Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገር ውስጥ ኃላፊ በኦነግና ግንቦት ሰባት አባላት ግድያ ተጠረጠሩ

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገር ውስጥ ኃላፊ በኦነግና ግንቦት ሰባት አባላት ግድያ ተጠረጠሩ

ቀን:

አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ያለ ፍርድ ቤት መጥሪያ መያዛቸውን ተቃወሙ

በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው የታሰሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን፣ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና በአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ግድያ ተጠረጠሩ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት እንደገለጸው፣ በወቅቱ በሽብርተኝነት ተፈርጀው በነበሩት ኦነግና አርበኞች ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት ናቸው ተብለው ከታሰሩ በኋላ፣ በደረሰባቸው ድብደባና ከፍተኛ ጉዳት ሕይወታቸው ያለፈ ዜጎች መኖራቸውን አስረድቷል፡፡ ይኼም የሆነው አቶ ያሬድ በሥራቸው ላሉ የደኅንነት አባላትና ሠራተኞች በሰጡት ትዕዛዝ መሆኑን አክሏል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውስጥ ተጠርጣሪው ግለሰቦች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲያዙ፣ እንዲታሰሩና በሕግ ባልተፈቀደ ቦታ እስከ አምስት ወራት ድረስ እንዲቆዩ በማድረግ፣ የድብደባና የተለያዩ ማሰቃያ ዘዴዎችን በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡

በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩት የኦነግና የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት ናቸው በሚል፣ ታስረው በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት የሞቱ ሰዎች ማንነትና አድራሻ ከተለያዩ የምርመራ መዝገቦች የመለየት ሥራ መከናወኑን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪው የፖለቲካ ድርጅቶቹ ለአባሎቻቸው የሚልኩትን ገንዘብ ሐሰተኛ መታወቂያ ለሌሎች ግለሰቦች እንዲዘጋጅ አድርገው ከባንክ በማስወጣት፣ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘቱንም ገልጿል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ አቶ ያሬድ በባለቤታቸው እናት ስም የተመዘገበ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ማከራየት ንግድ፣ በባለቤታቸው ወ/ሮ አዳነች ተሰማ ስም የተመዘገቡ የተለያዩ ቤቶች፣ በራሳቸው ስም የተመዘገቡ ቤቶች፣ ድርጅቶች፣ ለባለቤታቸው አባት ውክልና የተሰጠ ድርጅት እንዳላቸውና ከገቢያቸው በላይ ምንጩ ባልታወቀ ገቢ ሀብት ማከማቸታቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በቀጣይ የሚሠራቸውን ምርመራዎች ለፍርድ ቤቱ የገለጸ ሲሆን፣ አቶ ያሬድ ተጨማሪ ንብረት በተለያዩ ግለሰቦች ስም እንዳላቸው የሚያውቁ ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው ገልጿል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማም በአቶ ያሬድና በባለቤታቸው ስም ተመዝግቦ የሚገኝ ቤት መኖሩን ጥቆማ እንደደረሰው፣ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች የተለያዩ ንብረቶች በባለቤታቸውና በባለቤታቸው እናት ስም ተመዝግበው እንደሚገኙ ጥቆማ እንደደረሰውና ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ በክልሎችም የምርመራ ቡድኖች በማቋቋምና በመላክ ተጎጂዎችን በማነጋገር የምስክርነት ቃል እየተቀበለ መሆኑንም አክሏል፡፡ በዱከም ከተማ በባለቤታቸውና በእሳቸው ስም ያለ ንብረት ማስገመት እንደሚቀረው በመግለጽ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

የአቶ ያሬድ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ መርማሪ ቡድኑ በደንበኛቸው ላይ የወንጀል ድርጊት አላገኘም፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም አድርገዋል ከሚል ያለፈ እሳቸው በቀጥታ የፈጸሙት አንድም ነገር እንደሌለና መርማሪ ቡድኑም ያለው ነገር አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ ከተያዙ ብዙ ቀናትን ያሳለፉ ቢሆንም፣ ቃላቸውን እንኳን እንዳልተቀበሏቸውና ይኼ የሚያሳየው ደግሞ ምንም ዓይነት ወንጀል አለመፈጸማቸውን በመሆኑ፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ሌሎች በሠሩት ሥራ እሳቸው ሊጠረጠሩ እንደማይገባ፣ የሕግም ድጋፍም እንደሌለው አክለዋል፡፡ ንብረትን በሚመለከት በሰነድ የሚረጋገጥና ሰነዱም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ስለሚገኝ እሳቸውን በእስር ሊያስቆያቸው የሚችል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአስከሬን ምርመራ በማለት መርማሪ ቡድኑ ቢናገርም እነማን እንደ ሞቱ፣ የት እንደ ሞቱ፣ የት እንደ ተቀበሩና በእነ ማን እንደ ተገደሉ መርማሪ ቡድኑ ያለው ነገር ስለሌለ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ጥያቄውም ውድቅ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ያቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ የሚታለፍ ከሆነም አጭር ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቀዋል፡፡ ደንበኛቸው እስከ ኅዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ የተከሳሽነት ቃላቸውን አለመስጠታቸውን በድጋሚ አስታውሰው፣ ቃላቸውን ሲሰጡ ግን ጠበቆቻቸው ባሉበት እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ዋስትናውን እንደሚቃወም ገልጿል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምርመራውን አለማጠናቀቁን፣ ከእስር ቢወጡ ምስክር ሊያስፈራሩ፣ ሊያጠፉ፣ ሊያባብሉና ራሳቸውም ከአገር ሊወጡ፣ ሰነዶች ሊያሸሹና ሊያበላሹ ስለሚችሉ መሆኑን አስረድቷል፡፡ አቶ ያሬድ በሰጡት ትዕዛዝ ማን እንደ ሞተ ማስረጃ መሰብሰቡንና ቀጥተኛ የምስክርም ቃል መቀበሉን ተናግሯል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ከመረመረ በኋላ፣ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን በአግባቡ እየሠራ መሆኑን ከመዝገቡ መረዳቱንና ለቀሪ ሥራዎችም ተጨማሪ የጠየቀው ቀናት እንደሚያስፈልጉት ገልጾ በመፍቀድ፣ የተጠርጣሪውን ጠበቆች ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ለታኅሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሌላ የምርመራ መዝገብ የቀረቡትና በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል መምርያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ናቸው፡፡  

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ አቶ ተስፋዬ ሐሰተኛ ሰነድ ማለትም በወቅቱ በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶችን መተዳደሪያ ደንብና የፖለቲካ ፕሮግራም በማዘጋጀት፣ የድርጅቱ አባላት ናቸው በተባሉ ግለሰቦች ቤት ውስጥ በድብቅ በማስቀመጥ በሽብርተኝነት ያስፈርጇቸው እንደነበር ገልጿል፡፡ የኦነግን ባንዲራ በማስቀመጥ እንዲታሰሩ ከማድረግም ባለፈ፣ በማስፈራራት ከ200 ሺሕ ዶላር በላይና ስድስት ሚሊዮን ብር መቀበላቸውንም አክሏል፡፡ ግለሰቦችን ሐሰተኛ ደብዳቤ በመጻፍ እያስፈራሩ ያሰቃዩ እንደነበር፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ እንደነበር መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪው በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በተለያዩ አካባቢዎች ከገቢያቸው በላይ ሀብት ማፍራታቸውን፣ በንግድ ባንኮችም ከፍተኛ ገንዘብ ማስቀመጣቸውንና በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ገልጿል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በቀጣይ የምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ተጠርጣሪውን በተጎጂዎች ማስለየት፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች የሕክምና ማስረጃና ሌሎችም ማስረጃዎችን መሰብሰብ እንደሚቀረው በመግለጽ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

አቶ ተስፋዬ በጠበቃቸው አማካይነት ባቀረቡት የመከላከያ ሐሳብ፣ እሳቸው ተጠርጥረው የታሰሩት በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የቦምብ ፍንዳታ ላይ አስተባብረሃል ተብለው ከሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ፍርድ ቤት ቀርበው እያሉ፣ የፍርድ ቤት መያዣ ሳይወጣባቸው መታሰራቸውንም ተቃውመዋል፡፡ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደመሆኑ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 113 መሠረት ሊነገራቸውና መያዣ ሊወጣላቸው ይገባ እንደነበር በመጠቆም አያያዛቸውን ተቃውመዋል፡፡

እሳቸው ይሠሩበት የነበረው ተቋም ውስጥ ከዋና ዳይሬክተሩ ሥር አራት ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች እንዳሉ፣ እሳቸው ከዚያ በታች ከተዋቀረው ሰባት መምርያ ውስጥ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል መምርያ ኃላፊ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ በሥራቸው ሌሎች ኃላፊዎች እንደነበሩ ጠቁመው፣ እሳቸው የሙያ ሥራ ከመሥራታቸው ውጪ ከተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ መረጃ የመተንተን ሥራ ነው የምሠራው፡፡ መርማሪ ቡድኑ ካመለከተብኝ ድርጊት ጋር ግንኙነት የለኝም፤›› በማለት አቶ ተስፋዬ ራሳቸው ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ አካባቢ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ሐሰተኛ ማስረጃ በማዘጋጀት እንደሚያሳስሩ መርማሪ ቡድኑ የገለጸ ቢሆንም የት፣ መቼና እንዴት እንደሆነ ስላላስረዳባቸው ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ ሐሰተኛ ስም እንዳላቸውና የሚታወቁት በሐሰተኛ ስማቸው መሆኑን መርማሪ ቡድኑ መናገሩን በሚመለከት የተጠርጣሪው ጠበቃ በሰጡት ምላሽ፣ ሌላ ስም ቢኖራቸው ኖሮ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ይናገር እንደነበር ገልጸው፣ ‹‹ሐሰተኛ ስም አላቸው የተባለው ሐሰት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከገቢያቸው በላይ ሀብት አከማችተዋል መባሉም የትና ምን ያህል እንደሆነ ባልተገለጸበት ሁኔታ፣ እሳቸውን አስሮ ማስቀመጡ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 17 ድንጋጌ አንፃር ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ የዋስ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በድጋሚ በተሰጠው ዕድል አቶ ተስፋዬ ድብቅ ስም እንዳለቸው ተናግሮ፣ ያልጠቀሰው ተጎጂዎች የሚያውቋቸው በድብቅ ስማቸው በመሆኑ እስከሚያስለዩዋቸው ድረስ እንጂ ካለማወቅ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት እንዳስታወቀው፣ የመርማሪ ቡድኑን የምርመራ መዝገብ ወስዶ ተመልክቶታል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን በአግባቡ እየሠራ መሆኑን ጠቁሞ፣ የተጠርጣሪውን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ የተጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለታኅሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...