Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ በተካሄዱ ሰላማዊ ሠልፎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙና መብት እንዲከበር ጥያቄዎች ቀረቡ

በኦሮሚያ በተካሄዱ ሰላማዊ ሠልፎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙና መብት እንዲከበር ጥያቄዎች ቀረቡ

ቀን:

ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠሩ ከ200 በላይ ግለሰቦች ተይዘዋል

ከአሥር በላይ በሚሆኑ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በርካታ ሕዝብ በተሳተፈባቸው ሰላማዊ ሠልፎች፣ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙና የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም እንዲከበር ጥያቄዎች ቀረቡ። በሰላማዊ ሠልፎቹ ላይ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ግድያዎችና ማፈናቀሎች ይቁሙ፣ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ፣ የኦሮሞ ገበሬዎች ከመሬታቸው አይፈናቀሉና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ወጣቶች፣ ተማሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞችና የክልሉ ፖሊስ አባላት ጭምር በተሳተፉባቸው በእነዚህ ሰላማዊ ሠልፎች የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚመራውን ሕዝብ ደኅንነት፣ መብትና ጥቅም በማስከበር ረገድ ቸልተኝነት እንደሚታይበት የሚገልጹ ወቀሳዎችም ተሰንዝረዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሰላማዊ ሠልፎቹ ከተካሄዱባቸው አካባቢዎች መካከል አምቦ፣ ጊምቢ፣ አደአ በርጋ፣ ሆለታ፣ ቡራዩ፣ ባኮ፣ መቱ፣ መንዲና በደሌ ይገኙበታል።

በሁሉም አካባቢዎች በተካሄዱት ሠልፎች በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሠልፈኞቹን ወደ አደባባይ ገፍቶ ያስወጣቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ አካባቢዎች በቅርቡ ማንነታቸው በግልጽ ያልታወቀ ታጣቂዎች፣ በኦሮሞ ተወላጆችና በኦሮሚያ ክልል የፖሊስ አባላት ላይ በከፈቱት ጥቃት በርካቶች መገደላቸው ነው።

ሰላማዊ ሠልፈኞቹ በተለያዩ የኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ይኼንን ድርጊት የፈጸሙ አካላት በፍጥነት ለሕግ ይቅረቡ የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ጥቃቶቹ እንደሚፈጸሙ ግልጽ የሆኑ አዝማሚያዎችን እየተመለከተ ቸልተኛ መሆኑን በመጥቀስም አውግዘዋል።

በተጨማሪም የክልሉ የፖሊስ ኃይል የኦሮሞ ሕዝብን ማስጠበቅ በሚያስችለው ደረጃ እንዲታጠቅም ሠልፈኞቹ ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች በኦሮሞዎች ላይ በሚሰነዘሩ ጥቃቶችና ማፈናቀሎች ምክንያት፣ በመጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በፍጥነት ወደ ቀዬዎቻቸው በመመለስ እንዲያቋቁሙም አሳስበዋል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተካሄዱትን ሠልፎች አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ሠልፎቹ ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቃቸውን በመግለጽ፣ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ የሚገኘውን የሕግ ማስከበር ተግባር አስታውቋል።

ቢሮው ባወጣው መግለጫ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ያጋጠመው የፀጥታ ችግር እንዲቆም የኦሮሚያ ክልል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር እየሠራ ቢሆንም፣ የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት በተቀናጀ መንገድ በሥልጠናና በተለያዩ ጦር መሣሪያዎች በመደገፍ በሕዝቡ ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ገልጿል። ችግሩን በፍጥነት መግታት ባለመቻሉ በሁለቱ ክልሎች ስምምነትና የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ኅዳር 21 ቀን 2011 ዓ.ም. የፌደራል የፀጥታ አካላት ችግር ባጋጠማቸው አካባቢዎች እንዲሰማሩ በወሰነው መሠረት፣ የፀጥታ ኃይሎች መሰማራታቸውንና ዕርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

እስከ ሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በተወሰደው ዕርምጃም በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በምዕራብ ወለጋ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠሩ፣ ከ200 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ቢሮው አስታውቋል።

በምዕራብ በኩልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች እያጋጠመ ካለው የፀጥታ ችግር ጀርባ ለዓመታት ሕዝቡን ሲያሰቃዩ የነበሩ፣ አሁን በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥና ሕግ የማስከበር ዕርምጃ ለማደናቀፍ እየተጣጣሩ መሆናቸውን የኦሮሞ ሕዝብ መዘንጋት እንደሌለበትም በመግለጫው አሳስቧል።

በተጨማሪም ኅብረተሰቡ መንግሥት ሰላም እንዳይሰፍን እያደረጉ ያሉ አካላት ላይ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ እንዲፋጠን በማድረግ፣ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና መፈናቀል እንዲቆም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪውን አስተላልፏል።

 በተወሰኑ አካባቢዎች በተካሄዱ ሰላማዊ ሠልፎች የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ አባላት በመሳተፍ፣ የክልሉ መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር መጠየቃቸው በርካቶችን እያነጋገረ ነው።

ሰላማዊ ሠልፎች ከመካሄዳቸው አስቀድሞ ማለትም ኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ፣ በሁሉም የኦሮሚያ ክልል መዋቅሮች ከሚገኙ ከፍተኛ የክልሉ ፖሊስ አዛዦች ጋር ውይይት አካሂደው ነበር።

በዚህ ውይይት ላይ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለማየሁ እጅጉ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ደረጃው ቢለያይም በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የፀጥታ ችግር እንደሚስተዋል አመልክተዋል።

የፀጥታ ችግሮቹን በመፍታት ረገድ የክልሉ ፖሊስ ድክመት እንደታየበት በወቅቱ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ከፖሊስ ሠራዊቱ አመራሮች ጀምሮ ውስጣችንን ማየት ይገባናል፤›› ማለታቸውን የክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቦ ነበር። ይኼንን ውይይት የመሩት አቶ ለማ መገርሳም ለፖሊስ አመራሮች ጥብቅ ማሳሳቢያ ሲሰጡ ተደምጠዋል።

ፖሊስ ሕግን በማክበር ሕግን የሚያስከብር እንጂ ጊዜና ቦታ የሚቀይረው አይደለም ሲሉ የተደመጡት አቶ ለማ፣ ‹‹የኦሮሚያ ፖሊስ የክልሉ መንግሥት ኃይል እንጂ የየትኛውም የፖለቲካ ኃይል አይደለም፣ ስለሆነም የየትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ዓርማ ይዞ ፎቶ መነሳት የለበትም፣ የእሱ ዓርማ የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ ነው፤›› በማለት አሳስበው ነበር።

ፖሊስ በወንጀለኞች የሚፈራ ነገር ግን የሕዝብ አመኔታ ኖሮት በአለኝታነት ተስፋ የሚጣልበት ሊሆን እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ለማ፣ የክልሉ ፖሊስ አደረጃጀቱን በማጠናከር አባላቱ ከአመራሩ የሚተላለፈውን ትዕዛዝ በመቀበል በመረጃ ብቁ ሆኖ ሊፈጽም እንደሚገባ መመርያ አስተላልፈው ነበር።

አቶ ለማ ከክልሉ ፖሊስ አመራሮች ጋር ካደረጉት ውይይት በተጨማሪ ከሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች ከተወጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በዚያው ሳምንት በአዳማ ከተማ የሰላም ኮንፈረንስ፣ የክልሉን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታና የማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በተመለከተ ውይይት በማካሄድ፣ ክልሉ ሕግ ማስከበርን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስረድተው ነበር።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ ማክሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፣ የክልሉ ሕዝብ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና የአገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥ እያቀረበ ባለው ጥያቄ መሠረት ዕርምጃዎች መወሰድ መጀመራቸውንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ የተፈጠረውን ችግር ከምንጩ ለመቅረፍ እየተከናወነ ባለው ዕርምጃ፣ ለጥፋት ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር የሚጥሩትን በንቃት እንዲከላከል ለሕዝቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ግድያና ማፈናቀልን ለማስቆም፣ እንዲሁም ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ለፀጥታ ኃይሎች ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...