Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሕዝብ ዕንባ ጠባቂን ሥልጣን የሚያጠናክርና በማይተባበሩት ላይ ጥብቅ ቅጣት የሚጥል አዋጅ ቀረበ

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂን ሥልጣን የሚያጠናክርና በማይተባበሩት ላይ ጥብቅ ቅጣት የሚጥል አዋጅ ቀረበ

ቀን:

የውጭ የንግድ ተቋማትም አቤቱታ ማቅረብ እንዲችሉ ይፈቅዳል

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያጠናክርና ተቋሙ ኃላፊነቱን እንዲወጣና ውሳኔዎቹን ለመፈጸም በማይተባበሩ ላይ የእስር ቅጣት የሚጥል ረቂቅ የማቋቋሚያ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ምክር ቤቱ ማክሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ውይይት የቀረበው የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን የሚያሻሽል ረቂቅ ነው፡፡ የአስተዳደር በደል በመንግሥት አካላት እንዳይፈጸምና ተፈጽሞ ሲገኝም በአፋጣኝ እንዲታረም፣ በተቋሙ የሚሰጡ የመፍትሔ ሐሳቦች እንዳይፈጸሙ መሰናክል የነበሩ ክፍተቶችን ለማስወገድ ማለሙን የረቂቅ ሰነዱ መግቢያ ያስረዳል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ከተቋቋመ ከ15 ዓመት በላይ ያሳለፈ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተቋሙ ዋነኛ ችግር ከሆኑት ውስጥ አንዱ ተቋሙ ፍትሐዊ ውሳኔ መስጠት እንዲያስችለው አቤቱታ ከቀረበባቸው የመንግሥት አካላት ማስረጃ ማግኘት አለመቻሉ፣ እንዲሁም የምርመራ ሥራውን አስቸጋሪና ረዥም ጊዜ እንዲወሰድ በማጓተት ዜጓችን ፍትሕ የሚያሳጡ መሆኑ በችግርነት መለየቱን የረቂቁ አባሪ የሆነው ማብራሪያ ሰነድ ያስረዳል።

በተጨማሪም ተቋሙ የቀረቡለትን አቤቱታዎች በመመርመር የመፍትሔ ውሳኔ ሲያሳልፍ ቢቆይም፣ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ውሳኔ የተላለፈባቸው የመንግሥት አካላት ውሳኔውን ለመፈጸም እንደሚቸገሩ የሚገልጽ ምላሽ ካቀረቡ ምን ሊደረግ እንደሚገባ የሚያስቀምጠው ድንጋጌ ባለመኖሩ፣ በደል መድረሱ ተረጋግጦ ሳይፈጸም እንደሚቀር ይህም በተበዳዮች ላይ ተጨማሪ በደል ሆኖ መቆየቱን አባሪ ሰነዱ ያትታል።

እነዚህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተቋሙ አግባብነት ያላቸውን ሰነዶች ወይም ማስረጃዎች እንዲያቀርቡ ወይም መልስ እንዲሰጡ ሲጠየቁ፣ የተጠየቀው አካል በተሟላ አግባብ የማቅረብ ግዴታ እንዲጣል በረቂቁ በድንጋጌ መልክ ቀርቧል። አስፈጻሚ አካላት ተቋሙ በምርመራ ላይ ተመሥርቶ የሚያሳልፈውን ውሳኔ በ30 ቀናት ውስጥ የመፈጸም ግዴታ እንዲጣልባቸውም በሕግ ሰነዱ የቀረበ ሲሆን፣ የመፍትሔ ዕርምጃውን ለመውሰድ ካልተቻለ ከበቂ ምክንያት ጋር ለተቋሙ በ30 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቁ እንዲገደዱ በማሻሻያነት ቀርቧል።

ሰነዶችን ወይም ማስረጃዎችን ተጠይቆ ተቋሙ በጠየቀው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያላቀረበና በተቋሙ የሚቀርበውን የመፍትሔ ሐሳብ ያለበቂ ምክንያት በ30 ቀናት ውስጥ ሳይፈጽም የቀረ የመንግሥት ተቋም ኃላፊ፣ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በአሥር ሺሕ ብር መቀጮ ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ በረቂቁ ድንጋጌ ሆኖ ቀርቧል።

የተቋሙን የምርምር ወይም የቁጥጥር ሥራ ያደናቀፈ፣ ወይም ምስክሮችና አቤቱታ አቅራቢዎች ወይም በማናቸውም መንገድ ተቋሙን በተባበሩ ወገኖች ላይ ጥቃት ያደረሰ በወንጀል ሕጎች ሊጠየቅ የሚችል ሆኖ፣ በተመሳሳይ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በአሥር ሺሕ ብር እንዲቀጣ በረቂቁ ሰፍሯል።

ተቋሙ ይኼንን ድርጊት መፈጸማቸውን የሚገልጽ ሪፖርት ከእነ ማስረጃዎቹ ለዓቃቤ ሕግ እንደሚያቀርብ፣ ዓቃቤ ሕግም አግባብ ባለው የወንጀል ሕግ ክስ እንደሚመሠርት በረቂቁ ተካቷል።

የአስተዳደር በደሎች በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ የሚሳተፉ የውጭ አገር ዜጎች ላይም የሚደርስ በመሆኑ፣ አቤቱታቸውን ማቅረብ እንዲችሉና መፍትሔ እንዲያገኙ ማሻሻያ ሆኖ ቀርቧል።

ተቋሙ የአስተዳደር በደሎችን ከመከላከልና እንዲታረሙ ከማድረግ በተጨማሪ፣ በመልካም አስተዳደር ላይ ለመንግሥት ምክረ ሐሳብ የማቅረብ ኃላፊነትም እንዲኖረው በረቂቁ ተካቷል። ተቋሙ ለመንግሥት የማማከር ሥራን እንዲያከናውን ተጨማሪ ኃላፊነቱ ሆኖ መቅረቡ፣ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወትና መብታቸውን ከማስጠበቅ አኳያ ያለውን ኃላፊነት በመሻማት አቅም ሊያሳጣው ስለሚችል፣ በዝርዝር እንዲታይ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ረቂቁ በዝርዝር እንዲታይ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...