Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግርግር በመፍጠር በአገሪቱ የተጀመረውን የነፃነት ትግል ለማኮላሸት እንደማይቻል ኦፌኮ ገለጸ

ግርግር በመፍጠር በአገሪቱ የተጀመረውን የነፃነት ትግል ለማኮላሸት እንደማይቻል ኦፌኮ ገለጸ

ቀን:

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ግርግር በመፍጠር ተጠቃሚ ለመሆን የሚሹ ኃይሎች በአገሪቱ የተጀመረውን የነፃነት ትግል ለማኮላሸት እንደማይችሉ፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አስታወቀ፡፡ መንግሥት ጥቃት በፈጸሙ ወንጀለኞችና ጥቃቶችን ቸልተኛ ሆነው ያለፉ የፀጥታ አካላት ላይ ዕርምጃ እንዲወስድም ጠይቋል።

ኦፌኮ ‹‹መንግሥት ሕዝባችንን ከጥቃት፣ ክልላችንን ከመደፈር እንዲታደግ እንጠይቃለን›› ሲል ማክሰኞ ኅዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ምሥራቅ፣ ሰሜን፣ ደቡብና ምዕራብ አቅጣጫዎች በሕዝቦች መሀል የተፈጠሩ ግጭቶች መፍትሔ ሳይበጅላቸው፣ ሰሞኑን ደግሞ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ ልዩ ስሙ አርቁምቤ በሚባል ሥፍራ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ወረዳዎች ከሚነሱ ኃይሎች በኦሮሚያ ፀጥታ አስከባሪዎች ላይ የደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከፍተኛ ሐዘን እንደፈጠረበት አስታውቋል፡፡

በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ትግል እየተፋፋመ ባለበት ወቅትና አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን አጥቶ ልጆቹን ለማብላትም ሆነ ለማስተማር ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት፣ ‹ሥልጣን ከእጃቸው ያመለጣቸው ኃይሎች› ወንድም ወንድሙን እንዲገድል በገንዘብ በመግዛት ሕዝብ በማጋጨት አገር እስከ ማፍረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ ኦፌኮ ሥጋቱ እንደሆነ፣ ይኼንንም በየጊዜው በሚያወጣቸው መግለጫዎችም ሆነ ማሳሰቢያዎች ሲያስጠነቅቅ መቆየቱ አስታውሷል፡፡

‹‹ግርግር በመፍጠር ተጠቃሚ ለመሆን የሚሹ ኃይሎች በአገሪቱ የተጀመረውን የነፃነት ትግል ለማኮላሸት እንደማይችሉ ተገንዝበው ለለውጡ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅዎ ማድረግ ተመራጭ ነው፤›› በማለት ጥሪውን ያቀረበው ኦፌኮ፣ መንግሥት የፀጥታ ችግሮቹን ከሁሉም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን ሊፈታ እንደሚገባ አሳስቧል።

ባወጣው ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫም መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነቱን በመወጣት በየቦታው በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያና ማፈናቀል በአስቸኳይ እንዲያስቆም፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ አካባቢዎች ዘግናኝ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት በቦታው የነበሩት የመከላከያ ኃይል አባላት ጥቃቱን ማስቆም እየቻሉ ይኼንን አለማድረጋቸው የሚያመላክቱ መረጃዎች በመኖራቸው፣ መንግሥት ይኼንኑ አጣርቶ በአስቸኳይ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጥያቄውን አቅርቧል።

መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች ላይ የጀመረውን ወደ ሕግ የማቅረብ ሒደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኦፌኮ የበኩሉን ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም በመግለጫው አመልክቷል።

በግፍ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሕይወት የማዳን ሥራ እየተከናወነ በዘላቂነት የሚቋቋሙበት መንገድ እንዲመቻችና ለሕዝባቸው ነፃነት ሲሉ ሲታገሉ ለተሰው፣ አካላቸው ለጎደለ፣ ቤተሰባቸው ለተበተነና ንብረታቸው ለወደመ ሁሉ በቂ ማካካሻ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችም ኦፌኮ ጥሪውን ለመንግሥት አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...