የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዓመታት በባለይዞታዎች ባለመልማታቸው ምክንያት የባለቤትነት ካርታ ካመከነባቸው ቦታዎች መካከል፣ በአሥሩ ላይ ያዘጋጃቸው ጊዜያዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች በሳምንቱ መጨረሻ ሥራ ጀመሩ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ ከጠየቃቸው 56 ቦታዎች መካከል 20 ቦታዎች የተፈቀዱለት ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በአሥሩ ላይ የተዘጋጁት የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች ቅዳሜ ኅዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ ሥራ ጀምረዋል፡፡ በዓመት 20 ሺሕ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ሲሆን፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እንዲከሰት ምክንያት ሆነዋል፡፡ በቂ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች ባለመኖራቸውና አሽከርካሪዎችም በየመንገዱ የሚያቆሙ ስለሆነ፣ ከቦታ ቦታ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ብዙ ጊዜ የሚወስድና አሰልቺ አድርጎታል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ጊዜያዊና ዘላቂ የተሽከርካሪዎች ማቆሚያዎችን ከመገንባት ባሻገር፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የንግድ ሕንፃዎች ለተሽከርካሪዎች ማቆሚያ የገነቡትን ቦታ ለሌላ ተግባር ያዋሉ መሆኑን ጠቅሶ፣ ቦታውን ለተሽከርካሪዎች ማቆሚያ እንዲያውሉ የአንድ ወር ጊዜ ሰጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በከተማው 120 የመንገድ ዳር የክፍያ ተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህን ጨምሮ በአዳዲሶቹ ተሽከርካሪ ማቆሚያዎች የሚሠሩት በጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች የተደራጁ ወጣቶች ናቸው ተብሏል፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታየው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ውስጥ በቅርቡ ከዲፕሎማቲክ ተቋማት የተወሰዱ ቦታዎች ላይ ከተዘጋጁ የተሽከርሪዎች ማቆሚያዎች መካከል አንዱ ነው፡፡