Thursday, October 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  የዲፕሎማቶቻችን ሹመት በብቃት ላይ ብቻ የተመሠረተ ይሁን

  የመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ያሉባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በተደጋጋሚ አንስተን ጥለናል፡፡ እከሌ ከእከሌ ሳይባል ለሕዝብ አገልግሎት የተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች ብዙዎችን አሰነብተዋል፡፡ አማረዋል፡፡ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ‹‹የመንግሥት ያለህ›› ያስባሉ የመንግሥት ተቋማት ‹‹በሽ›› ናቸው፡፡

  በአንድ ወቅት ከመንግሥታዊ ተቋማት በተለየ ነጥለን ስናሞግሳቸው የነበሩ መሥሪያ ቤቶች ሳይቀሩ እኛ ከማን አንሰን ብለው የቀደመ መልካም ስማቸውን ረስተው ተመሳስለዋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ኢሚግሬሽ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት የነበረው ስሙ ዛሬ ትዝታ ሆኗል፡፡ ዛሬ ፓስፖርት ለማግኘት ያለው ችግር ሲታይ የቀድሞውን ኢሚግሬሽን አሠራር እንዲናፈቅ ያደርጋል፡፡

  ሕዝብን ያማረሩ የተባሉ ተቋማትን መስመር ለማስያዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ቃል በገቡት መሠረት ይለወጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በአንዳንዶቹ ተቋማት ላይ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችላቸው ቁመና ላይ ለማድረስ እየተሠራ  ቢሆንም ዛሬም ምንም ለውጥ የማይታይባቸው፣ ስለመለወጣቸው ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ የማይታይባቸው መኖራቸው ደግሞ ጉዳዩ ትኩረት እንደሚያሻው መጠቆሙ ተገቢ ነው፡፡

  በእርግጥ ይቺ አገር አከማችታ የቆየችው ችግር እንኳን በወራት በዓመታት ሊፈታ የሚችል ያለ መሆኑ ቢታመንም፣ በተቻለ መጠን ቀልጠፍ በማለት የአገልግሎት አሰጣጣችንን ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ ይገባል፡፡

  ከዚህ ጎን ለጎን ግን የአንዳንድ ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ለመቀየር እየተሠራ ያለውን ሥራ ግን ማወደስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በቴሌ የታየው ለውጥ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ያሳየውም ተነሳሽነት መልካም ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ መንግሥታዊ ተቋማት የውስጥ አሠራራቸውን ለማሻሻል እያደረጉ ካለው ጥረት ሌላ በቀደመው ጊዜ ቁብ ለማይሰጡት ጉዳይ ዓይናቸውን እየከፈቱ መሆኑ አንዳንድ የለውጥ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ወትሮ የማኅበራዊ ኃላፊነት ስለመወጣት ትኩረት የሌላቸው ትላልቅ ተቋማት የተቋማቱ መሪዎች ሳይቀሩ እገዛ ወደ ሚሹ ወገኖች ድረስ በመሄድ ድጋፍ መስጠታቸውንና እየሰጡ መሆኑን ልብ ይላል፡፡ ለማንኛውም እስካሁን እያየናቸው ካሉ የለውጥ ሒደቶች ውስጥ በግሌ ትኩረት እንድሰጠው ያደረገኝ ከሰሞኑ ማጠቃለያውን እያገኘ ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አደረጃጀትና መዋቅራዊ ለውጥ ነው፡፡ የአገር ገጽታ በመገንባት ረገድ ትልቅ ኃላፊነት የተሸከመ መሥሪያ ቤት በተሰጠው የኃላፊነት ልክ እየሠራ እንዳልነበር ሲጠቀስ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ በየአገሩ የሚመደቡ ዲፕሎማቶች ለአገሪቱ የሚጠበቅባቸውን ሲሠሩ ነበር ለማለት አይቻልም፡፡

  ከዲፕሎማቶች ሹመት ጀምሮ ይታይ የነበረው አሠራር ይቺን አገር አልጎዳም ማለት አይቻልም፡፡ በትክክል ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ከሚሠራ ባለሙያ ይልቅ በአምባሳደርነት የሚላኩ ሰዎች የፖለቲካ ሹመኞች መሆን የአገር ዲፕሎማሲያዊ ሥራን ጎድቷል፡፡ አንዳንዴም ዲፕሎማት ሹመት በብቃት ማነስ ወይም በጡረታ የተገለሉና ከተለያዩ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የተባረሩ ፓለቲከኞች ሳይቀሩ ገለል ብለው እንዲቀመጡ፣ ዲፕሎማት ማድረግ ተለምዶ የነበር መሆኑን ስናይ ሊቆጭ ይገባል፡፡ አንዳንዱም በዘመድ አዝማድ ትስስር የዲፕሎማት ማዕረግ እየተሰጠ እጅግ ብዙ ሊሠራባቸው የሚገቡ ኤምባሲዎቻችን በስም የነበሩ ብቻ አስመስሏቸዋል፡፡

  ከሰሞኑ ግን እንዲህ ባለ ሁኔታ ሲገለጽ የቆየው ተቋም በተለየና እውነተኛ ተልዕኮውን ለማሳካት በሚችል ደረጃ በብቃትና ሙያተኛን ባማከለ መልኩ አዳዲስ ምደባ ሊደረግ መሆኑ መሰማቱ እንደ ትልቅ ዜና ሊወሰዱ ይገባል፡፡ በኤምባሲዎች የሚመደቡ ሰዎች የፖለቲከኛ ሹመኛ ሳይሆኑ ከሙያው ጋር የሚተዋወቁ እንደሚሆኑ መግለጹ በራሱ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ኤምባሲዎቻችን ኢትዮጵያን መሸጥ ዋነኛ ተግባራቸው ሆኖ በኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ አፈጻጸሙ ግን የሚፈልገውን ግብ የመቱ አልነበሩም፡፡ የአገሪቷን ምርቶችን ሊሸምቱ የሚችሉ ኩባንያዎችን አፈላልጎ ጠቃሚ በሆነ ኢኮኖሚ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል ቁመና ሊኖራቸው ይገባ እንደነበር ግን ግልጽ ነው፡፡

  ዛሬ የሚሻሙት ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያ ምርቶችን ለመሸጥ መታተር እስካልቻሉ ድረስ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ለማለት እንደማይችል ግንዛቤ መወሰድ አለበት፡፡ ኤምባሲዎቻችን በተለይ በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባስቡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳይሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል ቁመና እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡

  ኢትዮጵያውያን ባሉበት ቦታ በየጊዜው ሊጎበኙት የሚችሉ ኤምባሲ ሊሆን ይገባል፡፡ ስለአገራቸው የሚመክሩበት መሆን ይገባዋል፡፡ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው እንዲሠሩና ሀብታቸውን እንዲያፈሱ ማግባባት የሚችሉ ዲፕሎማቶች መሆን አለባቸው፡፡ በእነዚህ ኤምባሲዎች በሙያና በብቃት ተመዝነው ይመደባሉ የተባሉ ዲፕሎማቶች የአገልግሎት አሰጣጥ አገርም የሚያኮራ መሆን ያለበት ሲሆን፣ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሳሌ መሆን ጭምር ይኖርባቸዋል፡፡

  ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ሲነገር እንደነበረው ምን ያህል ዲፕሎማቶቻችን ለሥራም ሆነ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ አገር ቤት ሲመጡ ይዘው የሚመለሱትን በውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸውን ደመወዝ፣ ምን ያህሉ ከጥቁር ገበያ ውጭ በባንክ አስገብተው ምሳሌ ሆነዋል? ለሚለው ጥያቄ ይሰጥ የነበረውን መልስ እናውቃለን፡፡ አሁን ግን በብቃት ላይ የተመሠረተ ሹመት የሚሰጥ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ ኤምባሲዎቻችን በዲፕሎማቶቻችን ይህንን ታሪክ በመቀየር ለሌሎች ምሳሌ በመሆን አገርን በመጥቀምና ብዙ ተከታዮች እንዲኖራቸው ማድረግም ይገባል፡፡ ስለዚህ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተደረገ ነው ከተባለው ለውጥ ብዙ ይጠበቃል፡፡ እንደተባለው ብቃትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሹመት ብቻ ላይ ካነጣጠረ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ኤምባሲዎቻችን ብዙ ነገር ሊሠሩ ይችላሉና ተስፋ እያደረግነው መሆኑን ለመግለጽ እንፈልጋለን፡፡ ውጤታማነታችሁን የበለጠ ለማድረግ ደግሞ በሌሎች ተቋሞች ላይ እንደተደረገው ሁሉ መሥራት ያለባቸው ሥራን ቆጥሮ የመስጠትና ቆጥሮ የመቀበል አሠራር መተግበርም መልካም ነው፡፡ ኤምባሲዎችን በይበልጥ መመዘን ያለባቸው በዲፕሎማሲ ፖለቲካው የሚያስመዘግቡት ውጤት ነው፡፡