Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንደ አዲስ ለሚደራጀው የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም አመራርነት መታጨታቸው ተሰማ

ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንደ አዲስ ለሚደራጀው የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም አመራርነት መታጨታቸው ተሰማ

ቀን:

መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ በስደት ይኖሩ ከነበረበት አሜሪካ የተመለሱት የቀድሞ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ፓርቲ አመራር የነበሩት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ አዲስ ለሚደራጀው ብሔራዊ ምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ኃላፊ እንዲሆኑ ታጩ።

ወ/ሪት ብርቱካን በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተብሎ ለሚጠራውና በቅርቡም ስያሜውንና አጠቃላይ አደረጃጀቱን በማሻሻል ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ሆኖ ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቀውን አገር አቀፍ ምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ለመምራት፣ ዕጩ ሆነው በመንግሥት መጠራታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረዋል።

ሰሞኑን ጥቁር አንበሳ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅጥር ግቢ እንደታዩ የሚገልጹት ምንጮች፣ የተቋሙን አደረጃጀትና ሁኔታዎች በግላቸው ለማጤን ያደረጉት ጉብኝት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር ስለመረጃው ወ/ሪት ብርቱካንን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። ወ/ሪት ብርቱካን መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ፣ በየትኛው ተቋም ሊመደቡ እንደተስማሙ ከመገናኛ ብዙኃን ጥያቄ ቀርቦላቸው ጊዜው ሲደርስ እንደሚያሳውቁ ተናግረው ነበር፡፡ በሚታወቁበት የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደማይቀጥሉና በቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫም እንደማይሳተፋ በማስረገጥ፣ በተደጋጋሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቀጣይ መዳረሻቸውን ከመናገር መቆጠባቸው ይታወሳል።

ስመጥር ባለሙያዎችን አካቶ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር በገለልተኝነት የተደራጀው የሕግና የፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ አፋኝ ናቸው ተብለው በመንግሥት የተለዩ ፖለቲካ ነክ ሕጎችን ለማሻሻል፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ሚናቸውን በተገቢው ጥራትና ደረጃ በገለልተኝነት የሚወጡ ሆነው በድጋሚ እንዲደራጁ በጥናት ላይ የተመሠረተ የሕግ ማርቀቅ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

አማካሪ ጉባዔው በሥሩ ያደራጃቸውን በወጣት ባለሙያዎች የተዋቀሩ በርካታ ንዑስ ኮሚቴዎች በመጠቀም እያከናወናቸው ከሚገኙ የሕግ ማሻሻያዎች መካከል የፀረ ሽብር፣ የሚዲያ ነፃነት፣ የሲቪክ ማኅበራት አዋጅና አጠቃላይ የምርጫ ሕጎችና የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት ተጠቃሽ ናቸው።

ወ/ሪት ብርቱካን እንደ አዲስ የሚደራጀውን ምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ለመምራት መንግሥት ዕጩ እንዳደረጋቸው ቢገለጽም፣ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባዔ በምርጫ ቦርድ አደረጃጀትና በምርጫ ሕጎች ላይ በማካሄድ ላይ የሚገኘው የሕግ ማሻሻያ ከሚዳስሳቸው ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ፣ እንደ አዲስ ለሚደራጀው የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም አመራሮችን የመመልመል፣ የማጨትና የመሾም ኃላፊነት የማን ሊሆን ይገባል የሚለውን እንደሚያካትት ለማወቅ ተችሏል።

የሕግ ማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ለሚገኘው አማካሪ ጉባዔ በምርጫ አስፈጻሚ ተቋሙ አደረጃጀትና የምርጫ ሕጎች ማሻሻያ ላይ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ በፍጥነት እንዲያጠናቅቅ፣ መንግሥት ከሰሞኑ ማሳሰቢያ መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል።

ይኼንንም ተከትሎ የተጠናቀቁ የምርጫ ሕግ ማሻሻያ የመጀመርያ ረቂቆችን ለባለድርሻ አካላት ለማቅረብና ግብዓት ለመሰብሰብ፣ ሐሙስ ኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. የመጀመርያ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚያካሂድ ታውቋል።

በምርጫ ቦርድ አደረጃጀት ላይ የማሻሻያ ሐሳቦችን የያዘ ረቂቅ ለውይይት ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የተቋሙ አደረጃጀት በኮሚሽን ደረጃ እንዲሆንና መጠሪያውም የምርጫ ኮሚሽን እንዲሆን አማራጭ የማሻሻያ ሐሳብ ሆኖ ለውይይት እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል።

በተያያዘ ዜና መንግሥት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ለማጠናከር ባስቀመጠው ዕቅድ መሠረት፣ ተቋሙን የሚመራ ጠንካራና በዘርፉ ልምድ ያለው ባለሙያ በማፈላለግ ላይ እንደሚገኝ፣ በዚህ መሠረት በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት አክሽን ኤድ የተባለው የሲቪክ ማኅበር ባልደረባ፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሂውማን ራይትስ ዋች ለተባለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የአፍሪካ ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ከሚገኙት አቶ ዳንኤል በቀለ ጋር ንግግር በማድረግ ላይ እንደሚገኝ፣ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት አመራር ለሪፖርተር ጠቁመዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...