Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመቀንጨር የአፍሪካ ሕፃናት ችግር እንደሆነ ቀጥሏል

መቀንጨር የአፍሪካ ሕፃናት ችግር እንደሆነ ቀጥሏል

ቀን:

በአፍሪካ በአሁኑ ጊዜ በዋናነት የሚታየው ችግር የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው የተነሳ የተጎዱ ሕፃናት መኖራቸውና፣ ባለፉት 16 ዓመታት ውስጥ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ መቀንጨር የሚታይባቸው ሕፃናት ቁጥር ወደ ስምንት በመቶ ዝቅ ቢልም፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው አማካይ የመቀንጨር መጠን 30.4 በመቶ መሆኑን ዘ አፍሪካን ሪፖርት ኦን ቻይልድ ዌልፌር ዌልቢንግ 2018 አመለከተ፡፡

ከግማሽ በላይ በሚሆኑ የአፍሪካ አገሮች የሚታየው የመቀንጨር መጠን ከ30 በመቶ በላይ ሲሆን፣ በየአገሮቹም የመቀንጨር ሁኔታ የሚያጋጥማቸው ሕፃናት ዕድሜ ከአምስት ዓመት በታች ነው፡፡ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ፣ የመቀንጨር ችግር ያጋጠማቸው ሕፃናት ቁጥር ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ከነበረበት 50.4 ሚሊዮን ወደ 58.5 ሚሊዮን ከፍ ብሏል፡፡  

የተመጣጠነ ምግብ የማይመገቡ ሕፃናት የሚኖሩባቸው አገሮች አጠቃላይ ዓመታዊ የምርት መጠን በመቀንጨር ምክንያት ጫና ውስጥ የሚገባ መሆኑን፣ ኢትዮጵያና ኡጋንዳም ከአጠቃላዩ ዓመታዊ ምርታቸው 16.5 እና 5.5 ኪሳራ በየዓመቱ እንደሚያጋጥማቸውም ተመልክቷል፡፡

- Advertisement -

የኢኮኖሚው ችግር አንድ ነገር ሆኖ፣ በሰው ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ጥፋት ደግሞ የከፋ ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ሕፃናት ላይ ከሚደርሰው ሞት ግማሽ ያህሉ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰት ነው፡፡ ከሞት የተረፉትም፣ የአዕምሮ ዘገምተኛ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ከመሆኑም ባሻገር፣ የመማር፣ የማሰብ፣ የመረዳትና የማስታወስ ችሎታቸውም ዝቅተኛ ነው፡፡

በአፍሪካ ውስጥ የሚታየው የትምህርት ዘርፍ ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑም ሊተኮርበት እንደሚገባ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እንደገመተው ከአምስት ሕፃናት መካከል ሁለቱ ማንበብና መጻፍ ሳይችሉና የሒሳብ ሥሌት ሳይማሩ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ፡፡

እንደተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ደግሞ ዕድሜያቸው ለመጀመርያ ደረጃ ትምህርት የደረሱ 80 በመቶ የሚሆኑ ወንዶችና ከአሥር ልጃገረዶች መካከል ዘጠኙ አይማሩም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሆኑ አብዛኛዎቹ ሕፃናት የሚፈለገው ችሎታ፣ ዕውቀት፣ ግብዩነትና ተወዳዳሪነት የላቸውም፡፡

አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሕፃናት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን አይጠቀሙም፡፡ ይህም ሙሉ አካል ካላቸው የዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር ሲወዳደሩ ከ30 እስከ 50 በመቶ ዝቅ እንደሚያደርጋቸው ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

አፍሪካ ውስጥ በሕግ ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ብዙ ሥራዎች ቢከናወኑም አንዳንዶቹ አገሮች ዓለም አቀፍ መሥፈርት እንደማያሟሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የተባበሩት መንግሥት የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን በወንጀል ተጠያቂነት አነስተኛው የዕድሜ ጣሪያ 12 ዓመት አድርጎ ማስቀመጡን በማስታወስ፣ ሪፖርቱ ካካተታቸው 52 የአፍሪካ አገሮች መካከል 39 ያህሉ በወንጀል የተጠያቂነት ዕድሜ ጣሪያ 12 ዓመት ወይም ከዚያም በላይ ስድስት አገሮች ማለትም ኬፕቨርዴ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጊኒቢሳዋ፣ ላይቤሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሳኦና ቶሜ ፕሪንስፔ በወንጀል የተጠያቂነት ዕድሜ ከፍተኛ 16 ዓመት፣ ካሜሩን፣ ኮትዲቮር፣ ሌሴቶ፣ ማላዊ፣ ደቡብ አፍሪካና ታንዛኒያ ዝቅተኛው የወንጀል ተጠያቂ ዕድሜ አሥር ዓመት በኢትዮጵያ ዘጠኝ፣ በኬንያና ዛምቢያ ስምንት፣ ሞርታኒያ፣ ጋምቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ሲሸልስና ዚምባቡዌ እያንዳንዳቸው ሰባት ዓመት እንዲሆን መወሰናቸውንም አመልክቷል፡፡

አብዛኞች የአፍሪካ አገሮች የሕፃናት መብት ኮንቬንሽን እና የአፍሪካ ሕፃናት ቻርተርን ካፀደቁ በኋላ ልጃገረዶች በሕግ ፊትም ሆነ በኋላ በእኩልነት መታየት ጀምረዋል፡፡ ከ52 አገሮች መካከል 35ቱ ለሁለቱም ፆታዎች ያስቀመጡት የጋብቻ ዕድሜ ጣሪያ 18 ዓመት ነው፡፡ ቡርኪናፋሶ 17፣ ጊኒ ቢሳው፣ ማሊ፣ ሴኔጋልና ዛምቢያ 16፣ ካሜሩን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋቦን፣ ኒጀር፣ ሲሸልስና ታንዛኒያ 15፣ ሱዳን አሥር የጋብቻ ዕድሜ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

አፍሪካ ከየትኛውም ጊዜ ቢሆን በአሁኑ ሰዓት አንፃራዊ ሰላም የሰፈነባት መስላ ብትታይም፣ የውስጥ ግጭቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች በሕፃናት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው፡፡ ዘ አፍሪካን ኮሚቴ ኦን ኤክስፐርትስ ኦን ዘ ራይትስ ኤንድ ዌልፌር ኦፍ ዘ ቻይልድ እንደገመተው፣ በጦርነትና ግጭት ጊዜ የሚሞቱ ሕፃናት በሰላም ጊዜ ከሚሞቱት በ24 እጥፍ ይበልጣል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአኅጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕፃናት ላይ ትኩረት ያደረጉ የፖለቲካ መሻሻልም ተስተውሏል፡፡ ከ2022 ዓ.ም. ከዘላቂ ልማት አጀንዳ ባሻገር የአፍሪካን ልማትና የዕድገት ዕቅድን ለማሻሻልና ሕፃናትን ከኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ተቋዳሽ የሚያደርጋቸው በርካታ ተነሳሽነቶች ተቀርፀዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የአፍሪካ ኅብረት ያወጣው የ2033 ዓ.ም. የሕፃናት አጀንዳና የአሥር ዓመት የትግበራ ዕቅድ ይገኝበታል፡፡

ይህ ዓይነቱ አጀንዳና ፕላን የሴቶች ግርዛት፣ የልጅነት ጋብቻንና የሕፃናት ጥቃት የመሳሰሉ ጎጂ ልማዶችን ለመዋጋት የበኩሉን ዕገዛ እንደሚያደርግ ሪፖርቱ አመልክቶ፣ በአፍሪካ ውስጥ የሚታየው የኢኮኖሚ መሻሻል በሕፃናትና በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ መልካም አጋጣሚ መፈጠሩን አስታውቋል፡፡

በሚቀጥሉት ዓመታትም የአፍሪካ ኢኮኖሚ እያደገ እንደሚሄድ፣ የአገር ውስጥ ገቢን የማሰባሰብ እንቅስቃሴ እንደሚሻሻልና ሙስናን መዋጋት እንደሚቻል በየጊዜው ከሚወጡት ፕሮጀክቶች መረዳት እንደሚቻል ነው ሪፖርቱ ያመለከተው፡፡ ሙስና የሰብዓዊ መብትና የዘላቂ ልማት ፀር መሆኑን፣ የአፍሪካ ኅብረትም ይህንኑ ከግንዛቤ በመውሰድ በ2011 ዓ.ም. የአፍሪካ የፀረ ሙስና ዓመት እንዲሆን መወሰኑንም አስረድቷል፡፡

እንደ ሪፖርቱ ማብራሪያ ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ የሕፃናት ሞት በግማሽ ቀንሷል፡፡ የትምህርት በተለይም የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ከፍ ብሏል፡፡ የደሃ ወይም ገጠራማ በሆኑ ሥፍራ ከሚኖረው ቤተሰብ የወጡ ልጃገረዶች በትምህርቱ እምብዛም ተጠቃሚ ባይሆኑም በአጠቃላይ ሲታይ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገቡ ሕፃናት ቁጥር ጨምሯል፡፡

ባለፉት ሁለት አሠርታት ሕፃናትን ከልዩ ልዩ በሽታዎች ለመታደግ የሚያስችል ክትባት የመስጠት እንቅስቃሴ አድጓል፡፡ በአኅጉሩ በሚገኙ አንዳንድ አገሮች ደሃ የሆኑ ሕፃናት በብዛት ቢታዩም፣ ከአጠቃላዩ አንፃር ሲታይ ብዛቱ እያሽቆለቆለ ሄዷል፡፡

የአፍሪካን ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም መሥራችና ዋና ዳይሬክተር አሰፋ በቀለ (ዶ/ር) ሪፖርቱ ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ ሲሆን እንደገለጹት፣ በአፍሪካ ሕፃናት ላይ ትኩረት ያደረጉና ወጥነት የሌላቸው በርካታ ሪፖርቶች ቢኖሩም፣ የአሁኑ የተቀናጀ፣ ሁሉን አቀፍና ጥራት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

የሪፖርቱ የአፍሪካ አገሮች ለሕፃናት መብትና ደኅንነት መረጋገጥ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለባቸው የሚጠቁም መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...