Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የደረጃ ዕድገትና የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግላቸው ነው

የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የደረጃ ዕድገትና የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግላቸው ነው

ቀን:

በኢትዮጵያ በሚገኙ ከተሞችና ገጠራማ ሥፍራዎች ተሰማርተው የጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪና የደረጃ ዕድገት እንደሚደረግላቸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ባለፉት አምስት ዓመታት በተለያዩ ከተሞች ሲተገበር የቆየው የከተማ ጤና ማጠናከር ፕሮጀክት መጠናቀቁን አስመልክቶ የጤና ኤክስቴንሽንና የመሠረታዊ ጤና ክብካቤ ዳይሬክተሩ አቶ ተመስገን አየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለሙያዎቹ ከደረጃ ሦስት ወደ ደረጃ አራት፣ ከደረጃ አራት ላይ ያሉት ደግሞ ወደ ዲግሪ ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያድጋሉ፡፡

ለዚህም ዕውን መሆን የተሻሻለ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የተቀረፀ ሲሆን፣ የድርጊት መርሐ ግብርም ተዘጋጅቶ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅሰስቃሴ በመከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

በመርሐ ግብሩ መሠረት ባለሙያዎች የደመወዝና የደረጃ ዕድገት እንዲያገኙ የሚደረግ ከመሆኑም ባሻገር፣ ተጠቃሚው ኅብረተሰብ የሚያገኘው የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰፋና የአገልግሎት አሰጣጡ የጥራት ደረጃም ከፍ እንደሚል አስታውቀዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበረው በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ላይ ማሻሻያ ሊታከልበት የቻለው በርካታ ተግዳሮች ተጋርጠውበት ስለነበር ነው፡፡ ከተግዳሮቶቹም መካከል የአስተዳደር መጓደል፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች የሥራ ጫና፣ የዕድገትና የማትጊያ ሥርዓት አለመኖር ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም እንደተጀመረ ሲሰጥ የነበረው ክትትልና ድጋፍ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ መቋረጡ፣ እንዲሁም የጤና ኬላዎቹ በተፈለገው ደረጃ አለመገኘታቸው ተግዳሮቶቹን ውስብስብ እንዳደረጉት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡  

እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባን ጨምሮ በ49 ከተሞች ሲተገበር የነበረው ፕሮጀክት 2.5 ሚሊዮን ለሚጠጋ ሕዝብ ጥራቱን የጠበቀ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን አስችሏል፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ ከከተሞች መስፋፋት ጋር ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች መፍትሔ መፈለግ ሲሆን፣ በተለይ ትኩረት አድርጎ የተንቀሳቀሰውም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኘው የኅብረተሰቡ ክፍል ላይ ነው፡፡

የጤና ችግሮቹም ወባ፣ ቲቢ፣ ኤችአይቪ/ኤድስ የመሳሰሉ ተላላፊና ስኳርና ደም ግፊት የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸውን አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዳማና አዲስ አበባ ላይ ያካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በአብዛኛው ሰው የሚሞትበት ምክንያት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሳቢያ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተው፣ ከዚህ ትኩረት አንፃር የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እንደ አንድ ፓኬጅ ይዘው እንደሚያስተምሩና ወደ ጤና ጣቢያ ሪፈር እንደሚያደርጉም አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ቤት ለቤት እየተንቀሳቀሱ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ አጠቃላይ በሽታዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ምርመራና ሕክምና የሚሰጡ ሲሆን፣ ከአቅማቸው በላይ ከሆነ ደግሞ ወደ ጤና ጣቢያ ሪፈር አድረገው አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡

በዚህ ዓይነት የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረገው የአምስት ዓመቱ ፕሮጀክት ተግባራዊ የሆነው ዩኤስኤአይዲ በተገኘና በጄኤስአይ በኩል የተተገበረ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎች ነው፡፡ ከድጋፎቹም መካከል የቴክኒክ ድጋፍ የተደረገው ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ለክልል ጤና ቢሮዎች ለተዘጋጀው መመርያና የሥልጠና ሞጁሎች፣ እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ላካሄዱት ሱፐርቪዥን ነው፡፡

የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ባወጣውም ጋዜጣዊ መግለጫ 2,500 ለሚሆኑ ለከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቱን የተሻሻለ የውኃ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና አጠባበቅ እንዲኖር መደረጉንም አመላክቷል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ለሕክምናው ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ የምታደርግ መሆኑን መግለጫው ጠቁሞ በየዓመቱ ለኤች አይቪ ኤድስ፣ ለወባ፣ ለእናቶች ጨቅላ ሕፃናትና ጤና፣ ለሥርዓተ ምግብ፣ ለቲቪ፣ ለሳኒቴሽንና ለኃይጂን 200 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ባለፉት አምስት ዓመታትም ለልማትና ለሰብዓዊ ዕርዳታ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡    

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የማዕከላዊ ስታትስቲክስ በ2009 ዓ.ም. ያወጣውን መረጃ ዋቢ አድርጎ እንዳመለከተው ከ90.4 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው ከተማ ነዋሪ ነው፡፡

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም መተግበር መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ይህ ፕሮግራም በዋናነት ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች መፍትሔ ለመፈለግ የተጀመረ ሲሆን፣ በተለይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ባሉ ኅብረተሰብ ላይ ነው፡፡

እነዚህን አገልግሎቶች ወደ ኅብረተሰቡ የሚያደርሱ 5,000 ያህል የከተማ ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎችም 400 በሚሆኑ ከተሞች አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ በነርሲንግ ዲፕሎማ ወይም አሥረኛ ክፍል ያጠናቀቁና የሦስት ዓመት ሥልጠና የወሰዱ ናቸው፡፡ በአማካይ አንድ የኤክስቴንሽን ሠራተኛ 500 ለሚሆኑ ቤተሰቦች ቤት ለቤት አገልግሎት እንደምትሰጥ ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...