Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊማጨስ በተከለከለባቸው ከሚተን ጭስ ከአራት ሺሕ በላይ ጎጂ ቅንጣቶች መገኘታቸው ተገለጸ

ማጨስ በተከለከለባቸው ከሚተን ጭስ ከአራት ሺሕ በላይ ጎጂ ቅንጣቶች መገኘታቸው ተገለጸ

ቀን:

በአዲስ አበባ ትንባሆ ማጨስ በተከለከለባቸው 15 ቦታዎች ከተነነው የሽሻና ትንባሆ ጭስ ውስጥ ደባል አጫሾችን (የማያጨሱ ሰዎችን) ለከፋ የጤና ጉዳት የሚዳርጉ 4,189 እጅግ በጣም ደቃቅ ቅንጣቶች መገኘታቸው በጥናት ተመለከተ፡፡

ጥናቱን ያካሄደውና መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ‹‹ካምፔን ፎር ቱባኮ ፍሪ ኪድስ››፣ በየኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ደረጀ ሽመልስ እንደገለጹት፣ ጥናቱ የተካሄደው ቦሌ መድኃኔዓለም፣ ሃያ ሁለት፣ ቦሌ፣ ቦሌ ቺቺኒያ፣ ቦሌ ብራስ፣ ወሎ ሠፈር፣ ፒያሳ፣ ዓድዋ ድልድይ፣ ባልደራስ፣ መገናኛ፣ ገርጂ፣ ገርጂ መብራት ኃይል፣ አራት ኪሎ፣ ዮሐንስና መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኙና ትንባሆ ማጨስ ክልክል በሆነባቸው ሬስቶራንቶች፣ ቡና ቤቶችና የምሽት ክበቦች ውስጥ ነው፡፡

የአየር ብክለትን የሚያሳይ፣ በተለያዩ 60 አገሮች ውስጥ ጥቅም ላይ በዋለውና ‹‹ሳይድፓክ ኤኤም 520›› በተባለው መሣሪያ እየታገዘ ከነሐሴ 2010 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 2011 ዓ.ም. ድረስ በሬስቶራንቶች፣ ቡና ቤቶችና የምሽት ክበቦች ውስጥ በተከናወነው ጥናት፣ ለጤና ጠንቅ ሆነው ከተገኙት ቅንጣቶች መካከል ሺሻ ብቻ በሚጨስባቸው 2,568፣ ሺሻና ትንባሆ በሚዘወተርባቸው 1,050፣ ትንባሆ ብቻ በሚቦንባቸው 409፣ ትንባሆ ማጨስ ባልተስተዋለባቸው ቦታዎች 222  አደገኛ ቅንጣቶች ተመዝግበዋል፡፡

- Advertisement -

ይህም ውጤት ከማይጨስባቸው ቦታዎች አንፃር ሲታይ በሺሻው ጢስ የተገኘው ቅንጣት ከ11 ዕጥፍ በላይ፣ የሺሻና ትንባሆ ጭስ ያስከተሉት ቅንጣት ከአራት ዕጥፍ በላይ፣ የሲጋራ ጭስ ቅንጣት ወደ ሁለት ዕጥፍ ገደማ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ትንባሆ ማጨስ ባልተስተዋለባቸው ቦታዎች ላይ የተከሰቱት ቅንጣቶች የአደገኝነት መጠናቸውን ለማወቅ አልተቻለም፡፡ ይህም ሆኖ ግን ትንባሆ ባይጨስባቸውም በአካባቢው ያለው አየር መበከሉን ያመለክታል፡፡

ጥናቱ በተከናወኑባቸው 47 ቤቶች ውስጥ  በእያንዳንዳቸው መሣሪያው ለ30 ደቂቃ ያህል ተቀምጦ በየቤቱ ያለው የጢስ መጠን ምን ያህል ለጤና አደገኛ እንደሆነ መዝግቧል፡፡ የተመዘገበውንም ውጤት የሚያቀርበው በተሠራለት ሶፍት ዌር መሠረት ወደ ቁጥር በመቀየር ሲሆን፣ የተቀየረውንም ቁጥር ትርጉም በአግባቡ መረዳት የሚቻለው በዓለም ጤና ድርጅትና በአሜሪካ ተቀባይነት ባለው መለኪያ መሠረት ነው፡፡

እንደ አቶ ደረጀ የጥናቱ ዋና ዓላማ ትንባሆ ማጨስ በተከለከለባቸው ቦታዎች ውስጥ ያለውን የአየር ብክለት መጠን የሚያሳይ መረጃ ለአስፈጻሚ አካላት፣ ለፖሊሲና ለሕግ አውጪዎች ለማሳወቅ ነው፡፡ በትንባሆ ጭሱ ውስጥ ከሰባት ሺሕ በላይ በጣም አደገኛ የሆኑ ኬሚካሎች እንዳሉት፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ70 በላይ የሚሆኑት ካንሰር አምጪ ኬሚካሎች እንደሆኑ፣ ኬሚካሎቹም በዋናነት የልብ በሽታ፣ ስትሮክ፣ የኩላሊት፣ የሳምባ ካንሰር ያስከትላሉ፡፡ ትንባሆ በዓለም ላይ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የሚገድል ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን ያህሉ የሚሞቱት ቀጥታ ትንባሆን በማጨስ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች በሚያጨሱት ጭስ ምክንያት ተጋላጭ በመሆን ነው፡፡

ትንባሆ የማይጨስባቸውን ቦታዎች በሚመለከት የተቀመጡ የሕግ ድንጋጌዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካፀደቀው የዓለም ጤና ድርጅት የትንባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን አንፃር ሲገመገም በቂ ነው ወይ? ቅጣቶችንም አስቀምጧል ወይ? ጉድለቶቹ ምንድናቸው የሚለውንም ለመገምገም ይረዳል ተብሏል፡፡

አሁን ያለው ሕግ ትንባሆ በማይጨስባቸው ቦታዎች ውስጥ ትንባሆን ለሚያጨሱ የቤቱ ባለቤት የተለየ ክፍል ሊያዘጋጅ እንደሚችል ይፈቀዳል፡፡ ይህ ደግሞ ከዓለም ጤና ድርጅት የትንባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽንና ኮንቬንሽኑን ለማስፈጸም ከተዘጋጁ መመርያዎች ውስጥ ካሉ ድንጋጌዎች ጋር የሚቃረንና የሚያጨሱ ሰዎችን የሚጠብቅ አይደለም፡፡

ከዚህ አንፃር የማያጨሱ ሰዎችን ከደባል አጫሽነት መጠበቅ የሚቻለው ትንባሆ ማጨስ የሚከለከልባቸውን ሬስቶራንቶች፣ ቡና ቤቶችና የምሽት ክበባት ሙሉ ለሙሉ ከትንባሆ ጭስ ነፃ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

በትምህርትና በጤናው ዘርፎች የማማከር ሥራ የሚያከናውነው ዘሪሁን አሶሼትስ የግል ኩባንያ ተመራማሪ አቶ ቴዎድሮስ ደምለው እንዳብራሩት፣ በጥናቱ ላይ ከየክፍለ ከተሞቹ የተውጣጡ 1,000 ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህም 60 ከመቶው  ወንዶች 40 ከመቶው ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡

በጥናቱ መሠረት 95 በመቶ ያህሉ ነዋሪ ትንባሆ ማጨስና ለትንባሆ ጭስ መጋለጥ ለጤና በጣም አደገኛ መሆኑን ይረዳል፡፡ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካላቸው ወገኖች መካከል 88 በመቶ አዋቂዎች ሲሆኑ የቀሩት 97 በመቶ ወጣቶች ናቸው፡፡

96.7 ያህሉ ነዋሪዎች በሥራ ቦታዎች፣ በቢሮዎች፣ በሬስቶራንቶችና በቡና ቤቶች ጨምሮ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ትንባሆ ማጨስን የሚከላከለውን ብሔራዊ ሕግ ይደግፉታል፡፡ በአገሪቱ ትንባሆን የሚመለከቱ ማስታወቂያዎች እንዲከለከሉም ፍላጎት አላቸው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው ጥናት መሠረት ቡና ቤትና በምሽት ክበቦች ውስጥ 60.4 በመቶ፣ በሬስቶራንቶች 31.1 በመቶ፣ በዩኒቨርሲቲዎች 29.4 በመቶ ያህል ሰዎች ለደባል አጫሽነት መጋለጣቸውን አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡

ሲጋራ ከማያጨሱት ወገኖች መካከል 97 በመቶ ያህሉ፣ እንዲሁም 92 በመቶ የሚሆኑት የዱሮ አጫሾችና 82 በመቶ የሚጠጉት መደበኛ አጫሾች የትንባሆ ምርትን ማስተዋውቁ ሥራ እንዲቆም ይጠይቃሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ወረቴ ኅብረተሰቡ የትንባሆ ጉዳትን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የራሱንና የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችል ዕርምጃ መውሰድና በራስ መወሰን ላይ ግን ችግር እንዳለ አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩ ከጥቅም ጋር በመያያዙ የተነሳ ትንባሆ እንዲሸጥና እንዲስፋፋ በተለያየ መንገድ የሚንቀሳቀሱና አቅም ያላቸው አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ መፍጠራቸውም ችግሩን ለመፍታት እንቅፋት ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...