Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው የቋሚ ኮሚቴዎቹን አደረጃጀት ማሻሻያ አፅድቆ ለኮሚቴዎቹ አመራር እንዲሆኑ በቀረቡት ዕጩዎች ሳይስማማ...

ፓርላማው የቋሚ ኮሚቴዎቹን አደረጃጀት ማሻሻያ አፅድቆ ለኮሚቴዎቹ አመራር እንዲሆኑ በቀረቡት ዕጩዎች ሳይስማማ ተበተነ

ቀን:

የምክር ቤቱ አባላት መንግሥት ከፓርላማው እጁን እንዲያወጣ ጠይቀዋል

ነባር የቋሚ ኮሚቴ አመራሮችን ማየት እንደማይፈልጉ አምርረው ገልጸዋል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው ከቀረቡለት አጀንዳዎች መካከል የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት ማሻሻያን ሁለት ሰዓት ከፈጀ ክርክር በኃላ በሁለት የተቃውሞ ድምፅ አፅድቆ፣ ቋሚ ኮሚቴዎቹን በሰብሳቢነት እንዲመሩ በአፈ ጉባዔው በቀረቡ ዕጩዎች ላይ ሳይግባባ ተበተነ።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ የመጀመርያ አጀንዳ ሆኖ የቀረበውን ከዓለም ባንክ የተገኘ ለሥራ ፈጠራ የሚውል የብድር ስምምነት ካፀደቀ በኃላ፣ የቋሚ ኮሚቴዎችን አደረጃጀት ለማሻሻል በአፈ ጉባዔው አቶ ታገሰ ጫፎ የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ተመልክቷል።

አፈ ጉባዔው ያቀረቡት ይህ የውሳኔ ሐሳብ በሥራ ላይ የነበሩት 21 ቋሚ ኮሚቴዎችን እንደገና መልሶ በማደራጀት፣ ቁጥራቸው ወደ አሥር ዝቅ እንዲል የሚያደርግ ነው።

መንግሥት ለሚያከናውነው ሥራ የላቀ ውጤታማነትን ለማረጋገጥና ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን በተሟላ መልክ መወጣት እንዲችል፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በቅርቡ ለምክር ቤቱ ያፀደቀውን የአደረጃጀት ክለሳ ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴዎቹ አደረጃጀትና ብዛትም ሰብሰብ ብሎ፣ የሰው ኃይልና ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ታስቦ መዘጋጀቱን አፈ ጉባዔው ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት የሚወሰነው በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቢሆንም፣ የዚህ ደንብ አጠቃላይ ድንጋጌ ሳይነካ በአደረጃጀት ላይ ማሻሻያ ማድረግ የሚፈቅድ በመሆኑ፣ አደረጃጀቱ አፈ ጉባዔው ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ መሠረት እንዲሻሻል ተጠይቋል። ይሁን እንጂ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የምክር ቤቱን የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 145 (3)፣ ከአንቀጽ 158 እስከ 161፣ አንቀጽ 162 (1) እና (2)፣ ከአንቀጽ 179 አስከ 197፣ እንዲሁም በ2010 ዓ.ም. የተሻሻለው ደንብ ቁጥር 7 በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ እንደሚተኩ አፈ ጉባዔው ገልጸዋል።

በቀረበው የአደረጃጀት ማሻሻያ መሠረትም 21 የነበሩት ቋሚ ኮሚቴዎች ወደ አሥር ዝቅ እንዲሉ የምክር ቤቱን ውሳኔ በመጠየቅ አደረጃጀቱን ይፋ አድርገዋል።

ነገር ግን ከተሾሙ አንድ ወር እንኳን ያልሞላቸው አፈ ጉባዔ ታገሰ የመጀመርያው ምናልባትም ያልጠበቁት ሙግት ገጥሟቸዋል። በዚህ አጀንዳ ላይ ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ የፈጀ ክርክር የተደረገ ሲሆን፣ የመናገር ዕድል ካገኙ 20 የሚደርሱ አባላት ከሞላ ጎደል ሁሉም የቀረበውን የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀት በመቃወም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

የነበረበው የውሳኔ ሐሳብ የቋሚ ኮሚቴዎቹ አደረጃጀት እንዲሻሻል ያስፈለገበትን አመክንዮ የማያሳይና የምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ አንዳቸውም ምክረ ሐሳባቸውን ሳይጠየቁ የተሰናዳ እንደሆነና በጥናት ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ፣ በድጋሚ ጊዜ ተሰጥቶት በጥልቀት መታየት እንዳለበት አስተያየታቸውን የሰጡት አብዛኞቹ የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። ማሻሻያውን ማን እንዳሰናዳው እንደማይታወቅና ከላይ ወርዶ በምክር ቤቱ ላይ ለመጫን የተፈለገ እንደሚመስላቸውም ተናግረዋል።

ማሻሻያው እስከቀረበበት ቀን ድረስ የባህል ቱሪዝምና የመገናኛ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት መስፍን ቸርነት (አምባሳደር)፣ ጠንካራ የተቃውሞ አስተያየት ከሰጡት አባላት መካካል አንዱ ናቸው።

 ‹‹አንድ እስከ ዛሬ መናገር ያልቻልነውና አሁን ግን ልንናገረው የሚገባው ጉዳይ፣ ይህ ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት የሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለበት ነው፤›› ብለዋል።

የቀረበው የኮሚቴዎች አደረጃጀት ማሻሻያ ሥራ አስፈጻሚው በቅርቡ በራሱ አደረጃጀት ላይ ያካሄደው ማሻሻያ ቅጅ እንጂ፣ ምክር ቤቱ በራሱ መንገድ በጥናት ላይ ተመሥርቶ በሚመቸው መንገድ የተሰናዳ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለቁጥጥር በማይመች መንገድ በርካታ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን አጭቆ በአንድ ቋሚ ኮሚቴ ክትትል ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑንም ተችተዋል። አስፈጻሚው አደረጃጀቱን ስላሻሻለ ምክር ቤቱ የግድ የአደረጃጀት ማሻሻያ ማድረግ አለበት ማለት እንዳልሆነም አስረድተዋል።

ሌሎች አባላት በበኩላቸው የምክር ቤቱ ኮሚቴዎችን የሚያግዙ ድጋፍ ሰጪ የባለሙያዎች ቡድን ባልተደራጀበት አንድ ቋሚ ኮሚቴ የማይዛመዱ፣ እንዲሁም በሥራ ኃላፊነት የሚጣረስ ባህሪ ያላቸውን አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች እንዲከታተል ለማድረግ መሞከር፣ ምክር ቤቱ መንግሥትን የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባሩ እንዲሰናከል መፍቀድ መሆኑን በመጥቀስ ጊዜ ተወስዶ እንዲታይ ጠይቀዋል።

የአደረጃጀት ማሻሻያውን ማነው ያሰናዳው? ከላይ ከአስፈጻሚው የመጣ ከሆነ አስፈጻሚው መቼ ነው ከዚህ ምክር ቤት እጁን የሚያወጣው? ሲሉም ጠይቀዋል።

 አፈ ጉባዔ ታገሰ በሰጡት ምላሽ የአደረጃጀት ማሻሻያው ባለፈው ክረምት ወቅት በተደረገ ጥናት ላይ ተመሥርቶ መሰናዳቱን ጠቁመዋል። የቋሚ ኮሚቴዎቹ ብዛት ወደ አሥር ዝቅ እንዲል ቢደረግም፣ በእያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ ሥር ከሁለት እስከ አራት ንዑስ ኮሚቴዎች እንደሚደራጁ በመግለጽ ለአንድ ቋሚ ኮሚቴ ታጭቆ የተሰጠ የሚመስለው የክትትልና ቁጥጥር ኃላፊነት፣ ለየንዑስ ኮሚቴዎቹ እንዳይጣረስ ተደርጎ ሲበተን ለሥራ የሚመች መሆኑን አብራርተዋል። የአደረጃጀት ማሻሻያው ፀድቆ ወደ ሥራ ከገባ በኃላ የማይመቹ ሁኔታዎችን እያዩ ማስተካከል እንደሚቻልም ገልጸዋል።

መንግሥት የመሠረተው ገዥ ፓርቲ በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዙሪያ የወሰነውን በምክር ቤቱ የገዥው ፓርቲ አባላት መቀበል እንዳለባቸው አሠራሩ የትም አገር ያለ እንደሆነ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ መንግሥት የመመሥረት ወንበር ሳይኖራቸው ቢገቡም ተመሳሳይ ሁኔታን ተወካዮቻቸው እንዲከተሉ ማድረጋቸው የማይቀር መሆኑን አስረድተዋል።

‹‹ከዚህ በመለስ ግን ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በዚህ ምክር ቤት የክትትልና የቁጥጥር ተግባር እንደ ከዚህ ቀደሙ እንዲገባ አንፈቅድም፣ ይህ ሙሉ እምነቴ ነው በጋራ እንወጣዋለን፤›› ብለዋል።

የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ኮሚቴዎችን ለማደራጀት ብቻ እንደሆነ የጠቆሙት አፈ ጉባዔው፣ የቀረቡ ሌሎች ጉዳዮች በቅርቡ በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ላይ ማሻሻያ የሚደረግ በመሆኑ በአጭር ጊዜ እንደሚመለስ ተናግረዋል።

ከዚህ በመነሳትም የቀረበውን ማሻሻያ ለማፅደቅ ድምፅ እንዲሰጥ ላቀረቡት ጥያቄ የአዎንታ ምላሽ አግኝተው ድምፅ የተሰጠ ሲሆን፣ ለሁለት ሰዓታት ሲሞግቱ የነበሩት የምክር ቤቱ አባላት በሁለት ተቃውሞና በስድስት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቀውታል።

በመቀጠልም በአዲስ መልክ ለተደራጁት አሥር ቋሚ ኮሚቴዎች የሚሰበስቡ ሊቃነ መናብርት፣ የንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ እንዲሁም አባላትን ለመመደብ አፈ ጉባዔው ዕጩዎችን ያቀረቡ ቢሆንም ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።

በዋናነትም እንደ አዲስ የተደራጀውን የሕግ፣ የፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን በሊቀመንበርነት እንዲሰበስቡ ዕጩ ሆነው በቀረቡት አቶ አማኑኤል አብርሃምና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን እንዲመሩ በዕጩነት በቀረቡት የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቧል።

 የተጠቀሱት ዕጩዎች በስም እየተጠቀሱ ቀድሞ በነበሩበት የመንግሥት ኃላፊነት ውጤት እንዳላመጡ፣ ለዚህም ማስረጃ ጭምር ማቅረብ እንደሚቻል በመግለጽ የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞአቸውን አቅርበዋል።

ፓርላማው ጥርስ የለውም እያለ ማኅበረሰቡ የሚተቸው ከሥራ አስፈጻሚው በውጤት አልባነት የተነሱ ኃላፊዎች ወደ ምክር ቤቱ ተልከው መሸሸጊያ እንዲያገኙ ሥራ አስፈጻሚው ተፅዕኖ ስለሚያደርግ መሆኑን በመጥቀስ፣ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸውን አዳዲስ አመራሮች ብቻ እንደሚቀበሉ በመግለጽ ተቃውመዋል።

ይኼንን ጠንካራ ተቃውሞ እንደማያልፋት የተረዱ የሚመስሉት አፈ ጉባዔ ታገሰ፣ ያቀረቡት የኮሚቴ አመራሮች ድልድል እንዲፀድቅ ወይም አድሮ በሌላ ጊዜ ውይይት እንዲካሄድበት አማራጮችን አቅርበው በተሰጠ ድምፅ የምክር ቤቱ አብላጫ ድምፅ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በመወሰኑ፣ በዚሁ መሠረት የዕለቱ ስብሰባ ሌላ አጀንዳ እየቀረው ተበትኗል፡፡

በዚህ እንዲያድር በተወሰነ ጉዳይ ላይ የምክር ቤቱ አባላት በቀጣዮቹ ቀናት በየፓርቲያቸው እንደሚመክሩ ይጠበቃል። በወቅቱ ስማቸው ተጠቅሶ የተተቹት አቶ አማኑኤል አብርሃም ግን በወቅቱ ራሳቸውን ከዕጩነት ማግለላቸውን ተናግረው ነበር።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የሕግ ባለሙያ በአፈ ጉባዔው በሚቀርብ የውሳኔ ሐሳብ ፓርላማው በቋሚ ኮሚቴዎቹ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ማድረግ እንዲችል የአሠራር ደንቡ ቢፈቅድም፣ አሁን የተደረገው የአደረጃጀት ማሻሻያ ግን ሥር ነቀል በመሆኑ በውሳኔ ሐሳብ ሳይሆን ደንቡን በማሻሻል መቅረብ እንደነበረበት ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የሕግ ደረጃን በማያሟላ የውሳኔ ሐሳብ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የሕግ ጥሰት እንደተፈጸመ ገልጸዋል፡፡ ደንቡ በቅርቡ እንደሚሻሻል እየተገለጸ ለምን መጣደፍ እንዳስፈለገውም ግልጽ አይደለም ሲሉ ተችተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...