Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመጪው ምርጫና የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሸክም

መጪው ምርጫና የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሸክም

ቀን:

በ1993 ዓ.ም. የተፈጠረው የሕወሓት የመሰንጠቅ አደጋና አሸንፎ የመውጣት ፖለቲካዊ ትግል በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የፖለቲካ ሕይወት ላይ ትልቅ አሻራ ነበረው። የሚቀርቧቸው እንደሚናገሩት ደግሞ ከአሻራነት በላይ የሕይወት መስመራቸው የተቀየረበት እንደሆነ ይናገራሉ።

በወቅቱ በሕወሓት ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት አንዱ አንዱን አሸንፎ ለመውጣት የፖለቲካ ትግል ውስጥ ነበሩ። በወቅቱ ሕወሓት ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው መከፋፈል በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የኢሕአዴግና የሕወሓት ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ የፖለቲካ ልዩነት ላይ ያጠነጥናል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል በተፈጠረው መጠላለፍና አሸንፎ የመውጣት ትግል የመንግሥትን ሥልጣን የያዘውና በአቶ መለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው ቡድን፣ ከተቀናቃኙ ቡድን ጠንካራ ሰዎችን በመምረጥ የሙስና ወንጀል ክስ በመመሥረት ጉዳዩ በወቅቱ የፌዴራል ፍርድ ቤት ጀማሪ ዳኛ የነበሩት ወ/ሪት ብርቱካን ዘንድ ይደርሳል። የአቶ መለስ ቡድን በወሰደው ዕርምጃ የኤፈርት ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ወህኒ እንዲገቡ ተደርጓል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ ከፍተኛ የፖለቲካ ጠብ ውስጥ እጅን ማስገባት አይደለም ለአንድ ዳኛ ይቅርና ለሕወሓት እህት ድርጅቶችም አስፈሪ ነበር። አቶ ስዬን በቁጥጥር ሥር አውሎ የነበረው ፖሊስ በወንጀል እንደጠረጠራቸውና ተጨማሪ ምርመራ ለማካሄድ በማረሚያ ቤት ለማቆየት ያቀረበው ጥያቄ፣ ችሎቱን ይመሩ ለነበሩት ወጣት ዳኛ ወ/ሪት ብርቱካን ምክንያታዊ አልነበረም።

ለሕግ መከበርና የበላይነት ከነበራችው ፅኑ እምነት ውጪ ፖለቲካዊ ምክንያትም ሆነ ግኝኙነት ያልነበራቸው ወ/ሪት ብርቱካን ተጠርጣሪውን አቶ ስዬ በማረሚያ ቤት የሚያቆይ በቂ ማስረጃ አልቀረበም በማለት የዋስትና መብታቸውን እንዲከበር ውሳኔ ያሳልፋሉ።

ይሁን እንጂ የዳኛዋ ውሳኔ ለአቶ ስዬ የሰጠው ነፃነት ከፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ እስኪወጡ ብቻ ነበር። በከፍተኛ የፀጥታ አስከባሪ አካላት ወረራ ከአካባቢው ሳይርቁ አቶ ስዬ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደረገ፡፡ የተወሰደው ዕርምጃ ሕጋዊ ልባስ እንዲኖረው ሲባልም፣ በሙስና የተጠረጠረ የዋስትና መብት እንዳይኖረው የሕግ ማሻሻያ በቀናት ውስጥ በፓርላማው ፀደቀ።

 የዳኛዋ ውሳኔ በአገሪቱ የፖለቲካና የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ እስከ ዛሬ የዘለቀና መደብዘዝ ያልቻለ አሻራ እንዳለው ሁሉ፣ የእሳቸውንም ሕይወት ቀይሮታል።

ይህ ክስተት ወ/ሪት ብርቱካን ወደ ፖለቲካ ትግል እንዲገቡ ገፊ ምክንያት ቢሆንም፣ የጀመሩት መንገድ ግን አልጋ ባልጋ አልነበረም። በነበራቸው ከፍተኛ የፖለቲካ ተፅዕኖ ምክንያትም በፖለቲካዊ ክሶች ለተለያዩ ሁለት ጊዜያት ሕይወታቸውን በወህኒ ቤት አሳልፈዋል።

ለሁለት ጊዜያት እስር የተዳረጉባቸው ወቅቶች ከፖለቲካዊነታቸው ባሻገር፣ በሁለቱም ጊዜያት ተካሂደው ከነበሩት አገር አቀፍ ምርጫዎች ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ይነገራል። የመጀመርያው በ1997 ዓ.ም. ተካሄዶ ከነበረው ምርጫ በኋላ በምርጫው ውጤት ተዓማኒነት ጋር በተያያዘ በገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግና እሳቸው በአመራርነት የሚወክሉት ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ነው። ሁለተኛው እስር ከመጀመርያው ጋር ግንኙነት ቢኖረውም፣ አዲስ ፓርቲ በመመሥረት በ2002 ዓ.ም. ለሚካሄደው ምርጫ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ተቀባይነት ባገኙበትና ምርጫው ሊካሄድ የአንድ ዓመት ዕድሜ ብቻ ሲቀረው ነበር።

የ2002 ዓ.ም. ምርጫ ተጠናቆ ገዥው ፓርቲም በተለየ ሁኔታ የፓርላማውን 99.6 በመቶ ወንበሮች ማሸነፋ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ተደርጎና መንግሥትም ከተደላደለ በኋላ፣ ወ/ሪት ብርቱካን ዳግም ይቅርታ አግኝተው ከእስር ይለቀቃሉ።

የደረሰባቸውን መቋቋም የተሳናቸው ወ/ሪት ብርቱካን ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ስደትን መርጠው ኑሯቸውን በአሜሪካ በማድረግ፣ ቀጥተኛ የፖለቲካ ተሳትፎን እርግፍ አድርገው ይተዋሉ። ይሁን እንጂ በአሜሪካ ዝነኛው ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በመሥራት ራሳቸውን በትምህርት ከገነቡ በኋላ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታን ለመደገፍ በተቋቋመው ኔድ (National Endowment for Democracy) በተሰኘው ድርጅት ውስጥ ጊዜያቸውን በምርምር አሳልፈዋል። በተለይ በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርዎችን እንዲዳከሙ ያደረጋቸውን ምክንያቶችና እነሱን ለማጠናከር ምን ማድረግ እንደሚገባ መመራመር ትኩረታቸው ነበር።

 ወ/ሪት ብርቱካን ኑሯቸውን በስደት መምራት ሲቀጥሉ በኢትዮጵያ ደግሞ እሳቸው በወጣትነት የዳኝነት ቆይታቸው ለመትከል የሞከሩት እውነተኛና ገለልተኛ ፍትሕ፣ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት አለመረጋገጥ ዜጎችን ሲጨቁኑና ሲያማርሩ ከርመው ወደ ሕዝባዊ ቁጣ ተሸጋግረዋል።

ይህ ሕዝባዊ ቁጣ በተለይም ባለፋት ሦስት ዓመታት ተፋፍሞ በመቀጠሉ፣ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላይም ውስጣዊ የፖለቲካ ትግል በመቀስቀስ አገሪቷን እስከ መበተን ጫፍ አድርሶ፣ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. በኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የለውጥ ኃይል አሸንፎ ሥልጣንን ለመቆጣጠር በቅቷል።

በኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው ይህ የለውጥ ኃይል ባለፋት ዘጠኝ ወራት በወሰዳቸው የፖለቲካ ዕርምጃዎችና የዴሞክራታይዜሽን ጅማሮዎች፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ይሁንታና ቀልብ መግዛት መቻሉ በገሀድ የሚታይ እውነታና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ድጋፍ እየተቸረው ይገኛል።

በፖለቲካ ረገድ መካሄድ ከጀመሩ ተግባራት አንዱ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ላይ ቅድሚያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ሥልጣን በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ የሐሳብ ትግል በሕዝብ ይሁንታ ብቻ እንዲያዝ ማድረግ የቆይታቸው ዋነኛ ግብ እንደሆነ ለሚመሩት ሕዝብ በይፋ በመናገር ቃል ገብተዋል።

ይኼንንም ተከትሎ የአገሪቱን የምርጫ ሕጎች ማሻሻልና ምርጫን የሚያስፈጽመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ እንዲደራጅ፣ የማሻሻያ ሥራዎችን በአገር ውስጥ ገለልተኛ ምሁራን አማካሪነት በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

ይኼንን ሒደት በመከታተል ዕውን እንዲያደርጉና ምርጫ ቦርድንም በሰብሳቢነት እንዲመሩ በስደት ላይ ይገኙ የነበሩትን ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን በማጨት፣ ሐሙስ ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ በአብላጫ ድምፅ አፀድቀዋል።

በቀደሙት ዓመታት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆኖ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርብ ዕጩ በወቅቱ በፓርላማው ጥቂት መቀመጫ በነበራቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የገለልተኝነት ጥያቄ ይቀርብ ነበር። ፓርላማው በኢሕአዴግና አጋሮቹ ሙሉ በሙሉ በተያዙባቸው ወቅቶች ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ ወዳሉት ጥቂት የግል ሚዲያዎች በመቅረብ፣ በምርጫ አስፈጻሚ ተቋሙና በቦርዱ ሰብሳቢ ላይ የነበሯቸውን የገለልተኝነት ጥያቄ ለማሰማት ይሞክሩ ነበር።

ይህ ታሪክ የገጽታ ለውጥ አድርጎ ባለፈው ሳምንት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እንዲሆኑ በቀረቡት ወ/ሪት ብርቱካን ላይ መቶ በመቶ በኢሕአዴግና በአጋሮቹ የተሞላው ፓርላማ የገለልተኝነት ጥያቄ አንስተዋል።

ወ/ሪት ብርቱካን የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የነበሩ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ወይም ወገንተኝነት ንፁህ ስለመሆናቸው መረጋገጡንና እንዴት ሊረጋገጥ እንደቻለ ዕጩዋን ላቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አቅርበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የነበሩ ቢሆንም፣ በአሜሪካ በነበራቸው የጥቂት ዓመታት ቆይታ ከፖለቲካ ፓርቲ ወይም አባል ጋር ግንኙነት እንዳልነበራቸው መረጋገጡን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፖለቲካ አመለካካትን ማንም ሰው ሊይዝ እንደሚችልና ዋናው ጉዳይ ጠንካራ ተቋም መሥርቶ ሕግን አክብሮ መሥራት መቻላቸውን ማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል። ይኼንን ተላልፈው ከተገኙም በሕጉ መሠረት ሊጠየቁና ሊነሱ እንደሚችሉ አብራርተዋል። ማብራሪያውን ተከትሎም ፓርላማው ሹመቱን በአራት ተቃውሞ፣ በሦስት ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነቱ ከሚረጋገጥባቸው ወሳኝ ነገሮች አንዱ የቦርዱን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ጠንቅቀው በሚያውቁ፣ ገለልተኛ፣ የሙያ ብቃታቸው አስተማማኝ በሆኑና በመልካም ሥነ ምግባራቸው በሚታወቁ ሰዎች ሲመራ መሆኑን ገልጿል፡፡

‹‹ወ/ሪት ብርቱካን የፅናትና ለሕግ ልዕልና የመቆም አርዓያ ተደርገው በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የሚታዩ የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ በአገራችን የነበረውን የዴሞክራሲና የፍትሕ ዕጦት ለመታገልም የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር በመሆን ታግለዋል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ለዴሞክራሲና ለፍትሕ መስፈንም በገለልተኝነት፣ በብቃትና በሞገስ ሊያገለግሉ ከሚችሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ ናቸው፤›› ያለው መግለጫው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይኼንን ከግንዛቤ በማስገባት በዕጩነት አቅርበው እንደ ሾሟቸው ይገልጻል።

ከሹመቱ በኋላ ወ/ሪት ብርቱካን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ይህ ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ ሕይወታቸውን የሰጡት ለዴሞክራሲ መስፈንንና ለፍትሕ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ሰፍኖ ቢሆን ኖሮ መንገዳቸው ሌላ ይሆን እንደነበር አስረድተዋል።

ለአድልኦ የኖሩት ሕይወት እንዳልነበራቸውና ወደፊትም እንደማይኖራቸው፣ ይኼንን የኖሩ ቀን ራሳቸውን እንደሚጠሉም ተናግረዋል።

ቀጣዩ ሸክም

ወ/ሪት ብርቱካን በ1997 ዓ.ም. ከተካሄደው ምርጫና ከውጤቱ ጋር በተያያዘ ለሁለት ዓመታት በወህኒ አሳልፈዋል፡፡ ነገር ግን ከእስር በይቅርታ መለቀቃቸውን ክደዋል ተብለው የተዘጋጁበት የ2002 ዓ.ም. ምርጫ በተቃረበበት ወቅት በድጋሚ ለእስር ተዳርገዋል። በቆይታቸውም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከራ ተሸክመው አሳልፈዋል።

ቀጣዩ ሸክም ግን የተለየ ነው። ላሳለፉት የወህኒ ቤት መከራ ምክንያት የሆነውን የምርጫ ሥርዓት በገለልተኝነት መምራት።

በግላቸው ለቀረበባቸው የገለልተኝነት ጥያቄ መልስ የሰጡ ቢሆንም፣ ተቋማዊ ገለልተኝነትን በማረጋገጥ በምርጫ ቦርድ ላይ የሚቀርበውን ወቀሳ ማንፃትና ተዓማኒነት ያለው ተቋም አድርጎ መገንባት ፈቅደው የተቀበሉት የቀጣዮቹ ጊዜያት ፈተናቸው ይሆናል።

የተቋሙ ገለልተኝነት መገለጫዎች በርከት ያሉ ቢሆኑም የዋና ዋናዎቹ የዳሰሳ ጥናታዊ ሪፖርት ሐሙስ ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ለውይይት ቀርቧል። ጥናቱን በማካሄድ ለውይይት ያቀረበው የምርጫ ሥርዓቱንና የምርጫ ሕጎችን ለማሻሻል በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር የተደራጀው የዴሞክራሲ ተቋማት ጥናት ቡድን ሲሆን፣ ጥናቱን ያቀረቡት የቡድኑ ምክትል ሰብሳቢ ሲሳይ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ናቸው።

እንደሳቸው ገለጻ የቦርዱ ገለልተኝነትን ለማረጋገጥ በመሥፈርትነት ከሚታወቁ ልምዶች መካከል አንዱ፣ የቦርዱ አመራር አካላት አሰያየምን የተመለከተ ነው። በሌሎች አገሮች በውድድር ላይ የተመሠረተ የቦርድ አባላት አሰያየምን እንደሚከተሉ ለአብነት ጠቅሰዋል። ገለልተኛ መራጭ ኮሚቴ በማዋቀር ስምምነት በተደረገባቸው መሥፈርቶች የሚቀርቡ ዕጩዎችን በማወዳደር የሚሰየሙ መሆኑን፣ ሌሎች አገሮች ደግሞ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮንፈረንስ በመመሥረት የአባላት ምልመላ እንደሚያካሂዱና የተለዩትን ለሹመት እንደሚያቀርቡ ያስረዳሉ።

አባላቱ ከተሾሙ በኋላ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ የመምረጥ ተግባር ለራሳቸው የሚተው አገሮች መኖራቸውን አመላክተዋል። በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ አመራር አካላት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ እንደሚሾሙ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ ሲሆን፣ በዚህ መሠረትም ወ/ሪት ብርቱካን ተሹመዋል።

ይህ አሿሿም ገዥው ፓርቲ ወገንተኛ አመራር እንዲሾም ዕድል የሚሰጥ ቢሆንም፣ ወ/ሪት ብርቱካን የነበራቸው የኋላ የፖለቲካ ታሪክ ከወገንተኝነት ይልቅ በተቃራኒው መሆኑ የገለልተኝነት ጥያቄ አያስነሳም ብሎ ከመደምደም፣ የተሻለውን ተቋማዊ አሠራር ማስፈን እንደሚገባ ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

በሌላ በኩል የቦርዱ አባላት ከተሾሙ በኋላ የአገልግሎት ዘመን ጣሪያና ከኃላፊነት ሊሰናበቱ የሚችሉበት መንገድ፣ ሌላው የቦርዱ ገለልተኝነት የሚፈተንበት ሊሆን ይችላል።

አቶ ሲሳይ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ የቦርዱ አመራር አባላት በራሳቸው ፈቃድ ለመሰናበት ሲጠይቁ ወይም የሾማቸው ፓርላማ በሥነ ምግባር ጥሰት፣ አልያም በጤና እክል ሥራቸውን ለማከናወን አይችሉም ብሎ ሲያምን ሊያነሳቸው እንደሚችል በሕግ ተደንግጓል።

ይህ አሠራር ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ ለጣልቃ ገብነት የተመቸ መሆኑን ያስረዳሉ። ለምሳሌ ከላይ የተጠቀሱት ከኃላፊነት የሚነሱባቸው ምክንያቶች መሟላታቸው የሚረጋገጥበት አሠራር አለመኖሩን ይጠቁማሉ፡፡ በተጨማሪም የተጠቀሱትን ምክንያቶች በማቅረብ ለፓርላማው የሚያቀርበው ማን እንደሆነ በግልጽ አለመደንገጉን፣ እንዲሁም ይኼንን ለማድረግ የሚጠይቀው በአብላጫ ድምፅ መወሰን በመሆኑ ፍላጎቱ ያልተፈጸመለት ነገር ግን አብላጫ ድምፅ በፓርላማ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ጣልቃ መግባት እንደሚያስችለው ይጠቅሳሉ።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያ በሥራ ላይ የነበሩት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያ የተነሱበትን መንገድ በምሳሌነት ያወሳሉ።

ወ/ሮ ሳሚያ አገራዊ ለውጡን በመደገፍና የለውጡ አካል በመሆን በራሳቸው ፈቃድ ከኃላፊነት ለመነሳት አቅርበዋል ነው የተባለው፡፡ በመልቀቂያው ላይ ፓርላማው አንድም ጥያቄ ሳያነሳ ወ/ሪት ብርቱካንን እንደሾመ ገልጸዋል። በመሆኑም ወ/ሪት ብርቱካን የተቋሙን ገለልተኝነት ጨምሮ የመጡበትን መንገድ በማረም፣ የማስተካከል ኃላፊነት እንዳለባቸው ባለሙያው ያስረዳሉ።

 ሌላው የተቋሙን ገለልተኝት ለማረጋገጥ ፋይናንስ የሚያገኝበትን ሕጋዊ አሠራር መቀየር ያስፈልጋል። አሁን ባለው አሠራር ቦርዱ በጀቱን ለፓርላማ አቅርቦ እንደሚያፀድቅ በሕግ የተቀመጠ ቢሆንም፣ በተግባር ግን ገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጥናቱን ያቀረቡት ሲሳይ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።

ሌላው ጉዳይ ከገለልተኝነት ባለፈ የምርጫ ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ የመቀየር ጉዳይ የገዘፈው ሸክም እንደሚሆን ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ይህ የምርጫ ሥርዓት የአብላጫ ድምፅ መርህን (First Past the Post) የሚከተል ከመሆኑ የሚመነጭ ነው። ይህ የምርጫ ሥርዓት የሕዝብ ቅቡልነት ያገኘ መንግሥት እንዳይቋቋም፣ በውጤቱም ያልተሟላ የሕዝብ ውክልና ባለፋት ዓመታት በአገሪቱ እንደታየው የፖለቲካ ቀውስ ምንጭ ምክንያት ይሆናል።

 በዚህ ጉዳይ ላይ የምርምር ሥራቸውን ያሳተሙት አቶ ገብረ መስቀል ኃይሉ፣ ይህ የምርጫ ሥርዓት መሻሻል እንዳለበት በማስረጃ ላይ ተመሥርተው ይሞግታሉ።

ለአብነት ያህል በምርምር ሥራቸው ካሰፈሯቸው ማስረጃ ተጠቃሾች አንዱ፣ በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ የአዲስ አበባን መራጮችና ውጤቱን ይገልጻሉ።

አዲስ አበባ በፓርላማው ውስጥ 23 መቀመጫዎች ያሏት ሲሆን፣ ለእነዚህ መቀመጫዎች የሕዝብን ውክልና ለማግኘት በተካሄደው ምርጫ 1,041,180 መራጮች ድምፃቸውን መስጠታቸውን፣ በውጤቱም ለ23 መቀመጫዎች የተወዳደረው ኢሕአዴግ የ564,821 መራጮችን ድምፅ በማግኘት 22 መቀመጫዎችን ማሸነፋን ያስረዳሉ።

ይህም ማለት ከተጠቀሰው የመራጮች ቁጥር ውስጥ 41 በመቶ የሚሆኑት ኢሕአዴግን ሳይመርጡ በኢሕአዴግ ሊወከሉ ተገደዋል ሲሉ ይከራከራሉ። የምርጫ ሥርዓቱ የተመጣጠነ ውክልናን (Proportional Representation) የሚከተል ቢሆን ኖሮ፣ ኢሕአዴግ በተሰጠው ድምፅ ከ23 መቀመጫዎች ማግኘት የሚችለው 13 ይሆን እንደነበር በመጥቀስ የምርጫ ሥርዓቱ መሻሻል እንዳለበት ያሳስባሉ።

የተጠቀሱትንና ሌሎች በርካታ መዋቅራዊ ችግሮችንና ሕገ መንግሥቱን እንዲሻሻል በማድረግ የምርጫ ሥርዓቱን ማስተካከል፣ በወ/ሪት ብርቱካን ላይ የወደቀ ሸክምና ቀጣይ ኃላፊነት ነው።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...