Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቡና መገኛነት ውዝግብ በካፋ ዞን ተቃውሞ ፈጠረ

የቡና መገኛነት ውዝግብ በካፋ ዞን ተቃውሞ ፈጠረ

ቀን:

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ከኅዳር 24 እስከ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለሚያካሂደው ዓለም አቀፍ የቡና ሁነት በምድረ ቀደምት (“International Coffee Event in Ethiopia – The Land of Origins”) የተሰኘ ዝግጅት ላይ ተሳታፊዎችን ለመጋብ በወጡ ጽሑፎች፣ የካፋን የቡና መገኛነት የሚክዱ ጽሑፎች ወጥተዋል በማለት በደቡብ ክልል በካፋ ዞን በሁሉም ወረዳዎችና በቦንጋ ከተማ ከፍተኛ የተቃውሞ ሠልፎች ለሦስት ቀናት በተከታታይ ተካሄዱ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፌስቡክ ገጹ ያሠፈረው ለዝግጅቱ ተሳታፊዎች የተላለፈ መልዕክት፣ ‹‹ክብረ በዓሉ ቡና አምራቾችን፣ ቆዪዎችን፣ ላኪዎችን፣ ተመራማሪዎችን፣ ጸሐፊዎችንና ቡና ወዳዶችን ከመላው ዓለም የሚያሰባስብ ሲሆን፣ ዝግጅቱም ዓውደ ርዕይና ኮንፈረንስ ቡና ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ተገኘባትና ለዓለም ወደ ተሠራጨባት የቡና መገኛ ካፋ የሚደረግ ጉብኝትን ያጠቃልላል፤›› ይላል፡፡

ይሁንና በተመሳሳይ ይዘት በቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተላለፈው መልዕክት፣ ‹‹ኮንፈረንሱ ሲጠናቀቅ የቡና መገኛ ወደ ሆነችው ጅማ የሚደረገው ጉብኝት እንዳያመልጥዎ፤›› ሲል ይጋብዛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይሁንና ሁለቱም ድርጅቶች ጽሑፋቸውን የቀየሩ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ጉብኝት እንዳያመልጥዎ ሲሉ በገጾቻቸው አስፍረዋል፡፡

ይኼንንም ለአንድ ዝግጅት የተላለፈ የተምታታ መልዕክት የተመለከቱ የካፋ ዞን ነዋሪዎችና ምሁራን ከፍተኛ ‹‹ቁጣን›› ያዘለ ሠልፍ በቦንጋ ከተማና በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች እንዳደረጉ፣ የሠልፉ አስተባባሪዎችና የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ማስረሻ በላቸው ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

‹‹መጀመርያ የቡና መገኛ ወደሆነችው ካፋ ጉብኝት አለ ተብሎ ነበር፡፡ ከዚያ ጅማ ተባለ፡፡ ይህ ለረዥም ጊዜ መልስ ሳይሰጠው እየተንከባለለ የመጣ ጥያቄ ስለነበር ሕዝቡ ፈንቅሎ ወጣ፤›› ሲሉ ከሠልፉ አስተባባሪዎች አንዱ አቶ ምንውዬለት መላኩ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ይኼ ሕዝቡ የማይደራደርበት ታሪኩ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ሠልፉ በተደረገባቸው ሦስቱም ቀናት ከየወረዳው ወደ ቦንጋ በርካታ ሰዎች እንደመጡና ተቃውሞ እንዳሰሙ የገለጹት አቶ ምንውዬለት፣ መምጣት ያልቻሉት በየአካባቢዎቻቸው ሠልፎችን በማደራጀት ማካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በማስተካከል ባወጣው የፌስቡክ ጽሑፍ የቡና አብቃይ በሆኑ የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች ጉብኝት ይደረጋል ቢልም፣ ሠልፈኞቹ የካፋ የቡና መገኛነት ይነገርልን እንጂ ይህ አይደለም ጥያቄያችን ሲሉ፣ ‹‹ካፋ የቡና አብቃይ ብቻ ሳትሆን መገኛም ምድር ነች፤›› የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል፡፡

ይኼንን የሕዝቡን ተቃውሞ በማስመልከት የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምርያ ኃላፊ አቶ አስራት አጦ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ‹‹የቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን ሐሳቡን ገልብጦ ጅማ የቡና መገኛ ብለው መልቀቃቸው፣ በዚሁ በመደመር ወቅት ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት ሆነ ተብሎ ታሪክ ለመቀማትና በኅብረተሰብ ውስጥ ጥርጣሬ ለመፍጠር የተከናወነ ሥራ መሆኑን እንገልጻለን፤›› ብለው፣ ይህ ድርጊት እንዲቆም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሠልፉ በተካሄደባቸው ሦስት ተከታታይ ቀናት የመንግሥትም ሆነ ሌሎች ሥራዎች የቆሙ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት ንብረት እንዳልወደመና ሰው እንዳልተጎዳ የዞኑ አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከመንገድ መዘጋት በዘለለ የደረሰ ጉዳት የለም፡፡ የፌዴራል መንገዶች ተዘግተዋል፡፡ ይህ አግባብ አይደለም፡፡ ይሁንና ጥያቄው የአካባቢው ሰላም ሳይታወክ ሊቀርብና ምላሽ ሊሰጠው ይገባል፤›› ሲሉ አቶ ማስረሻ አስረድተዋል፡፡

የተቃውሞው መባባስ ዋነኛ ምክንያት የሆነው በሚሊኒየም በዓል አከባበር ወቅት በቦንጋ ከተማ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ፣ ከቆይታ በኋላ ግንባታው ተጠናቅቆ ቢመረቅም እስካሁን ሥራ ሳይጀምር መቅረቱ እንደሆነም አክለዋል፡፡

‹‹ይህ የቡና ሙዚየም ወደ ሥራ እንዳይገባ እንቅፋት የሆነው አንዱ ጉዳይ ይህ የቡና መገኛነት ላይ ያለው ክርክር ነው፡፡ የትኛውም የመንግሥት አካል ይኼንን በሚመለከት የሰጠው ምላሽ የለም፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ምላሽ ያገኝ ዘንድ እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡

በቦንጋ ከተማ በ27 ሚሊዮን ብር የተገነባው ዓለም አቀፍ የቡና ሙዚየም በሚሊኒየም አከባበር ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ በስምምነት የተደረገ እንደሆነና ምርጫውም ሳይንሳዊ እንደነበር፣ የኮሚቴው አባል የነበሩትና ለቡና ሙዚየሙ መገንባት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት፣ ብሎም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፊሎሎጂ መምህር የሆኑት ሐሰን ሰዒድ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የቡና ታሪክ ላይ መጽሐፍ እያዘጋጁ ያሉት ምሁሩ፣ ለሁላችንም መጥቀም የሚገባውን ጉዳይ እየተከራከርንበት ከቡና ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው አካባቢዎች ይበልጡኑ እየተጠቀሙ ነው ሲሉ ያሰምራሉ፡፡

እንደ እሳቸው ምልከታ ባህላዊ የቱርክና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የቡና አፈላል ሥርዓቶች በዩኔስኮ የተመዘገቡት ምንም ዓይነት ቡና ሳያበቅሉ ነው፡፡

‹‹እኛ ግን እጅግ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን ስንችል እስካሁን ሀ ሁ ላይ እንዳክራለን፤›› ሲሉም ይተቻሉ፡፡

የቡና መገኛ ከየትኛውም የዓለም ሥፍራዎች በተለየ ሁኔታ ካፋ መሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ ማስረጃዎች እንዳሉም ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡ በ2002 ዓ.ም. አካባቢ ይፋ የሆኑ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች፣ አምስት የቡና ፍሬዎች በካፋ ዞን ኩማሊ ዋሻ ውስጥ መገኘታቸውንና በተደረገባቸው ምርምርም ከ200 ዓ.ም. በፊት የነበረ፣ ዕድሜን ያስቆጠሩ መሆናቸውን በማስረዳት፣ የዚህን ያህል ዕድሜ ያለው የቡና ግኝት እስካሁን እንደሌለና በዱባይ አንድ ፍሬ፣ በቼክ ሬፐብሊክ ደግሞ አንድ ፍሬ የተገኙ ቢሆንም፣ እነዚህ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የሚመዘዝ ታሪክ ብቻ ነው ያላቸው ይላሉ፡፡

ይህ የአርኪዎሎጂ ጥናት የተደረገው በኤልዛቤጥ ሂልዴብራንድና በጆሴፊን ሌሱር ነው፡፡ የጥናቱ ርዕስ፣ ‹‹The Holocene Archaeology of Southwest Ethiopia: New Insights from the Kafa Archaeological Project›› የሚል ነው፡፡

በዚህ ጥናት የዩኒቨርሲቲ መምህሩ የሚጠቅሱት ግኝት ተተንትኗል፡፡

ከአርኪዮሎጂያዊ ግኝቶች ባለፈም በካፋ ቡና ከየትኛውም አካባቢ በበለጠ ማኅበራዊ ፋይዳ እንዳለው፣ የማኅበራዊ ጥናት ግኝቶች ያሳያሉ ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

‹‹በካፋ ሴት ልጅ ስታገባ ቡና ማፍላት ትችላለች ወይ ነው ተብሎ የሚጠየቀው፡፡ በንግድ ድርድር ላይ ቡና እንጠጣ ከተባለ ስምምነት ተደርሷል ማለት ነው፡፡ የማንኪራ የቡና ዛፍ የሚሰጣት ክብርም ምን ያህል እንደሆነ በአካባቢው ሄዶ ማየት ይቻላል፡፡ ፍሬዋ መሬት ሲወድቅ እንጂ ዛፉ ላይ ወጥተው አይለቅሙም፤›› ሲሉም ይሞግታሉ፡፡ ስለዚህ የቡና ሙዚየሙ ወደ ካፋ ቦንጋ የሄደው ተመክሮበት ነበር ይላሉ፡፡

ይሁንና በሁሉም የቡና አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች የተለያዩ ሙዚየሞችን ለመገንባትና አንድ ብሔራዊ የቡና ቀን ታውጆ በሁሉም አካባቢዎች ለማክበር ታቅዶ፣ በዚህ አለመግባባት እስከ ዛሬ ሊሳካ አለመቻሉንም ይገልጻሉ፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ጅማ የቡና መገኛ እንደሆነች የሚከራከሩ አካላት ቡና ጮጬ በተባለች አካባቢ ተገኘ በማለት፣ ካልዲ የሚባል የፍየል እረኛ በፍየሉ ላይ ባየው ባህርይ ተነሳስቶ ቡናን እንዳገኘ ይናገራሉ፡፡ ይህ ታሪክ በተመሳሳይ በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ማንኪራ ቀበሌ የምትገኘው ቡኒ መንደር የቡና መገኛነቷን ለማስረዳት የሚነሳ ትርክት ነው፡፡ ይሁንና ይህ ትርክት በ19ኛው ከፍለ ዘመን የተፈበረከ አፈ ታሪክ እንደሆነ የሚያስረዱት  ሀሰን (ዶ/ር)፣ ከዚህ የበለጠ ጉዳዩን የሚያብራራ ሳይንሳዊ ግኝት በርካታ ነው ይላሉ፡፡

በአገር ደረጃ የቡና ምርምር ለማድረግ ኃላፊነት የተሰጠው የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል ሲሆን፣ ማዕከሉ ግን ከታሪክ ይልቅ የቡና ጣዕም ልዩነትና ተያያዥ ጥናቶችን ስለሚደርግ ይህ ጉዳይ ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም የሚሉም አሉ፡፡

በተጨማሪ ቀድሞ በነበረው የአገሪቱ አወቃቀር ሥርዓት ካፋ ክፍለ ሀገር ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ ጅማን የሚያጠቃልል ስለነበር፣ ጅማም የክፍለ ሀገሩ መቀመጫ ስለነበረች ከዚህ ጋር በተገናኘ ጅማ የቡና መገኛ እንደሆነች እንዲታሰብ አድርጓል ሲሉም የሚከራከሩ አልታጡም፡፡

በዚህ የቡና መገኛነት ምክንያት ለተቃውሞ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማና በዙሪያው የወጡ ሠልፈኞች ከዚህ ጉዳይ ባለፈ የካፋ ክልልነት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ የዞኑ ርዕሰ መስተዳድር ክልሉ ኮሚቴ አቋቁሞ ጉዳዩን እያጠና እንደሆነና ሕጉን ተከትሎ የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል፡፡ በዋናነት በካፋ፣ ሸካና ቤንች ማጂ ያለው ጥያቄ የሚመነጨው ለክልሉ መቀመጫና ርቀትና ፍትሕ ለማግኘት የሚጓዙትን ርቀት መብዛቱን በመጥቀስ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...