Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እስቲ ሰው እንሁን!

እነሆ መንገድ ከጦር ኃይሎች ወደ አያት ልንጓዝ ባቡር ተሳፍረናል። ‹‹እስኪ ጠጋ ጠጋ በሉ። ምንድነው ሰው ባቡር ላይ ሲሆን ፍቅር ቀነሰ?›› ይላል አንድ ቀልድ የሚያምርበት ጎበጥ ያለ ወጣት። ‹‹ታዲያ ታክሲ ላይ በመጠጋጋት የተበደልነውን በደል ባቡር ላይ ባለመጠጋጋት ካላጠፋነው ምን ዋጋ አለው? ደግሞ ፍቅር ቀዘቀዘ ብላችሁ ልታሙን?›› ይለዋል ተደርቦ እንዲቀመጥ የተባበረው ተሳፋሪ። ‹‹ፍቅርማ ከባቡሩ በፊት፣ ከፌስቡክ በኋላ ነው የቀዘቀዘችው፤›› ትላለች ከፊታቸው ወንበር ይዛ የተሰየመች ለግላጋ። ‹‹እንዲያው አንድም ሰው እያደገ ነው የሚባለውን ኢኮኖሚ ለሞራልና ለፍቅር ውድቀት ተጠያቂ ሲያደርገው አልሰማም?›› የምትለው ደግሞ ቆማ ለመሄድ ቋሚውን ብረት ሙጥኝ ብላ የያዘች ወይዘሮ ናት። ‹‹መነካካት አልፈልግም ብለን እንጂ እሱስ አልጠፋንም። እንዴ አልተጠጋጋንም ብለን ጨዋታውን ጀመርነው ተብሎ ‘አንተካካም ወይ?’ ወደሚል ጨዋታ የግድ ማምራት አለብን ማለት ነው?›› ይላል በወዲያ ጥግ መስኮቱን ተደግፎ አነስ ያለች መጽሐፍ ገልጦ የሚያነብ ወጣት።

‹‹ኧረ እባካችሁ ፖለቲካና ኢኮኖሚ የተለያየ ነገር ነው፤›› ባዩ ደግሞ ከየት እንደመጣም አናውቅም። ‹‹ያንተ ይሻላል አቦ። በአደባባይ በገሃድ አዋቂን አሸማቆ በድፍረት ማውራት . . . ጭራሽ በዚህ ዘመን ኢኮኖሚና ፖለቲካ ለየቅል ናቸው ለማለት መድፈር . . . ፓ! ምነው አምላኬ እንዲህ ያለው የመዘባረቅና የመናጠቅ ድፍረትን ለእኔም ብትሰጠኝና እንደ ዘመኑ ሰው የመሰለኝን በማውራት፣ የእኔ ያልሆነውን በመቀማት ሀብታም ብሆን? ዝና ብገዛ?  . . . ምን ቸገረህ እሺ ብትለኝ?›› እያለ አንድ ጎልማሳ ያሳረረውና ያደበነውን እየዘከዘከ ወቀሳውን ወደ ሰማይ እያየ አዥጎደጎደው። ይኼኔ ባቡሩ መንቀሳቀስ ጀመረ። የአባቶቹን እምነትና ታሪክ መድገም በተሳነው ትውልድ ጆሮም የማሳሰቢያና የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች ያለ ቅጥ መደጋገማቸውን ጀመሩ። የወያላው ይሻል ነበር ሲሉ ሰማሁ?

‹‹ኡፍፍ. . . ጀመራት ደግሞ. . . ›› ትላለች ወይዘሮዋ ወደ ስፒከሩ እየጠቆመች። ‹‹ያለዎት ቀሪ ሒሳብ’ የምትለው እህት ሳትሆን አትቀርም፤›› ይላል ልጅ እግር ተሳፋሪ። ‹‹. . .ተቀጣጣይ ፈንጂ ወይም ቦምብ ይዞ መግባት የተከለከለ ነው. . .›› ትላለች መመርያ ሰጪያችን። ‹‹ድሮስ የት አገር ነው የተፈቀደው?›› ይጠይቃል ሌላው። ‹‹ምናለበት እዚህ ጆሯችንን ከሚያደሙት መውጫ መግቢያው ላይ መፈተሻ መሣሪያ ቢያኖሩ? በመለፈፍ ብቻ የታጠቀን ማስፈታት ይቻላል እንዴ?›› ይላል አንዱ ጎረምሳ። ‹‹እናንተ እሱን ትላላችሁ መቼ ቲኬት የሚቆጣጠር ሰውስ አለ? ይኼው ስንት ቀኔ ማንም ላያየኝ በነፃ ልሄድ ስችል እገፈግፋለሁ፤›› ትላለች ለግላጊት። ‹‹ቆይ አንቺ ለማንም ብለሽ ነው ቲኬት የምትቆርጭው? ለህሊናሽ ስትይስ ምን አለበት ማንም ባያይሽ ከፍለሽ ብትሄጂ?›› ይላታል ከጎኗ የተቀመጠው።

‹‹ተው ባክህ? ታዲያ ምነው ሹማምንቱና ባለሥልጣናቱ ለህሊናቸው ሲሉ በታማኝነትና በቁርጠኝነት የማያገለግሉን? ቅሬታችንን ሰምተው የማያስፈርዱልን? ምነው ህሊና ለጥቂቶች ብቻ የሚታደል የሎተሪ ዕጣ መሰለህ?›› ብላው ቁጭ። ‹‹አይደለም! እሱ ሌላ ጉዳይ ነው. . . ›› ብሏት ሳይጨርስ፣ ‹‹የምን ሌላ ጉዳይ? ከየት አምጥተን እንከፍላለን? ብር ሙጃ መሰለህ ዝም ብለህ በየሜዳው የምታጭደው? ለነገሩ ሙጃውም እንደ ደግነትና ርህራሔ ጠፍቷል፤›› ብላ ቱግ አለች። ብሶት አለ ማለት ነው። ‹‹አይምሰልሽ! ለአንዳንዱ ቄጤማ ሆኗል እህቴ። ሳያስበውና ሳያቅደው ሜዳ ወድቆ የሚታፈስ ሙጃ ሆኖልሻል የዛሬ ገንዘብ። ቀን እሱን ታዝበሽ ማታ ዜና ስትከፍቺ ደግሞ ‘የወጣቱ ሥራ ፈጣሪነትና ምርታማነት ኢኮኖሚውን እንዴት እንደሚያምዘገዝገው ይዘገብልሻል። ወጣቱ ሥራ ቢፈጠርለት ኖሮ እያሉ ነጋ ጠባ ከመለፈፍ እንዴት እንደሚፈጠር ባለሙያዎችን አማክረው ዳይ ወደ ሥራ ማለት ይቀል ነበር እኮ፡፡ ዜናው ሳይገባደድ ደግሞ በስልክ አንድ የምታውቂው የቅርብ ሰው መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር ያለ የሌለ ንብረቱን ተጭበርብሮ ወይ ተነጥቆ ራሱን ስቶ ሆስፒታል ገብቷል ትባያለሽ። ይኼን ሰበር ዜና ላይ አዳምጠዋለሁ ብለሽ ካሰብሽ ታዲያ ወዳጅሽን ዓይኑን ማየት አይደለም ለአርባውም አትደርሺም። ይኼው ነው. . . ›› ብሎ ደግሞ ሌላው ይተነፍሰዋል። ከዚህ በላይ ሰበር ዜና ያስፈልጋል ለመሆኑ? እንጃ!

ሜክሲኮን እያለፍን ነው። ቋሚው ተቀማጩን በልጦታል። በሁለት ኩርቱ ፌስታል ቲማቲምና ሽንኩርት የተሸከመ ቆፍጣና አባወራና ሽበት የወረረው ፌዘኛ ጎልማሳ ወዲህ ወደ እኛ ተቀላቀሉ። በቻይና አሠልጣኝነት የሐበሻ ልጆች የሚዘውሩት ባቡራችን የአየር እጥረት አጋጥሞታል። ‹‹ምን አለበት ‘ኤሲውን’ ቢከፍቱት?›› ይላል ጎልማሳው። ዝም… ዝም። አሁንም ደገመው። አሁንም ዝም። ‹‹አልታፈናችሁም? ኧረ ታፍነናል ፊርማ አሰባስበን እንተንፍስ እንጂ ጎበዝ፤›› ጎልማሳው ‘ፒቲሽን’ ለማሰባሰብ ያሰበ ይመስላል። ‹‹ምንድነው የሚለው? አሥር ጊዜ ታፍነናል እያለ ነገር ሊያመጣብን ነው እንዴ?›› ብለው ተሳፋሪዎች አጉተመተሙ። ‹‹እንዴ በገዛ አገራችን ደግሞ ብለን ብለን አየር እንለማመጥ? ሲቆም ንገረው እንጂ!›› አሉት አንድ አዛውንት። ‹‹በምን ቋንቋ ተነጋግረው ሊግባቡ ነው?›› ብላ ወይዘሮ ጣልቃ ገባች። ‹‹ቻይናውን ማለትሽ ነው? አገሪቱን ከአገርኛው ቀድሞ እያቀና ያለው ማን ሆነና ነው መግባቢያ የሚቸግረን? ሥራው እንጂ ወሬውማ የእኛ እኮ ነው፤›› ሲሏት አዛውንቱ ሽሙጡ ፈገግ አስባለን። ሽሙጥማ የተካንበት እኮ ነው፡፡

 ‹‹ታክሲ ላይ ስናዘጋው የኖርነውን መስኮት እዚህ እናስከፍት ለማለት መግባቢያ ያሳስበን?›› ይለኛል ከጎኔ የተቀመጠ ወጣት ግንባሩና አፍንጫው ላይ ችፍ ያለ ላቡን እየጠረገ። ባቡራችን እንደተለመደው በተደጋጋሚ መመርያና ማሳሰቢያው እያስለፈፈብን ለገሃር ላይ ሲቆም፣ ሽበታሙ ጎልማሳ ባለመስታወቱን የሾፌሩን መዝጊያ አንኳኳው። ‹‹አንኳኩ ይከፈትላችኋል ነው፤›› ትላለች ያቺ ዘንግ የመሰለች ቀዘባ ወጣት። ‹‹ኧረ ይኼኛውስ በር እንጃለት መከፈቱን?›› ይላታል ጎልማሳው በምልክት ለባቡሩ ሾፌር ኤሲውን እንዲከፍት እያስረዳ። ‹‹እኛ ከተባበርን አይደለም ይኼ ወዲያና ወዲህ የለያየንም ግድግዳም ይፈርሳል፤›› ስትለው መልሳ፣ ጎልማሳው ሾፌሩ እንደገባውና እንዳልገባው ለመረዳት እየጣረ፣ ‹‹ተይኝማ እህቴ እንኳን የበሩ የሐሳብ ነፃነት መስኮትም ሲታሸግ ዝም ነበር ያልነው፤›› ብሏት አረፈው። ‹‹ሰው በመስኮትና በበር እያሳበበ የቆረቆረውን ሲናገር ይውላል። ከዚህ በላይ የሐሳብ ነፃነት ያስፈልገናል? ይብላኝ ለመስኮትና ለበር መፈናፈኛ ያጣን ቀን ማጮለቂያችንን እሱ ይወቀው!›› ይለኛል ከጎኔ የተቀመጠው። ምን ዓይነቱ ነገረኛ ነው ይኼ ደግሞ!

ጉዟችን ቀጥሏል። የባቡሩ ዘዋሪ ‘ኤሲውን’ ከፍቶልን ዕፎይ ብለናል። ጎልማሳው ወደባለ ፌስታሉ አባወራ ዞሮ ቀልድ ጀምሯል። ‹‹ምንድነው ይኼ ፌስታል?›› ይለዋል። ‹‹ሽንኩርትና ቲማቲም፤›› ይመልሳል አባወራው። የጎልማሳው ፌዘኛ ጥያቄ ሳቅ ሳቅ እያለው። ‹‹እኔ ደግሞ ተቀጣጣይ ነገር መስሎኝ፣ ያው ተቆጣጣሪ ስለሌለ ራሴን በራሴ ካልተቆጣጠርኩ ማን ይቆጣጠረኛል በሚል ነው፤›› እያለ ይኮረኩረናል። መመርያ ሰጪያችን ለአንድ ሺሕኛ ጊዜ ባቡሩ ውስጥ እንስሳት ይዞ መግባት የተከለከለ ነው ትላለች። ‹‹ምን አለበት ይህችን ሴትዮ ትንሽ እንኳ ድን ቀነስ ቢያደርጉልን? ‘ቶርች’ አደረገችን እኮ!›› ይላል የወጣቱ ቡድን እየተቀባበለ። ‹‹ኖኖ! መመርያ. . . መመርያ ነው። እናንተ የዘንድሮ ልጆች ትልቁ ችግራችሁ መመርያ ሳታነቡ ጥያቄ ለመመለስ መቻኮላችሁ ነው፤›› ብለው አዛውንቱ ሲያዋዙዋቸው፣ ‹‹ችግራችን የአፈጻጸም እንጂ የመመርያ አይደለማ። ተሳሳትኩ?›› ወጣቱ መለሰላቸው። ‹‹ካሁን በኋላ የአፈጻጸም ድክመት እያሉ ማሾፍ እንደማይቻል አልሰማችሁም እንዴ?›› ሲሉ አዛውንቱ፣ ወጣቶቹ እርስ በርስ በግራ መጋባት ተያዩና መነጋገር ጀመሩ፡፡ የገባው ላልገባው እንዳያስረዳ ሁሉም ያው ነው፡፡

‹‹በሉ በሉ ደግሞ በየመሥርያ ቤቱ ሥራ ያስፈታንንና ያሰለቸንን ግምገማ እዚህ ልታስጀምሩን ባልሆነ፤›› ብሎ ጎልማሳው አቋረጣቸው። ደግሞ በወዲህ ጥግ፣ ‹‹ቆይ ግን ይኼ ባቡር እንዲህ እያዘገመ እስከ መቼ ነው የሚያስበላን?›› ትላለች የጠይም ዕንቁ። ‹‹ኧረ እዚያው በፀበልሽ እኛ እዚያም ሆነ እዚህ የጀመርነው ቁማር የለም፤›› ይላታል ከአጠገቧ አንባቢው ንባቡን አቋርጦ። ‹‹የምሬን እኮ ነው። ጊዜው እኮ የ‘ኮምፒቲሽን’ ነው፤›› ስትል፣ ‹‹በመኪና አደጋ አንደኞች ሆነናል። ምናለበት በባቡር አደጋ መጨረሻ ላይ ተቀምጠን ባላንስ ብንሠራ? ኧረ ‘ባላንስ’ እንልመድ ተው! ተው! ስንቱ ነገር ላይ ቸኩለን ይሆንልናል እንዴ?›› ሲሏት አዛውንቱ፣ ‹‹እውነትም የአዲስ አበባ ሰው መዋያ አጥቷል!›› ብላ አጉተምትማ ዝም አለች። ሕልምና ትርጉም በየፈርጁ በሆነበት ዘመን ዝም ብሎ መስማትን የመሰለ ነገር የለም!

ወደ መዳረሻችን ነን። ‹‹ማነህ በሩን በእጅህ አትያዘው ኋላ ደግሞ ኮረንቲው ቢፈጅህ የለንበትም፤›› ይለዋል አንዱን የዋህ ቢጤ የገባኝ ነኝ ባይ አራዳ እያሾፈ። እውነት መስሎት ያ በርግጎ ከበሩ ራቀ። ‹‹አይ እኛ እኮ በቃ በሩ ካልተከፈተ አንድም ቀን ሰብረነው አናውቅም፤›› አለች ቆንጂት ከተቀመጠችበት እየተነሳች። ‹‹እንዴ ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ የባቡር በር በመስበርና የሕዝብ ንብረት በማውደም ልታስከስሱን ነው? መጀመሪያ የቤታችሁን በር ስበሩና ጨርሱ፤›› ይላል ጎልማሳው ነገሩ ያልገባው መስሎ። ‹‹ግድ የለም መጀመሪያ የማርሻል ግራዚያኒን ሐውልት እናስፈርስና ከዚያ የገዛ ቤታችንን የገዛ ኑሯችንን አጥር ማጥበቅ እንጀምራለን፤›› ይላል በወዲያ በኩል እልባት ሠርቶ መጽሐፉን የሚያጥፈው ተሳፋሪ። ‹‹ምን? ምን? የግራዚያኒ ሐውልት ሮም እንጂ አዲስ አበባ ነው እንዴ የቆመው?›› ብሎ የምሩን ሌላ ተሳፈሪ ሲጠይቅ፣ ‹‹ኧረ ተወኝ። በእርግጥ የፈጸመው ግፍና ወንጀል የሚረሳ አይደለም። እሱ ሐውልት ቆሞለት የሠራው ግፍ ሲሸፋፈን የዚህችን ዓለም ጎዶሎነት ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ግፈኛና ጨቋኝ የሚወደስባት ዓለም የተረገመች ናት፡፡ ዓለምን ፍትሕ እየተማፀንን ቤታችን ሲተራመስ ዓይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን እንሆናለን። አጠገባችን እልፍ ግራዚያኒያን እንደ አሸን ሲፈሉ ጭጭ እያልን የሞተ ውሻ እንደበድባለን. . . ›› እያለ ያ ወጣት ተናግሮ ሳይጨርስ በሩ ተከፈተና ትርምስ ሆነ። አሁንማ ዕድሜ ለውሸት ወሬ ሁሌም እንደ ተተራመስን እኮ ነው!

ከትርምሱ ወጥተን በእየ አቅጣጫው ስንጓዝ አንዱ፣ ‹‹ይህች ፍትሕ አልባ ዓለም ዘመናት በተለዋወጡ ቁጥር ታንገበግበናለች፡፡ ጉልበተኛ ደካማውን እያጠቃ፣ ባለገንዘቡ ፍትሕን እያስጠመዘዘ፣ ዘራፊ አገር እያራቆተ፣. . . እህህ እያሉ ዕንባን ወደ ላይ መርጨት ነው. . . ›› ሲል፣ ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ትዝብት ነው ትርፉ እያሉ ማለቃቀስ ደግሞ ያናድዳል፡፡ ይልቁንስ ባይገባን እንኳ ያገባናል ማለት እንልመድ. . . ›› ብሎ ዕርምጃውን ፈጠን አደረገው፡፡ ይኼን ጊዜ አንድ ወፈፍ ያደረገው የሚመስል ጎልማሳ ከየት መጣ ሳይባል እጆቹን እያወናጨፈ፣ ‹‹አገሬን አገሬን አይልም ወይ ሰው፣ ሌቦች ሲያበራዩዋት ሆድ እየባሰው፤›› ሲል ሁሉም ከዕርምጃው ቀነስ እያደረገ ዲስኩር ለማዳመጥ ተዘጋጀ፡፡ ሰውየው የሰውን ሁኔታ ሲያጤን ቆይቶ፣ ‹‹አገር ማለት እኔ፣ አንቺ፣ እሱ፣ እነሱ. . . ናቸው፡፡ እኛ ሰዎች ነን አገር ማለት፡፡ ሰው ካልተከበረና በገዛ አገሩ ባይተዋር እንዲሆን ከተፈረደበት ውጤቱ እንደ እኔ ማበድ ነው፡፡ ሰው ለመሆን ከፈለጋችሁ እናት አገራችሁን ውደዱ፡፡ አገርን ጠልቶ መንደር ውስጥ መወሸቅ የሰው ባህሪ ሳይሆን የአውሬ ነው፡፡ እኔ ያበድኩት ሰው ለመሆን ስታገል፣ ሰው እንዳልሆን በታገሉኝ ክፉዎች ምክንያት ነው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ፊታችሁ ላይ ቆሜ ሰው እንድትሆኑ የምማፀናችሁ፡፡ ለመማሩማ እስከ ዶክትሬት ድረስ ዘልቄ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ሰው እንሁን ባልኩ ከመንገድ ቀጠፉኝ. . . እስቲ ሰው እንሁን!›› ብሎ በሐሳብ ጭልጥ ሲል፣ እኛም ልባችን ተነክቶ በምሬት ስሜት ቀሪውን መንገድ ተያያዝነው፡፡ አንዳንዴ እኮ የምንሰማቸው ነገሮች ይጨንቃሉ፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት