Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት መንገዷን እየቀየረች ስለመሆኗ የዓለም ባንክ ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም ባንክ ላለፉት 15 ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የቀጥታ በጀት ድጋፍ እንደ አዲስ በማስጀመር ለኢትዮጵያ የ1.2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር እየወሳዳቸው የሚገኙ ‹‹መዋቅራዊ የለውጥ ሒደቶች›› ላይ እምነት እንዳለውና እንደ ቴሌኮም፣ ሎጂስቲክስና የመሳሰሉትን ለግሉ ዘርፍ ክፍት የማድረጉ ዕርምጃም እንደሚደገፍ አስታውቋል፡፡

መንግሥት ባስቀመጠው ‹‹የሦስት ዓመታት የሪፎርም ፍኖተ ካርታ›› መሠረት፣ የባንኩ ባለሙያዎች እንደሚገምቱት መንግሥት ቀስ በቀስ ከልማታዊ መንግሥትነት የኢኮኖሚ ሞዴል እየወጣ መምጣቱን የሚያመላክት ነው፡፡ ምንም እንኳ የልማታዊ መንግሥት ሞዴል የማይካዱ በርካታ የልማት ስኬቶችን ለማስመዝገብ ቢያስችልም፣ ባንኩ እንደሚያምነው ነባሩ ሥርዓት አሁን ላይ ለኢትዮጵያ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ የመሆኑ ጉዳይ ግን እያበቃለት መጥቷል፡፡

በዓለም ባንክ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ማቴው ቬርጊስ እንደሚገልጹት፣ እስካሁን በመንግሥት መራሹ የኢኮኖሚ ሞዴል አማካይነት የታየውን ስኬት በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሚዛኑን የማስተካከል አካሄድን ይጠይቃል፡፡

መንግሥት ይፋ ባደረገው እንደ ቴሌኮም፣ ሎጂስቲክስና ትራንስፖርት ዘርፍ በተለይም የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ አካባቢ ወደ ግል የሚዛወሩት የልማት ድርጅቶች በከፊል ይዞታቸው እንደሆነ ቢገለጸም፣ ሚስተር ማቴውና የሥራ ባልደረቦቻቸው ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት መሠረት ግን የሪፎርም ዕርምጃዎቹ ከዚህም በላይ ይዘት ያላቸውና በመንግሥት በሞኖፖል የተያዙ በርካታ መስኮችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት የማድረግ ድባብ ያለው እንደሆነ መገንዘባቸውን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

‹‹ይፋ የተደረገው ጉዳይ የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል የማዛወሩ ተግባር ቢሆንም፣ ይህም በራሱ በጣም የሚያበረታታ ለውጥ ነው፡፡ ይሁንና በእኛ ምልከታ ኢትዮጵያ ከፕራይቬታይዜሽን የበለጠ ተጠቃሚ የምትሆነው በእነዚህ ዘርፎች ውስጥ ተወዳዳሪነትን ማስፈን ስትችል ነው፤ እንደሚገባኝም የመንግሥት ዓላማም በዚህ አቅጣጫ መጓዝ ነው፤›› በማለት ረቡዕ ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች አብራርተዋል፡፡

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ካሮላይን ተርክ በበኩላቸው፣ በመንግሥት የተካሄዱት ፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ከባለሥልጣናት ጋር መተማመንን በማስፈን የቀጥታ ድጋፍ ለመስጠት የሚያበቁ ጅምሮች ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡ 

ለ15 ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የቀጥታ በጀት ድገፍ በማስጀመር ባንኩ በሦስት ዋና ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩርም አስታውቋል፡፡ አንደኛ የልማት ፋይናንስ ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የንግዱን ከባቢ አየርና የፋይናንስ ዘርፉን ብሎም ሰፊ የግልጽነትና የተጠያቂነት መስኮችም የባንኩ የትኩረት መስኮች እንደሚሆኑ፣ በባንኩ የዕድገትና ተወዳዳሪነት ኦፕሬሽን ዘርፍን የሚመሩት ናታሊያ ማይሊንኮ ናቸው፡፡ እንደ ሚስስ ማይሊንኮ መንግሥት ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የልማት አጋርነት ሥርዓትን መመሥረት ጀምሮ በቴሌኮም መስክ ሲወስዳቸው የቆዩት የለውጥ ዕርምጃዎች፣ በንግድ ፈቃድ አወጣጥና አሰጣጥ ረገድ የታዩት ማሻሻያዎች ይታዩ የነበሩ መጓተቶችን በመቀነስ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ኃላፊዋ ጠቅሰዋል፡፡ በንግድ ውድድር ሕግና በኢንቨስትመንት አዋጅ መስክ የሚጠበቁ ለውጦች፣ በበጎ አድራጎት ሕግ ማሻሻልና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች መስክ የሚጠበቁት ባንኩ ለሚሰጣቸው ድጋፎች ለውጦች ማስተማመኛ እንደሆኑም አብራርተዋል፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥት በከፊል ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲዛወሩ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ድርጅቶች ጉዳይ እንደ ቀላል ተግባር የሚወሰድ እንዳልሆነ የሚጠቅሱት ሚስስ ናታሊያ፣ ፕራይቬታይዜሽን ውስብስብ ሒደት እንደሆነ፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለ የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ብቸኛ ተዋናዮች ባልሆኑበት አግባብ እንዲህ ያለው ዕርምጃ ቀላል እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡

‹‹ባለሥልጣናቱ በእነዚህ ዘርፎች ውስጥ መተግበር ስለሚገባው የሕግና የአስተዳደር ማዕቀፍ ማሰብ አለባቸው፡፡ መንግሥት በምን መልኩ ከልማት ድርጅቶች የሙሉ ባለቤትነት ይዞታ ራሱን በሚያስወጣበት ወቅት፣ የአነስተኛና የከፍተኛ ባለድርሻዎች መብት በምን አግባብ እንደሚታይ ማስቀመጥ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ወደፊት ዋና ዋና የሚባሉት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል በሚዛወሩበት ወቅት ኢንዱስትሪው ሊረበሽ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች እንደሚኖሩም አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም የገበያው ሁኔታ፣ የውድድሩ ደረጃ ብሎም ኢንዱስትሪው የሚመራባቸውን መንገዶች በሚገባ ማጤን የመንግሥት የቤት ሥራ ስለመሆኑም ሚስስ ናታሊያ አስታውሰዋል፡፡ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል በማዘዋወር ሒደት ውስጥ የሚታየው የዓለም ተሞክሮም በስኬትና በአስከፊ ውድቀት የታጀበ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ፕራይቬታይዜሽን በሁለት ምዕራፎች የሚከናወን ሒደት ሲሆን፣ አንደኛው ፕራይቬታይዜሽኑ የሚከናወንባቸውን ሒደቶች መምረጥ ነው፡፡ ሁለተኛውና ዋናው የዝውውር ሒደትም እንደ ጨረታ ያሉትን ልውውጦች የሚያካትተው ዋናው የፕራይቬታይዜሽን ሒደት ነው፡፡ በመሆኑም የዓለም ባንክ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የተጀመረው የፕራይቬታይዜሽን ሒደት በጅምር ላይ የሚገኝ ሒደት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዚህ አግባብ መሠረት መንግሥት የፕራይቬታይዜሽን ሴክሬታሪያት በማቋቋም ወደዚህ መንገድ የሚወስዱትን አማራጮች እየለየ በመሆኑ የዓለም ባንክም ይህንን ሒደት የሚያግዙ የቴክኒክ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ሚስስ ናታሊያ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ፕራይቬታይዜሽንን ማካሄድ ከባድ በመሆኑ የብዙ ማራቶኖች ሒደት ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡ 

እንደሚታወሰው ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ የተከሰተውን ግጭትና የ200 ዜጎች ሕይወት መጥፋትን ተከትሎ፣ በርካታ የኢትዮጵያ መንግሥት የልማት አጋር እየተባሉ የሚጠሩ የሁለትዮሽና የባለብዙ አጋሮች ለአገሪቱ የቀጥት በጀት ድጋፍ ከመስጠት ታቅበው ነበር፡፡ በመሆኑም ሲሰጡ የነበሩ ድጋፎች በሙሉ ወደ ፕሮግራም በጀት ሥርዓት ተቀይረው፣ ለመንግሥት ከሚሰጥ ድጋፍ ይልቅም በታችኛው የመንግሥት እርከን በሚገኙና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት በሚተገበሩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ያነጣጠሩ ሆነው ቆይተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎም በርካታ የለውጥ ዕርምጃዎች ይፋ በመደረጋቸው፣ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች ከሚባሉት ውስጥ አንዳንዶቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖሊሲዎች የቀጥታ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው የዓለም ባንክም የ50 በመቶ ዕርዳታና የ50 በመቶ የረዥም ጊዜ ብድር ይዘት ያለውን የ1.2 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ድጋፍ በማፅደቅ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች