የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ አበባን ቀዳሚና ተመራጭ የአየር ጭነት ማመላለሻ መናኸሪያ ለማድረግ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የአፍሪካ ካርጎ ጉባዔ ሰኔ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተከፈተበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን እርስ በርስና ከተቀረው ዓለም ጋር በማገናኘት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአፍሪካ ከኬንያ ቀጥላ ሁለተኛዋ አበባ ላኪ አገር ለመሆን እንደቻለች የገለጹት ዶ/ር ወርቅነህ፣ ለዚህ ውጤት መገኘት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቁን ሚና መጫወቱን ገልጸዋል፡፡ አዲስ አበባን የአፍሪካ ምርጥ የካርጎ ማዕከል ማድረግ የሚያስችል በዓመት 1.2 ሚሊዮን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም ያለው የካርጎ ተርሚናል በ107 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ በመገንባት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ የግንባታው 60 በመቶ ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም በሁለት ምዕራፍ እየተገነባ ያለው የካርጎ ተርሚናል እያንዳንዱ በዓመት 600,000 ቶን ካርጎ የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ገልጸው፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ በመጪው ዓመት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡ የካርጎ ተርሚናሉ በአንድ ጊዜ ስምንት ግዙፍ የጭነት አውሮፕላኖችን ማስተናገድ እንደሚችል የገለጹት አቶ ተወልደ ሁለቱ የግንባታ ምዕራፎች ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ የካርጎ ተርሚናሉ ከአፍሪካ አንደኛ እንደሚያደርገውና ከዓለም ግዙፍ የካርጎ ተርሚናል ከሚባሉት የአምስተርዳም ሲፎል ኤርፖርትና ከሲንጋፖሩ ቻንጋይ ኤርፖርት ካርጎ ተርሚናሎች የሚስተካከል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ አየር መንገዱ በራዕይ 2025 ካቋቋማቸው ሰባት የትርፍ ማዕከላት አንዱ ሲሆን፣ ስምንት የጭነት አውሮፕላኖች (ስድስት ቦይንግ 777 እና ሁለት ቦይንግ 757) ባለቤት ነው፡፡ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በእስያ 24 የጭነት በረራ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፣ በዓመት 346,000 ቶን ካርጎ የማመላለስ አቅም አለው፡፡
ዋና የካርጎ ማዕከሉ አዲስ አበባ ሲሆን፣ በአውሮፓ ቤልጄም ሊየዥ ኤርፖርት የካርጎ መናኸሪያ አለው፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ ተርሚናል በዓመት 250,000 ቶን ካርጎ የማስተናገድ አቅም አለው፡፡
አየር መንገዱ ከመላው ዓለም በቦይንግ 777 የጭነት አውሮፕላኖች ወደ አዲስ አበባ የሰበሰበውን ጭነት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በቦይንግ 757 አውሮፕላኖች እንደሚያሰራጭ፣ ከአዲስ አበባ ወደ አውሮፓ በዋነኛነት የሚያጓጉዘው የአበባ ምርቶች መሆኑን ከአቶ ተወልደ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ከካርጎ ዘርፍ በዓመት 465 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የሚያገኝ ሲሆን፣ በራዕይ 2025 ገቢውን ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ አቅዷል፡፡ የጭነት አውሮፕላቹን ቁጥር ከስምንት ወደ 18፣ የካርጎ በረራ መዳረሻዎችን ከ24 ወደ 37፣ የሚያመላልሰውን የጭነት መጠን ከ350,000 ቶን ወደ 820,000 ቶን ለማሳደግ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 93 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች፣ 78 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፣ በዓመት 7.6 ሚሊዮን መንገደኞች ያመላልሳል፡፡ አየር መንገዱ ካሉት 78 አውሮፕላኖች 13 ቦይንግ 787 ድሪም ላይነር ሲሆኑ፣ 43 አዲስና ዘመናዊ አውሮፕላች ገዝቶ ለመረከብ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ለረዥምና መካከለኛ ርቀት በረራ የቦይንግ አውሮፕላኖችን ብቻ ሲጠቀም የኖረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በ70 ዓመት ታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ 14 የኤርባስ አውሮፕላኖችን ገዝቶ ለመረከብ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
በመጪው ሳምንት አዲስ አበባ የሚገባው የመጀመርያው ኤርባስ 350 XWB አውሮፕላን የሰሜን ተራሮች ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ኤ350 XWB አውሮፕላን ወደ አፍሪካ በማስገባት የመጀመርያው አየር መንገድ ለመሆን በቅቷል፡፡