Thursday, April 18, 2024

የመንግሥት ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብትና የነባራዊ ሁነቶች አንድምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጀርመናዊው የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁር ማክስዌበር እ.ኤ.አ. በ1919 ባቀረበው የተደራጀ ንድፈ ሐሳብ አንድ የዘመናዊ መንግሥት አስተዳደር የመንግሥትነት ባህሪ ተላብሷል፣ ሥልጣንና ተግባሩን በተሟላ መንገድ መወጣት የሚችል ነው ለማለት፣ መንግሥትነቱ በሚገለጽበት ግዛትና ማኅበረሰብ ውስጥ ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም ልዕልናን ሲያገኝ ብቻ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ይህ የጀርመናዊው የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ ንድፈ ሐሳብ በመላው ዓለም ተቀባይነትን ከማግኘቱም ባለፈ በተግባርም የተፈተነ እውነታ ሆኗል፡፡

‹‹የአንድ ዘመናዊ መንግሥት አስተዳደር መገለጫ ኃይልን በብቸኝነት መጠቀሙ ነው፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ ይህ ካልሆነ በዚያ ግዛት ውስጥ ሥልጣን ተቆጣጥሯል የተባለ መንግሥት እንደ መንግሥት እየተንቀሳቀሰ ነው ለማለት አይቻልም ሲል ይደመድማል፡፡

ይህ ማለት ግን በብቸኝነት ኃይልን የመጠቀም መብት ሕጋዊ ቅቡልነትን ያገኘ መሆን ይገባዋል ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥትነት ተግባሩን የሚወጣው ይኼንን ኃይል እንደ ልቡ እየተጠቀመ ይሆናል ማለት እንዳልሆነም ያስረዳል፡፡

በሌላ በኩል ኃይልን በብቸኝኘት የሚጠቀም መንግሥት ባለበት የአገር አስተዳዳር ውስጥ ሌሎች መታጠቅ አይችሉም ማለት አለመሆኑ፣ በዚሁ ንድፈ ሐሳባዊ ትንተናው ያስረዳል፡፡ ነገር ግን ሌሎች የመታጠቅ መብትን ሊያገኙ የሚችሉት፣ በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም መብትን የያዘው መንግሥት ሲፈቅድ ብቻ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ኃይልን በብቸኝነት መጠቀም የመጨረሻና ብቸኛ ግብ መጠቀም ነው ማለት እንዳልሆነ፣ መብቱ የሚፈጥረውን ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ በማስቀደም ማስጠንቀቅንና የኃይል ዕርምጃ እንዲወስድ ማዘዝንም እንደሚያካትት ይገልጻል፡፡

የዚህ ጀርመናዊ ተመራማሪ የተደራጀ ንድፈ ሐሳብ ከኃያላኑ የዓለም አገሮች እስከ ታዳጊዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተቀባይነት አግኝቶ፣ የዘመናዊ መንግሥታት አስተዳዳር የሚገዙበትና የሚተገብሩት ቁልፍ የኃይል ምንጭ ነው፡፡

ከዚህ ንድፈ ሐሳባዊና ነባራዊ እውነት ከዕውቀትና ከስምምነት ተቃራኒ መንገድ መርጦ አገርና መንግሥት የሆነ ምሳሌ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ በንድፈ ሐሳብ ደረጃም ስለመቻሉ የሞገተ እስካሁን አልተገኘም፡፡ በመሆኑም በዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር መሠረታዊ የመንግሥት ሥልጣን መገለጫ በብቸኝነት ኃይልን የመጠቀም መብቱ ነው፡፡

ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብትን ማጣትና ቀውሱ

ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት የዘመናዊ መንግሥት አስተዳደር ሥልጣንና ተግባርን አሟልቶ ለመተግበር የሚያስችል ብቸኛ የመንግሥት ኃይል ምንጭ እንደ መሆኑ መጠን፣ በዕውቀት ላይ በተመሠረተ ስምምነት ይኼንን መሣሪያ ከመተግበር በተቃራኒው ተጉዞ የተሳካ የመንግሥት አስተዳሮችን ያሰፈነ አገርና መንግሥት ምሳሌ አይገኝም፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት አስተዳደርን በመቃወም የሚነሱ የፖለቲካ ኃይሎች የሚመርጡት ትጥቅን ያነገበ የፖለቲካ ትግል በግብታዊነት የተመራ እንደሆነ፣ ውጤቱ ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብትን የሚያሳጣ ደካማ መንግሥታዊ አስተዳደርን ሊፈጥር ወይም የአገር መፍረስን ሊያስከትል እንደሚችል፣ ይኼንን መሰል አጋጣሚዎችም በተለያዩ አገሮች መስተዋላቸውንና አሁንም ድረስ የሚስተዋልባቸው አገሮች መኖራቸውን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በደኅንነትና በግጭት አፈታት ከስዊድን ዩኒቨርሲቲ ያገኙትና በአሁኑ ወቅት በአንድ ዓለም አቀፍ ተቋም በማገልገል ላይ የሚገኙ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያ፣ በአሁኑ ወቅት በሊቢያ ያለውን ሁኔታ ለዚህ እንደ ማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡

እ.አ.አ. በ2010 አካባቢ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የተቀሰቀሱ ሕዝባዊ አመፆች ማዕበል የተጋባባቸው የሙአመር ጋዳፊን አስተዳደር ለመጣል የትጥቅ አብዮት የጀመሩ የሊቢያ የፖለቲካ ኃይሎች፣ በኃያላን አገሮች ጣልቃ ገብነት ታግዘው ያለሙትን ግብ ቢያሳኩም በወቅቱ ለአንድ ዓላማ ብቻ በአንድነት የተሠለፉ የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ያላስማሙ ኃይሎች ነበሩ፡፡ በመሆኑም ጋዳፊ እ.ኤ.አ. በ2011 ተገድለው ከተወገዱ በኋላ፣ እስከ ዛሬ ድረስ የሰከነ መንግሥት በሊቢያ ማቆም አለመቻሉን ያስረዳሉ፡፡

የዚህ ምክንያቱ በሊቢያ የሽግግር መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት (ቅቡልነት) ማግኘት ባለመቻሉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ኃይል የመጠቀም ተገዳዳሪ አቅምን የፈጠሩ በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች በአገሪቱ መፈጠራቸው፣ አሁን በሊቢያ ያለውን በአመዛኙ የመንግሥት መፍረስ (Failed State) ሁኔታ እንደፈጠረ ያስረዳሉ፡፡

ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድንና አስተዳደራቸውን በመቃወም ጦርነት ያወጁ ኃይሎች በሶሪያ የፈጠሩትም፣ ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት ያጣ የመንግሥት አስተዳደር ሁኔታን እንደሆነ በተጨማሪ ማሳያነት ያቀርባሉ፡፡

ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብትና ሁኔታን እንደሚያሳጡ ከተጠቀሱት በትጥቅ የሚመሩ የፖለቲካ ትግል ማሳያዎች በተጨማሪ፣ በትጥቅ የተደራጀ የአደንዛዥ ዕፆች ዝውውርና የተደራጀ የዘረፋ ወንጀል እንቅስቃሴም በመንግሥታት በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም መብት ላይ እንደ ስፋት መጠናቸው ተፅዕኖ በማድረስ፣ የመንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነት ላይ እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ

ወታደራዊ የደርግ መንግሥት 17 ዓመታት በፈጀ የትጥቅ ትግል አስወግደው ወደ ሥልጣን የመጡ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ከበርካታ ዓለም አቀፍ ተንታኞች ሥጋት በተቃራኒ የሰከነ የመንግሥት አስተዳደርን በኢትዮጵያ መትከል ችለዋል፡፡

ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት በአንድ አገር ማኅበረሰብ ውስጥ መልካም አስተዳደርንና የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርን ሊያረጋግጥ የሚገባ ቢሆንም፣ ይህ በተጓደለበት ሁኔታም ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት ተጠብቆ ሊቆይ እንደሚችል ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡

የደርግን መንግሥት ያስወገደው የኢሕአዴግ ስብስብም ይኼንን ላለፉት 27 ዓመታት አስጠብቆ ዘልቋል፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው የውስጥ ትግልና በሕዝቡ ተቃውሞ፣ በኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ግን በአዳዲስ ክስተቶች ታጅቦ የለውጥ ተስፋን በአንድ በኩል፣ ወደ ቀድሞው አልያም ወደ ባሰ ፖለቲካዊ ቀውስ የመመለስ ሥጋትን በሌላ በኩል ደቅኗል፡፡

በኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረውን የውስጥ ትግል ድል አድርገው ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና አጋሮቻቸው፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳርን ለማስፋትና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ተሳትፎ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ እንዲወስን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዚህ መሠረት ለሁሉም የፖለቲካ ወገኖች የትጥቅ ፖለቲካ ትግልን የመረጡትም ቢሆኑ ወደ አገራቸው እንዲገቡና በሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፉ ጥሪ በማድረጋቸው፣ በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡

የትጥቅ ትግል አማራጭን ትተው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመንቀሳቀስ ታቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ትጥቃቸውን አስረክበው ወደ አገር የገቡ ቢሆንም፣ በውስጥ በህቡዕ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የታጠቁ ኃይሎቻቸው ወይም ደጋፊዎቻቸው ትጥቅ አለመፍታታቸውና ይኼንንም ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን ፋዬሶ በምዕራብ ኦሮሚያ በወለጋ አካባቢ የተደራጁና የጦር መሣሪያ የታጠቁ ኃይሎች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ በጋራ ሆነው ትጥቅ የማስፈታት ሥምሪት ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የተጀመረውን ይኼንን የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ትጥቅ የማስፈታትና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት የማስፈን ተግባር ለማስተጓጎል፣ የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች መንገድ በመዝጋት የኃይል ጥቃት መሰንዘራቸው ተሰምቷል፡፡

ከዚህም አልፎ ታጣቂዎቹ ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በግልጽ ለመዋጋት በአካባቢው ጫካዎች መመሸጋቸውን፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በይፋ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ የፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን ታጣቂዎቹ በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ ቢገመትም፣ የኦነግ አመራሮች ከታጣቂዎቹ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ለክልሉ መንግሥት ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሽማግሌዎችንና ተሰሚነት ያላቸውን ወገኖች በመጠቀም፣ በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

‹‹በምንም ተዓምር ሁለት የታጠቀ ኃይል በኦሮሚያ ክልል ውስጥም ሆነ በአንድ አገር ውስጥ ሊኖር አይችልም፡፡ በዚህ ላይ መንግሥት የማያወላዳ አቋም እንዳለው ግልጽ ሊሆን ይገባል፤›› ሲሉ አቶ ሁሴን ያስጠነቅቃሉ፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ በተለይም በወለጋ አካባቢ የታጠቁ ኃይሎች በግልጽ መንቀሳቀሳቸውና ይኼንንም በይፋ እየተናገሩት ይሁን እንጂ፣ ተመሳሳይ አዝማሚያዎች በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በምሥራቅ ሐረርጌ አካባቢ በመስተዋል ላይ ይገኛል፡፡

የተደራጁ ወጣቶች የኢኮኖሚ ጥቅም ጥያቄዎች ከፊት በማስቀደም ለሕዝብ የሚቀርብ የመጠጥ ውኃ አገልግሎትን መተላለፊያ መስመሮችን በመዝጋት፣ የገንዘብ ጥያቄ ባለፉት ሳምንታት ማቅረባቸው አስደንጋጭ ክስተት ነበር፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ ያነገቡ ኃይሎች በአካባቢያቸው የሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆችን በኃይል የማፈናቀል ተግባር በመፈጸማቸውና ይኼንንም መንግሥት ሕግን በማስከበር መግታት ባለመቻሉ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ከቀዬአቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ሲባልም መንግሥት የውጭ ዕርዳታ እስከመጠየቅ ተገዷል፡፡ ቢሆንም ማናለብኝነት መገለጫው የሆነውን ሕገወጥ ተግባር ማስቆም ባለመቻሉ፣ ኃይል የተቀላቀለበት የማፈናቀል ተግባር በአሁኑ ወቅትም ቀጥሏል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነውም በቤኒሻጉል ጉምዝ ክልል የሚገኙ ከ70 ሺሕ በላይ ሰዎች እስካለፈው ሳምንት ድረስ መፈናቀላቸው ተጠቃሽ ነው፡፡

በአማራ ክልልና በትግራይ ክልል መካከል ሲነሳ የከረመው የክልል ወሰን ውዝግብም እየከረረ ከመሆኑ ባለፈ፣ ውዝግቡን በሕጋዊ ማዕቀፍ ለመፍታት የመንግሥት መዋቅሮችም ሆኑ ጥያቄ አቅራቢዎች የሚያደርጉት ጥረት ባለመኖሩን ምክንያት፣ ጥያቄውን በሕግ ሥርዓት ካልተፈታ በኃይል እንፈታለን የሚሉ ድምፆች ከሁለት ሳምንት በፊት በተለያዩ የአማራ ከተሞች በተካሄዱ ሠልፎች ተደምጠዋል፡፡

በቡራዩና በአዲስ አበባ የደቦ ፍርድ የማፈናቀል ድርጊቶች መከናወናቸውና ይህ ሲሆንም የሕግ አስከባሪ ኃይሎች ቸልተኛ እንደነበሩ መንግሥት ራሱ በይፋ አምኗል፡፡

በአገሪቱ ከሚታየው ኃይልን የመቆጣጠር ፍላጎቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ ዝውውር መኖሩ፣ የጦር መሣሪያዎችም በገፍ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው መቀጠሉ አሳሳቢ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

ወደ አገር ውስጥ እየገባ የሚገኘው የጦር መሣሪያና ይኼንኑ ወደተለያዩ አካባቢዎች በማዘዋወር ላይ የሚገኙት፣ በአገሪቱ እየነፈሰ የሚገኘው ለውጥ ጥቅማቸውን የጎዳባቸው ወይም በለውጡ የተጎዱ ኃይሎች የሚፈጽሙት ተግባር እንደሆነ አቶ ሁሴን ይገልጻሉ፡፡

የሚስተዋሉትን ሁኔታዎች በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የደኅንነትና የግጭት አፈታት ባለሙያው፣ በአገሪቱ የተረጋጋ መንግሥት እንዳይኖር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡

ከተጠቀሱት በተጨማሪ የክልሎች የፀጥታ መዋቅሮች እየፈረጠሙ መሄድና ልዩ ፖሊስ በሚል ስያሜ ያቋቋማቸው የፀጥታ መዋቅሮች ትጥቅ፣ ከአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ትጥቅ ጋር ባይወዳደርም ለመደበኛ የፖሊስ ኃይል መዋል የሌለባቸው መሆኑን እንደ ሥጋት ያነሳሉ፡፡

ይሁን እንጂ አሁን በአገሪቱ ያለው የትጥቅና የኃይል ፖለቲካ እንቅስቃሴ የመንግሥትን በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም መብት ይነጥቁታል፣ ወይም ያዛቡታል ብለው አያምኑም፡፡

ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት የመንግሥት የኃይል መጠን ልኬት፣ ከሌሎቹ የኃይል አሠላለፎች ጋር ሲወዳደር በእጅጉ ግዙፍ በሆነ መጠን የሚለያይ መሆኑን ነው፡፡

በሊቢያና በሶሪያ ለተፈጠሩት ሁኔታዎች የውጭ መንግሥታት የግል ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ ጣልቃ ገብነት ትልቁን ድርሻ እንደሚያበረክት፣ በኢትዮጵያ እንደዚያ ዓይነት ሁኔታን በመፍጠር ጥቅሙ የሚከበርለት የውጭ መንግሥት ፍላጎት አለመኖሩን፣ በኢትዮጵያ የመንግሥትን በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም መብት ማዛባትና መንጠቅ ይኖራል ብለው አይገምቱም፡፡

ከዚህ ይልቅ ያልተረጋጋ ወቅት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ለውጡን ሊያዘገይ እንደሚችል ግን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -