Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መካሪ አያሳጣ!

እነሆ መንገድ! ከመሪ ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ግጭት በማስቆም ሰላም ለማስፈን ውይይት ሊደረግ ነው፤” ይላል የሬዲዮ ጋዜጠኛው። “ዝንት ዓለም ውይይት! ዝንት ዓለም ስብሰባ! በስብሰባ ብቻ ነው እንዴ ሰላም የሚሰፍነው? ጥፋተኛን ለሕግ እያቀረቡ፣ በዳይ በይፋ ይቅርታ እየጠየቀ፣ ተበዳይ እየተካሰና የሕግ የበላይነት እየተከበረ እኮ ነው ሰላም አስተማማኝ የሚሆነው፡፡ ማዶ ለማዶ ተሁኖ እየተዛዛቱ የምን ውይይት ነው? ሁሉም ችግር የሚፈታው እንደ ዘበት በወሬ ይመስላቸዋል . . .” ይላሉ አንድ አዛውንት ተቆጥተው። “እና እርስዎ ምን መደረግ አለበት ነው የሚሉት?” አላቸው ገና ተሳፍሮ አጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት። “ዘመኑ የፍጥነትና የውድድር ነው እያላችሁ፣ ፍጥነትና ውድድርን ሁሉ ነገር ውስጥ ማስገባት ተው፡፡ አንተ አሁን የዘረዘርኩትን ነገር መቼ በቅጡ ሰማህና ነው ልጄ? ዘላችሁ ጥልቅ ከማለት በፊት ማዳመጥ ልመዱ፡፡ ችግር ፈጣሪ የመፍትሔ አካል ስለማይሆን፣ በምክንያታዊነት ሁሌም ራሳችሁን አዘጋጁ፣ ዩኒቨርሲቲን ሳይቀር በዱላ መናረቻ እያደረጋችሁ አታስቁቡን . . .” ብለው እየነገሩን ሳለ ብን ብን የምትል ሳላቸው ታጣድፋቸው ጀመር።

ወያላው ወዲያ ወዲህ እየተሯሯጠ ይጮሃል። ሾፌሩ ሞተር እያሞቀ በሞባይል ስልኩ ያወራል። “እኔ ለትምህርት ቤት ክፈይ ብያት እኮ ነው እሷ የዓመቱ ነው ብላ  የደገሰችው? እንዴ እኔ ከማያስብልኝ ሰው ጋር እንዴት እኖራለሁ?” ይላል። “እህ እና የምታምነውን ታቦት ላትደግስ ኖሯል? እሱ ሰይፍ ታጣቂው ሲጠሩት የማይዘገይ ባይኖርልን የዘንድሮን ነገር ብቻችንን እንችለዋለን? ምን ይላል ይኼ?” ይላሉ አዛውንቱ አሁንም ከሳላቸው ጋር እየታገሉ። ሾፌሩ ድምፁን ቀነስ አድርጎ፣ “ብቻ ምከሩዋት እኔ በዚህ ኑሮ ቀኑን ሙሉ አንድ መቀመጫ ላይ ተቀምጬ በፀሐይ ስቀቀል እየዋልኩ፣ እሷ ከልጆችዋ በፊት የምታስቀድመው ነገር ካላት ልንግባባ አንችልም። ሲኖር ምንም አይደል፣ ከሌለ እኮ ሁሉን የሚያውቅ አምላክ እንደ ሰው አይደለም ለምን ይቀየማል?” ብሎ ስልኩን ይዘጋል። ወያላው ወዲያው “ሞልቷል” ብሎ በሩን ከረቸመው። ከሾፌሩ ጋር ሁለት ሴቶች፣ ከጀርባው አዛውንቱና ወጣቱ ተሰይመዋል። ከእነሱ ጀርባ እኔና አንዲት ወይዘሮ አለን። ከኋላችን አንድ ጎልማሳ ከተማሪ ሴት ልጁ ጋር ተሰይሟል። መጨረሻ ወንበር አንዲት እናት አፍ የፈታች ሕፃን ልጇን ታቅፋ ከሦስት ወጣቶች ጋር ተጣባ ተቀምጣለች። ጉዟችን ተጀምሯል።

አዛወንቱና ወጣቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባብተው ጨዋታቸው ደርቷል። “እሱ ያልባረከው ኑሮ ምን ቢቆጠብለትና ቢታቀድለት ያዋጣ መስሎህ ነው? አይምሰልህ! የዘንድሮ ልጆች ለገንዘብ ብቻ እንጂ ለእምነት፣ ለባህል፣ ለትውፊትና ለአብሮነት ጉጉት የላችሁም። መስሏችሁ ነው . . .” ይሉታል። ወጣቱ በበኩሉ፣ “ኧረ እንደ እሱ አይደለም አባት! ፈጣሪ እኮ የብርና የወርቅ ችግር የለበትም። የእሱ ችግር የልብ ነው። ሰው ልቡን ከሰጠው ሌላ አይፈልግም። ደግሞ የቄሳሩንና የእግዜሩን መለየት ጥበበኝነት እንጂ ደንታ ቢስነት አይመስለኝም፤” ብሎ ይሞግታቸዋል። “ተወኝ እስኪ! እናንተና መንግሥት መቼም መልስ አታጡም። ምንም እንኳ መልስ ባይሆንም መልሳችሁ ግትር ነው . . .” እያሉት ሳላቸው ፀናባቸው።

ይኼን ጊዜ ከመጨረሻ ወንበር ወሬ ሰማንና ጆሯችን ወደዚያ ተጣደ። “ሚሚዬ ስምሽ ማን ነው?” አንደኛው ወጣት የታቀፈችዋን ሕፃን ያናግራታል። “አንጀሊና!” መለሰች ሚሚዬ እየተኮላተፈች። “እ?” ልጁ ደገመና ጠየቃት። “ስምን ሆሊውድ ያወጣዋል ማለት መጀመራችን እኮ ነው?” ይላል አንደኛው ጓደኛው። “እስኪ ወደፊት ምን መሆን ነው የምትፈልጊው ንገሪኝ?” እያባበለ በስሟ ቅስሙ የተሰበረው ወጣት በራዕይዋ ሊፅናና ሲጠይቃት፣ “ሞዴል!” ብላ መለሰችለት። ወጣቱ ጥያቄውን ቢያቆም እንደሚሻል አምኖ ግንባርዋን ሳመና ወደ ጓደኞቹ ዞረ። “አልሰማኋትም ምን አለች?” አለው ጓደኛው። “አንተ ደግሞ ደህና ደህና ነገር አትሰማም! ሞዴል አለችህ፤” አለው ሦስተኛው። “እሱንማ ሰምቻለሁ ግን ሞዴል ምን? አርሶ አደር? ተዋናይ? ነጋዴ? ዘራፊ . . .” እያለ ዘንዶ ሊጎትት አጥብቆ ሲጠይቅ ጓደኛው ‘እረፍ’ አለው። ዘንድሮስ ተስፋም የሚደረግበት ነገር የተነጠቅን ነው የምንመስለው፡፡

ሲኤምሲ አካባቢ ስንደርስ ጋቢና የተቀመጡት ሁለቱ ሴቶች “ወራጅ” ብለው ወረዱ። ሁለቱም የለበሱት ቀሚስ እጅግ በጣም አጭር ስለነበር ሲወርዱም ሆነ ሲሳፈሩ የሚያያቸውን አስበርግገዋል። ወያላው “ፓ! ኑሮዬ እንዲህ ሲኒማ ባይሆንልኝ ኖሮ በፓስቲና በሽሮ ብቻ እንዴት እገፋው ነበር?” ሲል ሾፌሩን አናገረው። ሾፌሩ ግን የባለቤቱ ጉዳይ አዕምሮውን የተቆጣጠረው ይመስላል አልመለሰለትም። “እናንተን እያየ በስንት ትግል ያገኘነውን እኩልነትና መብት ሲያቃልል የሚውለው ስንቱ ይሆን?” አሉ አጠገቤ የተቀመጡት ወይዘሮ። ከጀርባችን ደግሞ ጎልማሳው ወደ ደረሰች ኮረዳ ልጁ አፍጥጦ፣ “ታያለሽ አንቺ እንደዚህ የለበስሽ ቀን አባት የለሽም፣ እኔም ልጅ የለኝም፤” ይላታል።

በወረዱት ሴቶች ተተክታ የተሳፈረች እህት ጋቢና እየተመቻቸች፣ “እኛም እንዲህ ተጋልጠን እየለበስን መውጣታችን ጥሩ ባይሆንም፣ ይህንን ምክንያት በማድረግ መተንኮስ ወይም ሌላ ድርጊት ለመፈጸም መሞከር ግን ወንጀል ነው!” ብትለው ሾፌሩን፣ ከእንቅልፉ እንደቀሰቀሱት ሁሉ እየተደናበረ፣ “ምን አልሽኝ? የምን ወንጀል?” ብሏት አረፈው። “በል ተወው! እናንተማ ምን አለባችሁ እንደ ልባችሁ የፈቀዳችሁትን ታስባላችሁ፣ ታደርጋላችሁ። እኛ ሴቶች ነን እንጂ የማንም ወንበዴ ነውረኛ ደፋሪ ሰለባ የምንሆነው፤” ብላ በረጅሙ ተነፈሰች። ስለመደፈር ሲነሳ ወዲህ ደግሞ ጨዋታው ደርቷል። “ሰው ግን እንዴት ጨካኝ ሆኗል?” አለች ልጅ የታቀፈችው እናት። “እኔስ ይኼን ይኼን ስሰማ ሴት ልጅ መውለዴ ያሳስበኛል፤” ብትል ጎልማሳው ዘወር ብሎ፣ “አይምሰልሽ ልጅ በልጅነቱ ያስያዙትንና ያስተማሩትን አይረሳም። የራስን ኃላፊነት መወጣትና መከታተል እንጂ፣ ከዚህ አልፎ ለሚሆነው በወለዱት ልጅ ፆታ ማሳበብ አያስኬድም፤” ብሏት ‘ወራጅ’ አለ። ታክሲያችን ስትቆም አዛውንቱ፣ “ጊዜው የሰይጣን ሆኖ እንጂ እውነት ከአስተዳደግና ከሕግ አስከባሪዎች አቅም በላይ ሆኖ ነው ይኼን ሁሉ ጉድ የምንሰማው?” ይላሉ። ሌላውም እንደ ራሱ አመለካከትና እምነት የሚጠይቀውን ይጠይቃል። ጎዳናው ጊዜን ያስተቻል ጊዜ ደግሞ መልሶ ወደ እኛ ይጠቁማል፡፡ አዛውንቱ ግን፣ ‹‹ሆኖም ከሴት ልጆቻችን ጎን ቆመን ጥቃትን መመከት ብቻ ሳይሆን፣ እስከ መጨረሻው መፋለም አለብን!›› ሲሉ ሁሉም ተሳፋሪዎች አጨበጨቡላቸው፡፡ እንዲህ ነው እንጂ መተባበር!

ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። በጎልማሳውና በልጁ ምትክ ሁለት ወጣቶች ገብተው ተሰይመዋል። “ኧረ እንኳን እግዚአብሔር አተረፈህ!” ይላል አንደኛው። “በጣም እንጂ! እኔ አሁን እንኳን እንደ አህያ የምረገጥ ጥፊ አይበዛብኝም?” ሲል ከፍተኛ ድብደባ እንደ ደረሰበት ገባን። “ቆይ ግን ፀቡ በምን ተጀመረ? መቼም እዚህ አገር ስብሰባና ውይይት የማይፈልግ ነገር ፀብና ጭፈራ ብቻ ነው፤” አለ ወዳጁ። አጠገቤ የተቀመጡት ወይዘሮ፣ “እንዲያ ነው እንጂ! የዘንድሮ ምረጡኝ ደግሞ ከቅስቀሳው ስድቡ ብሶበታል፤” ይሉኛል ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብለው። ምኑን ከምን አገናኝተው ከምርጫ እንዳደረሱት ግን አልገባኝም። “ይኼውልህ እኔ ሱቄን እየዘጋሁ ነው፤” ተደብዳቢው ታሪኩን በአጭሩ ይናዘዛል። “አላየኋቸውም፣ ዘወር ስል ጭንቅሎን ያሯሩጡታል። ‘ኧረ በፈጠራችሁ ምንም አቅም የሌለው ልጅ ነው ተውት!’ ብዬ ልገላግል ስገባ እኔን ይዘው እንካ ቅመስ። የእኔ ስም ተጠርቶ ሲጮህ የሰማው ታላቅ ወንድሜ ዘሎ ሲወጣ እሱንም ይዘው ቀጠቀጡት። የሚገርምህ እኮ ‘ፌንት’ ሠርቼ ወድቄ በእግሩ አንገቴን ረግጦ ድንጋይ ሊጭንብኝ ሲል እኮ ነው ሰው ያተረፈኝ . . .” ብሎ ሳይጨርስ፣ “በስመ አብ ወልድ ምነው ከሰው ጋር ነው የተጣላኸው ወይስ ከእንስሳ ጋር?” ብለው አዛውንቱ ጠየቁት። “ምኑን አውቄ አባት? ሁሉም የተቀላቀለበት ዘመን አይደል?” አላቸው። ምን ይበል ታዲያ!

ወዲያው ትረካው ለመላው የታክሲዋ ታዳሚዎች ሆነና አረፈው። “ከዚያ ይኼንን ጆሮዬን አያችሁት? ስለተሰነጠቀ ለማስፋት አንድ አንጋፋ ሆስፒታል ብሄድ ማደንዘዣ የሚባል ነገር የለም። ዶክተሩ ‘የማደንዘዣ ያለህ’ ቢል ማን ይስማው? ሆስፒታል የወሰዱኝ ሰዎች ሮጠው ሄደው ሁለት ማደንዘዣ ገዝተው፣ አንዱን ሌላ ጊዜ እንዳትቸገር ብለው ሰጡት። ይኼውላችሁ እንዲህ የምታዩኝ በቸርነቱ ተርፌ እንጂ በሕግና በአፋጣኝ ሕክምና አይደለም፤” ብሎ ፈገግ አሰኝቶን አበቃ። እሱ ቢያበቃም የእሱ ዕጣ በምን ሰዓት ለማናችን እንደምትወጣ የማናውቅ ተሳፋሪዎች በሐሳብ መወዝወዛችን አላበቃም። ‹‹የሕክምና ነገር ሲነሳ ሕይወት አድን መድኃኒቶች በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ምክንያት ከፋርማሲ ጠፍተው ሕሙማን ሲሰቃዩ እኮ፣ ምድረ ሌባና ዘራፊ ዶላር ወደ ውጭ እያሸሸ የደረሰው መከራ እንዴት ይረሳል?›› የሚሉት አዛውንቱ ናቸው በሐሳብ ተመስጠው ከቆዩ በኋላ፡፡

ወደ መዳረሻችን ነን። መገናኛ እየደረስን ነው። በተዓምር የተረፈው ወጣት ገጠመኝ መላውን የታክሲ ተሳፋሪ ረብሾታል። “አያድርስ እንዲያው ሰውን ግን ምን ነካው? መተዛዘን እንደዚህ ብርቅ ሊሆን ጫፍ ደረሰ?” ስትል መጨረሻ ወንበር ላይ ልጇን ታቅፋ ራሷን እየዳበሰች አጠገቧ ከተቀመጡ ወጣቶች አንዱ፣ “ልብ ብለን ካየነው እኮ በየአቅጣጫው ለችግራችን መባባስ ተጠያቂው ራሳችን ነን፡፡ አገር ከመገንባት በፊት ራሳችንን ለመገንባት እንሮጣለን፤” አለ፡፡ “እንዴት?” አለው ተደብዳቢው አገጋሚ። “የመልካም አስተዳደር ችግር የእኛው የባህሪ ችግር ነው። ተቋም የሰዎች ስብስብ ነው። ቀበሌና ክፍለ ከተማ ስትሄድ የሚያስተናግድህ ሰው ነው። ያውም ማሰብና ማመዛዘን የሚችል የሰው ልጅ። ሰው ለህሊናው ሲል እንኳን በክፉ ጊዜ ይተባበራል። ሰው ራሱን ችግር ውስጥ ከቶ የሚረዳዳ ፍጡርም ነው። በናዚ ጊዜ ብዙ ጀርመኖች አይሁዶችን ደብቀው ከዕልቂት አትርፈዋል። እኛ ለአንድ ጉዳይ አንዲት የወረቀት ሥራ ለማስፈጸም ፍዳ ስናይ ምን ይባላል? ሌብነቱም እንዲያ ነው። ሰው ጠፋ ለሀቅ የሚቆም። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚሰፍነውና በነፃነት መኖር የሚቻለው እኮ፣ መጀመሪያ ራሱን አክብሮ ሌሎችን የሚያከብር ሰው ሲታነፅ ነው፤” ብሎ ዝም አለ። ወዲያው ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። እኛ አስተዋይ አዛውንት ሲሰናበቱን፣ ‹‹ሁላችንንም እንደ ሥራችን የሚጠይቀን ፈጣሪ ነው፡፡ ፈጣሪ ደግሞ ውሎው ከእውነት እንጂ ከሐሰት ጋር አይደለም፡፡ እውነት ዘንድ ለመገኘት ሀቀኛ መሆን ግድ ነው፡፡ ሀቀኛ ስንሆን እውነት ቅርብ ስለሆነች ሀቅን ፈልጉ፣ ያኔ ፈጣሪ ከአጠገባችሁ አይለይም፤›› ብለው መከሩን፡፡ መካሪ አያሳጣ! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት