ሰላም! ሰላም! እንዴት አላችሁ? ይኸው እኔ እንዲህ ትንፋሽ የማይሰጥ ትውስታ እየደራረበ የሚነጉድ ዘመን ይመጣል ሳልል ‘ፉል’ እያለ ባስቸገረኝ ‘ሚሞሪዬ’ ተወጥሬ አለሁላችሁ። ይኼ የ‘ዲጂታል’ ዘመን ከእኔ በባሰ ባሻዬን ክፉኛ አሥግቷቸዋል። ‘እንዴት?’ አትሉኝም? አዎ። በደህና ቀን የተማራችኋቸውን ትህትና አዘል ቃላት እንዳትረሱ። መቼም የነበረንን መልካም እሴት ከመርሳት የባሰ ወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚያዘቅጥ አይመጣብንም። እስኪ አስቡት ለራሳችን መውጪያ የሌለው ሦስተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ መራገጣችን ሳያንስ ደግሞ ከዚህ ስንወርድ። ሆ! የሆነስ ሆነና እንዴትም ተከርሞ መገናኘት ደግ ነውና እስኪ የሚያስጨንቀውን ትተን ገብስ ገብሱን እናውራ፡፡ በውጥረት ጊዜ ረገብ ማለት እኮ መልካም ነው፡፡
እና አደራችሁን ከስክሪን ጋር ተፋጦ ሲውል መሽቶ እንደሚነጋበት ደንታ ቢስ ትውልድ አሰዳቢ የቋንቋ ዳያስፖራ፣ ‘ዋትኤቨር’ እና ‘ሁ ኬርስ’ ብሎ ጨዋታ መዝጋት ሳታስቡት እንዳትለምዱ ጠንቀቅ እያላችሁ። ዘንድሮ ካልተጠነቀቁ መጠቀም ብቻ አላስተማመነም ነው የምላችሁ። እኔ ልሙት፡፡ በበኩሌ እነዚህን የራስ ወዳድ ቃላት ያለ ቦታቸው መጠቀም በራሱ፣ መተማመንና ፍቅር እያቀዘቀዙብን ከመጡ ዘመነኛ ድርጊቶች ተለይቶ የሚታይ አይመስለኝም። እስኪ አስቡት የጋራ ቁስላችን በጋራ መፍትሔ ብቻ መድረቅ በሚገባው በዚህ ጊዜ ‘እንዴት? ወዴት? ለምን?’ ካልተባባልን እንዴት ይሆናል? የአንዱን ሐሳብ ሌላው ካልሰማና ካላጤነ በቃ አበቃልን ማለት አይደል? እናም ‘እንዴት? ማለት ደግ ነው’ ሲሉ አበው፣ ዘመናቸው ትምህርት ነጠቆች ባይበዙበትም በዲግሪ ብዛት የማይገኝ ማስተዋል ስለነበራቸው ነው። እኔም ተራዬን “እንዴት?” ልበልና ባሻዬን ላዳምጥ።
ባሻዬ በተቆጣ ዓይናቸው ገላምጠውኝ ሲወጣላቸው፣ ‹‹ምን እንዴት ትለኛለህ?›› ብለውኝ እርፍ። ‹‹አባባሌ መቼም ይኼ ጊዜ እልፍ እየፀነሰ እልፍ ያመክናል። የ‘ዲጂታል’ ዘመን በሽምግልና ቀርቶ በጦር የማይፈታ ቅራኔ ያለው እያስመሰለ ሰውን ‘ከፍትፍቱ ስክሪኑ’ ያባብል በያዘ ጊዜ ሥጋትዎን ያጫውቱኝ ማለቴ ነው፤›› አልኳቸው። ይገርማችኋል ይኼን ጥያቄያዊ ረጅም ዓረፍተ ነገር ተናግሬ ስጨርስ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ጀግና አትሌት ውድድሩን በድል ተወጥቶ ከሳበው ትንፋሽ የማይተናነስ ሳብኩላችሁ። አይገርምም? ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ዓይናችን ብቻውን ሲንከራተት እየዋለ እኮ፣ ትናጋም የእንቅስቃሴ ‘አለርጂክ’ እንዳለበት ሁሉ ተሳስሮ ኖሮ፣ ‘ጂምናዚየም’ ሊከፈትለት ምንም አልቀረለትም። ‘ላንቃ የማላቀቅ፣ አንደበት የመተርተር፣ ምላስ የማፍታታት አገልግሎት እንሰጣለን!’ የመሳሰሉት ማስታወቂያዎች በቅርቡ ተለጥፈው ካያችሁ ታዲያ ‘አይዲያው’ የእኔ ነው እሺ? መቼም በአገራችን ሲከበር ያላየነው ባለ ‘አይዲያ’ ነው!
ባሻዬ ማብራራት ያዙ። ‹‹እንጃ! ልመናና ምልጃችን ከ‘ሶፍትዌርነት’ ወደ ‘ሃርድዌርነት’ እንዳይቀየር ሠጋሁ፤›› ብለውኝ ዝም አሉ። አፌን ከፍቼ ቀረሁ። ‘ሶፍትዌርና ሃርድዌር?’ እንግዲህ ከዳዊታቸውና ከዚያች የዛገች ሬዲዮናቸው ሌላ በማያውቁት ባሻዬ አፍ ተባለ ማለት፣ የ‘አርተፊሻል ህሊና’ ጠቢባን የ‘ሮቦት’ ማኅበረሰብ የመፍጠር ግስጋሴያቸው ምን ያህል እየሰመረላቸው እንደሄደ መገመት አላዳገተኝም። እኚህ ሰውዬ በስተርጅና ቅዳሴና ፆማቸውን ትተው የኮምፒዩተር ‘ኮርስ’ መውሰድ ጀመሩ? እንዴት ነው ነገሩ? ስል በልቤ፣ ‹‹. . .ሰው ትንሽ ቆይቶ ‘መንግሥቱንና ፅድቁን የምፈልግበት ኃይልና እምነት ጨምርልኝ ከማለት፣ ሀብት በሀብት ላይ የምጨምርበትን መረጃ የምይዝበት ‘ሚሞሪ’ ጨምርልኝ። ‘ሃርድ ዲስኬን’ አብዛው። ‘ፋይሎቼን’ እና ‘ሲስተሜን’ ከ‘ቫይረስ’ ጠብቅልኝ’ እያለ መፀለይ የሚጀምር መስሎኛል፤›› ብለው ይባስ አጃኢብ አሰኙኝ። እኛ ደግሞ ለምዶብን ከሚነሳው ዋና ሐሳብ የሚማርከን አተራረኩና ተራኪው አይደል? እንዲያ ሆኖ እኮ ነው “ያለምንም ደም” ሲሉን ስንከተል፣ የማሸነፍ አንድ ራዕያችንን በ ‘ሸ’’ እና በ ‘ቸ’ አለያይተን ጉድ ስንሆን የኖርነው። አሁንስ አላችሁ? አቤት ስታስወሩ!
ወዲያው ወደ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ደወልኩ። የባሻዬ ‘ኮምፒዩተራዊ’ ቃላት አመራረጥና አጠቃቀም ወትሮው የማውቃቸውን ባሻዬን እንዳልመሰሉኝ ስነግረው፣ ‹‹ማን ያውቃል ‘ሺፍትን’ ተጭኖ ዘመኑ ወደ ዕውቀት ሳይሆን፣ የቃላት ጋጋታ ‘ኢንተር’ ብሎ ይሆናላ። ደግሞ አይግረምህ መገለባበጥ በእኔ አባት አልተጀመረም፤›› ሲለኝ? ‘ወይ ሰው!’ አልኩ። የጠየቅኩትን ትቶ ያልጠየቅኩትን ሲቀባጥርብኝ፣ ለአፍታ የሰው ነገር አሳባሪነትና ሰንጣቂነት ትዝ ብሎኝ ከዚህ በላይ የሚጠቃ ምን ‘ሲስተም’ አለ? ‘ምቀኛና ነጃሳውን አርቅልን፣ ሰቡ ረቡ፣ ገቡ ወጡ የሚለንን ያዝልን’ ተብሎ ፈጣሪ የሚለመንበት ዘመነ ቅንነትን የሚያሳጣ የአስተሳሰብና አመለካከት ‘ቫይረስ’ ከአንጎል አንጎል በ‘ክሊክ፣ ላይክና ዲስላይክ’ ወደ ሚተላለፍበት ዘመን ከተሸጋገረ፣ ልመናችን ‘ዲጂታላዊ’ ቢሆን ምን ነውር አለው?’ አልኩ። ተሳሳትኩ? እሱም ፈጣን መልስ አይሰጥም እየተባለ የሚወርድበት ትችት ቀርቶ፣ ‘ቴሌ ኔትወርኩን ስሎው’ ስላደረገው ነው’ ወደሚል ይዞርለት ይሆናል። ማን ያውቃል?
ብቻ ከእነ ድንጋይ ኳሱ ዘመን ወደ ተንቀሳቃሽ ዳስተር ስልክ፣ ከዚያም ወደ ተንሸራታች፣ ተነካኪና አነካኪ ሞባይል ስልኮች በፍጥነት የመገለባበጣችን አጭር ታሪክ ብዙ የሚባልለት ነው። ከሚባልለት አንዱ ‘ሽምጥ መጋለብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው’ ለተባለው የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን፣ ብሎም ማኅበረሰባዊ እሴቶቻችን አሉታዊ ግብዓት አለው የሚባለው ነው። መቼ ዕለት አንድ ገልባጭ ላሻሽጥ በጣቶቼ ስልኬን ወዲያ ወዲህ ሳራግባት አንድ ወዳጄ ትኩር ብሎ ያየኛል። አስተያየቱ ስላልጣመኝ (ጠላት ከሩቅ አይመጣም ስንል ስንል ዘንድሮስ ጥላም የለን አሉ ሲያዩን) ኮስተር ብዬ፣ “በሰላም ነው?” ስለው፣ “ኧረ ሰላም ነው። እንዲያው ይኼ ጊዜና ሰዓቱን ጠብቆ ሳንዘጋጅ የመጣብን ቴክኖሎጂ እየገረመኝ እኮ ነው። ይኼው እንደምታየው ገበያውንም አደራው፣ ሰውንም አዳራው፤›› አለኝ። ዳር ዳርታው ገብቶኝ፣ ‹‹ይህ ሊሆን ግድ ነው አልኩት፤›› ከባሻዬ የሰማሁትን የመጽሐፍ ጥቅስ የራሴ አስመስዬ። ሰው በሰው ንብረት የፈጠራ ሥራና ሐሳብ የራሱ አስመስሎ እዩኝ ዕወቁኝ እያለ እያየን የእኔ ምን አላት ብላችሁ ነው?
ገመድ አልባ ‘ኔትወርክ’ ካመጣልን መልካም ነገር ያመጣብን የመፈላለጥ፣ እንደ ድመት የመሞነጫጨር ትግል ስለበለጠ አስተያየቱ አልጥም ብሎኝ፣ አንዴ ‘እህ’ ያልኩት ወዳጄ ሊላቀቀኝ ፈቃደኛ አይደለም። አንዱ በቫይበር ለእጮኛው የጻፈውን መልዕክት ፍፁም ለማያስባት በስህተት ልኮ ጥሩ አቀባበል ተደርጎለት በዚያው መቀጠሉን አጫውቶኝ ሳይጨርስ፣ በ‘ፌስቡክ’ ትዳሯን አስፈትቶ አሜሪካ መውሰዱን ‘ሰማሁ! አየሁ!’ ይለኛል። ‹‹ይኼ ‘ፌስቡክ’ መጣ ሲባል ‘የእነ ሶቅራጥስ የሙግት መንደር ወደ ዓለምነት ሰፋ’ እንዳልተባለ፣ ሰማንያ መፈራረሚያና ማቃደጃ ሆኖ ይረፍ?›› ሲለኝ ‘ምነው የሰው አፍ ባልቦላ በኖረውና ‘ኤልፓ’ በነካ እጁ ይኼን ሰውዬ ጭጭ አድርጎ ሳምንት ቢያሰነብትልኝ’ እላለሁ በልቤ። አንድም ለሥራ ሲሆን ድርግም እያለ ለወሬና ለዋዛ ሲሆን ኃይል እየጨመረ፣ የአንፖል ወጪያችንን ለኑሮአችን ከምንመድበው እኩል ያገሸበብን መብራት ኃይል ሳይሆን ይቀራል ነገሩን የሚያባብሰው?
እናላችሁ ያልኳችሁን ገልባጭ ጉዳይ ከዳር አድርሼ መገናኛ አካባቢ ጥሩ ይዞታ ያለው ቪላ ላሻሽጥ ደንበኞች ቀጥሬያለሁ። ገልባጩን በእጁ ያስገባው ደንበኛዬ የአውቶሞቢል ማሽከርከሪያ ፈቃዱ ጠፍቶ ኖሮ፣ ወደ መንገድ ትራንስፖርት ስለሚያመራ በዚያው ገፋ ሊያደርገኝ ተስማምተን ተጓዝን። ሰው መቼም በሕይወቱ ዘመን ከሰው ጋር አንድ ዕርምጃም ቢሆን ከተጓዘ መወዳጀቱ ግልጽ ነው። እንዳጋጣሚ ቤቱን ላሳያቸው የቀጠርኳቸው ሰዎች ትንሽ እንደሚያረፍዱ ደውለው ስለነገሩኝ የዕለት ወዳጄንና ደንበኛዬን ተከተልኩ። ሕጋዊ መንጃ ፈቃድ እንደነበረው ተረጋግጦ፣ የመታወቂያው ቁጥር ተጽፎ ሲሰጠው፣ “ቁጥሩንማ አውቀዋለሁ” እያለ “በቃ?” ሲል ሒደቱ ማብቃቱን ለማረጋገጥ ጠየቀ። “በቃ!” አሉት። ‹‹ሌላ ምንም የሚጠበቅብኝ ነገር የለም?›› ደግሞ ጠየቀ። “የለም!” አሉት። ተያይዘን አቅራቢያው ወዳለ ጣቢያ ሄድን። “የለም ‘ፋይልህ ኮፒ’ ሆኖ ሲያበቃ ሕጋዊ መንጃ ፈቃድ እንደነበረህ የሚገልጽ ደብዳቤ እንዴት ሳትይዝ መጣህ? ተመለስ፤›› አሉት። ‘ብርቅ ነው እንዴ መመላለስ?’ ስትሉ ሰማሁ?
በበኩሌ ቤቱን ዛሬ መጥተን እናያለን ያሉኝ ደንበኞቼ ደርሰናል ብለው እስኪደውሉ እየተጠባበቅኩ ነው። ሆኖም ሞባይሌ ድብርት ውስጥ የገባች ይመስል ጭጭ ማለቷ ገርሞኝ፣ ‘ደግሞ በግለሰብ ስልክ መስመር ላይ ማስደገም ተጀመረ? ወይስ ሕገወጥ ደላሎች ላይ የወረደው የዶፍ እርግማን ወደኛ አካፋ ይሆን?’ እያልኩ ደወልኩ። ደንበኞቼ ስልካቸው ዝግ ነው። ‘ይኼ ሆነ የለ፣ ይቅርታ የለ፣ ምን የለ፣ ምን የለ። ሰዎቹ እንደ ሰሞነኛ ተከሳሾች ተጠራርገው እስር ቤት ገቡ እንዴ እያልኩ ከራሴ ጋር እየተነጋገርኩ ወደ ወዳጄ ዘወር ስል፣ ‹‹በቃ ስላችሁ በቃ አላላችሁኝም?›› ይላል። “አላልንህም!” ይመልሳሉ ሰዎቹ በመተባበር። ‹‹እንዴ! ልሂድ ወይ? ጨረስኩ ወይ? ስል ሂድ አላላችሁኝም?›› አሁንም ሦስቱም ተባባሪዎች “አላልንህም፤” ይላሉ። ምስክር መሆን የምችል ሰው እኔ አለሁ እኮ። ሆኖም፣ ‹‹እሺ አሁን ጭቅጭቁን ትተን ምንድነው ማድረግ ያለብኝ?›› ብሎ ለመፍትሔ ቢቻኮል፣ ‹‹የሥራ መውጫ ሰዓት ደርሷል። ነገ ና!›› አሉት ይባላል። ተረት ነውና የሚመስለው የእኛ ዕድሜና ውሎ ጨዋታዬም ተረት ይምሰል ብዬ ‘ይባላል’ በማለት አጋጣሚዬን ደመደምኩ። እስኪ ተረቴን ሳትመልሱ ከተረታችሁ ጋር አነፃፅሩ! አፌን በዳቦ አብሱ ብዬ አይዟችሁ የማዝበት ዘመን ማለፉን አውቃለሁ!
በሉ እንሰነባበት። ጊዜዬ እንዲህ እንደነገርኳችሁ እንደ ግንቦት ፀሐይ ተቃጥሎ መልሶ እኔኑ ሲያቃጥለኝ፣ አንጀቴ ድብን እያለ ወደ ቤቴ አዘገምኩ። ስደርስ ማንጠግቦሽ እንደ ወትሮዋ በመተሳሰብና በፍቅር ያሞቅናትን ቤት አሰነዳድታ ራት ስታቀራርብ አላገኘኋትም። ሶፋው ላይ ጋቢዋን ለብሳ እንደ ዘንግ በሚሳብ አንገቷ ላቧ እንደ ፏፏቴ ወደ ደረቷና ጀርባዋ እያሳበረ ወርዶ ልብሷ ውኃ ሆኖ ደረስኩ። ይህን ሳይ ስታሊን መቃብር ፈንቅሎ ተነስቶ ዳግማዊ ትሮትስኪው እኔ እመስል፣ መሀል አናቴን በመጥረቢያ የፈለጠኝ መስሎኝ አናቴን ዳበስኩ። ፈላጭና ቆራጭ ዓይነቱና መልኩ በዝቶ ወገንን ለመከራ እየዳረገ ሚዲያውን ሁሉ እጅ እጅ ባስባለበት በዚህ ጊዜ፣ ‘እንዴት ስታሊን የትሮትስኪን አናት ያስፈለጠበት መጥረቢያ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ቤት መጣ?’ ብዬ እንዳሰብኩ ሊገባኝ አልቻለም። ወዲያው ጠጋ ብዬ ‹‹ምነው? ምንሆንሽብኝ?›› ስላት “ጨጓራዬን” አለችኝ። አጠገቧ ምንም የለም። ክሊኒክ እስክወስዳት ቢያስታግስላት ብዬ ወተት ልገዛ ወደ ሱቅ ሮጥኩ። “ወተት” ስለው ባለሱቁ ፈገግ ብሎ “ቢራ ነው ያለኝ. . . ” ብሎ ዓይነቱን ይዘረዝርልኝ ጀመር። ወተትና ቢራ ጎን ለጎን እየተሸጡ ታዳጊዎቻችንን ‹ከ18 ዓመት በታች የተከለከለ› እያልን እንሸነግላለን፡፡ በሌላ በኩል ለአቅመ አዳምና ሔዋን ያልደረሱ ልጆችን ቢራ እንዲገዙ እየላክን እንፈታተናቸዋለን፡፡ ከዚያም አለፍ ሲል ደግሞ ከእኛ የተረፈ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እየጋትን እርስ በርስ እናባላቸዋለን፡፡ በፍቅርና በይቅር ባይነት ክፉ ድርጊቶችን እንሻገር ተብሎ ሲለመን፣ የዘመናት ተረቶችንና ዝባዝንኬዎችን እየጎተትን ንፁኃንን እንማግዳለን፡፡ ይህንን እያውጠነጠንኩ ቆሜ ስወዛገብ ውድ ባለቤቴ ጨጓራዋ እየነደደ ነበር፡፡ አገሬም እንዲህ እርር ትክን ስትል ታየኝ፡፡ ገብስ ገብሱን ላውራ ብዬ ጭራሽ ሌላ ነገር ውስጥ ገብቻለሁ ለካ፡፡ ማን ነበር ‹ሮጠን ብንቀድምም ቆመን እየጠበቅን ነው› ያለው፡፡ እስቲ እናንተ ፈልጉት፡፡ መልካም ሰንበት!