ቀደም ብሎ ሲያዙ እውነተኛ ተጠርጣሪ ቢሆኑ ኖሮ እሳቸውም ሊያዙ ይችሉ እንደነበር ጠቁመው፣ እንኳን ሰው ሊያስደበድቡና ሰብዓዊ የመብት ጥሰት እንዲፈጸም ሊያደርጉ ቀርቶ፣ ‹‹ሰደበኝ የሚል ካለ ይቅረብ፤›› በማለት ዕንባና ሳግ እየተናነቃቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያንና ሕዝቧን እንዳያገለግሉ የማግለል ሥራ እየተሠራባቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡ ንፁህና ታታሪ ሠራተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከቀድሞ የፌዴራል ፖሊስ ዳይሬክተር ጄኔራል ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) መሸለማቸውንና አሁን በቅርቡም የዲፕሎማሲ ሥልጠና ወስደው ቱርክ ኢስታምቡል መመደባቸውም፣ ጥሩና ብቁ ሠራተኛ መሆናቸውን የሚመሰክር እንጂ በዶሴ ተዘጋጅቶ እንደቀረበባቸው ያለ ሰብዕና እንደሌላቸው ምስክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ ችሎት ቀርቤ ይኼ ዶሴ ሲነበብልኝ አዝኛለሁ፡፡ እኔ ታጋይ ነኝ፡፡ ሁለት ሦስት ጊዜ ቆስያለሁ፡፡ ይኼንን የማደርግ አይለሁም፤›› በማለት ይህንን ያደረጉ አካላት በቂምና በቀል በእሳቸው ላይ ለመሥራት አስበው ያደረጉት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከገቢ በላይ ሀብት ስለማከማቸታቸው በሰጡት ምላሽ፣ በመሥሪያ ቤታቸው ተደራጅተው እየሠሩት ያለ 72 ካሬ ሜትር ጅምር መኖሪያ ቤት ብቻ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ይኼንንም ውክልና ለቤተሰቦቻቸው የሰጡት ለሥራ ወደ ውጭ (ቱርክ) በመመደባቸው እንጂ፣ በሐሰት እንደተቀነባበረባቸው ክስ አለመሆኑን አክለዋል፡፡ ‹‹እናውቀዋለን በፌስቡክ ገጽ ሳይቀር ዘመቻ ተከፍቶብናል፡፡ የተጻፈው ዶሴ ለምንም አይጠቅምም፡፡ የትም የምሸሽ አይደለሁም፡፡ ብጠራ የምቀርብ ነኝ፡፡ በመሆኑም ዋስትናዬ ይጠበቅልኝ፤›› በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

አቶ ሀዱሽ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ፣ በኢሚግሬሽን ሥራዎች በሞያሌና በተለያዩ ጠረፎች ተመድበው ሲሠሩ የኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ምንም ዓይነት ኃላፊነት የሌላቸውና ተራ ሠራተኛ እንደነበሩም አክለዋል፡፡ ወደ ኃላፊነት የመጡት ከሁለት ዓመት ወዲህ መሆኑን ጠቁመው፣ ይኼም የዋናው መሥሪያ ቤት የኦፕሬሽን ኃላፊነት ማለትም የፅዳት፣ የአትክልተኛና የትራንስፖርት ሥምሪት ኃላፊ ሆነው እየሠሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በሕይወታቸው ምንም ዓይነት ወንጀል ሠርተው እንደማያውቁ ተናግረው፣ የዚህ ዓይነት ወንጀል ከየት እንደመጣባቸው እንደማያውቁም ገልጸዋል፡፡ ማንም እንደሚያውቃቸውና የተባለው ሁሉ እንደማይመለከታቸው አክለዋል፡፡ ‹‹እየወረደብኝ ያለው ጥቃት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከባለቤታቸው ጋር የተፋቱ ቢሆንም ሁለት ልጆቻቸውን በጋራ እያሳደጉ መሆናቸውን፣ የልጆቻቸው እናት ዳቦና እንጀራ ጋግራ እየሸጠች ሕይወቷን እየመራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን መርማሪ ቡድን የእሷንና የእሳቸውን የባንክ ቡክና ለልጆች ትምህርት ቤት የሚከፈል አሥር ሺሕ ብር መውሰዱን በመገለጽ፣ እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል፡፡ ገንዘቡን የወሰዱት ቤታቸው በተበረበረበት ወቅት መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ከገቢ በላይ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት እንዳፈሩ የተገለጸው፣ አንድ ኮንዶሚኒየም ቤት ደርሷቸው መክፈል ስላቃታቸው ከማከራየታቸው ውጪ ሌላ ነገር እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡  

መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን ዋስትና ተቃውሞ ምክንያቱን አስረድቷል፡፡ አቶ መአሾ የታሰሩት ‹ትግሬ ስለሆኑ ወይም በፖለቲካ ውሳኔ› አለመሆኑ፣ ፖሊስ ሕግ ማስከበር እንጂ ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ አስረድቷል፡፡ ሕገ መንግሥቱንና የአገሪቱ ሕጎችን የጣሰ ድርጊት በመፈጸም ስለተጠረጠሩ እንጂ፣ እሳቸው ስላሉት ነገር የሚያውቀው ነገር እንደሌለም አክሏል፡፡

አቶ ሀዱሽ ከባለቤታቸው ጋር ለመፋታታቸው የተናገሩትን በሚመለከት፣ እንደተፋቱ በማስመሰል የማዘጋጃ ቤት ወረቀት ቢይዙም አብረው እየኖሩ መሆናቸውን እንዳረጋገጠ ገልጿል፡፡ ሥራም አብረው እየሠሩ መሆኑንም አክሏል፡፡ ሁሉንም ነገር በሰነድ እንደሚረጋግጥም ገልጿል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን በአዳር አስቅርቦ ካየ በኋላ፣ ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. የተጠርጣሪዎቹን መከራከሪያ ሐሳብ ውድቅ በማድረግ፣ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት ለተጨማሪ ምርመራ ፈቅዷል፡፡ ሀብት እንደሌላቸው በመግለጽ መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው የጠየቁትን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ፣ አቶ መአሾ በባንክ ከ400 ሺሕ ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ እንዳላቸውና አቶ ሀዱሽ በባንክ በባለቤታቸው ስም ካስቀመጡት 500 ሺሕ ብር ላይ ባለቤታቸው ሰሞኑን 50 ሺሕ ብር ብቻ አውጥተው፣ 450 ሺሕ ብር እንዳላቸው ማረጋገጡንና ከባንኮቹ ማረጋገጫ ሰነድ እንደሚያቀርብ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ ማረጋገጫውን ለታኅሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከሚያቀርብ ቃለ መሃላው እንዳይፈጸም ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ክርክሩን ለታኅሳስ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው ከጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙትና በእነ አቶ ጎሃ አጽብሐ የምርመራ መዝገብ ተካተው እየተመረመሩ የሚገኙ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር 33 ተጠርጣሪዎች ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ  የሠራውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በተሰጠው ጊዜ የ21 ተጎጂዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ድብቅ እስር ቤት መኖሩን መለየቱን፣ ተጠርጣሪዎችን በተጎጂዎች ለማስለየት ያደረገው ጥረት ተጠርጣሪዎቹ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካለት እንደቀረ አስረድቷል፡፡ ከሁሉም ተቋማት ተጠርጣሪዎቹን የሚመለከቱ ሰነዶችን በደብዳቤ መጠየቁን፣ በግፍ የተገደሉ ዜጎች የአስከሬን ምርመራ ሰነድ ከዳግማዊ ምኒልክና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች መጠየቁን፣ ተጠርጣሪዎቹ ሲጠቀሙበት የነበሩትን የተለያዩ የምርመራ መዛግብትን ከየተቋማቱ መጠየቁንና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የታሰሩ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩ የተረጋገጠባቸው የምርመራ ሰነዶችን መጠየቁን አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በቀጣይ በቅርብ የሚያገኛቸውንና ራሳቸው እየመጡ የምስክርነት ቃል የሚሰጡትን ተጎጂዎችና አካላቸው በመጉደሉ ወደ ተቋሙ መምጣት የማይችሉ፣ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ተጎጂዎችን የምስክርነት ቃል የሚቀበል የምርመራ ቡድን አቋቁሞ ሊልክ መሆኑን አስረድቷል፡፡

የሕክምና ማስረጃዎችን መሰብሰብ፣ በተጎጂዎች ንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለይቶ ማስገመት፣ በቂሊንጦ ማረፊያ ቤት ቃጠሎ ምክንያት ሸዋ ሮቢት ተወስደው በደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ጉዳት የደረሰባቸውን የምስክርነት ቃል መስማት እንደሚቀረው አስረድቶ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በተለይ አቶ ጎሃ አጽብሐ፣ አቶ አማኑኤል ኪሮስ፣ አቶ ደርበው ደምመላሽ፣ አቶ ተስፋዬ ገብረ ፃዲቅና ሸዊት በላይ በሰጡት ምላሽ፣ ደንበኞቻቸው በሥውር እስር ቤት እንዲታሰሩ በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ሰጥተዋል ተብለው መጠርጠራቸውን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ራሱ መርማሪ ቡድኑ በጥቅሉ ‹‹በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረዋል›› ከማለት ውጪ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ በምን ወንጀል እንደተጠረጠረ እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(1) ላይ እንደተደነገገው አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ፣ በምን እንደተጠረጠረ፣ በግልጽና በሚያውቀው ቋንቋ እንዲነገረው መደንገጉን አስረድተዋል፡፡ ደንበኞቻቸው ለ31 ቀናት የታሰሩ ቢሆንም፣ የተጠረጠሩበት ወንጀል እንዳልተነገራቸው አክለዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ባለፈው ቀጠሮ የማስረጃ ሰነዶችን ለመሰብሰብ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ እንደተፈቀደለት አስታውሰው፣ ከ14 ቀናት ቆይታ በኋላ በድጋሚ ሰነድ ለመሰብሰብ 14 ቀናት የሚጠይቅ ከሆነ፣ ሥራ አለመሥራቱን እንደሚያመለክት በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በአንድ ተቋም ውስጥ የሚሠሩ በመሆናቸው የሚፈለግባቸውን የሰነድ ማስረጃ በቀላሉ መሰብሰብ እንደሚችል ጠበቆቹ ተናግረው፣ ሆን ተብሎ በዋስ እንዳይወጡ የሚደረግ መሆኑንና ይኼም የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አሥራ አንደኛ ተጠርጣሪ በቅርቡ ባላቸው ሥነ ምግባር የተነሳ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል መምርያ ምክትል ዳይሬክተር ተደርገው መሾማቸውን ጠቁመው፣ በሥርዓቱ ለስብሰባ ተጠርተው ከመታሰራቸው ውጪ ምንም የሚውቁትና የሠሩት ወንጀል እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ መረጃ የመሰብሰብና ተንትነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር ለተቋቋመው ብሔራዊ ምክር ቤት የሚያቀርቡ ባለሙያ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በማን ላይ ምን ያህል የምስክር ቃል እንደተቀበለና የተጠረጠሩበትን ወንጀል ለይቶ ማሳወቅና ለፍርድ ቤቱም ማቅረብ ሲገባው፣ ዝም ብሎ በጥቅል የ21 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን ብቻ መግለጹ ተገቢ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ ምርመራው ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(4) ድንጋጌ አኳያ መታየት እንዳለበት ጠበቆቹ አሳስበው፣ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ማየት እንዳበት ያሳሰቡት ጠበቆቹ፣ ምክንያታቸው ደግሞ መርማሪ ቡድኑ በጅምላ ‹‹በሰብዓዊ መብት ጥሰት›› እያለ በየቀጠሮው ተጨማሪ ጊዜ ከመጠየቅ ባለፈ፣ በደንበኞቻቸው ላይ ምንም ዓይነት ምርመራ የጀመረ ስላልመሰላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሠራኞች ከመሆናቸው አንፃር፣ ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ከማዋሉ በፊት፣ የምስክሮችን ቃል ሳይቀበልና ሰነዶችን ሳይሰበስብ እንዲታሰሩ ማድረግ ሕገ መንግሥቱንና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ጭምር መጣስ ስለሆነ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ ከእስር እንዲፈቱም ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን የሚያልፈው ቢሆን እንኳን፣ እያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ወንጀል ተገልጾና መዝገቡ ተለይቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች በመሆናቸው የተጠረጠሩት ወንጀልም አንድ ሆኖ መቅረብ እንደሌለበት በማስረዳት፣ ተቃውሞአቸውን አቅርበዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ክርክራቸውን ሳይጨርሱ የፍርድ ቤቱ የሥራ ሰዓት በማብቃቱ፣ የቀሪዎቹን ተጠርጣሪዎች ክርክር ለመስማት ለረቡዕ ታኅሳስ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ በአዳር ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...