Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትኩረት ለገቢና ወጪ የውጭ ምንዛሪ

ሰሞኑን በተደጋጋሚ የምናደምጠው ማስታወቂያ ትኩረቴን ስቦታል፡፡ ማስታወቂያውን በሰማሁ ቁጥር ማስታወቂያው በሚነገርበት ልክ የተንሰራፉ ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልና ሕግ ለማስከበር ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እምነት አሳድረውብኛል፡፡ በአንፃሩ ቆፍጠን ያሉ አሠራሮችን በመከተል ሕግ ማስከበር ለምን  ተስኖን እንደቆየን ሳስብ ግራ መጋባቴ አልቀረም፡፡

ማስታወቂያው ወደ ውጭ የሚሄዱ መንገደኞች ወደ ውጭ የሚያወጡት የውጭ ገንዘብ ከባንክ ተፈቅዶላቸው ወይም መንዝረው የያዙት ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ መረጃ መያዝ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ነው፡፡ ይህንን ማሟላት ያልቻሉ ተጓዦች የያዙት ገንዘብ ተቀባይነት ስለማይኖረው አላስፈላጊ መጉላላት እንዳይደርስባቸው ቀድመው እንዲጠቀቁ የሚያሳስብ መልዕክት ያዘለ ማስታወቂያ ነው፡፡

 በማስታወቂያው እንደተጠቀሰው ከሆነ ከውጭ የሚገቡ መንገደኞችም ይዘው የሚገቡትን የውጭ ገንዘብ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን የጉምሩክ ኮሚሽን ማስታወቂያ ስሰማ ወደ ሐሳቤ የመጣው ጉዳይ፣ መንገደኞች ከአገር ሲወጡና ሲገቡ የያዙትን የውጭ ምንዛሪ እንዴት ነበር ስንቆጣጠር የቆየነው የሚለው ነው፡፡

በተለይም የውጭ ገንዘብ ሲሆንና መጠኑ ከፍተኛ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ሲወሰድ የነበረው ዕርምጃ ምን ነበር? ያሰኛል፡፡ አንድ ተጓዥ ሲገባና ሲወጣ ምን ያህል የውጭ ገንዘብ መያዝ አለበት? የሚለውም በሕጉ መሠረት ስለመተግበሩ ያጠያይቃል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጉዞ ወቅት የሚፈቀደው የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ገንዘብ ምን ያህል መሆን እንዳለበት መደንገጉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም በኤርፖርቶች አካባቢ በየጊዜው በሕገወጥ መንገድ ሊወጣ ሲል ተያዘ እየተባለ የሚነገረው የውጭና የአገር ውስጥ ገንዘብ መጠን እንቅስቃሴ እንዴት ቁጥጥር ይደረግበት እንደነበር እንተወውና ጉምሩክ ባስነገረው ማስታወቂያ መሠረት፣ ቁጥጥር የሚያደርግ ከሆነ አገር የሚታደግ ተግባር ሊፈጽም ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሕጋዊ አሠራርን ለማስፈን የጥርጊያ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡

በአንፃሩ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለውን የመቆጣጠሪያ መንገድ ሲተገብር አልነበረም ማለት ነው ወይ ሊያሰኝም የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ከአገር የሚወጣ ተጓዥ  በውጭ ቆይታው ወቅት እንደሚያስፈልገው በማሰብ የሚይዘው የውጭ ምንዛሪ ምንጩ ከየት እንደሆነ አይታወቅም ነበር ማለት ነው? ዶላር በገፍ ሲጫን ከርሞ ነበር ወይ? ከማስታወቂያው መገንዘብ እንደሚቻለው ተጓዥ ሲገባም ሆነ ሲወጣ የሚይዘው የውጭ ምንዛሪ ሕጋዊነትን በተመለከተ ይኼ ነው የሚባል ግንዛቤና ቁጥጥር አይደረግም ነበር ማለት ነው፡፡ ለምን? ለሚለው ጥያቄ እግዜር ይወቀው እንጂ ምን ሊባል ይችላል፡፡

ቁጥጥር መላላቱ ቢኖርም የላላ መሆኑ አገርን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለ እንገምታለን፡፡ በተለይ ለውጭ ጉዞ እየተባለ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ከባንክ በሕጋዊ መንገድ ተመንዝሮ የተያዘ መሆኑ አጠራጣሪ ነው፡፡ እርግጥ ባንኮች ለውጭ ጉዞ የሚሰጡት የውጭ ምንዛሪ መጠን አለ፡፡ ሆኖም መጠኑ አነስተኛ ስለሚሆን ተጓዦች ከጥቁር ገበያ ለመግዛት ሲገደዱ ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ ባሻገር በተደጋጋሚ ወደ ውጭ እየተመላለሱ ያለ ንግድ ፈቃድ ዕቃዎችን በገፍ ገዝተው አገር ቤት የሚቸበችቡ ግለሰቦች እስከዛሬ እንዴት ሲስተናገዱ ነበር? እንዴትስ የውጭ ምንዛሪውን ይዘው ይወጡ ነበር የሚለው ጉዳይ ብዙ ሊያነጋግር ይችላል፡፡   

ከውጭ የሚገባውም ቢሆን በጉምሩክ ተመዝግቦና ወደ ሕጋዊ የገንዘብ ፍሰቱ እንዲገባ ለማድረግ ምን ያህል ጥረት ሲደረግ እንደነበር አናውቅም፡፡ ቁጥጥር ቢደረግ ቢያንስ ከውጭ የሚገባው ዶላር በአብዛኛው ወደ ጥቁር ገበያ ባልሄደ ነበር፡፡ የገባው ሁሉ ወደ ባንክ እንደሚሄድ መጠበቅ ሞኝነት ቢመስልም፣ ቢያንስ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን መጠን ለማወቅ ያስችላል ተብሎ ይገመታል፡፡  

የቀደመውን ጉዳይ እንተወውና ተጓዦች የሚይዙት የውጭ ገንዘብ ሕጋዊነት እንዲረጋገጥ በጉምሩክ በኩል በተባለው መንገድ ከተተገበረ፣ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ሕጋዊነትን የማረጋገጡ አንድ ሁለት የለውም፡፡ ምክንያቱም የግብይት ሥርዓቱን እንዲበላሽ ካደረጉት ጉዳዮች አንዱ ከመደበኛ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት ይልቅ ከጥቁር ገበያ በገዙት የውጭ ምንዛሪ ሸቀጦችን ከውጭ በማስገባት ገበያውን የሚያተራምሱ ሥውር እጆች መበራከት ነው፡፡ አሁን ግን ይህ እጃቸው ሊሰበሰብ ይችላል፡፡ በተለይ ከዱባይ፣ ከታይላንድ፣ ከቻይናና ከሌሎችም አገሮች ሸቀጦችን እየጫኑ በማስገባት የሚቸበችቡትን ያስታግሳል የተባለው ቁጥጥር ሕገወጥ ንግድ እንዲገታም ያግዛል፡፡

የሚወጣውና የሚገባው የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ እንዲመነዘር የሚደረግ ከሆነ፣ ጥቁር ገበያ እንዲቀጭጭ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በባንክ ያልተመነዘረ የውጭ ምንዛሪ ይዞ መውጣት እንደማይቻል ከታወቀ፣ በጥቁር ገበያ የሚደረገውን የምንዛሪ ሒደት በመቀነስ ሕገወጥ ንግድ እንዲቀዛቀዝ ሊያደርግ የሚችልበት አቅሙ ሰፊ ይሆናል፡፡ ዶላር ለመሸመት ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄደው ሰው ቁጥሩ ይቀንሳል፡፡ ተጓዦች ወደ ጥቁር ገበያ እንዳይሄዱና ለጉዟቸው በቂ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ማድረጉ መዘንጋት የለበትም፡፡ አሳማኝ ለሆኑ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቶች አዎንታዊ መልስ የሚሰጥበት አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡   

የቁጥጥሩ በትክክል መተግበር በኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የውጭ ምንዛሪና የአገር ውስጥ ገንዘብ ዝውውር መጠንን ለማወቅ የሚረዳ መረጃ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ካሉባት ብርቱ ችግሮች አንዱ በየትኛውም ዘርፍ በትክክል የተመዘገበ መረጃ ዕጦት ነው፡፡ ቢያንስ በአውሮፕላን ማረፊያዎች በኩል በሕጋዊ መንገድ በጥሬው ተይዞ የሚወጣና የሚገባው የውጭ ምንዛሪ ተመዝግቦ እንዲወጣ ለማድረግ ይረዳል፡፡ በተለይ ከውጭ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ በኤርፖርት ተመዝግቦ የማን መሆኑን ጭምር የሚያሳውቅና በመደበኛ ባንኮች እንዲመነዘር የሚያስችል አሠራር ሊሰፍን ይችላል፡፡

የውጭ ገንዘብ በኤርፖርት ማስመዝገብ ማለት ይህ ገንዘብ ወደ ጥቁር ገበያ ሄዶ መመንዘር የሌለበት በባንኮች መመንዘር የሚኖርበት በመሆኑ ለአገር የውጭ ምንዛሪ ግኝት ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄደውን የውጭ ምንዛሪ የሚቀንስ ያደርጋል፡፡ ይህም ጥቁር ገበያን ለመግታት የመንግሥትን ሰዶ ማሳደድን ሊቀንስለት ይችላል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ዜጎች እንዲህ ባለው ጉዳይ መረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በአገሪቱ ሕግ አንድ ተጓዥ እንደየጉዞው ዓይነት ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ከባንኮች ሊያገኝ ይችላል? የሚለውን ጥያቄ ሊመልስ በሚችል ደረጃ ባንኮችም ሆኑ እንዲህ ያለውን ዝውውር የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው አካል ሁሉም ወገን እንዲያውቀው ማድረግ አለባቸው፡፡ ተጓዦች በሕግ የተቀመጠላቸውን የውጭ ምንዛሪ የማግኘት መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ አሠራሩን ማሳወቅም ተገቢ ነው፡፡

ለዚህ ሁሉ ግን ቴክኖሎጂ ፍቱን ገላግሌ መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ክሬዲት ካርድ መጠቀምና ዜጎች ከባንክ ሒሳባቸው መክፈል የሚችሉበት አሠራር ቢሰፍን፣ ይህ ሁሉ የማኑዋል አሠራር ቀርቶ በባንክ የሚንቀሳቀስ የውጭ ምንዛሪ ግብይት በተስፋፋ ነበር፡፡ ይሁንና ይህንን ለማድረግ ያልተቻለው ግን በዶላር እጥረት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ላሉ ሥርዓቶችም በሩን መክፈት፣ ዕድሉን መስጠት መታየት፣ መሞከርና መለመድ ይኖርበታል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት