Thursday, April 18, 2024

በኦሮሚያ ከተካሄዱ ሰላማዊ ሠልፎች መልዕክት የወሰዱት ፓርቲዎች የትብብር ጉዞ ጅማሮ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ኦሮሞ እንኳን ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስተዳደር ይቅርና ራሱን እንደማያስተዳድር ተደርጎ ይታሰብ የነበረውን የመቶ ዓመት ጥያቄ አልፈን፣ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኦሮሞ ያስተዳድረናል የሚሉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ በሥራ እንጂ እንዲሁ አልመጣም። የኦሮሞ ሕዝቦች አንድ ሆነን ጠንክረን ሠርተን ታሪክ ተቀይሯል። ከመቶ ሃምሳ ዓመት በላይ ታግለን ዛሬ የነበረብንን እድፍ ታጥበናል፡፡ በዚህ ደረጃ የኦሮሞ ታጋዮች በጋራ ትግል እዚህ ደርሰናል፤›› ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም. በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረው ነበር።

አቶ ለማ ይኼንን ሲናገሩ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በኢሕአዴግ ውስጥ የነበረውን ትግል ጨርሶ ባያሸንፍም፣ ውጤቱ ከሞላ ጎደል ወደዛ እንደሚሆን የፓለቲካ ሚዛኑ ያሳይ ነበር።

ይኼንን ለመናገር ምክንያት የሆናቸው ይመሩት የነበረው ኦሕዴድ በተጠቀሰው ወር የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደዚህ ሥልጣን እንዲመጡ ለማመቻቸት የአመራር ለውጥ በማድረግ፣ በወቅቱ በኦሮሞ ሕዝብ ትግል ውስጥ ከፍተኛ ዕውቅና የነበራቸውን ራሳቸውን ከድርጅቱ ሊቀመንበርነት እንዲለቁና በዶ/ር ዓብይ እንዲተኩ ማድረጉ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ብዥታን በመፍጠሩ ነው።

በወቅቱ በሰጡት ሰፊ ማብራሪያም ኦህዴድ (ኦዴፓ) በፌዴራል አመራርነት ውስጥ በሚገባ ሚናውን እንዲወጣ ሲታገል እንደነበርና እየታገለም እንደሚገኝ ገልጸው፣ ፓርቲው በፌዴራል ደረጃ የሚኖረውን ኃላፊነት ብቻ በማየት በክልል ያለውን ጉዳይ የሚያንጠባጥብ ከሆነ ውድቀት ማስከተሉ ስለማይቀር፣ ይኼንን መሠረት ያደረገና በፌዴራልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የሚኖረውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ተብሎ የተደረገ የአመራር ለውጥ መሆኑን አስረድተው ነበር፡፡

 ‹‹የክልላችን መንግሥትና ድርጅት ለማጠናከር የተለያዩ ትግሎችንና ዕርምጃዎችን እየወሰድን እዚህ ደርሰናል፡፡ ነገር ግን አሁንም ጠንካራ ሆኖ የወጣ አይደለም፡፡ አሁንም በተለየ መንገድ ማጠንከር ያስፈልጋል፡፡ በሕዝብና በጠንካራ ድርጅት ከተደገፈ ግን ምንም አይሆንም፣ ስለሆነም በኦሮሚያ ላይ የሚሠራው ሥራ ወሳኝ ነው። ዋናው ትኩረት ኦሮሚያ ላይ መሥራት ነው፡፡ ምክንያቱም የሥልጣናችን ምንጭ ሕዝባችን ስለሆነ፤›› ብለው ነበር፡፡

በክልል ደረጃ ፍፃሜ ሳያገኙ የቆዩ የቤት ሥራዎችን ሙሉ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ በወቅቱ የተናገሩት አቶ ለማ፣ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የኦሮሞ ሕዝብን የሞራልና ኢኮኖሚ ጥያቄ የመመለስ አቅም በመገንባት የኢኮኖሚ ጥያቄውን መመለስ ግዴታ እንደሆነ፣ ለዚህም በኦሮሚያ ያለውን የሰው ሀብትና የተፈጥሮ ሀብት በማቀናጀት ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ በዚሁ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም. መግለጫቸው አስረድተው ነበር፡፡

ቃልና ተግባር

አቶ ለማ ከላይ የገለጹትን ዕቅዳቸውን በተናገሩበት ወቅት የኦሮሞን ሕዝብ የኢኮኖሚ ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር ጥምረት በመፍጠር ‹‹የኦሮሞ የኢኮኖሚ አብዮት›› የሚል ስያሜ የተሰጠውና የበርካቶችን ቀልብ የገዛ ሰፊ እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር።

በዚህ እንቅስቃሴም ኬኛ ቤቨሬጅ የተሰኘ ግዙፍ የለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ፣ ኦዳ ትራንስፖርት ኩባንያ፣ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካና ሌሎች ተመሳሳይ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይፋ ተደርገው ነበር። ይኼንንም ዕውን ለማድረግ ማንኛውም አቅም ያለው የኦሮሞ ተወላጅና በኦሮሞዎች የተመሠረቱ የንግድና የገንዘብ ተቋማት ለተጠቀሱት ፕሮጀክቶች በትንሹ ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የአክሲዮን ድርሻዎችን በመግዛት፣ እንዲሁም ለመግዛት በመስማማት ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

ይሁን እንጂ ከስምንት ወራት በኋላ ዛሬ ስለነዚህ የኦሮሞ ሕዝብ ከፍተኛ መነሳሳት ስላሳየባቸውና ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚያስገኙ ስለታመነባቸው ፕሮጀክቶች የሚሰማ ነገር የለም።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የክልሉ ሕዝብ ተወካይ የሆኑ የተወሰኑ የፓርላማ አባላት፣ የእነዚህ ፕሮጀክቶች ደብዛ መጥፋት በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ጥያቄ እየቀሰቀሰ እንደሆነ ያምናሉ።

 የኦሮሞ ሕዝብ በትግሉ የቀደመ ታሪኩን በመቀየር ኢትዮጵያን የማስተዳደር ስኬት ቢቀዳጅም፣ የተደረገው ትግል የሥልጣን ጥያቄ ብቻ ለመመለስ እንዳልነበር ያስረዳሉ።

የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄ አንዱ ሰበዝ እንጂ የትግሉ አልፋና ኦሜጋ እንዳልነበር የሚጠቅሱት የሕዝብ ተወካዮቹ፣ ከፖለቲካ ትግሉ ባለፈ ለበርካታ ዓመታት የተጓደለ የኢኮኖሚ ጥያቄ በመመለስ የኦሮሞ ሕዝብ ካለውና ከሚያመነጨው የሀብት መጠን ተጠቃሚ መሆን ሌላኛው የህልውናው ጥያቄ እንደነበር ያስረዳሉ።

የክልሉ ፓርቲና መንግሥት ይኼንን ዘንግተውታል የሚል ጥርጣሬ ባይኖራቸውም፣ የፖለቲካ ለውጡን ተከትሎ በሚስተዋለው የሽግግር ሒደት መራዘሙና ለውጡ መስመሩን እንዳይስት ሁለት ቦታ በመጣዱ የተልዕኮ ሚዛኑን እንዳዛባው፣ ይህም የፖለቲካ ሽግግሩ የሚጠይቀውን ጊዜና ጉልበት እንዲሁም ውስብስብነት ላይ የማኅበረሰቡ ይኼንን የመረዳት ውስንነት ሲታከል ጥያቄዎች መነሳታቸው እንደማይቀር ይናገራሉ።

ከዚህ ጎን ለጎን የሚሄደው ደግሞ የፖለቲካ ሽግግሩን ለማፅናት በሚደረገው ትግል በተለያዩ አካባቢዎች የኦሮሞ ሕዝብና ንብረት ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸው፣ በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው ኦሮሞዎች ተፈናቅለው ሕይወታቸውን በመጠለያ ውስጥ መግፋት መቀጠላቸው ሊቆም አለመቻሉ ቅሬታውን እንዳባባሰው ይገልጻሉ።

በዚህ ትንታኔ ላይ በርካታ የፖለቲካ ልሂቃንና የኅብረተሰብ ክፍሎች ይስማማሉ። በቅርቡ ከሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች ከተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ምሁራን ጋር በአዳማ ከተማ የሰላም ኮንፈረንስ አካሂደው የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ፣ ከተሳታፊዎቹ ቀርበውላቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል የኦሮሞ ሕዝብ የኢኮኖሚ ጥያቄና በየማዕዘኑ እየደረሰ ያለውን ጥቃት የሚመለከት ነበር።

አቶ ለማ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ የኦሮሞ ሕዝብ የኢኮኖሚ ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ እንደሆነ የክልሉ መንግሥት እንደሚያምን፣ ነገር ግን በመዘንጋት ሳይሆን ቅድሚያ ትኩረት የሚሻ አንገብጋቢና የህልውና መሠረት የሆነ ሕግ የማስከበር ጥያቄ አፍጥጦ በመምጣቱ ወደዚያ ማድላቱን አስፈላጊ እንዳደረገው ተናግረዋል።

 ሕግን የማስከበር ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል።

ሌሎች የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ወደ ሥልጣን የመጣው ተራማጅ ኃይል የዴሞክራሲ ሜዳውን ለሁሉም እኩል በመክፈት ያገባናል የሚሉ ሁሉ እንዲሳተፋ ጥሪ ማድረጉን ተከትሎ፣ ለበርካታ ዓመታት የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር ሲታገሉ የነበሩ ተቀባይነት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ማኅበራዊ መሠረታቸው መመለሳቸው፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ቢቆዩም በነበረው ጨቋኝ የፖለቲካ ምኅዳር ምክንያት ደካማ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሻለ ነፃነት አግኝተው የሚወክሉትን የፖለቲካ ማኅበረሰብ የማንቀሳቀስ ዕድል ማግኘታቸው፣ በክልሉ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ማስከተሉ እንደማይቀርና የዚህ ምልክትም መታየት መጀመሩን ይናገራሉ፡፡

በተለይም የክልሉ ሕዝብ ሲያደርገው የነበረውን የፖለቲካ ትግል በመጨረሻም ቢሆን በማስተባበርና የበለጠ በማቀጣጠል ሚና የተጫወተው ኦዴፓ የፖለቲካ ድሉ ከተገኘ በኋላ የሽግግር ጊዜውን ማሳጠር አለመቻሉ፣ ይህም በክልልና በፌደራል ደረጃ የያዘውን ሁለት የፖለቲካ ኃላፊነትና ተልዕኮ ሚዛኑን ጠብቆ ከመጫወት ይልቅ ወደ አንዱ የመሳብ ሁኔታ በማመዘኑ በክልል ደረጃ ባለው የፖለቲካ ተልዕኮ ላይ ክፍተት መፍጠሩ፣ ለሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ዕድል መፍጠሩ እንደማይቀር ሁሉ በገሃድም በመታየት ላይ መሆኑን ያስረዳሉ።

ይህ ፖለቲካዊ ክስተትም በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ሰሞኑን የደረሰውን አሰቃቂ ግድያ ተከትሎ ጎልቶ እንደወጣ፣ ሁኔታውም የክልሉ መንግሥትን እንዳነቃው ይናገራሉ።

በዚህ አካባቢ በተከሰተው ግጭት በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች በታጣቂዎች መገደላቸው፣ በተለይም በጥቃቱ የኦሮሚያ ክልል 11 የፖሊስ አባላት መገደላቸው ጭምር የክልሉ ሕዝብ ቁጣ እንዲገነፍል ምክንያት ሆኗል። ጥቃቱን ተከትሎ ክልሉን የሚያስተዳድረው የኦዴፓ ማዕከላዊ አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

በመግለጫው ሥልጣን የተነጠቁና በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ እንዲሁም በሙስና ወንጀሎች ላይ በተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠያቂ እየሆኑ ያሉ ኃይሎች በእጅ አዙር የጀመሩት የፖለቲካ ሴራ መሆኑን አመልክቷል።

‹‹በሕዝባችን ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አካላትንም የገቡበት ጉድጓድ በመግባት ለሕግ በማቅረብ ተመልሰው ጉዳት ማድረስ እንዳይችሉ እንሰብራቸዋለን፤›› በማለት አቋሙን ገልጿል። ይሁን እንጂ ተደራጅቶ በእጅ አዙር ጥቃት እየሰነዘረ ያለውን ወገን በግልጽ አልተናገረም።  

በአካባቢው ያፈነገጡ የኦነግ ኃይሎች እንቅስቃሴ ቢገለጽም፣ ኦነግ ስለዚህ ኃይል መኖር ያመነውም ያስተባበለውም ነገር የለም።

የሰሞኑ ግጭት ከመድረሱ ቀደም ባሉ ቀናት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳነት አቶ ለማ መገርሳና የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ተገናኝተው በክልሉ የሰላምና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተባብረው ለመሥራት መግባባታቸው ተገልጾ ነበር።
በቅርቡ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ኦነግ ባወጣው መግለጫ፣ በአሁኑ ወቅት በምዕራብ ኦሮሚያ በኩል እየደረሰ ያለው ጥቃት በጉሙዝ ሕዝብ ስም እንዲታጠቁ በተደረጉ ኃይሎች መሆኑንና በአካባቢው በሚገኙት ኦሮሞዎች ላይ እየተካሄደ ያለው የግድያ ዘመቻ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክቷል።

እየተፈጸመ ላለው ጥቃት መንግሥት እንደ ችግር እያቀረበ የሚገኘው ኮንትሮባንዲስቶች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎችና በሌሎች ስየሜዎች የተሰየሙትን መሆኑን የሚገልጸው የኦነግ መግለጫ፣ እስካሁን ግን የችግር ምንጭ ናቸው የተባሉትን ለሕግ በማቅረብ ችግሩን ለመፍታት በቂ ዕርምጃ አልተወሰደም በማለት ወቅሷል።

የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ የሚጠቅሰው የኦነግ መግለጫ፣ ‹‹በተጠያቂነት መንፈስና ባለን ራስን የመከላከል መብት ተጠቅመን እንደ ብሔር እየተፈጸመብን ያለውን ግድያና ማንኛውንም ችግር መከላከል፣ የሕዝባችን መብትና ግዴታ መሆኑን እናሳስበለን፤›› ብሏል። በጥቃቱ የተቆጡ የምዕራብ ወለጋ ነዋሪዎች በጥቃቱ ማግሥት ግዙፍ ሰላማዊ ሠልፍ በማካሄድ፣ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነቱን በመወጣት የኦሮሞዎችን ደኅንነትና ሰላም ማስከበር እንዳልቻለ ወቅሰዋል።

ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣና የኦሮሞ ሕዝብ መብትና ጥቅምን እንዲያስከበር ጠይቀዋል። ይኼንን ስላማዊ ሠልፍ ተከትሎ ኦዴፓ ባወጣው መግለጫ ሰላማዊ ሠልፉ መደረጉ ተገቢ ቢሆንም፣ ለውጡን ለማደናቀፍ ለሚጥሩ ኃይሎች ቀዳዳ መክፈት እንደማይገባና ብስለት የተሞላበት አካሄድን መከተል አስፈላጊ መሆኑን አሳስቧል። ይሁን እንጂ በጥቃቱ ማግሥት በምዕራብ ወለጋ ከተካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ በኋላ በነበሩት ቀናት 20 በሚደርሱ ሌሎች የኦሮሚያ ከተሞች ተመሳሳይ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች፣ በተወሰኑ አካባቢዎችም የክልሉ የፖሊስ ሠራዊት አባላት የተሳተፉባቸው ሠልፎች ተካሂደዋል። በዚህም ክልልሉን በሚያስተዳድረው የፖለቲካ ድርጅትና መንግሥት ላይ ወቀሳ ተሰንዝሯል። በተጨማሪም የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ግብ የፖለቲካ ሥልጣን ብቻ እንዳልነበር የሚገልጹና የኦሮሞ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጥቅምና መብቶች እንዲከበሩ የሚጠይቁ ድምፆች ተሰምተዋል።

የፖለቲካ መፍትሔው ጅማሮ

በክልሉ መስተዋል የጀመረውን አዲስ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የገመገመው የኦዴፓ ከፍተኛ አመራር፣ በተለይም የመንግሥትና የድርጅት አካሉ የታችኛው መዋቅር በአካል እንጂ በመንፈስ አብሮት አለመሆኑን እንደተረዳ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች ያስረዳሉ።

ከሚያቀርቧቸው ማሳያዎች መካከልም ቁጣ ገንፍሎ በበርካታ አካባቢዎች ሰላማዊ ሠልፎች ከመካሄዳቸው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ፣ የክልሉ የፕሬዚዳንት አቶ ለማ ከክልሉ የፖሊስ ሠራዊት ኮማንደሮች ጋር ውይይት በማድረግ ጥብቅ መመርያ አስተላልፈው እንደነበር ያስታውሳሉ።

በዚህም ወቅት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር በሠራዊቱ ውስጥ የቅንጅት መጓደል፣ ደረጃዎቹ ቢለያዩም በሁሉም ዞኖች የፀጥታ ችግሮች እንደሚስተዋሉ በሪፖርታቸው አመላክተው ነበር። የክልሉ ፕሬዚዳንት በሰጡት ማሳሰቢያም የክልሉ ፖሊስ የክልሉ መንግሥት ኃይል እንጂ የፖለቲካ ድርጅት ኃይል አለመሆኑን ተገንዝቦ የፖለቲካ ፓርቲ ዓርማ ይዞ ፎቶ መነሳት እንዲያቆም፣ ሠራዊቱ በሙሉ በጠንካራ መዋቅር የሚመራና ትዕዛዞች ከላይ ወደታች በተገቢው ሁኔታ ሳይጓደሉ እንዲፈጸሙ አሳስበው ነበር።

ይህ ቢሆንም በቀጣዮቹ ቀናት በበርካታ ከተሞች በተካሄዱት ሠልፎች የፖሊስ ሠራዊት አባላት የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው በሠልፎቹ ተሳትፈዋል። ከዚህ ባለፈም በክልሉ የታችኛው የመንግሥት መዋቅር ዝቅተኛ አመራሮችም ተሳታፊ መሆናቸው ተነግሯል።

ከተካሄዱት ሠልፎች ማግሥት የክልሉ መንግሥት ካቢኔ ስብሰባ ተጠርቶ እንደነበር የሚገልጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ በስብሰባውም የክልሉ መንግሥት የታችኛው መዋቅር የተለየ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል። ካቢኔው ባካሄደው ስብሰባም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ውሳኔ አሳልፏል።

የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ እንደገለጸው፣ ካቢኔው የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞችን እንደ አዲስ ለመመደብ የቀረበ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይም ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል።

 ካቢኔው በስፋት መክሮ አቅጣጫ ያስቀመጠው የኦሮሚያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በያሉበት ደረጃ መመርያውን በመጠቀም፣ ሥራቸውን ውጤታማ እንዲሁም በተቀናጀና ወጥ በሆነ መንገድ እንዲወጡ አፅድቋል፡፡

በተመሳሳይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎች በሰዓት እንዲሆን፣ የመንግሥት ሠራተኞች የአገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነትና በምደባ ወቅት ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም አቅጣጫ መቀመጡን አመልክቷል፡፡

በመቀጠል የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንርና የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚታገሉ 14 የፖለቲካ ድርጅቶችን በመጥራት፣ በወቅታዊ የክልሉ ጉዳዮች ዙርያ ሐሙስ ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. አወያይተዋል።

 አቶ ለማ በስብሰባው ባቀረቡት ሐሳብ የኦሮሞ ሕዝብ የከፈለውን ዋጋ የሚመጥን ጥቅም ማግኘት ሲገባው፣ ዛሬም ድረስ ሕዝብን ሰላም የሚያሳጡ ክስተቶች መቀጠላቸው እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።

አሁን የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል እንደ አገር የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ መሆኑ ሁሉም መገንዘብ እንደሚገባው ያሳሰቡት አቶ ለማ በአሁኑ ወቅትም፣ ‹‹የምንተቻችበትና የምንፎካከርበት ሳይሆን አገር የምናድንበት ነው፤›› ብለዋል።

ለሥልጣን ሲባል በኦሮሞ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ፉክክር የኦሮሞ ሕዝብን የዘመናት ትግል ማጨናገፍ እንደሆነና ያለው ትክክለኛ ምርጫ የኦሮሞን ጥቅም ለማስከበር መከባበር መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህ ጉዳይም ሁሉም ተሳታፊ የነበሩ የኦሮሞ ፓርቲዎች ተቀብለው በትብብር ለመሥራትና በኃላፊነት ስሜት ለመንቀሳቀስ እንዲቻል፣ የኦሮሞ ፓርቲዎች የትብብር ፎረም ለመመሥረት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ይህ መንገድ የኦሮሞ ፖለቲካን መስመር በማስያዝ የሕዝቡን ጥቅምና መብት ለማስከበር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በደስታ የተቀበሉትን ያህል፣ የይስሙላ ስምምነት አለመሆኑን በእርግጠኝነት ለመናገር ጊዜው ገና መሆኑንም የሚገልጹ ይስተዋላሉ።

ይሁንና የጋራ ፎረሙን መቋቋም በማስመልከት መግለጫ የሰጡት የኦዴፓ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ዶ/ር) የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመደማመጥና በመወያየት ለመፍታት የጋራ ፎረሙን መመሥረታቸውን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -