Monday, June 17, 2024

መነሻን እንጂ መድረሻን አለማወቅ ለበለጠ ስህተት ይዳርጋል!

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚፈጸሙ ስህተቶች ሕዝብንም ሆነ አገርን ይጎዳሉ፡፡ ስህተቶቹ ሲደጋገሙ ደግሞ የጉዳታቸው መጠን ከመጨመሩም በላይ፣ አድማሳቸው እየሰፋ የአገርን ህልውና ይፈታተናሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በልሂቃንና ከኅብረተሰቡ ሻል ያለ ግንዛቤ አላቸው በሚባሉ አካላት ጭምር ተደጋጋሚ ስህተቶች ይፈጸማሉ፡፡ መንግሥት አገር የማስተዳደር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት አካል ነውና የሚፈጽማቸው ስህተቶች ከባድ ስለሚሆኑ ውዝግብ ለመፍጠር አመቺ ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጨዋታው ሕግ አፈንግጠው ያልተገባ ድርጊት ውስጥ ሲገቡ ለግጭት መቀስቀስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ምሁራንና ልሂቃን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሚያሠራጩዋቸው መረጃዎች ወይም መልዕክቶች፣ በተለይ ወጣቶችን በማነሳሳት ያልተገባ ድርጊት ውስጥ ይከቱዋቸዋል፡፡ ባለፉት ስምንት ወራት በአገሪቱ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ለውጡ በግስጋሴ ላይ ቢሆንም፣ እዚህና እዚያ በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት ንፁኃን ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ የአካል ጉዳት ገጥሟቸዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ አሳዛኝ ድርጊት አሁንም እያገረሸበት ለአገር ሰላምና ደኅንነት ጠንቅ እየሆነ ነው፡፡ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለልማት በጋራ መነሳት ሲገባ የማያባራ ግጭት ውስጥ መገኘት ልማድ ከሆነ፣ ስህተቶች እየተደጋገሙ ከባድ ጉዳት ይደርሳል፡፡

በምክንያታዊነት የሚመራ ለውጥ ለስሜታዊነትና ለግብታዊነት ክፍተት መስጠት የለበትም፡፡ ምንም እንኳ የሽግግር ወቅት ላይ በምትገኝ አገር ውስጥ ውጣ ውረዶች መኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ነፍጥ አንግቦ ከጦርነት ያልተናነሰ ግጭት በመፍጠር የንፁኃንን ሕይወት መቅጠፍና ከቀዬአቸው በገፍ ማፈናቀል አደገኛ ነው፡፡ መንግሥት ባለበት ኃላፊነት መሠረት እንዲህ ዓይነት ተከታታይ አደገኛ ድርጊቶችን ማስቆም ባለመቻሉ መጠየቅ አለበት፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ሕጋዊና ተቋማዊ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ፣ በየሥፍራው እያጋጠሙ ያሉ አደገኛ ድርጊቶችን ማስቆም ካልተቻለ ለሕዝብና ለአገር ህልውና ከፍተኛ ሥጋት ይፈጥራሉ፡፡ በሕዝብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ መሰናክል ከሚፈጥሩት ጀምሮ ሕይወቱን የሚቀጥፉትን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ ማቅረብ ካልተቻለ፣ እንኳን የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት ለመግፋት ህልውናም አጠራጣሪ ይሆናል፡፡ ከሕዝብ አልፎ የፀጥታ አስከባሪዎች ሳይቀሩ ግድያ እየተፈጸመባቸው ነው ሲባል ያስደነግጣል፡፡ አገሪቱስ ከየት ወዴት እየተጓዘች ነው ያስብላል፡፡ የለውጡ ጉዞስ መነሻው ከየት ወዴት ነው ተብሎም ሌላ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በየደረጃው ያሉ አመራሮችን ብቃትና ቁርጠኝነት መፈተሽ ካልተቻለም ፈተናው ከባድ ነው፡፡

በለውጥ ጊዜ የተለያዩ አሠላለፎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ በለውጡ ምክንያት አገርና ሕዝብ ይጠቀማሉ ብለው በጋራ የሚነሱ የለውጥ ኃይሎች ያሉትን ያህል፣ ለውጡ ተጠቃሚነታቸውን ከማሳጣት አልፎ ተጠያቂነት የሚያመጣባቸውም አሉ፡፡ በእነዚህ ሁለት ኃይሎች መካከል በሚካሄድ ፍትጊያ የበላይነቱን ይዞ ለመውጣት ትንቅንቅ ይኖራል፡፡ እዚህ ላይ ግን መዘንጋት የሌለበት ለውጡን የሚመራው ኃይል አብዛኛውን ሕዝብ ከጎኑ አሠልፎ አዋጭ የሆነ የግል ሥልት በመንደፍ ካልተንቀሳቀሰ፣ ለውጡን የሚያደናቅፈው ኃይል ያሰባሰበውን ሀብት በመጠቀም ቀደም ሲል በሚያውቀው መዋቅር ውስጥ ሰርጎ በመግባትና ክፍተቶችን በመጠቀም የበላይነቱን ሊይዝ ይችላል፡፡ ይህ እንዲህ በግርድፍ የሚታወቅ እውነታ ሲሆን፣ በሥውር ደግሞ ከዚህ የባሱ ውስብስብ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ያልጠሩ ነገሮች ሲኖሩ ደግሞ ለሐሰተኛ መረጃዎች ፈጣሪዎችና ለሴረኞች ትንተናዎች የሚመቹ አጓጉል ቅስቀሳዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተለቀቁ ግራ መጋባቶች ይፈጠራሉ፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ኃላፊነት በጎደላቸው ልሂቃን ነን ባዮች በሚለቀቁ ውዥንብሮች አገር ይታመሳል፡፡ አንድ ላይ ቆመው ለጋራ ዓላማ መሠለፍ የሚገባቸው በተቃራኒ ጎራ ውስጥ ራሳቸውን ያገኙታል፡፡ መነሻቸውን እንጂ መድረሻቸውን አያውቁምና፡፡

የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በቅጡ የሚከታተል ማንም ሰው መልካም አጋጣሚዎች መፈጠራቸውን በቀላሉ ይረዳል፡፡ እነዚህ መልካም አጋጣሚዎች አስተማማኝ እንዲሆኑ ግን የፖለቲካ ጨዋታውን ማሳመር ይገባል፡፡ ከውጤት በፊት ሒደትን በመግራት በተፈጠሩት መልካም አጋጣሚዎች ምን መደረግ አለበት የሚለውን ጠንቅቆ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ አገር የለውጥ ጀልባ ስትቀዝፍ ዓላማው ምን መሆን እንዳለበት መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እንደ አገር ከየት ወዴት መሸጋገር እንደሚያስፈልግ፣ በየመንገዱ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ መሰናክሎች፣ ተስፋዎች፣ በተጨማሪም ዓላማን ለማሳካት ሲባል ሊኖሩ ስለሚችሉ የተለያዩ አማራጮች በስክነት ማሰብ የግድ ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአገር ህልውናን ማስቀደም የለውጡ ዓላማ መነሻ ሊሆን ይገባል፡፡ ከኢትዮጵያ በፊት ምንም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የለም ማለት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ይቅደሙ ማለት ነው፡፡ የሚፈለገው ለውጥ ሁሉን አሳታፊ፣ በመርህ የሚመራና ከውዥንብር የፀዳ እንዲሆን ለሰላምና ለዴሞክራሲ ልዩ ሥፍራ ሊኖር ይገባል፡፡ መነሻን አውቆ መንቀሳቀስ ለመድረሻ አያስቸግርም፡፡

መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን መመኘት መልካም ቢሆንም፣ በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ ነገሮች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ከወዲሁ መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ በቀላሉ ሊከናወኑ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ጉዳዮች ከሚታሰበው በላይ ሊከብዱ ይችላሉ፡፡ በፖለቲካው መስክ እየተሰሙ ያሉ ዝብርቅርቅ ነገሮች፣ የቢሮክራሲው ውጥንቅጥ፣ በማንነት ስም የሚካሄዱ መከፋፈሎች፣ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ እየታዩ ያሉ መከፋፈሎችና የጎሪጥ መተያየቶች፣ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር ሊኖሩ በሚችሉ ድርድሮች የሚያጋጥሙ ውዝግቦች፣ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚከናወኑ ደም አፋሳሽ ግጭቶች፣ እንደተለመደው ጠላት ፍለጋ የሚደረጉ እንካ ሰላንቲያዎች፣ አሁንም ለሐሳብ ነፃነት የሚሰጠው እዚህ ግባ የማይባል ግምት፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያለው መጠነ ሰፊ ችግር፣ የሕዝቡ የመግዛት አቅም መዳከምና የኑሮ መቆርቆዝ፣ አገሪቱ ላይ የተቆለለው የዕዳ ጫና፣ የምርትና የምርታማነት መቀዛቀዝና የመሳሰሉት አገራዊ ፈተናዎች ያሳስባሉ፡፡ በአጠቃላይ እንደ መርግ ከከበዱ ችግሮች ለመላቀቅ የምትፍገመገም አገር ውስጥ ለውጥ ሲመጣ፣ በረባ ባልረባው እየተናጀሱ መልካም አጋጣሚዎችን ማበላሸት የባሰ ቀውስ መፍጠር ነው፡፡ ከተጨባጩ የአገሪቱ ሁኔታ አኳያ ሰከን ብሎ ለጋራ ጉዳይ በአንድነት መቆም ይሻላል፡፡ መነሻን እንጂ መድረሻን አለማወቅ ለበለጠ ስህተት ይዳርጋልና!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...